ስለ አፍሪካ አህጉር ነፃ የንግድ ቀጠና ግንዛቤ ያላቸው አስራ ሁለት በመቶ አያልፉም
አዲስ ሪፖርተር – በኢትዮጵያ ከተጠቃሚዎቹ ጋር “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” እንደሆነ የተነገረለት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) በአፍሪካ ህብረት (AU) የተፈረመ የዘመኑ ትላቅ ሰነድ የተባለለት ነው። ስምምነቱ ይፋ ሲሆን እንደተሰማው በአፍሪካ ንግድን ለማሳደግ፣ ኢንዱስትሪዎችን ለማነቃቃት እና ከታሪፍ ጋር የተያያዙ እንቅፋቶችን በማስወገድ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማሳደግ ያለመ ስለመሆኑ ነው። ይህ 55 የአፍሪካ አገሮችን ያገናኛል፣ በዓለም ላይ ትልቁን የነፃ ንግድ ቀጠና ይመሰርታል፣ ጉልህ የሆነ የኢኮኖሚ ጥቅሞችን፣ የድህነት ቅነሳን እና የስራ ፈጠራን አዋህዶ ሰፊ ገበያን ይፈጥራክ ተብሎ ተስፋ የተደረገበት ስምምነት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያውቁት ወይም እንዲተዋወቁት የተደረጉት ምን ያህሎቹ ናቸው?
ይህ ለአንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን የአህጉሪቷ ሕዝብ የተዋሃደ ገበያ በመፍጠር እስከ 3.4 ትሪሊዮን ዶላር የሀገር ውስጥ ምርት ለመገበያየት አልሞ የተነሳውና እስከ ዘጠና በመቶ ታሪፎችን መቀነስ እና ከታሪፍ ጋር የተያያዙ ማነቆዎችን በማስወገድ በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለውን ንግድ በማሳደግ ረገድ ተስፋ የተደረገበት እድል አስመልክቶ ጭራሹኑ ግንዛቤው የሌላቸው የአገራችን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዳሉ በጥናት ተረጋግጧል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና በአፍሪካ አጀንዳ 2063 የልማት ማዕቀፍ ከተያዙ ግዙፍ አህጉራዊ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ስር ከሰደደ ድህነት እንደሚያላቅቅ የተነገረለት ይህ ፕሮግራም የንግድ ቀተናዊ ፅር ሚኒስቴር እያደመቀ ከሚያወጣቸው የስኬት ሪፖርቶች ጋር የሚጣረስ እንደሆነ የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ። በ2023 የአፍሪካ ሕብረት የዓመቱን መሪ ቃል”የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ትግበራን ማፋጠን” አድርጎ በርብርብ ተገብራዊ ሊያደርገው የተነሳው አፍሪካን በንግድ የማስተሳሰር ዕቅድ በኢትዮጵያ እውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚለውና እንደሚያሰራጨው ሪፖርት ስኬታማ ነው? በዚህ ሪፖርት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን አሳብ ለማካተት ቢሞከርም ስላካቸው ስለማይመልስ ማካተት አልቻልንም።
የኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) ተሳትፎ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ለሚሆን ህዝብ የገበያ በር ይከፍታል ተብሎ የታለመ ነበር። ሆኖም የነጻ ወጠናው በር ለብዙዎቹ የኢትዮጵያ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች (SMEs) ክፍት ይሆናል ተብሎ ቢታመንም የታሰበውና በተግባር የታየው ልዩነቱ የሰማይና የምድር እንደሆነ የተረጋገጠው በዳታና መረጃ በተደገፈ ጥናት ነው።

እ.ኤ.አ በህዳር 2025 የወጣው እና በዩኤንዲፒ (UNDP) ድጋፍ የተደረገው “የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተወዳዳሪነት ፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፍ ቅንጅት “የኢትዮጵያ ጉዞ ወደ AfCFTA ትግበራ” ጥናት እንዳለው የኢትዮጵያ ለስምምነቱ ያላት ቁርጠኝነት በወረቀት ላይ ጠንካራ ቢሆንም የአገሪቱ ትናንሽ የንግድ ተቋማት ግን በተግባር ተጠቃሚ ለማድረግ በቂ ዝግጅት አላደረጉም።
በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ድጋፍ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ያጠናው ጥናት በተለያዩ አግባብ ያላቸው ዳታዎችን አስደግፎ የተሰራ ነው። በጥናቱ ጥቅል አሳብ ላይ እንደሰፈረው የአፍሪካ ነጻ ንግስ ተቋማትና የአገራችን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ገና የተዋወቁ አይመስልም። መረጃዎቹ እንደሚያሳዩት ነገሩ “ፍየል ወዲህ፣ ቅዝምዝም ወዲያ” እንዲሉ ዓይነት ነው።
በዋና ዋና የኢትዮጵያ ከተሞች በሚገኙ 355 ኢንተርፕራይዞች ላይ የተደረገው ይህ ጥናት እንደሚጠቁመው በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ አህጉር ውስጥ በንግድ እንቅስቃሴ ላይ የተሰማሩት ኢንተርፕራይዞች 11.4 በመቶ ብቻ ናቸው። ይበልጥ አስገራሚው ደግሞ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ከሚያካሂዱት ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት ስራውን የሚሰሩት ባልተጠናከረ (ኢ-መደበኛ) መንገድ ነው። 88 በመቶ የሚጠጉት ኢንተርፕራይዞች ትኩረታቸው ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ገበያ ላይ ብቻ የተገደበ ነው። ይህ የሆነው ደግሞ የገበያ ዕድል ጠፍቶ ሳይሆን፣ ቀጠናዊ ተደራሽነታቸውን ለማስፋት የሚረዱ ሥርዓቶች እና ድጋፎች ባለመኖራቸው ነው።
እንደ ጥናቱ ገለጻ የኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ፖሊሲዎች አሁንም ትኩረት የሚያደርጉት በአገር ውስጥ ተወዳዳሪነትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ሲሆን እንደ የታሪፍ ነፃነት፣ የንግድ እንቅፋቶችን ማስወገድ እና የአህጉራዊ የባለሙያዎች ዝውውር ላሉ የAfCFTA ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው። ይህ ወደ ውስጥ ብቻ የሚመለከት አካሄድ የደረጃዎች ዝግጅትና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ስራዎችን በማዘግየት የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች በአህጉራዊ የንግድ ሰንሰለት ውስጥ እንዳይገቡ እንቅፋት መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል።
የድርጅቶች መጠንና አቅም በንግድ ተሳትፏቸው ላይ ግልጽ ተጽዕኖ አለው። ጥናቱ እንደሚያሳየው በዓመት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያላቸው ተቋማት የወጪ ንግድ ተሳትፎ 35 በመቶ ሲሆን፤ ከ1 ሚሊዮን ብር በታች ገቢ ያላቸው ግን 4.1 በመቶ ብቻ ነው።

በጥናቱ መሰረት የሠራተኛ ብዛትም በመቶኛ ሲሰላ ያሳየው ተመሳሳይ ውጤት ነው። ከ100 በላይ ቋሚ ሠራተኞች ያሏቸው ድርጅቶች 45.8 በመቶ የወጪ ንግድ ተሳትፎ ሲኖራቸው፣ ከ10 እስከ 50 ሠራተኞች ያሏቸው ግን ተሳትፏቸው 5.8 በመቶ ብቻ ነው። በተጨማሪም በፈጠራ፣ በጥራት ወይም በብራንድ ምርታቸውን የሚለዩ ተቋማት በቀጠናዊ ገበያው ስኬታማ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑ አመልክቶ ይህም በAfCFTA ዕድል መጠቀም ያለውን እሴት የመጨመር አስፈላጊነትን ያሳያል።
ለትግዳሮቶቹ ዋና ዋናዎቹ እንቅፋቶች አንዱ የግንዛቤ ማነስ ነው። ጥናቱ እንደሚያሳየው ለAfCFTA ንግድ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነን የሚሉት 13.99 በመቶ ብቻ ሲሆኑ 17.78 በመቶው ደግሞ ስለ ስምምነቱ ምንም ዓይነት እውቀት የላቸውም። የሥልጠና ዕድሎችም በጣም አነስተኛ ናቸው። ተዛማጅ ሥልጠና ያገኙት ኢንተርፕራይዞች 11.43 በመቶ ብቻ በመሆናቸው ወደ ዘጠና በመቶ የሚሆኑት የንግድ ተቋማት ከኢትዮጵያ ድንበር ውጭ ለመወዳደር የሚያስፈልገው እውቀትና ክህሎት ሳይኖራቸው ቀርተዋል።
ምንም እንኳን የሴቶችና ወጣቶች የድጋፍ ማዕቀፎች ቢኖሩም፣ ጥናቱ እነዚህ ፖሊሲዎች ወደ ተጨባጭ የንግድ ውጤት መለወጥ እንዳልቻሉ ያሳያል። የኢትዮጵያ የማብቃት ስራዎች በንድፈ-ሀሳብ ደረጃ ከAfCFTA አካታችነት ግቦች ጋር ቢጣጣሙም የንግድ ተኮር እርምጃዎች፣ የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በጀት እና ቀጠናዊ ተሳትፎን የሚለኩ ግልጽ አመልካቾች ይጎድላቸዋል። በዚህም ምክንያት አህጉራዊ ንግዱ ሲሰፋ በሴቶችና ወጣቶች የሚመሩ ድርጅቶች ወደ ጎን የመገፋት ስጋት አለባቸው።
የፋይናንስ ተደራሽነት ብቻውን መፍትሄ ሊሆን አልቻለም። የወጪ ንግድ ተሳታፊዎች ከሌሎቹ በበለጠ (69.23 በመቶ) ብድር ያገኙ ቢሆንም ብድር ማግኘት ብቻውን የወጪ ንግድ ተሳትፎን በከፍተኛ ሁኔታ እንደማያሳድገው ጥናቱ ጠቁሟል። ያለ ስልጠና፣ ቀላል የንግድ አሰራር እና የገበያ ተደራሽነት ድጋፍ ብድር የሚኖረው ፋይዳ ውስን ነው። ውጤም አያመጣም።
በዩኤንዲፒ (UNDP) ድጋፍ የተደረገው ጥናት የኢትዮጵያ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከየአፍሪካ አህጉር ነጻ የንግድ ቀጣና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መለወጥ ያለባቸውን ነጥቦችም በዝርዝር አስቀምጧል። ጥናቱ በመንግሥት ተቋማት መካከል የአፍሪካ የነጻ ንግድ ቀጠና ትግበራን የሚከታተልና የሚመራ ራሱን የቻለ አካል እንዲቋቋም ማድርገን ጨምሮ ጠንካራ ብሔራዊ ቅንጅት እንዲኖር ጥሪ ያቀርባል። ሪፖርቱ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የሥልጠና ሥራዎች አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት የሰጠ ሲሆን እስካሁን ከ12 በመቶ ያነሱ ኢንተርፕራይዞች ብቻ ስለ አፍሪካ አህጉር ነጻ የንግድ ቀጣና ተዛማጅ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ማግኘታቸውን ገልጿል።
የጉምሩክ ሥርዓቶችን ማቅለል፣ የጥራት ደረጃዎችን ማጣጣም እና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ሂደቶችን ለአነስተኛ ቢዝነሶች ምቹ ማድረግ ትናንሽ ተቋማት ወደ ቀጠናዊ ገበያ እንዲገቡ የሚረዱ ወሳኝ እርምጃዎች እንደሆኑ ተለይተዋል። በተጨማሪም ጥናቱ ሴቶች እና ወጣት ስራ ፈጣሪዎች ከፖሊሲ ቁርጠኝነት ባለፈ የንግድ ተኮር ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ያሳስባል። እነዚህ ማሻሻያዎች ካልተደረጉ ግን፣ AfCFTA ሁሉንም ያሳተፈ የዕድገት ሞተር ከመሆን ይልቅ በጥቂቶች ብቻ የሚታጠር ዕድል ሆኖ የመቅረት ስጋት እንዳለው ሪፖርቱ ይገልጻል።
በዩኤንዲፒ ድጋፍ የተደረገው ይህ ጥናት መልእክቱ ግልጽ ነው። AfCFTA ለኢትዮጵያ ትልቅ ዕድል ቢሆንም ስኬቱ የሚመሰረተው ትናንሽ የንግድ ተቋማት በሚያገኙት ድጋፍ ላይ ነው። የተቀናጀ አሰራር፣ ቀላል የንግድ ስርዓት እና የታለመ የአቅም ግንባታ ካልተደረገ AfCFTA በተግባር ከመዋል ይልቅ በፖሊሲ ደረጃ ብቻ ሆኖ ሊቀር ይችላል። ለኢትዮጵያ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የአህጉራዊ ንግድ ተስፋን ወደ እውነተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር ከቁርጠኝነት ባለፈ ወደ ተግባራዊ እርምጃ መሸጋገር ወሳኝ እንደሆነ ገልጿል።
በአፍሪካ ደረጃ በዚህ ጥናት ባለመከታተሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ደረጃ ከሌሎች አገራት አንጻር ምን ያህል ትጋት እንዳለው በዚህ ሪፖርት አልተካተተም። ፕሮግራሙ ትግበራ ላይ ሰፊ ተግዳሮች እንዳለው አንዳንድ መረጃዎች አሉ። በ2023 ናይሮቢ በተካሄደው የየአገራቱ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ መፍትሄ መቀመጡ አይዘነጋም።
በተለያዩ የመንግስት መገናኛዎች የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርን በመጥቀስ የሚወጡ መረጃዎችና ዜናዎች ሰፊ ስራ መሰራቱን የሚጠቁም ቢሆንም፣ የቀረበው ጥናት እንደሚያመልክተው ነገሩ “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” እንዲሉ ነው። ሚኒስቴት መስሪያ ቤቱ ሌላ መረጃ ካለው ለማስተናገድ ዝግጁ ነን።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






