የአፍሪካ ቀንድ የረዥም ጊዜ ቀጠናዊ ጥልፍልፎሽ (regional security complex) የተመሰረተው በትብብር ሳይሆን፤ በጥሎ ማለፍ (mutual subversion) ላይ ነውና፤ ኢትዮጵያ በዚህ አስቀያሚ ስትራቴጂክ ጨዋታ ውስጥ “ጥዬ ማለፍ ያስችለኛል” ያለችውን ሁሉ የማድረግ ሉአላዊ መብቷን በመጠቀሟ ተነጥላ ልትኮነን አይገባም። ብትኮነንም ከቁብ ልትቆጥረው አይገባም። አጠቃላይ ሁኔታውን የኢትዮጵያ መንግስት ጥፋት አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩ ድኩማንም ከፍ ሲል ሊታዘንላቸው ዝቅ ሲል ሊሳቅባቸው እንጂ ከቁም ነገር ሊወሰዱም አይገባም። ከሰሞኑ በዓለም አቀፍ እና በቀጠናዊ ደረጃ እንዳየነው፤ ሀገራት ብሄራዊ ጥቅም እና ደህንነታቸውን ለሞራል እና ለህግ መርሆዎች ለመተው ፈቃደኛ አይደሉም። በዚህ አውድ ውስጥ ኢትዮጵያም የጨዋታውን ህግ ከመከተል ውጪ ምርጫ የላትም! ስለዚህ don’t hate the player, hate the game ነው ነገሩ። Period!
Oluma M. Wodajo| ነጻ አስተያየት
እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ እንዲህ ብለህ ስለገዛ ሀገርህ ለማሰብ በተፈጥሮ ወይም በሰው ሰራሽ አደጋ የጎደለ የአንጎል ክፍል ሊኖርህ ይገባል!
በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያን የመሩ መንግስታት (ወይም በጥቅሉ አብዛኞቹ ታዳጊ ሃገራት) ውስጣዊ፣ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶቻቸውን ለማርገብ አንድ ሁነኛ (ኢኮኖሚያዊ ወይም ወታደራዊ አቅሙ የፈረጠመ) ወዳጅ ያበጃሉ። ብዙ ምዕተ አመታት ወደኋላ ሳንሄድ በ20ኛው እና በ21ኛው ክፍለ ዘመናት ኢትዮጵያን የመሩት መንግስታት በዚህ አካሄድ የተካኑበ ነበሩ። ለምሳሌ የአጼ ኃይለስላሴ መንግስት ከአሜሪካ፣ የኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም መንግስት ከሶቭየት ህብረት፣ የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ መንግስት ከአሜሪካ (በኋላም ከቻይና) ጋር ጥብቅ ትስስር መስርተው ከፍተኛ ድጋፍ ያገኙ ነበር።
እነዚህ መንግስታት በተቀናቃኞቻቸው “የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ወኪል”፣ “የሶቭየት ሶሺያል ኢምፔሪያሊዝም ጥገኛ”፣ “በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ፍላጎት እና ጉዳይ ፈጻሚ (proxy)” ሲባሉ ነበር። መንግስትታቱ አሜሪካን ወይም ሶቭየት ህብረትን የቀረቡት ዝቅ ሲል ለራቸው አገዛዝ ከፍ ሲል ለሀገራቸው ጥቅም ነው የሚል ተንታኝ ብዙም አይገኝም ነበር። ምክንያቱም እንዲህ አይነቱ የሰከነ ግምገማ ለመንጋ ፍርድ እና መገለል ያጋልጣልና። ለምሳሌ የሶማሊያው ዚያድ ባሬ ኢትዮጵያን መውረሩን ተከትሎ በነበረው ጦርነት መሀል “ጦርነቱ የሶቭየቶችን በአፍሪካ ቀንድ መስፋፋት እና ተጽዕኖ ለማጠናከር የሚደረግ ነው፣ ርዕዮተ አለማዊ ነው፣ ኢትዮጵያ በብሄረሰቦች ላይ የጫነችውን ቅኝ አገዛዝ ለመገርሰስ ነው…ወዘተ” የሚሉ ኢትዮጵያዊ የሆኑም ያልሆኑም “ተንታኞች” ነበሩ።
የኢትዮጵያ መንግስት ከሶማሊያ ጋር የሚዋጋው የሃገሩን ብሄራዊ ጥቅም እና ደህንነት ለማስከበር ነው ብሎ መሞገት ዝቅ ሲል እንደ ደርግ/ሶቭየት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ከፍ ሲል ደግሞ እንደ ደርግ/ሶቭየት “ቅልብ ካድሬ” ያስቆጥር ነበር። በኢህአዴግ ጊዜም ተመሳሳይ ሁኔታ ለሁለት ጊዜያት ተከስቶ ያውቃል። በ1990/92ቱ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት እና በሶማሊያ በተደረገው የ1999ኙ የኢትዮጵያ ጸረ አል ኢትሃድ/UIC ዘመቻ ወቅት። በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ለኢትዮጵያ መንግስታት ፈታኙ ነገር የቀጠናውን ተቀናቃኞች ብቻ ሳይሆን፤ በሀገር ውስጥ እና በዳያስፖራ የተኮለኮሉትን አንድን አገዛዝ መቃወምን እና የሀገርን ዘላቂ ጥቅም መጻረርን ያልለዩ ደናቁርትን ተጽዕኖ መቋቋም ነበር። ምክንያቱም የፈለገ ጡንቸኛ ቢሆን፤ አንድ ሀገር/መንግስት የውስጥም የውጪም ግንባር ተከፍቶበት የሚያካሂደው “ዘመቻ” የማይቻል ባይሆንም እንኳን ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል እና ከባድ ነውና!
ወደኋላ ሄጄ ይህን ያህል ያልኩበት ዋነኛው ምክንያት ዛሬ ላይ ሆኜ ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ ስገመግመው ታሪክ ራሱን መልሶ መላልሶ በሚደግምበት ሁኔታ እና ሀገር ውስጥ መኖሬ እየተሰማኝ ስለሆነ ነው። አንድ ሰነፍ፣ ደንቆሮ እና እንጭጭ የጀመረው አማተር ፕሮፓጋንዳ፤ “ከእኔ በላይ ላ’ሳር” በሚሉ እንኩቶ “ተንታኞች” ተደጋግሞ ሲስተጋባ በማየቴም ነው። ጉዳዩን ችላ ብዬ ባልፈውም እንደ ባለሙያ በተካፈልኩባቸው ዝግ እና ይፋዊ መደረኮች እንዲሁም የኮንሰልታንሲ ስራዎች ጭምር ከመደጋገሙ የተነሳ፤ እንደ አንድ የማያሻማ ሀቅ እየተወሰደ የመጣ አጀንዳ በመሆኑም ጭምር ነው። ይኸውም “ኢትዮጵያ የUAE ጉዳይ ፈጻሚ/proxy ሆናለች” የሚል አስቂኝ ፕሮፓጋንዳ ነው። ይህ ፕሮፓጋንዳዊ ውንጀላ ኢትዮጵያዊ ካልሆኑ ሰዎች ሲመጣ አይገርመኝም። ከኢትዮጵያውያን ሲመጣ ግን እጅግ ግርም ይለኛል። “ሰው ሀገሩን እንዴት በዚህ ልክ አያውቅም፤ የገዛ ሃገሩን የሚመለከቱ ጥቅሞችን እና ጂኦፖሊቲካዊ ጉዳዮችንስ እንዴት በዚህ ደረጃ ለመረዳት ይቸገራል?” የሚለው ሃሳብ ይረብሸኛል።
የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (UAE) ከ2010 ጀምሮ “ሞቅ ያለ” ሊባል የሚችል ግንኙነት መመስረታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። UAE አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ ኮከቧ በገጠመላት ሃገራት እንደምታደርገው ሁሉ በኢትዮያም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና የብሄራዊ ደህንነት ፋይዳ ያላቸው ኢንቨስትመንቶችን እያደረገች ነው። በምላሹ የምታገኘው ጥቅም አይነት፣ ብዛት እና ጥራት ቢያከራከርም፤ በዚህ ዓለም ዓቀፍ ድጋፍ በተመናመነበት ወቅት የዚህ ፈርጀ ብዙ ኢንቨስትመንት ዋነኛ ተጠቃሚዋ ኢትዮጵያ መሆኗ ግልጽ ነው።
የገልፍ ሃገራት ዋነኛ የተጽዕኖ ምንጭ በሌሎች ሀገራት እንደ ልብ የሚያፈሱት መዋዕለ ነዋይ ነውና፤ የኢትዮጵያ መንግስትም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅሞች ባማከለ መልኩ ይሄን አጋጣሚ መጠቀሙ የሚበረታታ ነው። ከዚህ አልፎ ተርፎ ግን እንደ ኢትዮጵያ ያለን የረዥም ዘመናት የመንግስትነት ታሪክ፣ ለዘመናት የዘለቀና የተደራጀ የውጪ ግንኙነት ልምምድ/ልምድ፣ ፈርጀ ብዙ ሀገራዊ፣ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፍላጎቶች (interests) ያሉት ሀገር እና መንግስት የአንድ ሀገር “ጉዳይ ፈጻሚ” አድርጎ ማቅረብ ከዚህ ቀደም በነበሩት መንግስታት ወቅት ትክክል እንዳልነበረ ሁሉ፤ ዛሬም ጭልጥ ያለ ቅጥፈት እና የመረዳት አቅም ንጥፈትን ያጋለጠ ተራና ያረጠ ፖለቲካ ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ በሁለቱ ሀገራት መሀከል ያለው ግንኙነት ከዚህ ቀደም የነበሩ መንግስታት ከተለያዩ ሀገራት ጋር በተለያዩ ጊዜያት እንደመሰረቷቸው ግንኙነቶች ሁሉ በጋራ ጥቅም እና መጠቃቀም ላይ የተመሰረተ፤ የኢትዮጵያን መዋቅራዊ ልምሻ (structural predicaments) ከግምት ያስገባ ነው። እንደማንኛውም የሁለትዮሽ ግንኙነት በሂደቱ ውስጥ እንደ ሀገር የምናተርፈውም የምንከስረውም ነገር መኖሩ ደግሞ አይቀሬ ነው። የትኛውም ግንኙነት ጠቃሚም ጎጂም ጎን አያጣውም። ዋናው ነገር ትርፉ ከኪሳራው እንዲበልጥ (maximizing self-interest) መትጋቱ ላይ ነው።
ለምሳሌ በቅርብ ሳምንታት “ኢትዮጵያ የሱዳኑን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል (RSF) ትረዳለች፤ የስልጠና እና ሎጂስቲክስ ማዕከል በግዛቷ እንዲኖር ፈቅዳለች” የሚለው ውንጀላ ኢትዮጵያዊ በሆኑም ባልሆኑም አካላት እንደ ትኩስ አጀንዳ እየተራገበ መሆኑን፤ በዚህም የኢትዮጵያን መንግስት አንድም የቀጠናው በጥባጭ በተጨማሪም በሱዳን የUAE ፍላጎት አስፈጻሚ አድርጎ ለማቅረብ የሚኬድበትን ርቀት ብንመለከት ነገሩ ከፕሮፓጋንዳ ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው መረዳት አይከብድም። ምክንያቱም የሱዳን ሁኔታ ከUAE ይልቅ አብዝቶ የሚመለከተው ኢትዮጵያን ነውና። የአልቡህራን መንግስት የለየለት ባላንጣነቱ ለኢትዮጵያ እንጂ ለUAE አይደለምና።
ቢያንስ ቢያንስ ከ2013 ጀምሮ ያልተካለሉ የድንበር ቦታዎችን ከመያዝ አልፎ በአባይ ውሃ ጉዳይ ለግብጽ ተደርቦ የሚዝተው፤ በውስጥ ጉዳይ ገብቶ ለህወሐት/ወያኔ “አርሚ 70” ስልጠና፣ ሎጂስቲክስ እና መረጃ የሚያቀርበው፣ የተለያዩ ታጣቂዎች መጠለያ እና መንደርደሪያ የሚያመቻቸው፤ IAEን ሳይሆን ኢትዮጵያን ለመጉዳት ነውና። በዚህ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ ከሱዳን አንጻር ያላት ፍላጎት/ጥቅም ከUAE ከገጠመ፤ ሁለቱን ሃገራትም በጋራ እንዲሰሩ ካደረገ so be it! የአልቡህራኗ ሱዳን የጸረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች መናኸሪያ ሆና እስከቀጠለች ድረስ፤ ሱዳንን በተመለከተ እንደ ሀገር ሞራላዊም ሆነ መለኮታዊ አቋም የሞንይዝበት ምድራዊ ምክንያት የለም።
በመጨረሻም….የአፍሪካ ቀንድ የረዥም ጊዜ ቀጠናዊ ጥልፍልፎሽ (regional security complex) የተመሰረተው በትብብር ሳይሆን፤ በጥሎ ማለፍ (mutual subversion) ላይ ነውና፤ ኢትዮጵያ በዚህ አስቀያሚ ስትራቴጂክ ጨዋታ ውስጥ “ጥዬ ማለፍ ያስችለኛል” ያለችውን ሁሉ የማድረግ ሉአላዊ መብቷን በመጠቀሟ ተነጥላ ልትኮነን አይገባም። ብትኮነንም ከቁብ ልትቆጥረው አይገባም። አጠቃላይ ሁኔታውን የኢትዮጵያ መንግስት ጥፋት አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩ ድኩማንም ከፍ ሲል ሊታዘንላቸው ዝቅ ሲል ሊሳቅባቸው እንጂ ከቁም ነገር ሊወሰዱም አይገባም። ከሰሞኑ በዓለም አቀፍ እና በቀጠናዊ ደረጃ እንዳየነው፤ ሀገራት ብሄራዊ ጥቅም እና ደህንነታቸውን ለሞራል እና ለህግ መርሆዎች ለመተው ፈቃደኛ አይደሉም። በዚህ አውድ ውስጥ ኢትዮጵያም የጨዋታውን ህግ ከመከተል ውጪ ምርጫ የላትም! ስለዚህ don’t hate the player, hate the game ነው ነገሩ። Period!
የግርጌ ማስታወሻ፦ “ይሄን ረዥም እና አሰልቺ ፅሁፍ የፃፍከው ስንት ተከፍሎህ ነው?” ለምትሉ፤ መልሱ “አንድ የነዳጅ ጉድጓድ በUAE እና አንድ ባለ 3 መኝታ ኮንዶሚኒየም በአዲስ አበባ” የሚል ነው
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






