የኢሳያስ ዕቅድ እንደሆነ የተነገረለት ወረራ በአፋር ክልል ተፈጸመ፤ አፋር ክልል “ራሴን እከላከላለሁ” አለ

Date:

በአፋር ክልል ተጀመረ የተባለው ወረራ፣ “የፌደራል ስርዓቱን እናፈርሳለን” በሚል ወታደራዊ ዝግጅቱን እያጠናከሩ ያሉት የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ዕቅድ መሆኑን አቶ ጌታቸው ረዳ አመለከቱ። በአፋር ክልል ላይ የተጀመረውን ወረራ አስመክቶ “እናንተ ኋላ ቀር ቡድኖች ወደ አፋር የሚወስደውን መንገድ በመዝጋት የአፋርን ህዝብ እንደ መደራደሪያ መሳሪያ ለመጠቀም ፍላጎት እንዳላችሁ አውቃለሁ” ሲሉ አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል። ድርጊቱንም “ክህደት” ብለውታል። የአፋር ክልል ራሱን ለመከላከል እንደሚገደድ አስታውቋል። ከመንግስት ወገን የተባለ ነገር የለም።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ፈረሰ፤ በአፋርን ስድስት መንደሮች ተወረሩ፤ መንግስት የውጊያ ግብዣ ቀረበለት

ከአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ወረራ መካሄዱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ “ካለፉት ጥፋቶች መማር ያልቻለ” በማለት በእነ ዶክተር ደብረጽዮን የሚመራውን የትህነግ አንድ ክፋይ ይከሳል።  አክሎም

“ከጥፋቱ የማይመረው ጉጅሌው የትህነግ ቡድን በ26/02/2018 ዓ.ም በአፋር ክልል ወሰን ውስጥ በማግባት ስድስት መንደሮችን በጉልበት በመቆጣጠር ንጹሃንን በሞርታርና በዙ-23 በመደብደብ የተለመደውን የሽብር ተግባሩን በግልጽ ጀምሯል” ሲል ክስ ያሰማበትን ምክንያት ያስረዳል።  

“ኋላ ቀር የሆነው ቡድን የፕሪቶሪያን ስምምነት ለማፍረስ የተለያዩ ትንኮሳዎችን ሞክሯል። ነገር ግን የፌደራል መንግስቱ ታግሷል” ሲሉ በትግርኛ ቋንቋ በግል ኤክስ ገጻቸው አቶ ጌታቸው አስጠንቅቀዋል።

አቶ ጌታቸው እንደወትሮው ትንኮሳው ሕዝብን ለመጫፍጨፍና ለስቃይ ለመዳረግ የተደረገ መሆኑን አመክልክተው፣ ወረራውን “ አሁንም የፌዴራል መንግስትን ጎትቶ ወደ ግጭት ለማስገባት በአፋር ክልል ትንኮሳ ፈፅሟል። ይህ የሻቢያ አጀንዳን ለማስፈፀም የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፣ለዚህ ዋና ተጠያቂዎቹ ፍሳሃ ማንጁስ እና ዮሐንስ ናቸው” ብለዋል።

የአፋር ክልላዊ መንግስት መግለጫው “አዛውንቶቹ” ሲል የጠራቸውን እነዚህኑ ክፍሎች፣ “የህወሓት ጉጅሌ በአፋር ክልል በዞን ሁለት በመጋሌ ወረዳ ቶንሳ ቀበሌ ዋራዓ እና ሚልኪ በሚባሉ ልዩ አካባቢዎች ወሰን ተሻግሮ በመግባት ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ በንጹሐን የአፋር አርብቶ አደሮች ላይ የከባድ መሳሪያ ተኩስ በመክፈት የፕሪቶሪያ ስምምነትን በግጭት አዋጅ በግልጽ አፍርሷል” በማለት ጦርነት መታወጁን አስታውቋል።

“ይህ የህወሓት ጣባጫሪ ቡድን በቶንሳ ቀበሌ ላይ ተኩስ በሚከፈትበት ወቅት ሰላም ወዳድ የአፋር ሽማግሌዎች እንዲመለሱ ቢማፀኗቸውም ጉጅሌው ግን አሻፈረኝ ብሏል” ያለው የአፋር ክልል መግለጫ፣ የአዛውንቶችን ተማጽኖ ወደ ጎን በመተው ጥፋት መፈጸሙን አመልክቷል።

መግለጫው እንዳለው “ይህ ከትናንት ጥፋቱ የማይማረው ተስፋ ቢሱ የህወሓት ጉጅሌ ቡድን ከድርጊቱ በአስቸኳይ ካልተቆጠበ የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የዜጎች ደህንነትና የወሰኑን ክብር የማስጠበቅ፣ እንዲሁም ራስን ከማንኛውም ውጫዊ ጥቃት የመከላከል ኃላፊነቱን እንደሚወጣ እንገልፃለን” ሲል ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

አቶ ጌታቸው “ምክር” ሲሉ ባሰራጩት ጹፋቸው፣ የአፋርን ስድስት ቀበሌዎች ወሯል የተባለውን ቡድን “ይህ እንቅስቃሴ ለህዝቡ ስቃይ ለማምጣት እና ህዝቡን ለመጨፍጨፍ የሚደረግ የክህደት እንቅስቃሴ ነው” ብለውታል።

“እናንተ ኋላ ቀር” አሉ አቶ ጌታቸው “እናንተ ኋላ ቀር ቡድኖች ወደ አፋር የሚወስደውን መንገድ በመዝጋት የአፋርን ህዝብ እንደ መደራደሪያ መሳሪያ ለመጠቀም ፍላጎት እንዳላችሁ አውቃለሁ” ሲሉ አስቀድመው የሚያውቁትን ሚስጢር ይፋ አድርገዋል።

“ይህ እንዲሆን በፍፁም አታስቡ” አሉ አቶ ጌታቸው አከሉና  “የትግራይ ጦር (TDF እና TPF) ትግራይን ከፌዴራል መንግስት ጋር በምንም መልኩ የሚያጋጭ አጀንዳ የላቸውም። ስለዚህ ይህ ኋላ ቀር ቡድን የሻቢያ አጀንዳ መጠቀሚያ እንዳይሆን መታገል ያስፈልጋል” ሲሉ ሁሉም ወገኖች ሊይዙት የሚገባውን አቋም አስታውቀዋል። ብለዋል። የአፋርን ክልል ዘልቆ የገባው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ጦር አንድ ክፋይ በወረራ ያዛቸው የተባሉት ቀበሌዎች ወርዓ፣ ኩስ ሰበበራ፣ ዶያ፣ ገደ ባለዓ፣ ካርማ ኣጋና ሚልኪ መሆናቸው ታውቋል።

በሌላም አቅጣጫ የከባድ መሳሪያ ልውውጥ እንደሚሰማ ምስክሮች እያስታወቁ ነው። የአፋር የፀጥታ ኃይሎችም ሆነ መከላከያ በግልጽ ምላሽ መስጠት ስለመጀመራቸው የተባለ ነገር የለም። ይሁን እንጂ ክልሉ ወረአውን ለመከላከል እንደሚገደድ ባስታወቀው መሰረት ኃይሉን ማዘጋጀቱ ታውቋል።

በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው ትህነግ ይህ እስከተጻፈ ድረስ ያለው ነገር የለም። አስቀድሞ ግን የፌደራል መንግስት የፕሪቶሪያውን ስምምነት አፍርሷል በሚል ክስ አቅርቦ ነበር።

እነ ዶክተር ደብረጽዮንና ሻዕቢያ የፈጠሩትን ጥምረት የሚቃወሙና እዛው መካከላቸው ያሉት መኮንኖችም ይሁን ተዋጊዎች ወደ አፋር ክልል የገባውን ሰራዊት አስመልክቶ ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም አልተሳካም።  

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related