አሜሪካ በአዲሱ ብሔራዊ ደህንነት ስትራቴጂዋ ከአፍሪካ ጋር ባላት ግንኙነት ላይ መሻሻያዎችን አስፍራለች
አዲስ ሪፖርተር – አሜሪካ ይፋ ባደረገችው አዲስ “የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ስትራቴጂ” ሰነድ ላይ ከዓለም አገራት ጋር የምትገናኝበትንና አብራ የምትሰራበትን መርህ ይፋ አድርጋለች። በዚሁ ሰነድ ላይ እንደተመለከተው አፍሪካም ላይ የምትከተለውን ፖሊሲና የፖሊሲ አቅጣጫ ይፋ አድርጋለች። ፖሊሲዋ ሰጥቶ መቀበል ላይ የተተከለ መሆኑ “እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም” እየተባለ ነው።
ለረጅም ጊዜ የአሜሪካ መርህ በአፍሪካ ላይ ትኩረት አድርጎ የቆየው የሊበራል ርዕዮተ ዓለምን (Liberal Ideology) በዋነኛነት መትከልና በማስፋፋት ላይ ነበር። ይህን አካሄድ የቀየረው የአሜሪካ በአዲሱ ብሔራዊ ደህንነት ስትራቴጂዋ ከቀደመው አካሄድ ይልቅ ፣ አሜሪካ ግጭቶችን ለማርገብ እና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሰፍን የንግድ ግንኙነት ለመፍጠር ከተመረጡ ሀገራት ጋር በሽርክና ልትሰራ መወሰኗን ያሳያል። ይህ የአቋም ለውጥ ዘርዝር አካሄዱን ተረዱ “ሰጥቶ መቀበል” እንደሚሉት ዓይነት መሆኑን እየገለጹ ነው።
አሜሪካ ከአፍሪካ የሚኖራትን ግንኙነት ከእርዳታ ተኮር ወደ ኢንቨስትመንት እና እድገት ተኮር ማሸጋገር እንዳለባት፣ ይህን ማድረግ የአፍሪካን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት እና ድብቅ የኢኮኖሚ አቅም ለመጠቀም እንደሚያስችል በሰነዱ ስለአፍሪካ በተገለጸበት ገጽ 39 ላይ በይፋ ተቀምጧል።
አዲሱ ፖሊሲ ይፋ ባደረገው መሰረት አሜሪካ ግንኙነቶቿ የሚያመጧቸው የድርድር እድሎችን በምሳሌ ይዘረዝራል። አሁን ላሉ ግጭቶች (ለምሳሌ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ሩዋንዳ፣ እንዲሁም በሱዳን) መፍትሄ መፈለግን፣ እና አዳዲስ ግጭቶችን (ለምሳሌ በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ) መከላከል ያለውን የጦርነት ስጋት ያካትታሉ። በተጨማሪም፣ ከእርዳታ እና ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ ሲከተሉ የነበረውን አካሄድ ማሻሻል (ለምሳሌ የአፍሪካ እድገት እና እድል ህግን /AGOA/ ማስተካከል) ወይም ዳግም መቃኘት እንደሚገባ ሰነዱ ጠቅሷል።
በአንዳንድ የአፍሪካ ክፍሎች ዳግም እያንሰራራ ያለውን እስላማዊ የሽብር እንቅስቃሴ፣ የአሜሪካን የረጅም ጊዜ ወታደራዊ ቆይታ ወይም ግዴታዎች ውስጥ በማስገባት በንቃት መከታተል እንደሚያስፈልግ ሰነዱ አመልክቷል። ይህ ሰነድ ይፋ ከመሆኑ በፊት የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ (U.S. Africa Command – AFRICOM) አዛዥ በሆኑት ጄኔራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰን የተመራ ልዑክ ከኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል። በዚሁ ውይይት ማብቂያ ላይ ይፋ እንደሆነው ኢትዮጵያና አሜሪካ ሽብርተኛነትን ለመዋጋት ከቀድሞው የበለጠ ተባብረው እንደሚሰሩ፣ ከዚህ ቀደም ጀምሮ እስካሁን ኢትዮጵያ ሽብረተኝነትን ለመከላከል ያደረገችውን ተጋድሎ ዕውቅና እምደሚሰጠው መመለከቱ አይዘነጋም።
አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ከእርዳታ ወደ ንግድ እና ኢንቨስትመንት መሸጋገር እንዳለበት ያተተው ይህ ሰነድ፣ በዚህም ገበያቸውን ለአሜሪካ ምርቶች እና አገልግሎቶች ክፍት ለማድረግ ቁርጠኛ ለሆኑ፣ ብቁ እና አስተማማኝ ሀገራት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ አመልክቷል። በአፍሪካ ለአሜሪካ ኢንቨስትመንት አፋጣኝ እና አትራፊ ሊሆኑ የሚችሉ ዘርፎች የኃይል (Energy) ዘርፉ እና የወሳኝ ማዕድናት (Critical Minerals) ልማት እንደሆኑም ተጠቁሟል። በዚህ እሳቤና አካሄድ መሰረት አሜሪካ ነግዳ ከማታተርፍባቸው፣ አብራ ሰርታ የጸጥታ ማስተማመኛ እንድታገኝ ከማያስችሏት አገራት ጋር ጊዜዋን አታጠፋም።
በአሜሪካ የሚደገፉ የኒውክሌር ኃይል፣ ፈሳሽ ፔትሮሊየም ጋዝ (LPG) እና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ (LNG) ቴክኖሎጂዎችን ማልማት ለአሜሪካ ኩባንያዎች ትርፍ የሚያስገኝ ሲሆን፣ በወሳኝ ማዕድናት እና ሌሎች ሀብቶች ላይ በሚደረገው ዓለም አቀፍ ፉክክር አሜሪካን ያግዛል።
ጆ ባይደንን አሸንፈው አሜሪካን ለመመራት ዋይት ሃውስ የገቡት ዶናልድ ትራምፕ ” አሜሪካን ዳግም ታላቅ እናድርጋለን” በሚለው ቀዳሚ መርሃቸው መሰረት ዓለምን ያናጉ ውሳኔዎችን እየወሰኑ ነው። ወደ ስልታን እንደመጡ ዩኤስ አይ ዲን መዝጋታቸው አይዘነጋም። በዚህ ሳቢያ አሜሪካ ምንም ለማትጠቀምበትና ለማታተርፍበት በአገራቱ በዕርዳታ ስም ጣልቃ በመግባት ምርጫ፣ ዴሞክራሲ፣ አስተዳድር፣ የፓሪቲዎች ፉክክር ላይ ተቆጣጣሪ ሆና ያሳለፈችበት የኪሳራ ዘመን ያከተመ እንደሆነ ያመላከተው የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ስትራቴጂ በርካታ ጉዳዮችን ያካተተ ነው።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






