“የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ልሂቃኑ እና ህዝቡ በሰሜኑ ያንዣበበውን ጦርነት ካላስቆሙ በኦሮሚያ ምናልባትም በተለይ በወለጋ Ethnic confrontation (ብሄር ተኮር ግጭት) እንደሚነሳ ጀዋር ያስጠነቅቃል። ጃዋር በዚህ ፅሁፉ እንደውም ኦሮሚያ ላይ የብሄር ግጭት እንዳይከሰት ቀድሞ አስጠነቀቀ ከሚባል እሱ ያለው ካልሆነ እልቂት እንደሚከሰት በመግለፅ አስፈራራ ቢባል ይቀላል። የእኔ ስጋት ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው”
በአለባቸው ጉብሳ- ነፃ አስተያየት
ሰሞኑን ጀዋር መሃመድ በፌስቡክ ገፁ ለተከታዮቹ ባስነበበው ፅሁፍ የፌዴራል መንግሥት በሰሜን ከኤርትራና ትግራይ ሃይሎች ጋር ጦርነት ውስጥ ሳይገባ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎችና ልሂቃኑ ጦርነቱን መቃወምና ማስቆም እንደሚገባቸው አሳስቧል። ለዚህ መቃወሚያ ያቀረበው ሀሳብ በፅሁፉ ተደጋግሞ እንደገለፀው “ጦርነቱ ኦሮሞን አይመለከተውም” የሚል ነው። በጥቅስ ውስጥ ያስገባሁት ይሰመርበት። ይህ ሃሳቡ ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ ሃገራዊ ሉዓላዊነትና አንድነት ይልቅ “ቅድሚያ ኦሮሞ” ወይም Oromo first ብሎ የተነሳበትን የተገንጣይ ርዕዮተ ዓለሙን አሁንም እንደዋነኛ የትግል ስልት እንደያዘው መረዳት ይቻላል።
በዚሁ ፅሁፎ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ልሂቃኑ እና ህዝቡ በሰሜኑ ያንዣበበውን ጦርነት ካላስቆሙ በኦሮሚያ ምናልባትም በተለይ በወለጋ Ethnic confrontation (ብሄር ተኮር ግጭት) እንደሚነሳ ያስጠነቅቃል። ጃዋር የኢትዮጵያ መንግስት የሃገሩን ብሄራዊ ደህንነትና ሉኣላዊነት ለማስከበር በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል የሚያደርገውን ማናቸውም ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎች ሳቢያ ኦሮሚያ ውስጥ የብሄር ግጭት እንደሚከሰት በግልፅ በማስጠንቀቂያ ጭምር ነግሮናል።
ይህ የጀዋር የብሄር ግጭት ማስጠንቀቂያ የጀዋርን የቀደመ “የቅድሚያ ኦሮሞ” የትግል ስልትና ያስከተለውን ጉዳት እንደገና እንድንመረምር ያስገድዳል። በሌላም በኩል ሃገራችን በአሁኑ ወቅት በውክልና ጦርነት እና በቀጠናው ውስጥ የሚካሄደው የሃያላንና መካከለኛ ሃገራት የጂኦፓለቲካ ሽኩቻና ፉክክር በሕልውናዋ ላይ ስጋት ደቅኖ እያለ ወታደራዊ የወትሮ ዝግጁነት ማድረጓና ዲፕሎማሲያዊ ድርድር እያደርገች መሆኗ፤ ጀዋር መሃመድና ሌሎች የኤርትራና የግብፅ ተከፋይ “የእናት ጡት ነካሽ” ዲያስፓራዎች ይህን ጥረት ለማደናቀፍ መንግስትን እንደ “ጦረኛና ፀረ-ሰላም” አድርገው ለምን ይከሳሉ? አሁናዊ የዓለምንና የአፍሪካ ቀንድን ነባራዊ የጂኦፓለቲካ ሁኔታ ያላገናዘበ “የሰላም ጥሪ” ብሄራዊ ጥቅማችንን እንዴት. ሊጎዳው ይችላል? የሚሉትን ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ ማግኘት ያለባቸው ናቸው።
በመሆኑም በዚህ ፅሁፍ እነዚህን ወሳኝ የወቅቱን ጥያቄዎች በመመርመር ከታሪክና ከአሁናዊ የሃገራችን ተጨባጭ ጂኦፓለቲካ ሁኔታ አንፃር ምላሽ ለመስጠት ይሞከራል።
አቧራውን አራግፎ የተነሳው የጀዋር “Oromo first”
የጃዋር መሐመድ የፖለቲካ አልፋና ኦሜጋ የሆነው “ኦሮሞ ፈርስት” (Oromo First) ትርክት ተራ የብሔር መብት ጥያቄ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር የሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰቦችን እንደ ባዕድና እንደ ጠላት የሚፈርጅ አክራሪ ርዕዮተ ዓለም ነው። ይህ አስተሳሰብ ባለፉት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለተከሰቱት ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የጅምላ ግድያዎችና የንብረት ውድመቶች ዋነኛው የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። በዚሁ መርዘኛ ርዕዮተ ዓለም ሳቢያ ሲደርስ የነበረውን ግፍ ለዕቅዱ ማስፈጸሚያ ግብአት በማድረግ በፈለፈላቸው ሚዲያዎች ሲረጭ የነበረው እሱው ነበር።
ጃዋር ይህንን አጀንዳ ሲያራምድ፣ በክልሉ የሚኖሩ የሌሎች ብሔር ተወላጆች (በተለይም የአማራ፣ የጉራጌ፣ የወላይታ፣ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች) ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በዝምታ ከማለፍ ባለፈ፣ ለጥቃቶቹ መነሻ የሚሆኑ ቀስቃሽ ንግግሮችን በማሰራጨት ጃዋር ቀዳሚውን ሚና ተጫውቷል። የቅርብ ጊዜ ኩነት በመሆኑ ፋይል ገልበጥ፣ ገልበጥ ቢደረግ የሰለባዎቹ ደም ከሚያሰማው ጩኸት ጋር አብሮ የሚሰማ ስለሆነ እማኝ መጥራት አያስፈልግም።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወቅቶች በጃዋር መሐመድ የፌስቡክ መልዕክቶችና የቴሌቪዥን ቅስቀሳዎች ሳቢያ የተነሱት ሁከቶች፣ የ”ኦሮሞ ፈርስት” አስተሳሰብ ምን ያህል አጥፊ እንደሆነ በተግባር አሳይተዋል። አዲስ ሪፓርተር ከዚህብቀደም በዚህ የጀዋር ደም አፋሳሽ ቅስቀሳዎች የደረሱትን ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመቶች ለግንዛቤ ያህል ቢነበቡ መልካም እንደሚሆን እጠቁማለሁ። ይህ ክስተት ጃዋር የሰዎችን ስሜት በማነሳሳትና “የእኛ” እና “የእነሱ” የሚል የጥል ግድግዳ በመገንባት፣ የሌላ ብሔር ተወላጆችን ለጥቃት ተጋላጭ የማድረግ ስልታዊ ልምድ እንዳለው ያረጋግጣል። አሁንም በዚህ ጽሁፍ “ብሔር ተኮር ግጭት ይነሳል” ብሎ ማስፈራራቱ፣ ያንኑ አሮጌና ደም አፋሳሽ የፕሮፓጋንዳ ስልት መልሶ ለመጠቀም ማሰቡን ያሳያል። ለዚህም ዝግጅት እንዳለው ያሳብቃል። ለምንደርደሪያ ይሆነው ዘንዳ ይህን ባለ በማግስቱ ጀምሮ “ተቃጠል፣ ተገደለ” ወዘተ ማለት ጀምሯል።
የጃዋር ርዕዮተ ዓለም ኦሮሚያን እንደ ተለየች ደሴት በመመልከት፣ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር የሚደረገውን ማንኛውንም ግንኙነት ከብሔር ጥቅም አንጻር ብቻ ይተረጉመዋል። በሰሜኑ ጦርነት ዙሪያ የያዘው “አይመለከተንም” የሚለው አቋም፣ የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ለ”ኦሮሞ ፈርስት” አጀንዳ መስዋዕት መሆን እንዳለባቸው የሚያምንበትን ጥንታዊ አቋሙን ዳግም ያረጋገጠበት ነው። ይህ አቋም ግን በቃላት ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን፣ በተግባር በክልሉ የሚኖሩ አናሳ ብሔረሰቦችን ለጽንፈኛ ታጣቂዎች ኢላማ አድርጎ የመስጠት ያህል አደገኛ ነው።
ጃዋር ሰላማዊ ትግልን ሳይሆን፣ የንጹሐንን ሕይወትና ንብረት እንደ መደራደሪያ ካርድ በመጠቀም መንግሥትን የማስጨነቅ ስልትን አሁን በፌስቡክ ለደጋፊዎቹ ያስነበበው ጽሁፍም፣ በክልሉ የሚገኙ ታጣቂዎች በንጹሐን ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ “በተዘዋዋሪ ትዕዛዝ” እንደመስጠት ሊቆጠር ይችላል፤ ምክንያቱም ግጭት ይነሳል ብሎ በገለጸባቸው ቦታዎች ሁሉ ቀደም ሲል መጠነ ሰፊ እልቂቶች ተከስተዋል። አሁንም በፅሁፉ የገለፀው “የብሔር ግጭት ስጋት” እሱ ራሱ የፈጠረውና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ “እንዲፈነዳ” የሚያደርገውና እንደ የፖለቲካ ቦምብ ሊጠቀምበት ዝግጅቱ እንዳለው ማረጋገጫ ነው።
በመሆኑም፣ ጃዋር አሁንም የ”ኦሮሞ ፈርስት” መርዛማ ርዕዮቱን ለፖለቲካ መቆመሪያነት እያዘጋጀ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ንጹሐን አማራዎችና ሌሎች ብሔረሰቦች በወለጋና በሌሎች አካባቢዎች የሚደርስባቸው መከራ፣ የዚህ አክራሪ ርዕዮተ ዓለም ቀጥተኛ ውጤት ነው። የጃዋር ማስጠንቀቂያ “ሰላም ፈላጊነት” ሳይሆን፣ በንጹሐን ደም ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሴራ መሆኑን ተገንዝቦ፣ ለሚከሰተው ማንኛውም ጥፋት ግለሰቡና አክራሪ ታጣቂዎች በቀጥታ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል። የኢትዮጵያ አንድነት የሚረጋገጠው እንዲህ ያሉ በብሔር ስም የሚነግዱና ለንጹሐን ሕይወት ግድ የሌላቸውን ኃይሎች ሴራ በማጋለጥና ለሕግ በማቅረብ ብቻ ነው። ከሃምሳ ሚሊዮን ኦሮሞ አርባ ሚሊየኑን አስጨረሼ አንድ ሚሊዮኑን ነጻ አወጣለሁ” ማለቱን ማስታወሰ ልብ ይሏል።
የሠላም ጥሪ ወይስ የስነ ልቦና ጦርነት
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ቀጠናና በአፍሪካ ቀንድ ባለው ውስብስብ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሽኩቻ ውስጥ ህልውናዋን ለማስጠበቅ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። የኤርትራ መንግሥት የሀገሪቱን ዳር ድንበር መደፈሩና በውክልና ጦርነት የውስጥ መረጋጋትን ለማናጋት መሞከሩ፣ መንግሥት የመከላከያ ሠራዊቱን በከፍተኛ የወትሮ ዝግጁነት (High-level combat readiness) እንዲያደራጅ አስገድዶታል። ይህ ወታደራዊ ዝግጁነት ጦርነት ናፋቂነት ሳይሆን፣ ከውጭ የሚሰነዘርን ወረራ ለመመከት፣ የሀገርን ክብር ለማስጠበቅና ጠላትን በድፍረት እንዳይጥስ ለማድረግ (Deterrence) የሚከናወን ሕገ-መንግሥታዊና ስትራቴጂካዊ ግዴታ ነው።
በቀጠናው የሚታየው የኃይል አሰላለፍና የኤርትራ መንግሥት ከተለያዩ ታጣቂዎች ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያን በበርካታ ግንባሮች ለመወጠር የሚያደርገው ጥረት፣ የሠራዊቱን ስነ-ልቦናዊና ቁሳዊ አቅም ማሳደግን ቀዳሚ የብሔራዊ ደህንነት ተግባር ያደርገዋል። ሉዓላዊነት በተደፈረበትና የውክልና ጦርነት በታወጀበት ሁኔታ ውስጥ፣ ወታደራዊ ቁርጠኝነትን ማሳየት ከሀገር ህልውና የሚመነጭ ግዴታ ነው። በመሆኑም የመከላከያ ኃይሉ ጥቃትን ለመቀልበስ በማንኛውም ሰዓት ዝግጁ መሆኑ፣ ሀገሪቱ በቀጠናው እንደ አንድ ኃያል ሀገር ተከብራ እንድትቀጥል የሚያደርግ ብቸኛው የዘላቂ ሰላም ዋስትና ነው።
ይሁን እንጂ፣ ጀዋር መሃመድና በውጭ ሃገር የሚኖሩ የኤርትራና የግብፅ መንግስት ምንደኛ ሊሕቃን ይህን የሃገራችንንና የቀጠናውን ነባራዊ ሁኔታ በቅጡ ሳይረዱ የሰራዊቱን ዝግጁነት እንደ ጦረኛነት ቆጥረው “ጦርነት ይብቃ” የሚል ጠላት ያዘጋጀው የታቀደና የተናበበ የሚድያ ዘመቻ ጀምረዋል።
ይህን ነባራዊ ሁኔታ ያልተረዳ የሰላም ጥሪ ዘመቻ በታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚ እንደታየው ሃገርን ለወራሪ ኃይሎች አመቻችቶ የሚሰጥ፣ በጠላት በሕቡዕ የሚዘጋጅ የስነ ልቦና ጦርነት አካል ነው። ይህ እነ ጃዋርና ተባባሪዎቻቸው ላይ የወደቀ አገርን የመሸጥ፣ ለጠላቶቿ አሳልፎ የመስጠት ፕሮጀክት “በጦርነት ይብቃ” ተቀባብቶ የሚቀርብ የክህደትና ሕዝብን አገር አልባ የሚያደርግ ወገን ላይ የሚፈጸም ግፍ ነው።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት በአውሮፓ የታየው የሰላም ጥሪ (Pacificism) እንደ ናዚ ጀርመን ያሉ አምባገነን መንግስታት ለጦርነት ዝግጅት ጊዜ መግዣ በማድረግ በድፍረት ጎረቤት ሀገራትን እንዲወርሩና እልቂት እንዲፈጠር መንገድ እንደከፈተ ሁሉ፣ አሁንም እንዲህ ያሉ አስተሳሰቦች የሀገርን ብሄራዊ ጥቅምን የማስከበር ወኔ የሚሰብሩ የጠላት የስነ ልቦና ጦርነት አካል እንደሆኑ መገመት አይከብድም። በስነ-ልቦና ጦርነት ስልት ውስጥ የሰላም ጥሪ ተከላካዩ ወገን ራሱን የመከላከል ሞራል እንዲያጣና በውስጥ ክፍፍል እንዲዳከም ለማድረግ የሚነዛ ፕሮፓጋንዳ ነው። ጀዋር “ተካንኩበት” እያለ በኩራት የሚናገረውና እንዲህ ያለ ሴራ ሲጫን “እሰይ” ብሎ የሚቀበልበትን ትከሻውንና አመድ ላይ የተለውሰውን ሞራሉን እንጂ ሌላ ተነቅሶ የሚታይ ሞራል ኖሮት አይደለም።
በጃዋር መሐመድ እና መሰሎቹ የሚያሰራጨው “ጦርነት ይብቃ” የሚል የሰላም ጥሪ፣ ኦሮሞ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለመከላከያ ሠራዊቱ በተለያየ መንገድ የሚሰጡትን ድጋፍ እንዲቁንሱ የሚያደርግ ስልታዊ የስነ-ልቦና ዘመቻ ነው። ሀገር በውጭ ኃይሎች ተወራና በውስጥ አማፂያን እየታመሰች ባለችበት ወቅት እንዲህ ዓይነቱን ጥሪ ማቅረብ፣ ከሰላም ወዳድነት ይልቅ የጠላትን ስትራቴጂ በተዘዋዋሪ ከመደገፍ ጋር ይቆራኛል። ሰላም የሚረጋገጠው ለወራሪ እጅ በመስጠት ሳይሆን ጠላትን ሊመክት በሚችል ጦር ሰራዊት ዝግጁነት ሆኖ እያለ የሰላም ጥሪው በተግባር ሲታይ ለሰራዊቱ የሚሰጠውን የሞራል ስንቅ ትጥቅ በማስፈታት ወራሪውን ወገን ማጠናከሪያ መሣሪያ ሆኖ ያያገለግላል።
በሌላ በኩል እንዲሁ ይህ በጃዋር መሐመድ እና ሌሎች ባንዳዎች የሚያካሄደው የ”ሰላም ጥሪ” ቅስቀሳ፣ ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊና ኢኮኖሚያዊ ህልውናዋን ለማረጋገጥ የጀመረችውን የታቀደና የተቀናጀ የባሕር በር የማግኘት የግፊት ዘመቻ (Pressure Campaign) ከጀርባ የሚወጋ ተግባርም ነው። ሀገሪቱ በቀይ ባሕር ቀጠና ያላትን ተፅዕኖ ለመመለስና የባሕር ባለቤትነቷን ለማረጋገጥ በምታደርገው ከፍተኛ የዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ግፊት ወቅት፣ እንዲህ ያሉ የውስጥ የ”ሰላም” ድምፆች የመንግሥትን የድርድር አቋም (Positions of strength) ያዳክማሉ። መንግሥት ለብሔራዊ ጥቅሙ የሚያሳየው ቁርጠኝነት በልሂቃን ትርክት ሲሸረሸር፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ውስጣዊ አንድነት እንደሌላት እንዲያስብ በማድረግ ሀገራዊ ግፊቱ ግቡን እንዳይመታ እንቅፋት ይፈጥራል። እነ ጃዋርና ልደቱ አያሌው የዚሁ ዘመቻ አስተባባሪነታቸው ኢላማውና ዓላማው ይህና ይህ ነው።
በተጨማሪም የኢትዮጵያን ሉዓላዊ የባሕር በር ጥያቄ እንደ “ጦርነት ናፋቂነት” በመፈረጅ፣ ወራሪውንና የውክልና ጦርነት አቀጣጣዩን የኤርትራ መንግሥት እንደ ሰላም ወዳድ እንዲቆጠር ስልታዊ የፕሮፓጋንዳ ሽፋን እየሰጡት ይገኛል። ይህ ዓይነቱ አካሄድ ኢትዮጵያ በታሪካዊ አጋጣሚ ልታገኝ የምትችለውን የባሕር በር ዕድል አጥታ በድጋሚ በጎረቤት ሀገራት በጎ ፈቃድ ሥር እንድትወድቅ የሚያደርግ ስትራቴጂካዊ ክህደት ነው። የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነፃነትና የደህንነት ዋስትና መሆኑ እየታወቀ፣ ይህንን ሀገራዊ የግፊት ዘመቻ ለማዳከም የሚደረግ ማንኛውም ቅስቀሳ የሀገርን የልማትና የሉዓላዊነት ጉዞ ሆን ብሎ ማደናቀፍ ነው። በድጋሚ ቃሉን ለመጠቀም ከዚህ ቀደም ከተፈጸሙት ክህደቶች ሁሉ ጎልቶ የሚወጣ ክህደት ነው።
ራሱን “አብሮነት” ብሎ የሚጠራውና ለይስሙላ ከየብሄሩ አባላትን ሰብስቦ በሻዕቢያና ትህነግ የጋራ ዕቅድ፣ በግብጽና መሰል የኢትዮጵያ ጠላቶች ከጀርባ የሚነዳ ስብስብ እንዴት እንደሚሰራ በአዲስ ሪፖርተር በስፋት ተዘግቧል። በውስጡ ራሳቸውን ለታሪክ ሲሉ አካተው መረጃ የሚያቀብሉ እንደነገሩን ግብጽ ብር የምታፈስበት ፕሮጀክት ነው። የዚህ ስብስብ እንግዴ ልጅ ሆኖ የወጣው ሰባት አባላት ያሉበት ግብረኃይል “ጦርነት ይብቃ” ብሎ በሰላም የተለውሰ የክህደት መርዙን ዛሬ ማክሰኞ በልደቱ አያሌው አቅራቢነት፣ በጀዋር ማብራሪያ ሰጪነት ይቀርባል። ይህንኑ እንዲያከፋፍሉና እንዲረጩ የመረጡ የማህበራዊ ሚዲያ ግልገሎች ተዘጋጅተዋል። “የመጤዎችን ቤት ተከፋፈሉና ውሰዱ” በማለት መመሪያ ሲሰጥ የነበረው ጀዋር፣ የገጀራ ፖለቲካውን በእምብርቱ ይዞ ያልተቋጨ ፕሮጀክቱን ሊቁጭ አንደበቱን ያላቅቃል። በዘጠና ሰባቱ የቅንጅት ፖለቲካ በተራራ ጸሐይ ያለቁ ምስኪኖች ደም የሚጮህበት ልደቱን የተጣመረው ጀዋር “ሰሚ ቢያገኝ” በማለት ጉም የሚሆነውን ምኞቱን አስፍሬያለሁ።
ይህ ዓይነቱ የሰላም ጥሪ ዜጎች የሃገራቸውን ሉዓላዊነት ለመከላከል እና ሉአላዊ የባህር በር መብት ለማስከበር በቁርጠኝነርና በጀግንነት በአንድነት እንዳይቆሙ በማዘናጋት ጠላት ያለምንም ከፍተኛ መስዋዕትነት ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ግቡን እንዲመታ ዕድል የሚሰጥ ዘመን የማይሽረው ውስልትና ነው። በመሆኑም ዜጎች በ”ሰላም” ሰበብ የሀገርን ሞራል የሚንዱ ንግግሮችን በጥንቃቄ ሊመረምሩ ይገባል። የኢትዮጵያ ህልውና የሚጠበቀው በሐሰተኛ የሰላም ትርክቶች ሳይሆን፣ በውስጥ አንድነትና በማንኛውም ጊዜ ጠላትን ለመመከት በሚችል ብቁና ዝግጁ በሆነ ወታደራዊ ኃይል ብቻ መሆኑን መረዳት ለሀገራዊ ደህንነት እና ስትራቴጅክካዊ ጥቅሞች መከበር ውሳኝነው።
አቶ ተስፋዬ ከበደ የተባሉ ጸኃፊ ይድረስ ለወንድሜ ጀዋር ካሉ በኋላ “የእኔ ስጋት ቀጥሎ ያለው ነው” በማለት ያቀረቡትን ጥያቄ አንባቢያን ጃዋርን ስጸሙ እንድትጠይቁ እንዳለ አቅርቢያለሁ። ጸሐፊው ጃዋር በፌስቡክ ገጹ በእንግሊዝኛ አስፈራርቶ ላቀረበው መርዛማ ጽሁፍ እንደ ዜጋ ስጋታቸውንና የብልህ ጥያቄ አቅርበዋል።
“የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ልሂቃኑ እና ህዝቡ በሰሜኑ ያንዣበበውን ጦርነት ካላስቆሙ በኦሮሚያ ምናልባትም በተለይ በወለጋ Ethnic confrontation (ብሄር ተኮር ግጭት) እንደሚነሳ ጀዋር ያስጠነቅቃል። ጃዋር በዚህ ፅሁፉ እንደውም ኦሮሚያ ላይ የብሄር ግጭት እንዳይከሰት ቀድሞ አስጠነቀቀ ከሚባል እሱ ያለው ካልሆነ እልቂት እንደሚከሰት በመግለፅ አስፈራራ ቢባል ይቀላል። የእኔ ስጋት ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። ሁለት ጥያቄዎችም አሉኝ፤ እነርሱም፦
፩) የፌደራሉ መንግሥት በሚይዘው አቋም የተነሳ ኦሮሚያ ላይ የብሄር ግጭት የሚነሳበት ምክንያት ምንድን ነው?
፪) ጃዋር የሚለው የብሄር ግጭት ኦሮሚያ ክልል በተለይ ወለጋ ከአሁን በፊት ተደጋግሞ እንደተስተዋለው ምስኪን አማሮች ላይ ግድያ ከተፈጸመ ይህ የጃዋር ፅሁፍ እንደ ቀጥተኛ ማስፈራሪያ ተወስዶ ጃዋር መሀመድ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚያውቀው የታቀደ ነገር ያለ ስለሚያስመስል ኃላፊነት የሚወስድ መሆኑን ለማመልከት ነው። በማለት አቶ ተስፋዬ በስጋት ስሜት ውስጥ ሆነው የጃዋርን የልቂት ጥንስስ ማሰሮ ሰብረዋል። እውነት ኢትዮጵያ ጠላቶቿን ለማሳፈርና ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ መዘጋጀቷ በወለጋ እንዴት የብሄር ግጭት ያስነሳል? የሴራውን ደራሲ፣ ዘፋኝና ተወዛዋዥ ጠይቁልን፤ እናነት ይህንኑ ከጀዋር የሚወጣ እሳት ረጭታችሁ በሰበር አመድ ልታከፋፍሉ የተመረታችሁ ሚዲያዎችም ይህን ጥያቄ ጠይቁልን? ድጉም ሆነ ክፉው ምግባር በዚህ ዘመን አይደበቅምና !!
ዝግጅት ክፍሉ አለባቸው ጉብሳ የአዲስ ሪፖርተር ቋሚ አምደኛ ናቸው፤ የህግ ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኝ ሲሆኑ በአዲስ ሪፖርተር የሚያትሙት ማንኛውም አሳብ የግላቸው እንጂ የዝግጅት ክፍሉ አቋም እንዳልሆነ ለማሳወቅ እንወዳለን።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






