ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆም በሃንጋሪዋ ቡዳፔስት ሁለተኛ ጉባኤ እንደሚያካሂዱ ይፋ አደረጉ። ይህ መግለጫ ትራምፕ ከፑቲን ጋር የሁለት ሰዓት የስልክ ውይይት ካደረጉ በኋላ የተሰጠ ነው። የጉባኤው ቀን እስካሁን አልታወቀም።
ዋና ዓላማ እና ቅድመ ዝግጅት
ትራምፕ የጉባኤው ዋና ዓላማ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለውን ጦርነት ማስቆም ይችሉ እንደሆነ መመልከት ማጤን ወይም መገምገም እንደሆነ ገልጸዋል። መሪዎቹ ከመገናኘታቸው በፊት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ለዕቅዱ መሳካት “እጅግ የበዛ ማዕከላዊ” የሆነ ሚና እንደሚጫወቱ እና የመጀመሪያዎቹን ስብሰባዎች እንደሚመሩ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የጉባኤው ዋና ዓላማ ሲሉ የገለጹት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለውን አስከፊ ጦርነት እንዲያበቃ በአላስካ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር መክረው እንደነበር አይዘነጋም።
የቶማሃውክ ሚሳኤሎች ጉዳይ
ከጉባኤው በፊት ትልቅ አጀንዳ የሆነው፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የቶማሃውክ ሚሳኤሎችን ትሰጣለች ወይ የሚለው ጥያቄ ነው። ዘለንስኪ ሚሳኤሎቹን ለመጠየቅ ከዚህ መግለጫ በኋላ ዋይት ሀውስ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። እነዚህ ሚሳኤሎች ለዩክሬን መሰጠታቸው በጦርነቱ ሂደት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ትራምፕ ስለ ቶማሃውክ ጉዳይ ውሳኔ እንደሚሰጡ ቢገልጹም፣ ውሳኔው የሚሰጠው ግን ከቡዳፔስቱ ጉባኤ በፊት እንደማይሆን ጠቁመዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ እንደተለመደው “ጦርነቱ መጀመር አልነበረበትም” የሚል አስተያየት ያላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።




