የእነ ንጉሴ አክሊሉ ድርጅት የአገር መከላከያ ፈርሶ [እንደ ሶማሊያ] በውጭ አገራት የሰላም አስከባሪ እንዲተካ ጠየቀ

Date:

አዲስ ሪፖርተር – የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሠራዊት በውጭ የሰላም አስከባሪ እንዲተካ የሚጠይቅ የሽግግር ሰነድ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በድጋሚ ይፋ ሆነ። ሰነዱ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምርጫ እስከ አርባ በመቶ ሊሳካ እንደሚችል ጎን ለጎን ትንቢቱን አስፍሯል። ሰነዱን ያሰራጨው የቀድሞ የቪኦኤ አለቃ የነበሩት እነ አቶ ንጉሴ አክሊሉ የሚመሩት ድርጅት ነው።

ዶክተር አቻምየለህ ደበላ እንዳዘጋጁት ተገልጾ Save Ethiopia (ኢትዮጵያን አድን) “Ethiopia Path to Democratic Transition: A Scenario-Based Analysis of Governance Models and Sustainable Peace” በሚል ርዕስ ያሰራጨው ይህ ሰነድ ፋኖን፣ ኦነግን፣ ትህነግን እንዲሁም በጥምረት የሚሠሩትን ትጥቅ ያነሱ ኃይሎች ዘርዝሮ ለውጥ ለማምጣት ይችላሉ የሚል እሳቤ እንደሌለው በመቶኛ አስቀምጧል። አንዳንዶቹን “ዋጋ ቢስ፣ አቅም የሌላቸው፣ የጠላቴ ጠላት በሚል እሳቤ የተጣመዱ በባህሪያቸው የማይግባቡ” ብሏቸዋል።

ሰነዱ “ለውጥ እናመጣለን” ጠብ መንጃ ያነሱትን ቡድኖች “ተስፋ የሚጣልባቸው አይደሉም” በማለት በመቶኛ ካስረዳ በሁዋላ ነው፣ የአገር መከላከያ ሰራዊት እንዲበተን በይፋ ባያውጅም በተዘዋዋሪ “የውጭ አገር ሰላም አስከባሪ ይግባ” በማለት የጠየቀው።  ይህ ሰነድ፣ የሰላም አስከባሪ ኃይል በምዕራብ አገራት ድጋፍና በእነሱ ቁጥጥር ሥር እንዲሆን ይጠይቅና፣ መልሶ ስለ ምርጫ በማንሳት የአፍሪካ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የዓለም ዓቀፍ ተቋማት ከተሳተፉ ምርጫው የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ግምቱን ያኖራል።

በ1983 ዓ.ም የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት “የደርግ ሠራዊት” በማለት ከነ ሙሉ መዋቅሩ እንዲፈርስና ለአገራቸው የተዋደቁ በጎዳና ላይ ለማኝ እንዲሆኑ መደረጉን በማስታወሰ ይህ አካሄድ ተመሳሳይና ተመጋጋቢ እንደሆነ በስብሰባው ከሚካፈሉት መካከል ለአዲስ ሪፖርተር ተናግረዋል። “አሁን በተመሳሳይ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት የብልጽግና፣ የዐቢይ በማለት ማጠልሸት ከተጀመረ ሰነባብቷል” የሚሉት እኚሁ የስብሰባው ተካፋይ፤ “ሰነዱን ያዘጋጁት አካላት የውጭ አገር የሰላም አስከባሪ ኃይል መጠየቃቸው መከላከያ ላይ ሲደረግ ከከረመው የማቆሸሽ ዘመቻ የተቀዳና በመናበብ የሚሠራ መሆኑን አመልካች ነው” ብለዋል።

አያይዘውም አገሪቱ በተለያየዩ አቅጣጫዎች ትንኮሳ እየተደረጋባት ባለችበት በዚህ ወቅት በሽግግር ስም የአገር መከላከያ እንዲፈርስ በተዘዋዋሪ ሰላም አስከባሪ ከውጭ እንዲመጣ መጠየቅ ኢትዮጵያን እንደ ሶማሊያ የማለት ያህል እንደሆነ አመልክተዋል። ስብሰባውን የሚካፈሉትም ይህንኑ ለታሪክና ለሕዝብ ለማሳወቅ ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል።

ስብስቡ ከተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን ጀምሮ ከሀገር በመኮብለል ኑሯቸውን በውጪ ያደረጉ ዕድሜ ጠገብ አዛውንቶች ያካተተና ወጣቶች የሌሉበት፤ የሴቶች ቁጥር በጣም ኢምንት የሆነበት እንደሆነ ሰነዱን ሲያሰራጭ ኢትዮጵያ አድን ድርጅት ከዘረዘረው ስም ለመረዳት ትችሏል። በተለይ በዚህ ልክ የተለያዩ ትንታኔዎችን የሚሰጡና ሀገር ለመመሥረት የሚያስችል ሥራ ለመሥራት የተሰባሰቡ ምሑራን፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 91 ሚሊዮን የሚሆነውን ወጣት ያላሳተፈ “ሰነድ” ማዘጋጀታቸው በአካል ብቻ ሳይሆን በሃሳብም ከሀገር መራቃቸውን አመላካች እንደሆነ ሰነዱን ያጋሩን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በተለያዩ አገራት በሰላም ማስፈን በኩል ያበረከተችው አስተዋጾ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በጎረቤት አገራት በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ያሰማራቸው የመከላከያ ሰራዊት በሰላም ማስከበሩ ስራ ሕዝብ “እንዳይወጡብን” በማለት ውለታቸውን በማንሳት ፍቅሩን የሚገልጽላቸው እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። አሁን ላይ ደግሞ የፈረሰውን የአየር ኃይልና ባህር ኃይል ዳግም በማቋቋም ሰፊ መሰረት ይዞ እየተገነባ ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ እያለ እነዚህ በአሜሪካና በተለያዩ የውጭ አገራት የሚኖሩ ቡድኖች እንደ ሶማሊያ የውጭ አገር ሰላም አስከባሪ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ መጠየቃቸው በስብሰባው እንዲሳተፉ ከተጋበዙት መካከል በግልጽ ተቃውሞ እንደሚያስነሳ መረጃውን ካካፈሉን ሰዎች ለመረዳ ተችሏል።

ፎቶ ሰነዱን ያዘጋጅት ዶክተር ዶክተር አቻም የለህ ደበላ

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related