አዲስ ሪፖርተር – “ገዳዮቹን አስመልክቶ ምንም መናገር አይቻልም” ይላል አዲስ ሪፖርተር ያናገራቸው የአርሲ ቤተክህነት ሰራተኛ። “ለምን” ሲባሉ ዝርዝር መናገር ፈቃደኛ አልሆኑም።
ስለሞቱት መናገር እንጂ ስለገዳዮች ማሰብ በራሱ ክልክል የሆነ ይመስላል። አዲስ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች “መንግስት መጠየቅ” እንዳለበት ደጋመው ከማሳሰብ በዘለለ የተለየ አሳብ አያራምዱም።
ስለ ገዳዮቹ መረጃ እንዳላቸው ለተጠየቁት፣ ሊቀ ኅሩያን ታምራት“ ከወረዳ ቤተ ክህነት በተገለጸልኝ መሰረት ነው የማስተላልፈው” የሚል ምላሽ ነው ያላቸው። ከወረዳው የተላለፈላቸው መረጃ ምን እንደሆነ ማብራሪያ ሲሰጡ “ የማይታወቁ ታጣቂ ኃይሎች ” ከማለቱ ውጭ ዝርዝር አያቀርብም። እሳቸውም ልክ እንደደረሳቸው መረጃ “የማይታወቁ ያታጠቁ ኃይሎች” በማለት ለበላዮቻቸውና ለሚመከታቸው ከማሳወቅ የዘለለ የሚሉት ነገር እንደሌለ ነው የሚናገሩት።
የመላው ኢትዮጵያ አማራ ድርጅት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ማሙሸት በበኩላቸው “ስለገዳዮቹ ልንጠየቅ አይገባም” ሲሉ ፍትህ የሚበየንበት ቀን እንደሚመጣ አስታውቀዋል።
በፓርቲ ደረጃ ስለ ገዳዮቹ ማንነት ለማወቅ ሙከራ ስለመደረጉ ለተጠየቁት “ መንግስት ነው የዜጎቹን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ ያለበት” በሚል ምላሽ ከመስጠታቸው ውጪ ስለ ገዳዮቹ ምንም ማለትን አልወደዱም። በጋራ የፓርቲያቸው አቋም የወጣውን መግለጫ መከታተሉ እንደሚበጅ አመልክተዋል።
አቶ ጥሩነህ ገምታ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው፣ እሳቸው እንደሚሉት ፓርቲያቸው ዝምታን መርጧል። ምክንያቱ ደግሞ ጉዳዩ ማጣራት የሚያሻው በመሆኑ ነው። ማጣራትና ጥንቃቄ ከጉዳዩ ስስነት አንጻር ቁልፍ ጉዳይ ነው።
መንግስት ራሱንም ነጻ ለማድረግም ሲል ገለልተኛ አካል ተሰይሞ እንዲጣራ አስቻይ ሁኔታ ሊያበጅ እንደሚገባ ያመለከቱት አቶ ጥሩነህ “መንግስትን ሳንጠብቅ ኃላፊነት የሚሰማው አቋም ለመያዝ በፓርቲያችን መዋቅር መሰረት ማጣራት ጀምረናል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ራሔል ባፌ በበኩላቸው “ ማጣራት የእኛ ስራ አይደለም። ፖሊስ፣ መሳሪያና አቅም ያለው መንግስት ነው። ሕዝብ ኃላፊነት የሰጠው መንግስት የሚሰራውን ስራ እንድንሰራ አይጠበቅም” ሲሉ ስለ ገዳዮቹ ማንነት ለማወቅ በፓርቲ ደረጃም ይሁን በግል እየተደረገ ያለ ጥረት ስለመኖሩ ተጠይቀው መልሰዋል።
ዛሬ ላይ ሚዲያዎች፣ ፓርቲዎች፣ የፖለቲካ አመራሮች፣ በውጭ አገር የሚኖሩና ራሳቸውን የሰው ልጆች መብት ተቆጣጣሪ ያደረጉ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደሆኑ የሚናገሩ፣ የመንግስት ካድሬዎች፣ ችግሩ የሚፈጠርበት አካባቢ ያሉ ሰዎችና የሰለባዎች ቤተሰቦች እንዲሁም እማኞች “ ሰዎች ተገደሉ” ከሚለው ውጭ ሲናገሩ አይሰማም። እንዲናገሩ ሲጠየቁ ወይም በዝርዝር በተጠቀሱት አካላት ዘንዳ ስለ ገዳዮች አንስቶ መነጋገር ምክንያቱ ግልጽ ባይሆንም አይወደደም። በተለይ ሚዲያዎች እንደወረደ “ኦርቶዶክሳዊያን” በማለት የንጹሃንን ሞት ከመዘገብ ያዘለለ የማጣራት ለመስራት ሲሞክሩ አይታይም፤
ዶክተር ራሔል ሚዲያዎችን ይወቅሳሉ። ሚዲያዎች ሊመረምሩት የሚገባ ጉዳይ ሆኖ ሳለ አላደረጉትም በማለት ይናገራሉ፤ እሳቸውና ፓርቲያቸው ወይም አብረዋቸው በሕብረት የሚሰሩ ድርጅቶች በዚህ ረገድ ምን እየሰሩ እንደሆነ ሲጠየቁ “ ህዝብ ጥቆማ ሊሰጥ ይችላ። እኛም ልንተባበር እንችላለን። ዋናው ተጠያቂው ግን መንግስት ነው” ባይ ናቸው።
አቶ ጥሩነህ ገምታ መንግስትን በተመሳሳይ ተጠያቂ አድርገው፣ ፓርቲያቸው ጉዳዩን በጥንቃቄ እንደሚያየው ደጋግመው ይገልጻሉ። ክርስቲያኖችም ሙስሊሞችም እንደተገደሉ መስማታቸውን አስታወቀው በስሜት የሚወጡ መረጃዎች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው እንዳያመዝን ጥናት ማድረጉ ላይ ፓርቲያቸው ቅድሚያ መስጠቱን ይገልጻሉ። በራሳቸው መስመር ጥናቱን ሲያጠናቅቁ መግለጫ እንደሚያዘጋጁም አመልክተዋል።
በዓለም ላይ እንደሚሰማው የሚያግቱ፣ በጅምላና በተናጠል ግድያ የሚፈጽሙ፣ ንብረት የሚያወድሙና የተለያዩ እርምጃዎች የሚወስዱ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጥቃት ከፈጸሙ በሁዋላ ኃላፊነት እንደሚወስዱ የዓለምን ልምድ ጠቅሰው የሚናገሩ“ የኢትዮጵያዎቹ አፋኞችና ገዳዮች ጥቃት ፈጽመው ጸጥ ማለታቸው ግራ ያጋባል። ፖለቲካም አይመስልም። ሲያግቱም ገንዘብ እንጂ ሌላ ነገር ሲጠይቁ አይሰማም። ይህ ጉዳዩን ወደ ውንብድና ያወርደዋል” ሲሉ አስተያየት ይሰታሉ። አለያም አድሮ ገሃድ የሚወጣ ጉዳይ ሊኖር እንደሚችል ያስባሉ።
ሰሞኑን በተከታታይ በአርሲ መፈጸሙ የተነገረለት ግድያ ዕምነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው በርካታ በውጭ አገር የሚገኙ የተቃዋሚ ሚዲያዎች ሰፊ የዜና ሽፋን ሰጥተውታል። በመሃል አገርም ተቀምጠው በግል የማህበራዊ ገጻቸው እንደ ቅስቀሳ አይነት ይዘት ያለው መረጃ ያሰራጩም አሉ።
ጥያቄው ግድያውን ተከትሎ የሚነሱ የብስጭት ስሜቶች ሳይሆኑ፣ ድርጊቱ ይህ የብስጭት ስሜት እንዲፈጠር ተብሎ ይፈጸም አይፈጸም ለማጣራት መሰረታዊ የኃላፊነት ስሜትን የሚጠይቁ ጥያቈዎች አለመጠየቃቸው መሆኑን የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
መንግስት በተለይም የአካባቢው መዋቅር በወጉ አፍንጫውን ተይዞ ሊጠየቅ እንደሚገባው የሚናገሩ የሕግ ሰዎች፣ ከላይ እንደተገለጸው ገዳዮችን በምልክት፣ በሚናገሩት ቋንቋ፣ በሚናገሩት ንግግር የድምጽ ቅላጼ፣ በአጠቃላይ ስብዕናቸው አማካይነት፣ የተረፉ፣ ግድያውን ያዩ፣ የተጎጂ ቤተሰቦች፣ ዕማኞች ፍንጭ ሊሰጡ አለመቻላቸው በርካቶችን እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው።
በንጹሃን ሞት የፖለቲካ አጀንዳቸውን የሚጠብሱትን አጥበቀው የሚቃወሙ “ በሰው ደም የግልና የቡድን ፖለቲካ አጀንዳን ማራባት አሳፋሪ ነው፣ ልንቃወመው ይገባል” ይላሉ። እነዚህ ወገኖች በሚመሯቸው ሚዲያዎች አማካይነት ገዳዮችን በመተው፣ መንግስት ላይ ብቻ የሚደረገው ርብርብ ተመሳሳይ ሃዘን ከመስማት ሊታደግ እንደማይችል። እንዲያውም ለወንጀለኞቹ ምሽግ የማበጀት ያህል እንደሆነ የሚናገሩ እየበረከቱ ነው። እነዚህ አካላት ገለልተኛ አካላት የማጣራት ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ አበክረው ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ህዝብ ተቀላቅሎና ተዋልዶ እንደሚኖር የሚናገሩ “ መንግስትን ለማሳጣት ሲባል የሚቀርቡ ዘገባዎች ችግሩን በቂምና ቁርሾ ወደ ሌሎች ስፍራ ሊያዛምቱ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ያሻል” ባይ ናቸው።
አቶ ጥሩነህ ገምታ “ በአማራ ላይ፣ ሆነ በኦሮሞ ወይም በማናቸውም ብሔር አባል ላይ የሚፈጸም ጥቃት ዓላማ የለሽ፣ በንጹህ ሰው ላይ የሚቃጣ ግፍ ነው” ይላሉ። በአንድ ወገን ላይ የተነጣጠረ በሚል የሚወጡ መረጃዎች በጥናት ተደግፈው በዝርዝር መረጃ ይፋ እስካልሆኑ ድረስ ሁሌም ወደ ሕዝብ ሲደርስ ጥንቃቄ እንደሚያሻው ያስጠንቀቃሉ።
ዲክተር ራሔል መንግስት ጉዳዩ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ማድረግ እንዳለበት ያነሱትን አቶ ጥሩነህ ይደግሙታል። አቶ ማሙሸትም ተመሳሳይ አቋም አላቸው።
የአርሲ ዞን አስተዳደ ሃሳቡን እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም “ዛሬ ነገ” በማለት ማፈግፈግ መርጧል። በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ጠንከር ያለ አስተያየት ያቀረቡት ዲያቆን ሄኖክ ጉዳዩ የሚመከታቸው፣ በተለይም ቅዱስ ሲኖዶስ ላይ አግባብ ያለው ጫና ማሳደር እንደሚገባ ጠቁመዋ። ዝረዝር ጉዳይ አንስተን አነጋግረናቸው ለማቅርብ እንሞክራለን።
የኦነግ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊንና መሪን በግል ስልካቸው በማግኘት አሳባቸውን እንዲያካትቱ ያደረገነው ጥረት አልተሳካም። ብልጽግናም በፌደራልና በክልል እንዲሁም በወረዳና ዞን ደረጃ አስተያየት እንዲሰጠ ሞክረን አልተሳካም። ይሁን እንጂ ስማቸውን ያልጠቀሱ የዞኑ አመራር ግዳዩ በተባለው መልኩ ሊጣራ ይገባል። ያም እንደሚደረግ አመልክተዋል።
” በአርሲ ዞን አራት ወረዳዎች ተከሰተ የተባለውን ችግር የሚያጣራ የልዑካን ቡድን የማጣራት ሥራውን በዛሬው ዕለት ጀምሯል ” – የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ” በኦሮሚያ ክልል፣ አርሲ ዞን በጉና፣ በመርቲ፣ በሸርካ እና በሆሎንቆ ዋቢ ወረዳዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች እና ካህናት እንዲሁም በሌሎችም የሃይማኖት ተቋማት አገልጋዮች እና ምዕምናን ላይ ግድያ እና ስቃይ መከሰቱን የሚያሳይ መረጃ መውጣቱን መነሻ በማድረግ ጉዳዩን ከመሰረቱ የሚያጣራ የተለያዩ የባለድርሻ አካላት ተወካዬች የተካተቱበት አጣሪ ቡድን ተቋቁሞ በዛሬው ዕለት የተከሰተውን ችግር በአካል ለማጣራት ችግሩ ወደ ተከሰተባቸው ቦታዎች በመጓዝ ሥራውን በይፋ ጀምሯል ” ሲል አሳውቋል።
” የሉዑካን ቡድኑ የማጣራት ሥራውን ጨርሶ የመጨረሻ ሪፖርቱን ሲያቀርብ በጉዳዩ ላይ በጉባኤችን በኩል ይፋዊ መግለጫ እና ማብራርያ የሚሰጥ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በትእግስት የማጠቃለያ ሪፖርቱን እንዲጠብቅ ጉባኤችን በአክብሮት ይጠይቃል ” ብሏል።
ጉባኤው ” ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ አካላት ኃላፊነት በጎደለው መልክ ከግምት እና ካልተሟላ መረጃ በመነሳት በማሕበራዊ ሚዲያ ጉዳዩን አስመልክተው መረጃዎች መስጠታቸውን ተመልክተናል ” ሲል ገልጿል።
መረጃዎቹ ምን እደሆኑ በግልጽ ያላሰፈረው ጉባኤው ” ይህ ተግባር የማጣራቱን ሂደት የሚጎዳ እና አንዳንድ አካላትን ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ ሊወስድ የሚችል ተግባር በመሆኑ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መረጃ የምታሰራጩ አካላት በሙሉ ከፍ ያለ ጥንቃቄ እንድታደርጉ እናሳስባለን ” ብሏል።
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/profile.php?id=61577410241403
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393





