ትህነግ “አፋር ክልልን አልረገጥኩም” አለ፤ አፋር ክልል በምስልና በቪዲዮ ማረጋገጫ አቅርቧል

Date:

ከተሰነጠቀው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር አንዱ የሆነው የእነ ዶ.ር ደብረጽዮን ቡድን የአፋር ክልል መሬትን እንዳልረገጠ ጠቅሶ መግለጫ አወጣ። የአፋር ክልል በበኩሉ “ተወረሩ” ያላቸውን ስድስት ቀበሌዎች ዘርዝሮ፣ በመስልና በቪዲዮ በማስደገፍ ራሱን የመከላከል እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቆ ነበር።

ወረራ መፈጸሙ ተገልጾ ክስ የቀረበበትና በርካታ የዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀሩ በዜናቸው ማረጋገጫ የሰጡበት የእነ ዶክተር ደብረዮን ቡድን ይህን በመቃውም “አንድም የተረገጠ መሬት የለም” ሲል የፌደራል መንግስትን ከሷል።

ከአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ወረራ መካሄዱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ “ካለፉት ጥፋቶች መማር ያልቻለ” በማለት በእነ ዶክተር ደብረጽዮን የሚመራውን የትህነግ አንድ ክፋይ ይከሳል።  አክሎም “ከጥፋቱ የማይመረው ጉጅሌው የትህነግ ቡድን በ26/02/2018 ዓ.ም በአፋር ክልል ወሰን ውስጥ በማግባት ስድስት መንደሮችን በጉልበት በመቆጣጠር ንጹሃንን በሞርታርና በዙ-23 በመደብደብ የተለመደውን የሽብር ተግባሩን በግልጽ ጀምሯል” ሲል ከሷል። ይህን ካለም በሁዋላ ወረራውን ተከትሎ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የሚያሳይ መረጃ በቪዲዮና በምስል ይፋ ሆኗል። ትህነግ በመግለጫው ጦርነት ፍላጎቱ እንዳልሆነ አመልክቶ ወቀሳውን አታጥሏል። ሙሉ መግለጫውን ያንብቡ።

ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰላማዊው እና ፖለቲካዊው ሂደት የሚያናጉ ክስተቶች እንዲሁም የፕሪቶሪያን ስምምነት የሚጎዱ እንቅስቃሴዎችን እየተመለከትን ነው።

ትግራይን ለማናጋትና እርስ በእርስ እንድንጣላ ሆን ተብሎ በአፋር ውስጥ ታጣቂዎች እንዲደራጁ፣ እንዲታጠቁ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እና ድጋፍ በመስጠት እንዲሁም ተልዕኮ በመስጠት በትግራይ ላይ ተደጋጋሚ የወሰን ጥሰት እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል አሁንም እየተደረገ ነው።

ይህ “ሓራ መሬት(ነፃ መሬት)” በሚል ስም በአፋር የሚገኝ ታጣቂ ኃይል ባለፈው ዓመት በተደጋጋሚ በዚህ ዓመት ደግሞ ቀደም ብሎ በኮነባና አብዓላ አቅጣጫ በተደጋጋሚ የመተንኮስ ተግባር ሲፈጽም ቆይቷል።

በመቀጠልም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በደቡብ ትግራይ ራያ አዘቦና ራያ ጨርጨር ከሕዝብና ባለሃብቶች ጋር የያዘውን የልማት ውይይት ለማደናቀፍ ሲባል ከመጋሌ እና ቶንሳ ተነስተው ደደርባ እና ጸሓፍቲ ገረብአገው ድረስ በመሄድ የአስተዳደሩ አመራሮች ያልፉበታል ተብሎ በሚጠበቀው የመቐለ-መኾኒ መስመር ላይ ሁከት ሊፈጥሩ የሚችሉ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

የትግራይ ሕዝብ እና ጊዜያዊ አስተዳደር ግን የውስጥ ችግሮቻችን በውይይት ለመፍታት እና ለሁለቱም ሕዝቦች ወንድማማችነት እና ጉርብትና ክብር በመስጠት፣ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት በመነሳት ሁኔታውን ከመግለጽ ተቆጥበው ቆይተዋል።

አሁንም ቢሆን በትግራይ በኩል ሁከት ወይም አለመረጋጋት እንዲፈጠር በፍጹም አይፈልግም።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ችግር እየፈጠረ ያለው አካል ተመልሶ ከሳሽ በመሆን ትናንት ረቡዕ ጥቅምት 26 ቀን 2018 ዓ.ል የብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የአፋር ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ባወጣው መግለጫ የትግራይ የጸጥታ ኃይሎች ወደ አፋር መሬት ዘልቀው በመግባት ጥቃት እንደፈጸሙ ገልጿል። ይሁን እንጂ ይህ መግለጫ መሠረት የሌለው ሲሆን የተረገጠ የአፋር ወሰን እንደሌለ እና በተቃራኒው እየተፈጸመ ያለው ተግባር ለሰላማዊ እና ታሪካዊ የወንድማማችነት እና የጉርብትና ግንኙነት የማይመጥን እንዲሁም በመኸር ወቅት የትግራይን ሕዝብ ለመጉዳት ሆን ተብሎ የተጠነሰሰ ክፋት መሆኑ ግልጽ ነው።

በፌዴራል መንግሥት በኩል የፕሪቶሪያ ውል በአግባቡ ባለመፈጸሙ ሰላማዊ ሂደቱን እና መተማመንን ከመጉዳት አልፎ የሕዝባችን መከራ እና ስቃይ እንዲቀጥል የሚያደርግ ሲሆን፣ በውጤቱም ሰላማዊውን ፖለቲካዊ ትግል የሚያናጋ መሆኑ ግልጽ ነው።

ይህ ደግሞ የኢትዮጵያንና የአካባቢውን ሰላም የሚያናጋ እና ያልተፈለገ ዳግም ጥፋት የሚያስከትል የጥፋት መንገድ ነው።

ስለሆነም የፕሪቶሪያ ውል ያለ መዘግየት እንዲፈጸም፣ የትግራይ ሕገ መንግሥታዊ ወሰን እንዲረጋገጥ እና ሕዝባችን ደኅንነቱ ተጠብቆ ወደ ቀዬው እንዲመለስ እንዲደረግ እንዲሁም በግዳጅ ትግራይን ለማዳከም የሚደረገው እንቅስቃሴ ታርሞ በተረጋጋ መንገድ ወደ ውይይት እና መፍትሔ እንድንገባ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል።

በሌላ በኩል የሚታዩትን ችግሮች እንደ ዕድል በመጠቀም የውስጥ ችግራችን እንዲወሳሰብ ትግራይ ዳግም የጦርነት ሜዳ እንድትሆን ለማድረግ ሆን ተብሎም ሆነ ባለማወቅ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የትግራይ እና የሕዝቧ መሠረታዊ ጥቅም እና ደኅንነት በአጠቃላይ የሚጎዳ ተግባር ነው።

ስለዚህ አንዱንም ይሁን ሌላውን እየደገፉና እያበረታቱ ትግራይን የጦር ሜዳ ለማድረግ የምትጥሩ አካላት የተለያዩ ምክንያቶችን በመጠቀም በውስጣችን ጥርጣሬ እንዲሰፍን የምትሠሩና ትዕዛዝ ተቀባዮች የሆናችሁ አካላት ከድርጊታችሁ እንዲቆጠቡ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በጥብቅ ያሳስባል።

የትግራይ ችግር በዘላቂነት የሚፈታው በትግራይ እና በትግራዋይ ነው የሚል ጽኑ እምነት ያለው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በውስጣዊ ፖለቲካዊ ችግር የሐሳብ ልዩነት መፈጠሩ መደበኛ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ችግራችን በውይይት እና በመግባባት ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት እያረጋገጠ ልዩነት ያለው የታጠቀ ይሁን ያልታጠቀ ሁሉም አካል ከውይይት እና ከመግባባት ውጭ ትግራይን የሚጠቅም ሌላ መፍትሔ እንደሌለ ይገነዘባል።

በኃይል እና ሕይወት በመክፈል የሚለወጥ ሁኔታ አይኖርም።

አሁንም ቢሆን ዘላቂ ደኅንነትና ቋሚ ሰላም በተአማኒነት የሚረጋገጠው የፕሪቶሪያ ውልን አጥብቆ በመፈጸም መሆኑን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በጽኑ ያምናል። ስለሆነም ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር እና የፕሪቶሪያን ውል ያለ መዘግየት ለመፈጸም ዝግጁነቱን በድጋሚ ያረጋግጣል።

በመጨረሻም መላው የትግራይ ሕዝብ በውስጥም ሆነ በውጭ አሁን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለመጠበቅ እና ለማጠናከር እንዲሁም ብሔራዊ አንድነትን ለማደላደል እንዲታገል በማሳሰብ በዚህ እና በዚያ በሚበተን ወሬ ከትግራይ ጦርነት ተጠቃሚ ነን ብለው እንቅልፍ በሚያጡ ነውረኞች በሚፈጠረው አለመረጋጋት ሳይረበሹ ተረጋግተው በዕለታዊ ሥራቸው ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲረባረቡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ እናቀርባለን።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ባለፉት ጊዜያት ከሕዝባችን ፍትሐዊ ጥያቄ ጎን በመቆም የሕዝቡ መከራ እንዲሰማ የ ዘር ማጥፋት ጦርነቱ በፕሪቶሪያ ውል እንዲቆም ታሪካዊ አስተዋጽኦ አበርክታችኋል። የትግራይ ሕዝብና ጊዜያዊ አስተዳደር ምስጋናቸውን እየገለጹ አሁንም ቢሆን የፕሪቶሪያ ውል በአግባቡ እንዲፈጸም እና ዘላቂና ቋሚ ሰላም ደኅንነት በኢትዮጵያ እና በአካባቢው እንዲረጋገጥ አዎንታዊ አስተዋጽኦአችሁን እንድትቀጥሉ ጥሪ እናቀርባለን።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር

ጥቅምት 27 ቀን 2018 ዓ.ል መቐለ

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related