አምስተርዳም ይካሄዳል ተብሎ ብውጭ አገር በሚኖሩ በተለያዩ የተቃዋሚ ርቲ አመራሮች የተሰራጨው የሽግግር መንግስት ምስረታ ጉባኤ ከአሜሪካ ወደ አምስተርዳም ያመራው አሜሪካ ጥያቄውን ባለመቀበሏ መሆኑ ተሰማ። ስብሰባው ከጀርባው ሆነው የሚመሩትና ሻቢያና ሌሎች ፍላጎት ያላቸው የሚታወቁ አካላት እንደሆኑም እየተነገረ ነው።
የቀድሞ የትህነግ አመራርና አሁን ላይ “ቪዝን ኢትዮጵያ” ከሚባለው አደረጃጀት ጋር እየሰሩ ያሉት አቶ ግደይ ዘርዓጽዮን በግል የኢሜል አድራሻቸው ” ለስብሰባው ተዘጋጁበት” ሲሉ ያሰራጩት ሰነድ ጉብኤው ለምን ወደ አምስተርዳም እንደተዛወረ፣ ወይም አምስተርዳም ለምን እንደተመረጠች አይስረዳም።
ይህንኑ አስመልክተን ተጋባዥ ከሆኑት መካከል የአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ተባባሪ ያነጋገራቸው ” ቅድሚያ ዕቅዱ ስብሰባውን በአሜሪካ ለማድረግ ነበር፤ ምላሹ ጥሩ ባለመሆኑ ወደ አውሮፓ እንዲሆን ተደርጓል” በማለት አስረድተዋል።
ለኢትዮጵያ አዲስ ህገመንግስት፣ መከላከያ፣ አዲስ የክልል አወቃቀር፣ አዲስ የሰራተኞች አቀጣጠር ህግ፣ እንዲሁም ባለፉት አምስት ዓመታት የተቀጠሩ ሰራተኞችን የማባረር እቅድ አካቶ በተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ላይ ለሚሳተፉ ማን ወጪ እንደሚሸፈን ለተጠየቁት ተሳታፊው ያሉት ነገር የለም።
ስቴት ዲፓርትመንትን በተለያዩ እንደራሴዎችና ኮንግረንስ አባላት የማግባባት ስራ ሲሰራ ” ዋናው ጉዳያችሁና ዓላማችሁ ምንድን ነው” በሚል ተጠየቀው እንደነበር ያስታወቁት የስብሰባው ተጋባዥ፣ ህገመንግስቱን ማፍረስና በማራ ክልል ልክ በትግራይ ጦርነት እንደተደረገው አሜሪካ ጣልቅ ገብታ የፕሪቶሪያው ዓይነት ውል እንድታዋውል እንደሚፈልጉ ገልጸው እንደነበር አመልክተዋል።
ከሌሎች ግሩፖች ጋር ማለትም ከኦሮሞና ከትግራይ ፖለቲከኞች ጋር በአሌክስ ድዋል አማካይነት ባተደርገ ውይይት ክልሎች በህገ መንግስቱ የጸና አቋም እንዳላቸው፣ ችግሩ ህገ መንግስቱ እንዳልሆነና ከላይ ከቀረበው አሳብ የተለየ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን እንደሰሙ የገለጹት እኚሁ የስብሰባው ተሳታፊ በምላሹ ” በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያንና አገር ቤት ያሉት ዜጎች ያላችሁ ዕይታ የተለያየ ነው” በማለት አሜሪካ ጀርባዋን መስጠቷን እንደሚያውቁ አመልክተዋል።
በቅርቡ ከኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች ጋር በፖሊሲ ጉዳዮችና በቀይ ባህር ጉዳይ መነጋገራቸውን ያስታወሱትና ተባባሪያችን ያነጋገራቸው እኚሁ ሰው ” አሜሪካ በቀይ ባህርና በኤርትራ ጉዳይ ከያዘችው አቋም ጋር የሚገጥም አካሄድ ባለመሆኑ ሰዎቹ ጀርባቸውን ሰጥተዋል” ሲሉ ያላቸውን ግርድፍ መረጃ በመንተራስ ተናግረዋል።
የዚህ ዝግጅት ዋና መሪ እንደሆኑ የሚነገርላቸውን የቪዝን ኢትዮጵያ ቁልፍ ሰው አቶ ክፍሉን፣ እንዲሁም ከሳቸው ጋር በመሆን የሚዲያውን ክንፍ ይመራሉ የሚባሉትን የቀድሞ የቪኦኤ ዝግጅት ክፍል መሪ አቶ ንጉሴ አክሊሉን ተባባሪያችን ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም። ሲሳካ የምናካትት ይሆናል።
በኖርዌይ የሚኖሩትና ብዙ ጊዜ በጀርመን ድምጽ በመቀርብ የኢትዮጵያ መንግስትን የሚተቹት አቶ ዩሱፍ ያሲንና አቶ ዘርዓይ እንዲሁም አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በጣምራ የአውሮፓውን ዝግጅት እየመሩ እንደሆነ ስለ ስብሰባው አካሄድ የሚያውቁ የኖርዌይ ዜና ምንጮች ነግረውናል።
ስብሰባው እንደሚካሄድ ከመውሰኑ በፊት በኖርዌይ ስብሰባ መደረጉን ያመለከቱ የስብሰባውን ወጪ የትኛው አገር እንደሰጠ ባይገልጹም በስፖንሰር በኩል በቂ ብር መገኘቱን እንዳረጋገጡ አስታውቀዋል።
የታጠቁ ኃይሎችንና የተለያዩ ድርጅቶችንና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት አካቶ የሚቋቋመው የሽግግር መንግስት ሰነድ ዝግጅት ውስጥ አንጋፋ ምን አላባትም በሰማኒያዎቹ ዕድሜ ክልል የሚገኙ የኢህአፓ አባላት ንቁ ተሳትፎ እንዳላቸው ስለ ዝግጅቱ የሚያውቁ አስታውቀዋል።
አምባሳደር ቲቦርናጌ የኤርትራን መንግስት፣ የኢትዮጵያን ወደ ቀይባህር መመልስ አስመልክቶ በተደጋጋሚ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩዋቸው ጽሁፎች፣ እንዲሁም ሰሞኑን ከኢትዮጵያዊ የዩቲዩብ አምድ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የሰጡት ሰፊ ምላሽ አሜሪካ አሁን ላይ ኢትዮጵያን አስመልክቶ የምትከተለውን አቋም አመልካች እንደሆነ የሚናገሩ አሜሪካ ጀርባዋን ሰጥታለች መባሉን ይቀበላሉ። በተለይም በቀይ ባህርና በሶማሊላንድ አሜሪካ ከእስራኤል ጋር የጀመረችው ፕሮጀክት የሁሉም ነገር አመላክች እንደሆነ እነዚሁ ወገኖች አክለው ይገልጻሉ፤
ስብሰባውም ሆን ዝግጅቱ ከሻዕቢያ ጋር የሚሰሩ ኢትዮጵያዊ ከለር ያላቸው እንደሆኑ የሚናገሩና መደረኩ ላይ ለመገኘት ፈቃደኛ ያልሆኑ አሉ። እነዚህ ወገኖች ይህ የሽግግር መንግስት አጀንዳ በመናበብ የታቀደው ኢትዮጵያ የያዘቸውን የአሰብ ጉዳይ ለማጓተት ወይም ጫና ለመፍጠር እንደሆነ እነዚሁ ስብሰባውን የማይሳተፉ ወገኖች አመልክተዋል። የሁሉንም አሳብ በማሰባብሰብ ተጨማሪ ሪፖርት እናቀርባለን።




