አንዱ ወገን ሌላውን “አጥቂ” አድርጎ በመፈረጅ በሚያገኘው ጊዜያዊ የሞራል የበላይነት ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ወገን በሌላው ላይ የሚሰነዝረውን ፍረጃና ጥላቻ በሐቀኝነት ለመጋፈጥ ሲቆርጥ ብቻ ነው። እንደ አሕመዲን ጀበል ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም፣ የሚጽፏቸው ሐሳቦች በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ብቻ ሳይሆን፣ በተቃራኒው ወገን ባሉት ዜጎች ዘንድም እንደ ተስፋና እንደ ሰላም ጥሪ እንዲታዩ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል። ጥላቻን በጥላቻ፣ ፍረጃን በፍረጃ ለመመከት መሞከር የጥፋት አዙሪቱን ከማቅለጥ ይልቅ ይበልጥ እንዲፋፋም ያደርገዋል።
አለባቸው ጉብሳ- ነፃ አስተያየት
እንደ መግቢያ
አሕመዲን ጀበል በሃይማኖታዊ፣ ፓለቲካዊና በማኅበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ በድፍረት በሰላ ብዕሩ የሚያነሳቸው ሃሳቦች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትኩረቴን ይስቡታል። በማህበራዊ ድረገፆቹ የሚያጋራቸውን እነዛን ረዣዥም ፅሁፎችን ጊዜ ወስጀ ማስታወሻ እየያዝኩ አነባቸዋለሁ። አህመዲን በተግባቦት ወይም በህዝብ ግንኙነት የፕሮፓጋንዳ ዘርፍ ልህቀት ያለው ብዕረኛ ነው። የነገርን ብልት ማውጣትና መሞገት ይችላል። የስላ ነው። ይህን የሰላ ብዕሩን በመጠቀም በየወቅቱ በመረጃ ምህዳሩ ውስጥ ስለ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የሚያስተውለውን ሥጋት በግልጽ ለሕዝብ ማጋራቱ የሚበረታታ ቢሆንም እንደ አንድ ከፍተኛ የማህበራዊ ድረገፅ ተከታይና ሃይማኖታዊ ተጽዕኖ እንዳለው መምህርነቱ፣ የሚጽፋቸው ሐሳቦች ከቁስል መነካካት ባለፈ ፈዋሽነታቸው ሊመዘን ይገባል ብዬ አምናለሁ።
እውነትን መናገር ተገቢ ቢሆንም፣ እውነቱ የሚቀርብበት መንገድ ግን ተከታዩን በስሜት ከመቆስቆስ ይልቅ በሰከነ አመክንዮ ወደ መፍትሔ የሚያመራ፣ ጥላቻን የሚያረግብና ለጋራ ህልውና የሚበጅ ሊሆን ይገባል። በተለይም ለጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ምላሽ በሚሰጥበት ወቅት፣ “ጠላት” ለሚላቸው ወገኖች ጭምር አዲስ የአብሮነት ብርሃን የሚያሳይና የመግባቢያ ድልድይ የሚጠቁም የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረብ ከእርሱ መሰል ታዋቂ ግለሰቦች የሚጠበቅ የታሪክ ኃላፊነት ነው።
ይህንን ትችት ለመሰንዘር የተገደድኩት ለአንድ ወገን ባለኝ ጭፍን ሃይማኖታዊ ወገንተኝነት ወይም ደግሞ የአሕመዲን ጀበልን ማንነት ለመኮነን ሳይሆን፣ የሁላችንም የጋራ ቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ እንድትቆም ካለኝ ጥልቅ ጉጉት የተነሳ ነው።
በሃይማኖቶች መካከል የሚደረጉ ውይይቶችና ትችቶች በጥላቻ መነጽር ሳይሆን ለሀገር ግንባታ አስፈላጊ በሆነው በዜግነት መብትና በሰው ልጅ ክብር ላይ የተመሠረቱ ሊሆኑ ይገባል። እርስ በርስ ከመካሰስና አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ ከመመልከት ይልቅ፣ የጋራ እሴቶቻችንን በማጉላትና ልዩነቶቻችንን በሰለጠነ መንገድ በማስተናገድ ረገድ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ ነው።
ይህንንም ስል በባዶ ስሜት ሳይሆን፣ ሙስሊምና ክርስቲያኑ ተከባብሮና ተዋዶ በሚኖርባት የወሎ ምድር ከሙስሊም ቤተሰቦች የወጣሁና አሁንም ቢሆን የኡስታዝ አሕመዲን ጀበል ወዳጆችና ተከታዮች የቅርብ ባልንጀሮቼ እንደመሆኔ መጠን የሞራልና ማህበራዊ ሃላፉነት ጭምር እንዳለብኝ በማመን ነው። ይህ ታሪካዊና ማኅበራዊ ትስስሬ በጽሑፉ ላይ የሚታዩትን የአመክንዮ ግድፈቶች እንድመለከትና ለሁላችንም የሚበጀውን ሚዛናዊ ዕይታ እንዳጋራ ያደርገኛል።
በመሆኑም አህመዲን ጀበል ዛሬ በፌስቡክ ገፁ “ትት! ወሃቢያ!፦ ውሸትን እውነት የማስመሰል የፕሮፓጋንዳ ወጥመድ” በሚል ርዕስ ያጋራው ጽሑፉ የያዛቸውን ስድስት መሠረታዊ ሕፀፆች ነቅሶ በማውጣት፣ ከፍረጃና ከጥላቻ ፖለቲካ የጸዳች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚረዳ መልኩ ያቀረብኩትን ትችትና የእርማት ጥሪ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
ከመጠን ያለፈ አጠቃላይ ፍረጃ (Over generalization)
አሕመዲን ጀበል በዚህ ፅሁፉ “የጅምላ ፍረጃን” ለመታገል በሚል ሰበብ ራሱ በጅምላ ፍረጃ ወጥመድ ውስጥ ይወድቃል። ለአብነት ያህል በጥቂት የማኅበራዊ ሚዲያ ተዋናዮች የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን “ፋኖ” ወይም “የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች” ከሚሉ ሰፋፊ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ማንነቶች ጋር በቀጥታ ያገናኛል። ይህ አካሄድ በግለሰቦች ስህተት መላውን ማኅበረሰብ ተጠያቂ የሚያደርግ በመሆኑ፣ ጽሑፉ ሊታገለው የቆመለትን “የፍረጃ ፖለቲካ” ራሱ እንዲደግመው አድርጎታል።
ይህ አይነቱ አጠቃላይ ፍረጃ በምክንያትና ውጤት መካከል ያለውን ስስ መስመር የሚጥስ ነው። ጥቂት የማኅበራዊ ሚዲያ “አንቂዎች” የሃይማኖት ምልክቶችን ወይም የፖለቲካ አርማዎችን ስለተጠቀሙ ብቻ፣ መላው የቤተክርስቲያን መዋቅር ወይም መላው የፖለቲካ እንቅስቃሴ “የጥላቻ ፋብሪካ” ተደርጎ ያቀርበል። ይህ “ባለቤት የሌለው ክስ” (Guilt by Association) ይባላል። በአንድ ወገን የሚታዩ የጽንፈኝነት ዝንባሌዎችን ነቅሶ በማውጣት ፋንታ፣ ሁሉንም የአንድ እምነት ወይም የብሔር ፖለቲካ ተከታዮች በአንድ ቅርጫት ውስጥ ከትቶ መፈረጅ፣ በንጹሐንና በጥፋተኞች መካከል ያለውን ልዩነት በማደብዘዝ የጥላቻውን አድማስ ያሰፋዋል።
በተጨማሪም፣ ጽሑፉ “እነዚህ አካላት ቤተክርስቲያንን እንደ ብቸኛ የሀገር ባለቤት አድርገው በመሳል…” የሚል ሰፊ ድምዳሜ ሲሰጥ፣ የቤተክርስቲያኒቱን ይፋዊ አስተምህሮና የታሪክ አብሮነት ከግምት ውስጥ አላስገባም። የማኅበራዊ ሚዲያ የግጭት ነጋዴዎችን ንግግር እንደ ተቋማዊ አጀንዳ መውሰድ፣ በተቋሙ ውስጥ ያሉትን የሰላምና የአብሮነት ድምፆች ሆን ብሎ እንደመሸፈን ይቆጠራል። እንዲህ ያለው ትረካ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ “ተጠቂ” አድርጎ በሚስልበት ፍጥነት፣ ሌሎች ወገኖችን ደግሞ “አጥቂ” አድርጎ ስለሚያቀርብ፣ በማኅበረሰቦች መካከል ሊኖር የሚገባውን የመተማመን መንፈስ ይበልጥ ይሸረሽረዋል።
ከአመክንዮ አንጻር ሲታይም፣ ጽሑፉ የሙስሊሙን ማኅበረሰብ “መጤ” ተብሎ እንዳይፈረጅ የሚያቀርበውን መከራከሪያ ለሌላው ወገን ሲሆን ይነፍገዋል። ለምሳሌ ፋኖን ወይም የተወሰኑ ብሔርተኞችን “ጽንፈኛ” ብሎ በመፈረጅ ረገድ ጽሑፉ ምንም አይነት የቃላት ቁጠባ አያደርግም። ይህ “እኛ ስንፈረጅ ስህተት ነው፣ ሌላውን ስንፈርጅ ግን ተገቢ ነው” የሚል ሚዛን የሳተ አቋም፣ ጽሑፉ ሊያመጣው የሚችለውን ሰላማዊ የማሳመን አቅም (Moral Authority) በእጅጉ ያዳክመዋል። ፍረጃን የሚቃወም ጽሑፍ ራሱ ከፍረጃ የጸዳ ካልሆነ፣ ተደራሲው ዘንድ የሚፈጥረው ስሜት “የእውነት ፍለጋ” ሳይሆን “የወገንተኝነት መከላከያ” ሆኖ እንዲታይ ያደርገዋል።
አህመዲን ጀበል በፅሁፉ የጅምላ ፍረጃን የሥነ-ልቦና ጦርነት ወጥመድ እንደሆነ ቢገልጽም፣ እሱ ራሱ ግን በዚያው ወጥመድ ውስጥ ወድቋል። ጥቂት ዲጂታል አክቲቪስቶችን እንደ መላው ማኅበረሰብ ወካይ አድርጎ መውሰድ፣ በጥላቻ ትረካዎች ላይ ቤንዚን እንደማርከፍከፍ ይቆጠራል። እውነተኛ የአስተሳሰብ ትግል መሆን የነበረበት ጥቂት አክራሪዎችን ከሰላማዊው ብዙኃን ነጥሎ በማውጣት አብሮነትን ማጠናከር ሲገባው፣ ጽሑፉ ግን “ሁሉንም በጠላትነት የመፈረጅ” አባዜን በማንጸባረቅ በዜጎች መካከል የጥርጣሬ ግንብ እንዲገነባ ሳያውቀው አስተዋጽኦ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ጸሐፊው ሊከላከለው የፈለገውን “የመገለልና የዝምታ” አዙሪት በሌላው ወገን ላይ እንዲጫን የሚያደርግ ስልታዊ ስህተት ነው።
የስሜት ቀስቃሽ ቃላት አጠቃቀም (Loaded Language)
አሕመዲ ጀበል ያቀረበው ፅሁፍ “ጥናታዊና አመክንዮአዊ” እንደሆነ በመግቢያው ቢገልጽም፣ በውስጡ የያዛቸው ቃላት ግን ከምሁራዊ ትንታኔ ይልቅ እጅግ ስሜት ቀስቃሽና ጽንፈኛ (Loaded Language) ናቸው። እንደ “የፕሮፓጋንዳ ወጥመድ”፣ “የጠላት ፈጠራ ፋብሪካ”፣ “መርዛማ ትረካ” እና “የጥላቻ ነጋዴዎች” ያሉ ቃላት አጠቃቀም፣ ጽሑፉ መረጃን ለተደራሲው ከማድረስ ይልቅ የተደራሲውን ስሜት ለመቀስቀስና የተወሰነ ጥላቻን ለማሳደር ታስበው የተቀመጡ ይመስላሉ። እንዲህ ያሉ ቃላት በአንድ ጽሑፍ ውስጥ ሲበዙ፣ ትንታኔው ወደ ፕሮፓጋንዳዊ መዝገበ-ቃላትነት እንዲቀየር ያደርጉታል እንጂ ተጨባጭ እውነትን እንዲያጎላ አይረዱትም።
የስሜት ቀስቃሽ ቃላት ዋነኛው ሕፀፅ አንባቢው የቀረበለትን መረጃ በአመክንዮ ከመመርመር ይልቅ፣ በቃላቱ ክብደት ተገፍቶ ወደ ጭፍን ፍረጃ (Prejudice) እንዲያደላ ማድረጋቸው ነው። ጸሐፊው “የጥላቻ ነጋዴዎች” ወይም “የጠላት ፈጠራ ፋብሪካ” የሚሉትን ቃላት ሲጠቀም፣ ተቀናቃኞቹን በምክንያት ከመሞገት ይልቅ ስብዕናቸውን በማጠልሸት (Ad Hominem) ውይይቱን ለመዝጋት ይሞክራል። ይህ ደግሞ በምሁራዊ ክርክር ውስጥ ትልቅ ድክመት ነው፤ ምክንያቱም ጠንካራ መከራከሪያ ያለው ሰው በቃላት ግዝፈት ሳይሆን በሚየርበው የማስረጃ ክብደትና ተአማኒነት ሐሳቡን ያሳምናልና።
በተጨማሪም፣ እንዲህ ያሉ ቃላትን መጠቀም የጽሑፉን ተአማኒነት (Objectivity) በእጅጉ ይጎዳዋል። አንድ ጽሑፍ “ጥናታዊ” ነው ከተባለ፣ የሚመረምረው ጉዳይ ላይ ገለልተኛና ሚዛናዊ ሆኖ መገኘት ይኖርበታል። ሆኖም ጸሐፊው እጅግ የከረሩና “መርዛማ” የሚሉ ቃላትን ሲያዘንብ፣ አንባቢው ጸሐፊው አስቀድሞ በአንድ ወገን ተሰልፎ ሌላውን ለማጥቃት እንደተነሳ እንዲረዳ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ ጽሑፉ ለጋራ መግባቢያነት የሚኖረውን ዋጋ አሳጥቶ፣ አንዱ ወገን ለሌላው ወገን የሚሰነዝረው “የቃላት ጦርነት” አካል ብቻ እንዲሆን ያደርገዋል።
ሌላው መሠረታዊ ችግር፣ እነዚህ ቃላት በደፈናው የቀረቡና ትክክለኛ ትርጉማቸው ያልተገደበ መሆኑ ነው። “የጥላቻ ነጋዴ” ወይም “የፕሮፓጋንዳ ወጥመድ” የሚሉት ቃላት ለማን እንደተሰጡ ወይም ምን አይነት ተግባርን እንደሚወክሉ በግልጽ በሕግና በአመክንዮ ሳይለዩ፣ ለሁሉም ተቃዋሚ ሐሳቦች እንደ ታርጋ ያገለግላሉ። ይህ ደግሞ ጽሑፉ ራሱ ሊታገለው የፈለገውን “የፍረጃ ፖለቲካ” በሌላ በኩል ራሱ እያከናወነው መሆኑን ያሳያል። ስሜትን የሚያሞቁ ቃላት ሲበዙ፣ የአንባቢው አእምሮ “ለምን?” እና “እንዴት?” ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ በቁጣና በበቀል ስሜት እንዲሞላ ያደርጋሉ።
ስሜት ቀስቃሽ ቃላት አጠቃቀም ጽሑፉን ካሰበው ዓላማ ይልቅ ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ ወስዶታል። አንባቢው በሰከነ መንፈስ ጉዳዩን እንዲመረምር ከማገዝ ይልቅ፣ በቃላት ጩኸት አእምሮው እንዲጠለፍ ያደርጋል። አንድ እውነተኛ ትንታኔ ቃላቱ ሳይሆኑ ሐሳቦቹ “መርዛማነትን” ወይም “የጥላቻ ንግግርን” በራሳቸው እንዲያጋልጡ ለተደራሲው ዕድል መስጠት ነበረበት። አህመዲን ግን ሁሉንም ነገር አስቀድሞ በስድብና በፍረጃ ቃላት ስላጨናነቀው፣ ጽሑፉ ከዕውቀት ምንጭነት ይልቅ ወደ ፖለቲካዊ መፈክርነት ተቀይሮ የራሱን ተአማኒነት አጥቷል።
የማስረጃ እጥረት (Lack of Empirical Evidence)
ጀበሉ በጽሑፍ ውስጡ ለዘረዘራቸው እጅግ አሳሳቢና ከባድ ክሶች የሚደግፍ አንድም ተጨባጭ ማስረጃ (Empirical Evidence) አያቀርብም። አንድ ትንታኔ “ጥናታዊ” ሊባል የሚችለው በምልከታ፣ በቁጥር ወይም በገለልተኛ ምንጮች የተረጋገጡ መረጃዎችን ሲያካትት ብቻ ነው። ሆኖም ይህ ጽሑፍ “የተቀነባበረ ዘመቻ”፣ “የተደራጀ የዲጂታል ሴራ” እና “በውጭ ሀገር የሚመሩ የጥፋት አውታሮች” እያለ ሲከስ፣ እነዚህን ክሶች የሚያረጋግጡ የዳታ ትንታኔዎችንም ሆነ ተጨባጭ የሰነድ ማስረጃዎችን ባለመጥቀሱ ትንታኔው ከእውነት ይልቅ ወደ ግምት ያዘነብላል።
በተለይም “ጥቂት ግለሰቦች በርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶችን በመጠቀም ሕዝባዊ ስምምነት ያስመስላሉ” የሚለው ነጥብ በዲጂታል ፎረንሲክስ (Digital Forensics) ሊረጋገጥ የሚችል ቴክኒካዊ ጉዳይ ነው። ጸሐፊው ግን ይህንኑ ለማረጋገጥ የሚያስችል የናሙና ጥናት፣ የተተነተኑ የፌስቡክ ወይም የቲክቶክ ገጾች ዝርዝር፣ ወይም ደግሞ የቦቶች (Bots) እንቅስቃሴን የሚያሳይ መረጃ አያቀርብም። ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ እንዲህ ያሉ ከባድ ድምዳሜዎችን መስጠት፣ ጽሑፉን ከምሁራዊ ትንታኔነት አውርዶ “የሴራ ትረካ” (Conspiracy Theory) እንዲመስል ያደርገዋል። ይህ ደግሞ አንባቢው በጽሑፉ ላይ ሊኖረው የሚገባውን አመክንዮአዊ እምነት ይሸረሽረዋል።
ጽሑፉ በውጭ ሀገር ስለሚገኙ “መምህራንና አንቂዎች” እንደ የጥፋት ዘመቻው ሞተሮች አድርጎ ቢጠቅስም፣ እነዚህ ግለሰቦች እነማን እንደሆኑ ወይም የትኛው ንግግራቸው ለተጠቀሰው ስልታዊ ጥቃት እንደዋለ በዝርዝር አያሳይም። በደፈናው “የተቀነባበረ ስልት” ወይም “የጥላቻ ትረካ” ብሎ መደምደም ብቻውን ማስረጃ ሊሆን አይችልም። በማስረጃ ያልተደገፈ ክስ ደግሞ ተከሳሹን ብቻ ሳይሆን ከሳሹንም ለትዝብት የሚዳርግ ነው። አንድ ጥናት “የሥነ-ልቦና ጦርነት” መኖሩን ለመተንተን፣ ያ ጦርነት የተካሄደባቸውን ግልጽ አጋጣሚዎች፣ የተሰራጩ መልዕክቶችን ይዘት ትንተና (Content Analysis) እና ያስከተሉትን ተጽዕኖ በሳይንሳዊ መንገድ ማሳየት ይኖርበታል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ጽሑፉ “በጥናት ላይ የተመሠረተ” ቢልም የጥናቱን ዓይነት፣ ዘዴ (Methodology) ወይም የተመረመረበትን የጊዜ ገደብ አይገልጽም። ይህ ደግሞ ጸሐፊው የራሱን የግል ምልከታ ወይም የፖለቲካ አቋም “ጥናት” በሚል ካባ ሸፍኖ ለማቅረብ መሞከሩን ያሳያል። ተጨባጭ መረጃዎችና ቁጥራዊ መረጃዎች በሌሉበት የሚቀርብ ትንታኔ፣ ለማኅበራዊ ሳይንስ ምርምር ከሚሰጠው ፋይዳ ይልቅ ለፖለቲካዊ ቅስቀሳ የሚሰጠው ግብዓት ይበልጣል። ይህም ጽሑፉ ሊያሳካ የፈለገውን “እውነትን የማጋለጥ” ዓላማ በጥርጣሬ ደመና እንዲሸፈን ያደርገዋል።
የማስረጃ እጥረት የዚህ ጽሑፍ ተአማኒነት ላይ ትልቅ ቀዳዳ ፈጥሯል። ከባድ ክሶች ከባድ ማስረጃዎችን ይፈልጋሉ። ጸሐፊው በደፈናው የሚሰነዝራቸው ድምዳሜዎች በተጨባጭ ዳታ ካልተደገፉ፣ ጽሑፉ “ውሸትን እውነት የማስመሰል የፕሮፓጋንዳ ወጥመድ” የሚለውን ርዕስ ለራሱም እንዲጋራ ያደርገዋል። ምክንያቱም ያለ ማስረጃ የሚቀርብ ትንታኔ ራሱ ሌላው የፕሮፓጋንዳ ዓይነት እንጂ የዕውቀት ምንጭ ሊሆን አይችልም። በዚህም ምክንያት ጽሑፉ በጥልቀት ከመታመን ይልቅ፣ በአንድ ወገን ስሜት ላይ የተገነባ የቅሬታ መግለጫ ሆኖ እንዲቀር ያደርገዋል።
ባለአንድ ወገን ትረካ (One-Sided Perspective)
ጽሑፉ በኢትዮጵያ ያለውን የፍረጃና የጥላቻ ፖለቲካ ሲተነትን፣ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ብቻ እንደ ብቸኛ ተጠቂ (Sole Victim)፣ ሌሎች ወገኖችን ደግሞ እንደ ብቸኛ አጥቂ (Sole Aggressor) አድርጎ ያቀርባል። ይህ “ባለአንድ ወገን ትረካ” በሀገሪቱ ያለውን ውስብስብና ዘርፈ-ብዙ የጥላቻ ንግግር ችግር አቅልሎ የሚመለከት ከመሆኑም በላይ፣ በሁሉም ወገኖች ላይ የሚደርሰውን ሰብዓዊና ማኅበራዊ ቀውስ እኩል እውቅና አይሰጥም። በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጥላቻና ፍረጃ ለአንዱ ወገን የተሰጠ “ልዩ ሲሳይ” ሳይሆን፣ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያየ አቅጣጫ እየለበለበ ያለ የጋራ እሳት ነው።
የጽሑፉ ትልቁ ሕፀፅ፣ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞችም ሆነ በሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚሰነዘሩትን መሰል “ጽንፈኛ”፣ “አክራሪ” እና “ፀረ-ለውጥ” የሚሉ የጅምላ ፍረጃዎችንና ጥቃቶችን ሙሉ በሙሉ ችላ ማለቱ ነው። አንድ “ጥናታዊ” ተብሎ የቀረበ ጽሑፍ በሀገሪቱ ያለውን የዲጂታል ምኅዳር ሲመረምር፣ ጥላቻውና ፍረጃው በሁሉም አቅጣጫ የሚወነጨፍ (Multi-directional) መሆኑን መረዳት ነበረበት። ይህን እውነታ ወደ ጎን በመተው ሙስሊሙ ላይ የሚደርሰውን ብቻ ነጥሎ ማውጣት፣ ትንታኔው ከፍትሕ ፍለጋ ይልቅ ለፖለቲካዊ “ተበዳይነት ትረካ” (Victimhood Narrative) መጠቀሚያ እንዲሆን ያደርገዋል።
በተጨማሪም፣ ጽሑፉ የሙስሊሙን ማኅበረሰብ ጥያቄዎች “ሕጋዊና መሠረታዊ” አድርጎ ሲያቀርብ፣ ሌሎች ወገኖች የሚያነሷቸውን ሥጋቶች ግን “የጥላቻ ነጋዴነት” ወይም “ታሪካዊ የበላይነትን የመፈለግ” ውጤት አድርጎ ያጥላላቸዋል። ይህ አድሏዊ አቀራረብ በማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ቅሬታ በውይይት ከመፍታት ይልቅ፣ “እኔ ብቻ ትክክልና ተበዳይ ነኝ፣ አንተ ግን አጥቂና ስህተት ነህ” የሚል ግድግዳ ይገነባል። እውነተኛ አብሮነት የሚመጣው ግን የእያንዳንዱን ወገን ሥጋትና በደል በእኩል ሚዛን መመልከትና እውቅና መስጠት ሲቻል ብቻ ነው።
ሌላው የዚህ ባለአንድ ወገን ትረካ አደገኛ ውጤት፣ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ስም የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ጽንፈኛ ግለሰቦች የሚያሰራጩትን የጥላቻ ንግግር ወይም የሚያደርጉትን የፍረጃ ዘመቻ አለመጥቀሱ ነው። ጽሑፉ ሌሎች ወገኖችን “የጥላቻ ፋብሪካ” ሲል ቢከስም፣ በውስጥ በኩል ያሉትን መሰል ድክመቶች አለመነካቱ ትንታኔው “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ደግሞ በሌላው ወገን ዘንድ ጽሑፉን እንደ “መከላከያ ፕሮፓጋንዳ” እንጂ እንደ “ሐቀኛ የሰላም ጥሪ” እንዳይቆጠር ያደርገዋል።
በማጠቃለያው፣ ባለአንድ ወገን ትረካ የጽሑፉን ሰብዓዊና ሀገራዊ ፋይዳ በእጅጉ አውርዶታል። በኢትዮጵያ ያለው የፍረጃ ፖለቲካ ሰለባው ሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የሀገሪቱ ህልውና መሆኑን ጽሑፉ በመግቢያው ላይ ቢጠቅስም፣ በዝርዝር ትንታኔው ግን ያንኑ “ወገንተኛ” አጥር ጥሶ መውጣት አልቻለም። ይህ ደግሞ ችግሩን ከምንጩ ከመፍታት ይልቅ፣ አንዱ ወገን በሌላው ላይ የሞራል የበላይነት ለመያዝ የሚያደርገው የቃላት ሽኩቻ አስመስሎታል። እውነተኛ መፍትሔ የሚመጣው ግን ሁሉንም ወገን እኩል የሚያይና የጋራ ስቃይን በአንድነት የሚኮንን ሚዛናዊ ትረካ ሲገነባ ብቻ ነው።
የአመክንዮ ግጭት (Logical Contradiction)
በጽሑፍ ውስጥ ሌላኛው የሚታየው ትልቁና መሠረታዊው ድክመት የአመክንዮ ግጭት (Logical Contradiction) ነው። ጽሑፉ “ፍረጃ የሥነ-ልቦና ጦርነት መሣሪያ ነው”፣ “ፍረጃ አመክንዮአዊ ሽባነትን ይፈጥራል” እና “ፍረጃ ጥላቻን ያመርታል” በሚሉ ጠንካራ መርሆዎች ላይ ቆሞ ይነሳል። ሆኖም ግን፣ ጸሐፊው እነዚህኑ እሴቶች ለራሱ ትንታኔ ተግባራዊ ሲያደርጋቸው አይታይም። ፍረጃን እያወገዘ በሌላ በኩል ራሱ እጅግ የከረሩ የፍረጃ ቃላትን መጠቀሙ ጽሑፉ በራሱ ላይ እንዲዘምትና የአመክንዮ መሠረቱ እንዲናጋ ያደርገዋል።
ይህ የአመክንዮ ግጭት በግልጽ የሚታየው ጸሐፊው “የጅምላ ፍረጃን” እንደ ስልታዊ ስህተት በሚተነትንበት አንቀጽና ሌሎች ወገኖችን በሚከስበት አንቀጽ መካከል ነው። በአንድ በኩል “ማንኛውንም ሃይማኖታዊና ብሔራዊ ስሜት ቀስቃሽ ጉዳዮችን በመጠቀም ሕዝብን ለራሳቸው ስውር አጀንዳ ማሰለፍ ስህተት ነው” ይላል። በሌላ በኩል ግን እሱ ራሱ “ጽንፈኛ ብሔርተኞች”፣ “የፋኖ ደጋፊዎች” እና “በእምነት ስም የሚንቀሳቀሱ አክራሪዎች” የሚሉ ታፔላዎችን በመጠቀም ሰፋፊ ማኅበረሰባዊ ክፍሎችን በጠላትነት ይፈርጃል። ይህ “ሌላው ሲያደርገው ጽንፈኝነት፣ እኔ ስናገረው ግን ጥናታዊ ትንታኔ” የሚል የአመክንዮ ስህተት (Double Standard) የጽሑፉን ሞራላዊ ልዕልና ያሳጣዋል።
በተጨማሪም ጽሑፉ “ከወዳጅ ይልቅ ጠላትን ማምረት ስልታዊ ኪሳራ ነው” በማለት ምክር ይለግሳል። ነገር ግን ጽሑፉ ራሱ ካለው ርዝመት ውስጥ አብዛኛው ክፍል የሚያተኩረው “ጠላት” ያላቸውን አካላት ማንነት በመተንተን፣ ስልታቸውን በማጋለጥና በስማቸው ላይ ጥቁር ቀለም በመቀባት ላይ ነው። ጸሐፊው ጠላትን ማምረት ኪሳራ መሆኑን እየሰበከ፣ በገጽታው ላይ ግን ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ በርካታ “ጠላቶችን” (ከፋኖ እስከ ኦርቶዶክስ አንቂዎች) በዝርዝር እያስተዋወቀ ይገኛል። ይህ መመሪያውና ተግባሩ የማይገጣጠምበት (Inconsistency) አካሄድ አንባቢውን ግራ ያጋባል።
ሌላው የአመክንዮ ግጭት የሚታየው “ዝምታና መገለል” የሚለውን ነጥብ በሚተነትንበት ወቅት ነው። ጽሑፉ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በፍረጃ ምክንያት ድምፁን እንዳያጠፋና እንዳይገለል ያስጠነቅቃል። ሆኖም ጸሐፊው የሚጠቀምባቸው ቃላትና የሚሰነዝራቸው ክሶች ሌሎች ወገኖች (ለምሳሌ ለትችቱ ሰለባ የሆኑት) ራሳቸውን እንዲከላከሉና በምላሹ እነሱም የራሳቸውን የፍረጃ ግንብ እንዲገነቡ የሚገፋፋ ነው። ፍረጃን ለማቆም በሚል ሰበብ ሌላ የፍረጃ ግንባር መክፈት፣ ጸሐፊው ሊያስቆመው የፈለገውን “የፍረጃና የጥርጣሬ አዙሪት” (Cycle of Labeling) ይበልጥ እንዲሽከረከር ያደርገዋል።
የአመክንዮ ግጭት የጽሑፉን ተአማኒነት ወደ ዜሮ ያወርደዋል። አንድ ሐሳብ ትክክል የሚሆነው ለሁሉም ወገን በእኩልነት ሲሠራ ብቻ ነው። ፍረጃን እንደ ክፋት የሚያይ ጽሑፍ፣ የራሱ ቃላትና ትንታኔዎች ከፍረጃ የጸዱ ሊሆኑ ይገባ ነበር። ጸሐፊው ግን “እሳትን በእሳት” ለማጥፋት በመሞከሩ፣ ጽሑፉ ከሰላም ጥሪነት ይልቅ ወደ ሌላኛው የግጭት መሣሪያነት ተቀይሯል። ይህ የአመክንዮ ግጭት ጽሑፉን ለትችት የተጋለጠና ውጤቱንም “ስልታዊ ኪሳራ” እንዲሆን ያደርገዋል።
መፍትሔ-አልባ ትንተና
ጀበሉ በጽሑፍ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ለመተንተን ሰፊ ገጾችን ቢጠቀምም፣ በመጨረሻ ግን ላነሳቸው የተወሳሰቡ ችግሮች ምንም ዓይነት ተግባራዊ መፍትሔ ሳያሳይ ያጠቃልላል። አንድ ጽሑፍ “ስልታዊ አካሄድን” እና “የሥነ-ልቦና ጦርነትን” ለመመከት ካለመ፣ ከትነተናው ባሻገር ተቋማዊ፣ ሕጋዊ ወይም ማኅበራዊ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን መጠቆም ነበረበት። ሆኖም ይህ ጽሑፍ በችግሮች ትረካ (Problem-oriented) ላይ ብቻ የተንጠለጠለ በመሆኑ፣ ለአንባቢው የሚሰጠው ፋይዳ ከቅሬታና ከቁጭት መጨመር ባለፈ ዘላቂ መረጋጋትን ሊያመጣ አይችልም።
የጽሑፉ ዋነኛ ሕፀፅ፣ “ይህንን የሐሰት ትርክት መመከት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው” የሚል ጥሪ ከማቅረብ ባለፈ፣ ያ “መመከት” እንዴት ሊከናወን እንደሚችል ግልጽ መንገድ አያሳይም። ለምሳሌ፦ የተጠቀሱትን “የዲጂታል ዘመቻዎች” በሕግ አግባብ እንዴት መጋፈጥ ይቻላል? በማኅበረሰቦች መካከል ያለውን የጥርጣሬ ግንብ ለማፍረስ ምን ዓይነት የውይይት መድረኮች ያስፈልጋሉ? ወይም ደግሞ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ራሱን ከፍረጃ ለመከላከል ምን ዓይነት የውስጥ ማሻሻያዎችን ማድረግ ይኖርበታል? ለሚሉት ጥያቄዎች ጽሑፉ ምላሽ የለውም። መፍትሔ የሌለው ትንተና ደግሞ ችግሩን ከማጋለጥ ይልቅ “ተስፋ መቁረጥን” እና “መካሰስን” የማራዘም ዕድሉ ሰፊ ነው።
በተጨማሪም ጽሑፉ “ጠላትን ማምረት ስልታዊ ኪሳራ ነው” ቢልም፣ ራሱ ግን አዲስ የጋራ መግባቢያ መንገድ (Common Ground) አይዘረጋም። አንድ እውነተኛ የመፍትሔ ሰው ችግሮችን ከጠቀሰ በኋላ፣ ተቀናቃኝ ወገኖች እንኳ ሳይቀሩ ሊቀመጡበት የሚችሉትን የሰላም ጠረጴዛ ማመቻቸት ይኖርበታል። ይህ ጽሑፍ ግን “እነዚህ አካላት ሊደገፉ ወይም የትግሉ አካል ሊደረጉ አይገባም” በማለት ማግለልን (Exclusion) እንደ ብቸኛ መፍትሔ ያቀርባል። ይህ ደግሞ ግጭቶችን ከማርገብ ይልቅ የልዩነት መስመሩን ይበልጥ እንዲሰመር በማድረግ የፖለቲካና የሃይማኖት ውጥረቱ እንዲቀጥል ያደርገዋል።
ሌላው የመፍትሔ-አልባነቱ መገለጫ፣ ጽሑፉ “የእኛን የሰላም እሴት ሊያፈርሱ አይችሉም” በሚል የተለመደ ንግግር መደምደሙ ነው። ይህ “የምኞት ሐሳብ” (Wishful Thinking) እንጂ ተጨባጭ መፍትሔ አይደለም። በጽሑፉ መጀመሪያ ላይ “የሥነ-ልቦና ጦርነቱ ማኅበረሰቡን ሽባ እያደረገ ነው” ተብሎ ከተገለጸ በኋላ፣ መጨረሻ ላይ “ሊያፈርሱን አይችሉም” ብሎ መደምደም ራሱ ግጭት ያለበት ድምዳሜ ነው። ችግሩ ያን ያህል አደገኛ ከሆነ፣ መፍትሔውም እንደ ችግሩ ክብደት ጠንካራና ተግባራዊ ሊሆን ይገባ ነበር። ጽሑፉ ግን በምሬት ጀምሮ በተስፋ-ቢስ ዛቻ ወይም በደፈናው ማስጠንቀቂያ ይቋጫል።
ጽሑፉ ቁስልን በማከክ ረገድ ስኬታማ ቢሆንም፣ መድኃኒት በመጠቆም ረገድ ግን እጅግ ደካማ ነው። መፍትሔ-አልባ ትንተናዎች አብዛኛውን ጊዜ ተከታዮችን ለቁጣና ለተቃውሞ ከማነሳሳት ባለፈ፣ አርቆ አሳቢና ገንቢ የሆነ ማኅበረሰባዊ ንቅናቄ እንዲፈጠር አይረዱም። በመሆኑም ጽሑፉ በኢትዮጵያ ዲጂታል ምኅዳር ለሚታየው የጥላቻ ፖለቲካ መፍትሔ ከመሆን ይልቅ፣ የችግሩን መኖር በምሬት የሚያስተጋባ ሌላኛው የጩኸት ድምፅ ሆኖ እንዲቀር ያደርገዋል።
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ የአሕመዲን ጀበል ጽሑፍ በኢትዮጵያ ዲጂታል ምኅዳር ውስጥ ያለውን የፍረጃና የሥነ-ልቦና ጦርነት ሥጋት ለመጠቆም ቢሞክርም፣ የቀረበበት መንገድ ግን ራሱ በፈረጀው ስህተት ውስጥ የወደቀ ሆኖ ተገኝቷል። በጅምላ ፍረጃን፣ ስሜት ቀስቃሽ ቃላትንና የማስረጃ እጥረትን መሠረት ያደረገ ትንታኔ፣ ችግሩን ከማከም ይልቅ በዜጎች መካከል ያለውን የጥርጣሬ ግንብ ያገዝፋል። እውነተኛ ምሁራዊና ሃይማኖታዊ ተልዕኮ የሰዎችን ቁስል በመነካካት ስሜትን መኮርኮር ሳይሆን፣ የቁስሉን ምንጭ በጥናት ለይቶ ለሁሉም ወገን የሚተርፍ የጋራ መፍትሔ ማመንጨት ነው።
የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አብሮነት የሚጸናው አንዱ ወገን ሌላውን “አጥቂ” አድርጎ በመፈረጅ በሚያገኘው ጊዜያዊ የሞራል የበላይነት ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ወገን በሌላው ላይ የሚሰነዝረውን ፍረጃና ጥላቻ በሐቀኝነት ለመጋፈጥ ሲቆርጥ ብቻ ነው። እንደ አሕመዲን ጀበል ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም፣ የሚጽፏቸው ሐሳቦች በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ብቻ ሳይሆን፣ በተቃራኒው ወገን ባሉት ዜጎች ዘንድም እንደ ተስፋና እንደ ሰላም ጥሪ እንዲታዩ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል። ጥላቻን በጥላቻ፣ ፍረጃን በፍረጃ ለመመከት መሞከር የጥፋት አዙሪቱን ከማቅለጥ ይልቅ ይበልጥ እንዲፋፋም ያደርገዋል።
የጋራ ቤታችንን ለማጽናት የምናደርገው ጉዞም መሠረቱ እርስ በርስ መናናቅ ሳይሆን መከባበር፣ መካሰስ ሳይሆን መመካከር ሊሆን ይገባል። የወሎው የአብሮነት እሴት እንደሚያስተምረን፣ ልዩነቶቻችንን በውይይትና በአመክንዮ መፍታት ስንችል ብቻ ነው የፍረጃ ፖለቲካን ማሸነፍና ለትውልድ የምትሆን ሀገር ማቆየት የምንችለው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






