ስምረት፡ ምርጫን የሚያደናቅፉ በሕግ ይጠየቁ

Date:

እኔ ከሌለሁኝ ምርጫ አይካሄድም የሚል ኃይል በሕግ ሥርዓት ይያዝ: ስምረት ፓርቲ።

ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ (ስምረት) በትግራይ ክልል ሊካሄድ በታቀደው 7ኛው ሀገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ ዙሪያ ያለውን ጽኑ አቋም ለአዲስ ሪፖርተር አስታቋል። ፓርቲው “የሥልጣን ሽግግር የሚካሄደው በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በሕዝብ ምርጫ ብቻ መሆን አለበት” ሲል በድጋሚ አረጋግጧል። በቅርቡ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር / ትህነግ በኩል ምርጫውን አስመልክቶ የቀረበውን ቅድመ ሁኔታ በተመለከተም ፓርቲው ግልጽ ምላሽ ሰጥቷል።

የስምረት ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ አባልና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ ብርሃነ ገብረኢየሱስ ለአዲስ ሪፖርተር እንደተናገሩት ፤ፓርቲያቸው በግንቦት ወር የሚካሄደው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍና ለመወዳደር እንዲሁም ለሕዝብ አማራጭ ሐሳብ ለማቅረብ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዚህ ሂደትም የዕጩዎች ዝግጅትና ምልመላ ሥራን እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል። ፓርቲው የትግራይም ሆነ የሀገሪቱ የስልጣን ሂደት በምርጫ እና በሕዝብ ድምፅ ብቻ መካሄድ እንዳለበት በፅኑ በማመን በሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ትግሉን ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ ውጪ ያለው የኃይል አማራጭ ጠቃሚ እንዳልሆነ በማልከት አስጠንቅቀዋል።

ስምረት ፓርቲ ማንኛውም የፖለቲካ ቡድን ሥልጣንን በኃይል ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ሙከራ እንደማይቀበል በግልጽ አስታውቀዋል። ፓርቲው ራሱን “የስክርቢቶና የሐሳብ ታጋዮች እንጂ የመሳሪያና የኃይል ታጋዮች አይደለንም” በማለት ከትጥቅ ትግል የራቀ እሳቤና እምነት እንዳለው አመልክቷል።

ፓርቲው የትህነግን ቅድመ ሁኔታ “እኔ ከሌለሁኝ ምርጫ ክልሉ ውስጥ አይካሄድም” እንዲሉ ዓይነት መሆኑን ገልጿል። አክሎም ማንኛውም ኃይል በሀገሪቱ ሕግ መሠረት ሥርዓት መያዝ እንዳለበትም አሳስቧል። ሥርዓትን የማስያዝ ኃላፊነት በሀገሪቱ ሕግ መሠረት የፌደራል መንግሥት መሆኑን አብራርተዋል። ይህ አቋም “የስልጣን ሽግግር ሂደት በዲሞክራሲያዊ ተቋማት እና በሕግ የበላይነት መመራት አለበት” የሚለውን መሰረታዊ መርህ ፓርቲው አጥብቆ እንደሚያምን የሚያሳይ እንደሆነም አስታውቋል።

ምንም እንኳ ፓርቲው ለምርጫው ለመሳተፍ ጽኑ ፍላጎት ቢኖረውም በትግራይ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ ለፖለቲካ እንቅስቃሴ እንቅፋት መሆኑን አቶ ብርሃነ ጠቁመዋል። ፓርቲው የመስራች ጉባዔ ስብሰባውን አዲስ አበባ ለማድረግ የመረጠበት ዋና ምክንያትም በክልሉ ውስጥ ያለው ይህ የፀጥታ ችግር መሆኑን አስረድተዋል።

በክልሉ ውስጥ ሰው በሰላም ወጥቶ ለመግባት እንኳ የሚቸገርበት ሁኔታ መኖሩን በመጥቀስ ለሰላማዊ ፖለቲካዊ ሥራ መሠረታዊ የሆነው ሰላም እና ፀጥታ የማረጋገጥ ጉዳይ የፌደራል መንግሥት እና የክልሉ መንግሥት ዋና ኃላፊነት መሆኑን አሳስበዋል። የክልሉ መንግሥት በኃላፊነት ቦታ ላይ ተቀምጦ የሚጠበቅበትን የሥራ ድርሻ በአግባቡ መወጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ የሰላምና የዲሞክራሲ መርሆዎች በሀገር ውስጥ እንዲሰፍኑ ቁርጠኛ አቋም ማሳየቱ በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ተስፋ ሰጭ እርምጃ እንደሆነ ኃላፊው ተናግረዋል።
በክልሉ ያለው የፀጥታ ስጋት ቢኖርም ፓርቲው በምርጫ ለመሳተፍ ስራውን እየሰራ መሆኑን ለአዲስ ሪፖርተር ያስረዱት የፓርቲው የኮሙኒኬሽን ኃላፊ፣ በሀገሪቱ ታሪክ የስልጣን ሽግግር በሕዝብ ድምፅ ብቻ ሊረጋገጥ እንደሚገባ አሳስቧል።
ከጥላቻና ከብጥብጥ ይልቅ በምክንያታዊ ሐሳቦች እና በሰከነ ውይይት የሚመራ ጤናማ የፖለቲካ ባህል እንዲዳብር መሠረት መጣል እንደሚገባ በማሳሰብ፣ በመሆኑም የፌደራል መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት በማረጋገጥ ፓርቲዎች ያለስጋት በሰላም ተንቀሳቅሰው አማራጭ ሐሳብ የሚያቀርቡበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት ጠቁመዋል። የፓርቲው አቋም የዴሞክራሲያዊ መርሆዎችን ለትግራይ ሕዝብም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያውያን ማስረጽ ትልቅ ትርጉም እንዳለው መክረዋል።

የዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ (ስምረት) በክልሉ የፀጥታ ሁኔታና በምርጫ ላይ ያሳየው ጽኑ አቋም በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ትልቅ ትኩረት ስቧል። የፖለቲካ ተንታኞች እና የሕግ ባለሙያዎችም በሰላማዊ ትግል እና በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተውን የስምረት ጥሪ አበረታች እንደሆነ ነግረውናል።

አዲስ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ክብሮም ወልደፃዲቅ ስምረት ፓርቲ የኃይል አማራጭን ሙሉ ለሙሉ በመቃወም በምርጫ የመሳተፍ ቁርጠኝነቱን ማሳየቱ ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ምሳሌ እንደሆነ ጠቅሰዋል። በጦርነትና አለመረጋጋት በሰፊው ለተጎዳ ክልል የስክርቢቶና የሐሳብ ታጋዮች የሚል አቋም ማቅረቡ በትግራይ ውስጥም ለሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር በር እንደሚከፍት ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ፓርቲው የገለጸው የፀጥታ ችግር አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመው ምርጫ ቦርድና የፌደራል መንግሥት በክልሉ የሚደረጉ የፀጥታና የደኅንነት ሁኔታዎችን በግልጽ በመቆጣጠር ሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች እኩልና ያለስጋት መንቀሳቀስ የሚችሉበትን አካባቢ እንዲፈጥሩ አሳስበዋል። እኔ ከሌለሁኝ ምርጫ አይካሄድም የሚል አካል በሕግ ሥርዓት መያዝ አለበት የሚለው የስምረት ጥያቄ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ለሚደረገው ጥረትም ትልቅ ድጋፍ የሚሰጥ እንደሆነም አመልተዋል።

የሕግ ባለሞያ አቶ አለምሰገድ እስጢፋኖስ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግና ሕገ መንግሥት የሥልጣን ሽግግር የሚከናወነው በምርጫና በሕዝብ ድምፅ ብቻ መሆኑን በግልጽ አስቀምጠዋል።

ስለሆነም የትኛውም አካል በኃይል ምርጫን ለማደናቀፍ የሚያደርገው ጥረት የሕገ መንግሥት መሻር ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ሕጉ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በሰላማዊ መንገድ የሚካሄደውን የፖለቲካ ውድድር ማክበር እንዳለበት ይደነግጋል። የፌደራል መንግሥትም በሀገሪቱ ሕግ መሠረት ሰላምንና ፀጥታን የማስከበር ዋነኛ ኃላፊነት ስላለበት በትግራይ ክልል ሰላማዊ ምርጫ ለማካሄድ እንቅፋት የሚሆኑ ማናቸውንም አካላት በሕግ ሥርዓት የመያዝ ግዴታ አለበት ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

የስምረት ፓርቲ በትግራይ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር ለምርጫው ዝግጅት ዋና እንቅፋት መሆኑን በግልጽ ማስታወቁ፣ አሁን ኳሱ ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሜዳ ላይ ነው። ቦርዱ በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ፓርቲዎች በሰላም ተንቀሳቅሰው መወዳደር የሚችሉበት ደረጃ ላይ መድረሱን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል። የፀጥታው ሁኔታ ካልተረጋገጠ ቦርዱ የምርጫውን ሂደት በክልሉ ውስጥ ለማካሄድ ሊወስዳቸው የሚችሉ አማራጭ ዕርምጃዎች ምን እንደሆኑ ግልጽ ማድረግ እንዳለበት አዲስ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አዲስ አበባ የሚገኙ የትግራይ ትርወላጆች አስታውቀዋል። በዚህ አሳሳቢ የፀጥታ ጉዳይ ላይ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምን ምላሽ ወይም አቅጣጫ ሊሰጥ እንደሚችል በርካቶች በትኩረት የሚጠብቁት ጉዳይ በመሆኑ የቦርዱን አስተያየት ለማካተት ያደረኘው ሙከራ አልተሳካም።

ትህነግ ለውጡን ተከትሎ በራሱ አነሳሽነት ወደ ትግራይ ካቀና በሁዋላ ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጪ ምርጫ ማካሄዱ፣ ለተቀሰቀሰው አውዳሚ ጦርነት ምክንያት መሆኑን የሚናገሩ፣ አሁን ላይ ካለው ውጥረት ጋር ጉዳዩ ወደ ግጭት እንዳያመራ ስጋት አላቸው።

በቀርቡ በክልሉ ጊዚያዊ መሪ ታደሰ ወረደ የተመራ ልዑክ አዲስ አበባ በመገኘት ምርጫ ቦርድ የጣለውን እገዳ እንዲያነሳ መጠየቁ አይዘነጋም። ከታደሰ ወረደ በቀር ሌሎቹን ማናገር ያልፈለጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥያቄው ለምርጫ ቦርድ ብቻ የሚቀርብና ምርጫ ቦርድ ብቻ የሚወስነበት እንደሆነ በመግለጽ መልስ መስጠታቸውን የተለያዩ ምንጮች ማመልከታቸው አይዘነጋም።

በቀድሞ የወታደር ማዕረጋቸው የሚጠሩት ታደሰ ወረደ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች ስኬታማ እንደነበር የጠቆሙ፣ በቀጣይ የትግራይ ሁኔታ እንደሚቀየር ዕምነት እንዳላቸው እየጠቆሙ ነው። ታደሰ ወረደ አብረዋቸው የመጡትን ይዘው አሜሪካና እንግሊዝ ኤምባሲ “ጣል ጣል አደረጋችሁን” በሚል ላቀረቡት ዝርዝር ዕርዳታ የተሰጣቸው መልስ ” ከሻዕቢያ ጋር የጀመራችሁትን ኝኙነት አቁሙ፣ ከፌደራሉ መነግስት ጋር ተስማምታችሁ ስሩ” የሚል መሆኑ ተስፋውን እንደሚያለመልም እነዚሁ ወገኖች አስታውቀዋል።

ትህነግ ለምርጫ ወደ ትግራይ የሚመጣ ማናቸውም ፓርቲም ሆነ ዕጩ እንደሚታሰር በገሃድ ማስታወቁ አይዘነጋም። ትህነግ እንደሚለው የፌደራል መንግስት ጫና እያደረሰበት ነው። የፌደራል መንግስት ኝ ትህነግ በተከታታይ ለሚያወጣው መግለጫ ምላሽ አይሰጥም።

Website፡ https://addisreporter.com/

Email፡ info@addisreporter.com

Telegram፡ https://t.me/addisreporter2

X፡ https://x.com/addisreporter

Phone no ፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

“አሳጋቾቹን ካህናት ስም ዝርዝር ይፋ እናደርጋለን”

አዲስ ሪፖርተር - የወረታ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ...

ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ነፃ የሃሳብ ሪፐብሊክ፣ የሁምቦልድት ፍልስፍና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሪፎርም እይታ

ቢልዱንግ እና የሃሳብ ትውልድ እሳቤዎች ሲቀናጁ ምሁራን የቆዩ የትርክት...

የኤርትራ አፋር ተቃዋሚ ድርጅቶች ግንባር ፈጠሩ፤ “ስምምነቱ ለሻዕቢያ አስደንጋጭ መርዶ ነው” አቶ አብዲ ሼኽ መሐመድ

አዲስ ሪፓርተር - በኤርትራ የሚንቀሳቀሱት ሁለት የአፋር ተቃዋሚ ድርጅቶች...