“ያለበት ይግነንበት” እንዲሉ በማህበራዊ ሚድያ ላይ ከሚቅበዘዝበዙት የኤርትራ ባለስልጣናት መካከል ዋናው የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል እንደ አገርም፣ በግልም ደረጃቸውን ያወቁ የመስላል። አገራቸው ኤርትራና ሕዝቧን ያፈኑት ሳያንሳቸው ኢትዮጵያዊ አክቲቪስቶችን “አትተንፍሱ” በሚል እሰጥ አገባ ገጥመዋል። አንዳንድ ታዛቢዎች ከመገረም ይልቅ የሻዕቢያ መሪዎች “ደረጃቸውን አወቁ” በማለት ሲላላጡባቸው አየሁን ይህቺን ጣፍኩ።
የማነ ገብረመስቀል ዛሬ በማኅበራዊ ሚድያ ኤክስ ገፁ ላይ ባሰፈረው መልዕክት፣ የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ የሆነውን የብልጽግና ፓርቲ “አንቂዎች” እና “ተንታኞች” የተባሉ አካላት የኤርትራ የነጻነት ትግል በውጭ ኃይሎች “ቀስቃሽነት” እና “ድጋፍ” የተካሄደ ነው ማለታቸውን በፅኑ አውግዘዋል።
ሚኒስትሩ “የትናንት ታሪክ በውሸት ብዛት ሊፋቅ አይችልም” ሲሉ፣ ኤርትራ ነፃነቷን ያገኘችው በልጆቿ መስዕዋትነት፣ በየተራ በአሜሪካ እና በሶቪየት ኅብረት ይደገፍ ከነበረ መንግሥት ጋር ተዋግታ መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህም አልፈው፣ በኤርትራ ላይ አስከፊ ግፍ የፈጸሙ ኃይሎች “ለታሪካዊ ወንጀሎቻቸው ይቅርታ መጠየቅ እንጂ በኤርትራ ቁስል ላይ ጨው መነስነስ አልነበረባቸውም” በማለት ሕዋሪያም ለመምሰል ሞክረዋል።
የይማነ ክህደት ሲጋለጥ…
የማነ ገብረመስቀል የውጭ ኃይሎችን ሚና ለመካድ ቢሞክሩም፣ የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት መዛግብት እና ምስጢራዊ ሰነዶች (Declassified documents) ትግሉ የዓለም አቀፉ የሃያላን ሀገራት ፍላጎት ውጤት እንደነበር ያመለክታሉ።
ለምሳሌ፣ ኢሳያስ አፈወርቂ በሶቭየት ግንባር ድርጅት በነበረው አፍሮ ኤዥያ ፌደሬሽን ተመልምለው በኮሚኒስት ቻይና ወታደራዊ ስልጠና እንደተሰጣቸው እና ሌሎችም ታጋዮች በድብቅ ወደ ኩባ በመሄድ ስልጠና እንደወሰዱ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በተመሳሳይ፣ የጀብሃ አመራር ከሶርያ፣ ከግብፅ እና ከሱዳን የስልጠና፣ የገንዘብና የጦር መሳሪያ ድጋፍ ሲያገኙ እንደነበር የታወቀ ነው። ከደርግ መንግሥት ወደ ምስራቅ ጎራ ማዘንበል በኋላ ደግሞ ነፃ አውጪ ኃይሎች በፕሬዝዳንት ሬገን አስተዳደር ከነበረው የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ ማግኘታቸውን የሲአይኤ ሰነዶች ያሳያሉ። ይህና ሌሎች ለጊዜው ያጠቀስኳቸው መረጃዎች ትግሉ ከኤርትራውያን ባሻገር በወቅቱ በነበሩት ዓለም አቀፍ ሃያላን ሃገራት የኃይል ሚዛን የተደገፈ መሆኑን ያመለክታል።
በወቅቱ የሲአይኤ ወኪል የነበሩትና ቀጠናውን በቅርበት ያጠኑት ፖል ሄንዝ፣ በጻፉት “The Myths of Ethiopian Revolution” (የኢትዮጵያ አብዮት ተረቶች) በተሰኘው ጥናታዊ ጽሑፋቸው ላይ ይህንኑ እውነታ ያጠናክራሉ። ሄንዝ ነፃ አውጪዎቹ በውጭ ኃይል ባይደገፉ ኖሮ ኢትዮጵያን ያህል የአፍሪካ ትልቅ ኃገር በጦርነት የማሸነፍ እድል እንዳልነበራቸው በግልፅ አስቀምጠዋል። ሄንዝ በደርግ መውደቅ ጉዳይ የተጨወቱትን ሚና ለሚረዳው የኢሳያስ አፍና ጆሮ ይህ ሃቅ ሬት ቢሆንበት አይገርምም። በተለይ በሶቭየት የሚመራው የምስራቁ ብሎክ መዳከም እና በስነ ልቦና ጦርነት ቀድሞ መሸነፉ ለነፃ አውጪዎቹ ትልቅ በር ከፍቷል፤ ይህም ሃብት፣ የሰው ሃይል እና ምቹ ወታደራዊ ገዥ መሬት የነበረውን የማዕከላዊና ደቡብ ኢትዮጵያን ክፍል ያለምንም ከባድ ትግል እንዲቆጣጠሩ አስችሏቸዋል።
በአጠቃላይ፣ የማነ ገብረመስቀል የትግሉን ታሪክ በኤርትራውያን ብቻ መስዋዕትነት ማዕከል አድርገው የማቅረብ ጥረታቸው የአንድ ሀገርን የነጻነት ታሪክ የመወሰን ፍላጎትን የሚያንፀባርቅ ቢሆንም፣ ታሪካዊ እውነታው ግን የኤርትራ ነፃነት ትግል በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት የጂኦፖለቲካዊ ሽኩቻ ጋር የተሳሰረ መሆኑን ያመለክታል። ሚኒስትሩ አምርረው በመቃወም በማኅበራዊ ሚድያ መቅበዝበዛቸው ይህንን ግልፅ ታሪካዊ እውነታ ለመሸሽና ለመካድ የሚደረጉት የፖለቲካ ጥረት እንደሆነ መረዳት አይከብድም። ከዛ በላይ የሰውየው “አትተንፍሱ” የኤርትራው አጉራ ዘለል መንግስት መጨረሻ መቃረብ የፈጠረው ስጋት ያዋለደው ኑዛዜ ከመሆን የሚያልፍ አይደለ። ” በመጨረሻ ይኮበልላሉ፣ ወይም የጋዳፊ ዕጣ ይደርሳቸዋል” የተባሉት ኢሳያስ ይህ ትንቢት የወጣባቸው ከፖል ሄንዝ አገር መሆኑ ስጋቱን ቢያንረውና “አትተንፍሱ” ቢሉ አይገርምም። ለማንኛውም በቀጣይ በዚህ ኤርትራን እስር ቤት ከቶ “ሰዓት በኤርትራ ቆሟል” ተረት ያስተረተውን “ንጻነት” ጉዳይ በስፋት እመለስበታለሁ።
ገሪማ ሳህሌ
ዝግጅት ክፍሉ / ይህ የጸሐፊው አቋም ነው። ምላሽ ወይም ተጨማሪ አስተያየት ላላቸው መድረኩ ክፍት ነው በ info@addisreporter.com ይላኩልን።




