ስማቸው የሚደበቅላቸው ታጣቂዎች በአርሲ የፈጸሙት ግድያ “ከፖለቲካ ፍጆታ በላይ ሊታይ ይገባል”

Date:

አዲስ ሪፖርተር – በኢትዮጵያ ሰላማዊ ሰዎችን የሚገድሉ፣ የሚያግቱና የሚያፈናቅሉ ታጣቂዎች ለሚፈጽሙት ጥቃት ኃላፊነት አይወስዱም። ለምን ዓላማ ድርጊቱን እንደሚፈጽሙም በገሃድ የድርጅታቸውን ስም ጠርተው አያስታወቁም። ሚዲያዎችም ሆኑ ያገባናል የሚሉ እዚህ ጉዳይ ላይ ዳተኛ መሆናቸው ወይም ከተቋቋሙበት ዓላማ ወይም ካቋቋማቸው ተቋም ፍላጎት አንጻር መስራታቸው አሳሳቢ እንደሆነ የህግ ባለሙያዎች አስታወቁ።

“በሌሎች ዓለማት ለምሳሌ ሂዝቦላ፣ አልቃይዳ፣ አልሸባብ ወዘተ ግድያም ሆነ እገታ ሲፈጽሙ ንብረት ሲያወድሙና የጅምላ ወንጀል ሲፈጽሙ ኃላፊነት ወስደው መግለጫ ያወጣሉ። በመግለጫቸው ወይም በቃለ ምልልስ ሳይሸማቀቁ  የፈጽሙትን ድርጊት ለምን እንደፈጸሙም ያብራራሉ። ይህ የተለመደ ነው። ” የሚሉት እነዚሁ የህግ ባለሙያዎች ” በአርሲ በተደጋጋሚ ደረሰ የተባለው ግድያ የጥቃት አድራሺዎቹን ማንነት እነሱ ራሳቸው ኃላፊነት ወስደው ባያስታውቁም የአገሪቱ ሚዲያዎች የግልና የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ የሚደብቁበት ምክንያት አሳሳቢ ነው” ይላሉ።

“በኢትዮጵያ ሰላማዊ ዜጎችን በጅምላም ሆነ በተናጠል የሚገሉ፣ የሚያግቱም ሆነ የሚዘርፉ ስለፈጸሙት ተግባር ኃላፊነት ሲወስዱ አይሰማም። የሚጠይቃቸውም የለም። እንደውም ማስተባበያ መድረክ የሚያመቻቹ ብዙ ናቸው። ይህ ብቻ አይደለም “ደረሰ የተባለውን” ጥቃት ለማውገዝና ለወንጀሉ ሌላ ባለቤት ለማበጀት እሽቅድምድሙ ሲታይ የተጠናና ዝግጅት ይተደረገበት መሆኑን ያሳብቃል።” በማለት በድፍረት የሚናገሩም አሉ። በአንድ ወቅት በወለጋ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሰራዊትን ሲከሱ ቪኦኤ አማርኛው ኩማ ድሪብሳ /ጃል መሮን በማቅረብ ማስተባበያ ሰርተውለት እንደነበር በምሳሌነት ያስታውሳሉ።

አንዳንዴ ተጎጂዎች “ የገደሉን እነ እገሌ ናቸው” በሚል ሲናገሩ ካልተሰማ በስተቀር በተደጋጋሚ የሚሰማው የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ግድያ ባለቤት አልባ የፖለቲካ አጀንዳ ማሟሟቂያ እንጂ የፍትህ ጥያቄ እንደማይታይበት የመለከቱት የህግ ባለሙያዎች፣ “ከየአቅጣጫው በራስ ፍላጎት በማጀብ የፖለቲካ ስራ የሚሰራበት የሰው ልጆች ሞት መቼ ተቆርቋሪ እንደሚያገኝ ማሰቡ ለብዙዎች ህልም እየሆነ ነው” ነው ብለዋል። የሰው ልጅ ሞት ከፖለቲካና ስልጣን በላይ በመሆኑ ሊታሰበበት እንደሚገባ መንግስትን ጨምሮ አሳስበዋል።

ሰሞኑን የሆነውም ይህ ነው፡፡ የተጎጂዎች ቤተሰቦች ማን ጥቃት እንደፈጸመባቸው ቢያውቁም በርካታ ሚዲያዎች በተለይም በውጭ አገር ያሉ ጉዳዩን ያቀረቡበት አግባብ አውዱ ሌላ መሆኑ እንዳሳዘናቸው ከስፍራው ያነጋገርናቸው ገልጸዋል።

“ግድያውን የፈጸሙትን ታጣቂዎች በስም ጠርቶ ከማውገዝ ይልቅ፣ ግፈኞቹን በስም ለይቶ ከማጋለጥና መሪዎቻቸውን ለፍርድ እንዲቀርቡ የተደራጀ እንቅስቃሴ ከማድረግ ይልቅ፣ ሃዘኑን በራሳቸው መንገድ፣ ለራሳቸው የፖለቲካ ስራ ሲያውሉት ማየት እጅግ አሳዛኝ ነው” በማለት አመልክተዋል።

ስማቸውን መናገር ያልፈለጉና ሰሞኑን ጥቃት በደረሰበት አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪ “የገደሉንና ሲገሉን የኖሩት ይታወቃሉ። ለእነሱ ቅርብ የሆኑትን ጨምሮ በስም ጠርቶ የሚያጋልጣቸው የለም” ብለዋል። አክለውም “ልክ ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ዕለት ከዕለት ሳይቋርጡ እየተቀባበሉ የሚያቀርቡ ሚዲያዎችና አክቲቪስቶች ይህንን ተደጋጋሚ ግድያ፣ አፈና፣ እገታና ዝርፊያ በተመሳሳይ የዕለት ስራቸው አያደርጉትም? ዜና በማቀጣጠል ብቻ ለሕዝብ መቆርቆርስ በምን መስፈርት ትክክል ይሆናል? በዚህ መሰሉ አሰራራቸው እነሱስ ከሚገሉን በምን ይለያሉ” የሚል ጥያቄ ያነሳሉ።

ሰሞኑን የተደረገውን ጨምሮ በተደጋጋሚ የሚፈጸመውን የሰዎች ግድያ አስመልክቶ ገዳዮቹ ኃላፊነት አለመውሰዳቸው ራሱን ችሎ የሚያነጋግር ጉዳይ እንደሆነ ጉዳዩ ያሳሰባቸው ይናገራሉ። በተደጋጋሚ ጉዳት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ያለውን የመንግስት አደረጃጀት ጨምሮ በጥብቅ ምርመራና መፍቴ እንዲበጅለት የሚጠይቁ “ ስጋቱ አሁንም አለ። ዋስትና የለንም” ብለዋል።

በጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም. ብቻ 25 የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች ሕይወታቸው እንዳለፈ ቅዱስ ሲኖዶስ አስታውቋል። “አገራችንና ምድራችን ብለው በሰላም በተኙበት በድንገት ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል ” ያለው ሲኖዶስ ገዳዮቹን ከተጎጂዎች አጣርቶ አላስታወቀም። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትm በተመሳሳይ ወገኖቼ ያላቸው እንደተገደሉ በመግለጫ አስታውቋል።  

ቋሚ ሲኖዶስ ፥ ” በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በምሥራቅ አርሲ ዞን አስተዳደር  በጉና፣ በመርቲ፤ በሸርካ እና በሆሎንቆ ዋቢ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

ጥቅምት 14 ለ15 ቀን 2018 ዓ.ም. በጉናና መርቲ ወረዳዎች 17 ክርስቲያኖች፣ ጥቅምት 17 ለ18 ቀን 2018 ዓ.ም. በሸርካ ወረዳ 3 ክርስቲያኖች እንዲሁም ጥቅምት 18 ለ19 ቀን 2018 ዓ.ም. በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ 5 ክርስቲያኖች በድምሩ በጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም ብቻ 25  ወገኖቻች አገራችንና ምድራችን ብለው በሰላም በተኙበት በድንገት ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉና ግድያውም ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ መሆኑን የምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የላከውን ሪፖርት ቋሚ ሲኖዶሱ የተመለከተው በከባድና ጥልቅ የኃዘን ስሜት እንደሆነ አስታውቋል። ይህ ሁሉ ጥቃት ሲሰነዘር ጥቃት አድራሾቹ “ያልታወቁ ታጣቂዎች” ነው የሚባሉት።

በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት እንዲህ ዓይነቱ አሰቃቂ ድርጊት ሲፈጸም የቆየው በተደጋጋሚ እንደሆነ የገለጸው ቋሚ ሲኖዶድ ” እንዲህ ዓይነቱ አስነዋሪ ድርጊት በቅዱሳት መጻሕፍት ሆነ በሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው፣ በነጻነት የማምለክ ሕገ መንግሥታዊ መብትን የሚጋፋ፣ ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር መንፈሳዊ ዕሴቶቻችንን የሚያጠፋ፣ ክብረ ነክና ሊወገዝ የሚገባው ኢ-ስነምግባራዊ ድርጊት በመሆኑ በጽኑ እናወግዛለን ” ያለው የቤተ ክርስቲያኒቱ መግለጫ፣ ከተጎጂ ቤተሰቦችና ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በመነጋገር የጉዳት አድራሺዎቹን ማንነት ይፋ ያላደረበትን ምክንያት አልገለጸም።

ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላትም ይህን ኢሰብዓዊ የሆነ ተግባር በጽኑ በማውገዝና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን በሕይወት የመኖርና የዕምነት ነጻነት መብትን እንዲያስከብሩ ይህን አስነዋሪ ድርጊት የፈጸሙትን ሕገ ወጥ ግለሰቦች ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪም በቀጣይ እንዲህ ዓይነቱ ሕገ ወጥ ተግባር እንዳይደገም አስፈላጊውን የሕግ ከለላ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ቋሚ ሲኖዶስ አሳስቧል፤ ሲኖዶሱ ህኛ ህገ መንግስት ጠቅሶ ጠንካራ ማሳሰቢያ የሰጠው በደፈናው “መንግስታው አካላት” በሚል ነው።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በበኩሉ “የተወሰኑ የእስልምና ዕምነት ተከታዮችም ህይወት ጠፍቷል ” ሲል መግለጫ አውጥቷል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል፣ አርሲ ዞን የተፈጸመውን ግድያ አስመልክቶ አርብ ምሽት ባሰራጨው የሀዘን መግለጫ ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምዕመናን በተጨማሪ የእስልምና ዕምነት ተከታዮችም መገደላቸውን አመልክቷል። የገዳዮቹን ማንነት አልተቀሰም።

“በአርሲ ዞን ውስጥ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዕምነት ተከታዮች ላይ ጥቅምት 14 ለ15  2018 እንዲሁም ጥቅምት 18 ለ 19 /2018 ወገኖቻችን በተኙበት ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና የኢትዮጵያ  የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ካወጧቸው መግለጫዎች ለመረዳት ችለናል” ያለው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መግለጫ ሞቱ ያላቸውን አልዘረዘረም።  

ምክር ቤቱ “በዚሁ አካባቢ በተፈጸመው ጥቃት ሳቢያ የተወሰኑ የእስልምና ዕምነት ተከታይ ወገኖቻችንም ህይወት መጥፋቱን ከአካባቢው ማህበረሰብ ለማወቅ ችለናል ” ነው ያለው።

ጠቅላይ ም/ቤቱ በደረሰው አሳዛኝ ጉዳት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል። “ለቤተሰቦቻቸው እና ለመላው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች መፅናናትን ፤ ለሙስሊም ወንድሞቻችንንም አሏህ ጀነተል ፊርደውስ እንዲወፍቃቸው እና ለመላው ህዝበ ሙስሊም መፅናናትን እንመኛለን ” ብሏል።

“መንግስት የሰው ልጅን በዚህ አይነት አሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው እንዲያልፍ ያደረጉ አካላትን በመከታተል ለህግ ያቅርብ ” ሲል ሌሎች እንዳሳሰቡት አሳስቧል።

በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በተለያዩ ቦታዎች የሚካሄዱ የዕገታ፣ የግድይና የዘረፋ ወነጀሎችን በተመለከተ የሚወጡ ዘገባዎች ድርጊቱን የፈጸሙትን የመደበቅ አሰራር መከተላቸው በርካታ ጥርጣሬ እንደሚያሳድርባቸው የህግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በተለይም “በጋራ እንታገላለን” በሚል ቃል ኪዳን ሚዲያዎችም በጋራ ከሚሰሩት ድርጅት ፍላጎት አንጻር ዜናውን በማድበስበስ በተጎጂዎች ላይ ሌላ በደል እየፈጸሙ እንደሆነ እነዚሁ የህግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤም ድርጊቱን አውግዟል። መንግሥት የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት ነፃነት የማረጋገጥ ዋንኛ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ችግሩ ከዚህ በላይ ተባብሶ ተጫማሪ ሀዘን እና ሰቆቃ ከመከሰቱ አስቀድሞ አስፈላጊውን የሕግ ማስከበር ሥራ እንዲሠራ በአጽንኦት አሳስቧል።

ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት እና ሕብረተሰቡ ይህን እጅግ የከፋ የጭካኔ ተግባር  በአንድ ድምጽ በግልጽ ማውገዝ እና ከሕግ አካላት ጋር በመተባበር ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲቀርቡ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ አደራ ብሏል።

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በምዕመኖቿ ላይ በምስራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት የተፈጸመውን ግድያ ኢሰብዓዊ ተግባር መሆኑን አመልክቶ በጽኑ አውግዟል።

ደርጊቱን የተቃወሙ የፖለቲካ ድርጅቶችም በደሀናው መንግስት ይቅርታ እንዲጠይቅና ህዝብን ይቅርታ እንዲጠይቅ ከማሳሰብ በዘለለ “ያልታወቁ” የተባሉትን ታጣቂዎች አስመልክቶ አልተነፈሱም።

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

ኃይሌ ገብረስላሴ “አረቄን እጠቀም ነበር” በማለቱ ዕግድ ተጣለበት፤ እግዱ ለዓለም ዓቀፍ ተቋማትና ማህበራት ተበትኗል

አዲስ ሪፖርተር - አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ አረቄን ከዶፒንግ ጋር...

“የኢትዮጵያዊያ መከራ የሆነውን ትህነግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያና ትግራይ ምድር መንቀል ዋና ዓላማችን ነው”

አዲስ ሪፖርተር - እስካሁን በመላው ኢትዮጵያ ለተፈጠሩ ምስቅልቅሎች፣ በትግራይ...

የአማራ ክልል የወሲባዊ ጥቃት አሳስቧል፤ “በማንና እንዴት ይፈጸማል? ለሚለው በጥናት የተረጋገጠ መረጃ የለም” ጤና ቢሮ  

አዲስ ሪፖርተር - በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባለው ጦርነትና...

በሻዕቢያና ህወሃት መካከል አለመተማመኑ ሰፍቷል፤ የሚታወቁ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ከእነ ሞንጆሪኖ ቡድን እየወጡ ነው

ስጋት ትልቁ ምክንያት ነው። ሻዕቢያ በተግባር የተፈተሸ ከሃጂ በመሆኑ...