“የአዕላፋት ዝማሬ” ከመስቀል አደባባይ እስከ ዓለም ዳርቻ ኢትዮጵያን የተረከ፣ ሟርትን የሰበረ ታሪካዊ ድግስ

Date:

የአዕላፋት ዝማሬ እንደምታው ብዙ ነው። ከዝግጅቱ ጀምሮ የታየበት መንፈሳዊ ልዕልና ለኢትዮጵያ ታሪክ ሆኖ የሚቀርብ፣ የአሳቡ አመንጪዎችንም ሆነ ተባባሪዎች ክብር የሚያሰጥ፣ ለእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያዊያን ሃሴትን የሆነ፣ ሲመከቱት ማራኪ፣ አብረው ሲያዜሙ ነብስን የሚያረሰስርስ … እንደ “የአዕላፋት ዝማሬ” ያሉ ግዙፍ መንፈሳዊ መርሃ ግብሮች በመንግስት ሙሉ ድጋፍ፣ ጥበቃ እና እውቅና በሰላም ሲከናወኑ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ማሳየትም ኢትዮጵያ ላይ የሚያሟርቱትን በቁም የማድረቅ ያህል ነው። በውጭ ሀገራት በሚኖሩ አንዳንድ የዲያስፖራ ክፍሎች የሚነዙትን አሉታዊ ትርክቶች ለማፍረስ ወሳኝ መሳሪያ ነው። ፅንፈኛው ዲያስፓራ በተለያዩ መድረኮች “መንግስት አማኞችን ያሳድዳል” ወይም “በኢትዮጵያ የሃይማኖት ነፃነት የለም” በሚል የሚሰራጩ የተዛቡ መረጃዎችን የሚአመክን ነው። በኢትዮጵያ የሃያማኖት ነጻነትም ሆነ ልዕልና ከላካይ የሌለበት ለመሆኑ በመስቀል አደባባይ ይፋ ታይቷል።

የኢትዮጵያ መንፈሳዊ እሴቶች እንደ ፐብሊክ ዲፕሎማሲና የብሄራዊ ጥቅም ማስከበሪያ መሳሪያ

በአለባቸው ጉብሳ | ነጻ አስተያየት

ኢትዮጵያ የክርስትና እና የእስልምና እሴቶችን ለሺህ ዓመታት በሰላም አቅፋ የያዘች ሀገር እንደመሆኗ፣ እንደ “የአዕላፋት ዝማሬ” ያሉ መርሃ ግብሮች የሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓት ብቻ ሳይሆኑ የሀገር መለያ ምልክቶች (National Brand) ናቸው። እነዚህ ሁነቶች ኢትዮጵያ በውስጧ የያዘችውን ረቂቅ ስልጣኔ፣ የስነ-ምግባር ልዕልና እና ማህበራዊ ትስስር ለውጭው ዓለም የሚያሳዩ አብነቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምዕመናን ማህበር በሆነው ጃንደረባው በየዓመቱ የገናን በዓል መሰረት በማድረግ በዋዜማው “የአዕላፋት ዝማሬ” የተሰኘ በመስቀል አደባባይ ሰፊ ቁጥር ያላቸው ምዕመናን በተገኙበት የምስጋና መዝሙር እና ፀሎት ያካሄዳል። ይህ መርሃ ግብር የኦርቶዶክስን ስርአትና ወግ ባከበረ መልኩ ይፈፀማል። የስርዓተ አምልኮው ድባባ፣ የሻማ ማብራት ሰነ ስርዓቱ፣ ዝማሬው፣ ሽብሸባው እጅግ የሚያስደንቅ እና ለተመልካች ሌላ ፕላኔት እንጂ ሃገር ውስጥ እየተፈፀመ ያለ ኩነት አይመስልም፣  እጅግ ግሩም ነው። የሕዝቡ ስልጡንነት፣ ጨዋነት፣ ሥነ-ስርዓት ፤ ባህሉንና ትውፊቱን፣ ወግ ማዕረግ አክባሪነት በግልፅ ያሳያል። በዚች አገር ተስፋ እንዳንቆርጥ ከሚያደረጉት አያያዥ ሙጫዎች መካከል እደዚህ አይነት ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ናቸው።

ይህ የህዝብ ስልጡንነት መገለጫ፣ በምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች ዘወትር የሚሳለውን የትርምስ፣ የረሃብና የጦርነት ምስል በመሰረቱ የሚቀይር ኃይል አለው። በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ በአንድነት ቆሞ ያለምንም ግርግር መንፈሳዊ ምስጋና ሲያቀርብ ማየት፣ ሃገራችን ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎችና ለዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ አስተማማኝ የቱሪዝም መዳረሻ፣ የተረጋጋ ማህበራዊ መሰረት ያላት እና ታላቅ የባህል ማዕከል መሆኗን በተግባር የሚያስገነዝብ ነው።

በዚህ ፅሁፍ እንዲህ አይነቶቹ ኩነቶች ከአሁናዊ ቀኝ ዘመም የዓለም የዘመን መንፈስ ጋር ስላለው ግንኙነት፣ እንደ ሃገራዊ ለስላሳ ሃይል በመጠቀም ለቱሪዝም፣ አሉታዊ ትርክቶችን ለመመመከት እና ሌሎች ብሄራዊ ጥቅሞችን ለማስከበር እንደ ውጭ ጉዳይ ግብ ማስፈፀሚያ መሳሪያ ሊውሉ እንደሚችል እናያለን።

የኢትዮጵያ “ለስላሳ ኃይል” እንደ ውጭ ጉዳይ መሳሪያ

ኢትዮጵያ በመደበኛው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና በፖለቲካዊ ንግግሮች ብቻ ሳትወሰን፣ ያሏትን ታሪካዊና መንፈሳዊ ሀብቶች እንደ ስልታዊ ተፅዕኖ መፍጠሪያ (Leverage) መጠቀም ይኖርባታል። እንደ አድዋ ድል ያሉ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌቶች፣ የሺህ ዓመታት ዕድሜ ያላቸው የሃይማኖት በዓላትና ጥንታዊው የሃገረ-መንግስት ታሪክ ተራ ትርክቶች ሳይሆኑ፣ በዓለም አቀፍ መድረክ የሀገሪቱን ክብርና ተሰሚነት ከፍ የሚያደርጉ የዲፕሎማሲ መሳሪያዎች ናቸው። በአሁኑ ወቅት ዓለም የ”እሴቶች ትግል” ውስጥ ባለችበትና የጋራ ስሜት (Common Sense) በፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ በሚፈጥርበት ዘመን፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው እነዚህን የህዝብ ሀብቶች እንደ ግብ ማስፈፀሚያ ሊጠቀምባቸው ይገባል። የኢትዮጵያን የሦስት ሺህ ዓመት የታሪክ ጉዞ ከወቅታዊው መንፈሳዊ ንቅናቄና እንደ “የአዕላፋት ዝማሬ” ካሉ ህዝባዊ ትርኢቶች ጋር አቀናጅቶ ማቅረብ፣ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የሞራል የበላይነት በፅኑ መሰረት ላይ ይገነባዋል።

ይህ የ”ለስላሳ ኃይል” አቀራረብ ኢትዮጵያ በጎረቤት ሀገራት፣ በአፍሪካና በታላላቅ ኃያላን ዘንድ ያላትን ገፅታ ይቀይረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እነዚህን እሴቶች እንደ ዲፕሎማሲያዊ ጥሬ ዕቃ በመጠቀም፣ ኢትዮጵያ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት ብቻ ሳትሆን ዛሬም ድረስ የራሷን ወግና ማንነት ጠብቃ የምትኖር ንቁ ማህበረሰብ ያላት ሀገር መሆኗን ማሳየት ይችላል። እንዲህ ያለው ብልህ የዲፕሎማሲ አካሄድ፣ ሀገሪቱ በታላላቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ያላትን የመደራደር አቅም (Bargaining Power) ከመጨመሩም በላይ፣ በሉዓላዊነቷና በብሔራዊ ጥቅሟ ላይ ለሚመጡ ማናቸውም ጫናዎች እንደ መከላከያ ጋሻ ያገለግላል። በባህልና በታሪክ ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲ በሰዎች ልብና አእምሮ ውስጥ ዘላቂ አሻራ ስለሚያስቀምጥ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ የሚገጥሟትን ፈተናዎች በብልሃት እንድትወጣና ብሔራዊ ጥቅሟን በፅኑ መሰረት ላይ እንድታስከብር ያስችላታል።

ይህንን የለስላሳ ኃይል leverage ውጤታማ ለማድረግ የመንግስት የኮሙኒኬሽንና የዲፕሎማሲ መዋቅሮች በፈጠራ የታጀበ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። የኢትዮጵያን ጥንታዊነት ከዘመናዊው ዓለም ፍላጎት ጋር በማጣጣም፣ በተለይም ለእሴት ትልቅ ቦታ ከሚሰጡ ሀገራትና አስተዳደሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ይገባል። ኢትዮጵያ ያላትን መንፈሳዊና ታሪካዊ ሀብት በስፋት ለዓለም ማስተዋወቅ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ከመሳብና ቱሪዝምን ከማሳደግ ባለፈ፣ የኢትዮጵያዊነትን “ብራንድ” (Brand) በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅና የተከበረ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ በረጅም ጊዜ ሂደት ሀገሪቱ በጂኦ-ፖለቲካዊ ሽኩቻዎች ውስጥ ሳይሆን በራሷ ሉዓላዊ ማንነትና ታሪካዊ ልዕልና እንድትታወቅ በማድረግ፣ የተረጋጋ የውጭ ግንኙነት እንዲኖራት ያደርጋል።

የኢትዮጵያ መንፈሳዊ እሴቶች እና  አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር ትስስር

በአሁኑ ወቅት በአሜሪካና በምዕራቡ ዓለም እየጎላ የመጣው የቀኝ ዘመም ፖለቲካ (Conservative Movement) ትኩረቱን በቤተሰብ፣ በሃይማኖት እና በሃገር ፍቅር እሴቶች ላይ አድርጓል። እንደ ማርኮ ሮብዮ፣ ስቲቭ ባነን እና ማይክ ፓምፒዮ ያሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች ዓለምን የሚያዩት በሊበራል ሉላዊነት (Liberal Globalism) መነፅር ሳይሆን፣ የየሀገራቱን ነባር ባህልና እምነት መሰረት ባደረገ “ሉዓላዊነት” ነው። ለእነዚህ ወገኖች ኢትዮጵያ እንደ “የአዕላፋት ዝማሬ” ባሉ ኩነቶች የምታሳየው ጥልቅ መንፈሳዊነት እና ህዝባዊ ስነ-ስርዓት፣ እነሱ በገዛ ሀገራቸው ሊመልሱት ከሚመኙት “የቀደመው ምዕራባዊ ክርስትና እሴት” ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው። ይህ ዝግጅት የሃይማኖት ስርዓት ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ የግራ ዘመም ማርክሲስት ሉላዊ ሊህቃን (Globalist elites) ለሚገፉት ልቅ አስተሳሰብ እጅ ያልሰጠች፣ ለራሷ ወግና ማንነት የቆመች ሀገር መሆኗን ለሪፐብሊካኖች የሚያስረዳ ትልቅ ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያ እነዚህን ትዕይንቶች በታቀደ መልኩ ለሪፐብሊካን ደጋፊና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያዎች (ለምሳሌ እንደ ታከር ካርልሰን ኔትወርክ ባሉ አውታሮች) በማቅረብ፣ ራሷን እንደ የጥንታዊ ክርስትና እና የቤተሰብ እሴቶች ጠባቂ (Bastion of Traditional Values) አድርጋ መሳል ትችላለች። እንዲህ ያለው አቀራረብ በአሜሪካ የፖለቲካ መደብ ውስጥ ለኢትዮጵያ ልዩ ቦታን ይፈጥራል። ሪፐብሊካኖች አጋርነታቸው ከጥቅም በላይ በእሴት የሚመራ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ የራሷን የሶስት ሺህ ዓመታት ታሪክና የክርስትና ባህል እንደ ዲፕሎማሲያዊ መሳሪያ (Soft Power) ብትጠቀምበት፣ በዋሽንግተን የሚኖራትን ተደራሽነት እና የፖለቲካ ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምረዋል። ይህ ደግሞ እንደ አባይ ግድብ ድርደር እና ሉዓላዊ የባህር በር  ያሉ ብሄራዊ ጥቅሞቻችን ላይ የአሜሪካን ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች ድጋፍ ለማግኘት እንደ አቋራጭ መንገድ ያገለግላል።

ይህ ስልታዊ ትስስር ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ከሚታይባት የድህነትና የትርምስ ምስል አውጥቶ፣ ወደ ታላቅ ስልጣኔና የሞራል የበላይነት ባለቤትነት ያሸጋግራታል። የሪፐብሊካን አስተዳደር ለሃይማኖት ነፃነትና ለባህላዊ ሉዓላዊነት የሚሰጠውን ትኩረት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ የኢትዮጵያን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ሃብቶች ለፐብሊክ ዲፕሎማሲ ግብዓትነት ማዋል የሀገርን ገፅታ መገንባት ይቻላል። በመሆኑም መንግስት በተለይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከመደበኛው የቢሮክራሲ ዲፕሎማሲ ወጥቶ፣ እነዚህን በህዝብ ዘንድ ያሉ ወርቃማ እሴቶች የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው ዋና አካል በማድረግ ከአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ጋር ዘላቂና እሴት-ተኮር ወዳጅነት መመስረት ይኖርበታል።

የፅንፈኛ ዲያስፖራን አሉታዊ ትርክት የመመከቻ ስልታዊ መሳሪያ

እንደ “የአዕላፋት ዝማሬ” ያሉ ግዙፍ መንፈሳዊ መርሃ ግብሮች በመንግስት ሙሉ ድጋፍ፣ ጥበቃ እና እውቅና በሰላም ሲከናወኑ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳየት፣ በውጭ ሀገራት በሚኖሩ አንዳንድ የዲያስፖራ ክፍሎች የሚነዙትን አሉታዊ ትርክቶች ለማፍረስ ወሳኝ መሳሪያ ነው። ፅንፈኛው ዲያስፓራ በተለያዩ መድረኮች “መንግስት አማኞችን ያሳድዳል” ወይም “በኢትዮጵያ የሃይማኖት ነፃነት የለም” በሚል የሚሰራጩ የተዛቡ መረጃዎችን፣ በመስቀል አደባባይ የሚታየው በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ እውነተኛ እና ደማቅ አምልኮ በተግባር ውድቅ ያደርጋቸዋል። ይህ ድርጊት መንግስት ለዜጎች የእምነት ነፃነት የሰጠውን ክብር እና የሃይማኖት ተቋማት ያለምንም ተፅዕኖ ስርአታቸውን እንዲያከናውኑ የሚያደርገውን ድጋፍ በዓይን የሚታይ ምስክር በማቅረብ፣ የጥላቻ ፖለቲካን አቅም ያዳክማል።

መንግስት እና የሃይማኖት ተቋማት ተቀናጅተው መስራታቸውን የሚያሳይ ግልፅ ምስል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ለዲፕሎማቶች መድረሱ፣ የኢትዮጵያን ገፅታ ከመጠበቁም በላይ በውጭ የሚኖረው ማህበረሰብ በሀገሩ ሰላም እና መረጋጋት ላይ ያለውን እምነት እንዲያጠናክር ያደርጋል። ዲያስፖራው በሀገሩ ውስጥ የሚከናወኑ እንደነዚህ ያሉ ታላላቅ መንፈሳዊ ድሎችን ሲመለከት፣ በሀሰተኛ መረጃዎች ከመታለል ይልቅ ለሀገሩ ልማት እና አንድነት አስተዋፅኦ ለማድረግ ይነሳሳል። ይህ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ ኢትዮጵያ በውስጣዊ ልዩነቶቿ የምትበታተን ሳይሆን፣ በእሴቶቿ የምትፀና ሀገር መሆኗን ለዓለም በማሳየት ረገድ የማይተካ ሚና ይጫወታል።

በመጨረሻም እንዲህ ያሉ ኩነቶችን ለዓለም ማስተዋወቅ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት የሚያስከብር የሞራል የበላይነትን ይፈጥራል። ዓለም አቀፍ ተቋማት እና መንግስታት የሀገሪቱን ሰላማዊ ድባብ እና የህዝቡን ስነ-ስርዓታማነት ሲመለከቱ፣ በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው አመለካከት በአክብሮት ላይ የተመሰረተ ይሆናል። ይህ ደግሞ በዲፕሎማሲያዊ መድረኮች የሀገሪቱን ድምፅ ሰሚነት ከመጨመሩም በላይ፣ የውጭ ጫናዎችን በብልሃት ለመመከት የሚያስችል ጠንካራ ማህበራዊ መሰረት እንዳለ ያሳያል። ስለዚህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እነዚህን እሴቶች እንደ ዲፕሎማሲያዊ ጋሻ በመጠቀም፣ የሀገርን አንድነት እና ክብር በአለም አቀፍ መድረክ ማስጠበቅ ይኖርበታል።

የቱሪዝም ኢንዱስትሪን ማነቃቃት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለዘመናት ጠብቃ ያቆየቻቸው ታላላቅ መንፈሳዊ ኩነቶች—እንደ መስቀል፣ ጥምቀት እና በቅርቡ እየጎላ የመጣው “የአዕላፋት ዝማሬ”—የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ የማሸጋገር ግዙፍ አቅም አላቸው። እነዚህ ትዕይንቶች በሺህ የሚቆጠሩ ካህናትና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በአንድነት የሚሳተፉባቸው በመሆናቸው፣ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደ “መንፈሳዊ የቱሪዝም ምርት” (Spiritual Tourism Product) ተቀርፀው ሊቀርቡ ይገባል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከታዋቂ ዓለም አቀፍ የኮሙኒኬሽን ካምፓኒዎችና የቱሪዝም አስጎብኚዎች ጋር በመቀናጀት፣ እነዚህን ኩነቶች በመላው ዓለም በሚታዩ የብሮድካስት ሚዲያዎችና በማህበራዊ ድረ-ገጾች እንዲተዋወቁ በማድረግ ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ያደርጋል። ይህ ተግባር ኢትዮጵያን የመንፈሳዊ ጥበብና የታሪክ መፍለቂያ አድርጎ በመሳል የባህል ተፅዕኖዋን (Soft Power) በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል።

እነዚህን መንፈሳዊ ኩነቶች እንደ ስልታዊ የቱሪዝም መዳረሻ መጠቀም የኢትዮጵያን የአገልግሎት ዘርፍና የቱሪዝም ኢንስትሪውን በእጅጉ ያነቃቃዋል። ቱሪስቶች ለሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶቹ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ሰላማዊ ድባባ፣ ለህዝቡ ጨዋነትና እንግዳ ተቀባይነት የሚሰጡት ምስክርነት ለሀገሪቱ ትልቅ ሀብት ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንን የዲፕሎማሲ እድል በሰፊው በመጠቀም፣ ኢትዮጵያ የጥንታዊ እሴቶች ባለቤትና ለዘመናዊ ዲፕሎማሲ ምቹ ሀገር መሆኗን በማረጋገጥ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱንና የኢኮኖሚ ትስስሩን ማጠናከር ይኖርበታል። ይህ ተግባር ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪና ተሰሚ ከማድረጉም በላይ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ ጠንካራ የሀገር ገፅታን ይገነባል።

ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ነፃ የሃሳብ ሪፐብሊክ፣ የሁምቦልድት ፍልስፍና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሪፎርም እይታ

ቢልዱንግ እና የሃሳብ ትውልድ እሳቤዎች ሲቀናጁ ምሁራን የቆዩ የትርክት...

የኤርትራ አፋር ተቃዋሚ ድርጅቶች ግንባር ፈጠሩ፤ “ስምምነቱ ለሻዕቢያ አስደንጋጭ መርዶ ነው” አቶ አብዲ ሼኽ መሐመድ

አዲስ ሪፓርተር - በኤርትራ የሚንቀሳቀሱት ሁለት የአፋር ተቃዋሚ ድርጅቶች...

የፕሮፌሰሩ እይታ “ጠንቋይ የሰዉን እንጂ የራሱን አያዉቅም” አብይ አሕመድ ነጥብ አስጥለዋል

ሀገር የምትገነባው መንግስት ያድርግ በሚሉ ጥያቄዎች ሳይሆን እኔ ይሄን...