የሐስን ሼኽ ኢትዮጵያ መመላለስ ለዕቅዱ እንቅፋት መሆኑ ተሰምቷል
አዲስ ሪፖርተር – “ጦርነት ያብቃ” በሚል እነ አቶ ልደቱ በመሰረቱት የአብሮነት ስብስብ ውስጥ በቦርድ አባልነት ከተመረጡት ሃያ አንድ አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል ገቢሳ ኢትዮጵያን የሚወጋ ጦር እንዲያደራጁ በግብጽ መሾማቸው ተሰማ። የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼህ የስልጣን ዘመናቸው ሊያበቃ መሆኑ ችግር ፈጥሯል።
የአዲስ ሪፖርተር የአሜሪካ ተባባሪ ከኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር የተከለውን ወገን አነጋገሮ ባገኘው መረጃ መሰረት ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል የተሾሙት በይፋ ኃላፊነቱን የወሰዱት ከሶስት ወር በፊት ሲሆን፣ ቀደም ሲል ጀምሮ ለዚህ ስራ ናይሮቢ፣ ሶማሊያና ቱርክ ይመላለሱ ነበር።
ፕሮፌሰሩ በኤርትራ በኩል ከግብጽ የወሰዱት ኃላፊነት በምስራቅ ኢትዮጵያ ጦርነት ለማስፋትና የኢትዮጵያን ጦር ኃይል ለመከፋፈል የተያዘውን ዕቅድ እንዲተገብሩ ነው። እንደ ተባባሪያችን ዘገባ ከሆነ “ጠብመንጃ ይብቃ” ከሚለው የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ያፈነገጠውን ኃይል በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር የሶማሌን ክልል በሚያዋስነው ኮሪዶር የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሰራዊትን በመሳብ አብሮ ለማቀናጀትና ሁከት ለማስነሳት ነው።
“በሰላማዊ ትግል ብቻ” የሚል አቋም እንደሚያራምድ በሚገልጸው የአብሮነት ስብስብ ውስጥ አንዱ ከሆኑት ፋይሰል ሮበሌ ጋር አብረው እየሰሩ እንደሆነ መረጃ ጠቅሶ የዘገበው ተባባሪያችን፣ “ በአብርሆት የዙም ስብሰባ ላይ ፋይሰል ሮበሌ ከናይሮቢ ሆነው ለሶስት ሳምንት ያህል እዚሁ እቆያለሁ ፕሮፌሰር ሕዝቅዔልም ይመጣል። ብዙ ስብሰባ አለን” በማለት መናገራቸውን እንደ አንድ አብይ በመጥቀስ ስራው ቀደም ብሎ የተጀመረ መሆኑን ገልጿል።
በዛው ቀን አቶ የስብሰባው መሪ አቶ ልደቱ “ ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል አውሮፕላን ልሳፈር ነው ብሎ የስልክ መልዕክት ልኮልኛል። ከቻልኩ እገባለሁ ብሏል ” በማለት ሲናገሩ መስማታቸውን ስብሰባው ላይ ከነበሩ መካከል ለአዲስ ሪፖርተር ምስክርነት ሰጥተዋል። በወቅቱ ፌይሰል ሮቤልን ለማግኘት በረራ ያደረጉት ወደ ኪንያ ነበር።
እሳቸው ኬንያ በገቡ ማግስት የሰላም መንገድ እንደማያዋጣ ጠቅሶ የተከፈለው የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ቡድን የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታውንና የጋዝ ፕሮጀክቱን በመቃወም መግለጫ ማውጣቱን ያስታወሱት እነዚሁ ወገኖች፣ ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል በኬንያና ኢትዮጵያ መንግሥት የጋራ ኦፕሬሽን የተመታውንና የተበተነውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አሰባስቦ በሶማሊያ በኩል ለማስረግ የተያዘው ዕቅድ ግን እንደታሰበው እንዳልተሳካ ራሳቸው ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል ሲናገሩ ከሰሙ ወገኖች ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
ለምርጫ አምስት ወር የቀራቸውና ዳግም ለመመረጥ ብዙም ዕድል እንደማይኖራቸው ከወዲሁ ግምት እየተሰጠባቸው ያሉት የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼኽ አቋም ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል በይፋ ለተሰጣቸው ኃላፊነት እንቅፋት እንደሆነ መሆኑ ተሰምቷል።
በሶማሊያ ጉዳይ የዘወትር ተባባሪያችን እንዳሉት ከሆነ ሶማሊያ ካሏት አምስት ክልሎች ሶስቱ ማለትም ጁባ ላንድ፣ ፑንት ላንድና ባይደዋ ለሐሰን ሼኽ ጀርባ ሰጥተዋል። አሜሪካ ትኩረቷ ወደ ሶማሊላንድ በመሆኑ በጀት ቀንሳለች፣ ግብጽም በኩርፊያ የሚጠበቅባትን የሰላም አስከባሪ ክፍያ 190 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል አልፈቀደችም።
በሶማሊያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሱሌማን የግብጽ ወታደሮች በሰላም አስከባሪ ስም ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ቀርበው የመስፈራቸው ጉዳይ የማይታሰብ መሆኑን ማስታወቃቸው አይዘነጋም። የሶማሊያ የአካባቢው መሪዎችና ሕዝቡም የኢትዮጵያን ሰራዊት እንደሚወድና ሌሎች ድርሽ እንዲሉበት እንደማይፈልግ በይፋ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።
በዚህ ምክንያት ሶማሊያ ድንበር ላይ የኦጋዴን ነጻ አውጪ አፈንጋጭ ቡድንና መበታተኑ እየተገለጸ ያለውን የኦሮሞ ነጻ አውጪ ኃይል በጋራ ለማደራጀት ያተያዘው ዕቅድ ዕክል እንደገጠመው ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል በአሜሪካ ላሉ ለሚቀርቧቸው “የትግል አጋሮቻቸው” መናገራቸው ተሰምቷል።
የሐሰን ሼኽ ወደ ኢትዮጵያ አብዝተው መመላለሳቸውና ቀደም ሲል ከግብጽና ኤርትራ ጋር ሲያደርጉት የነበረውን የዕለት ተዕለት ግንኙነት መቀነሳቸው ከላይ ለተገለጸው መረጃ ማሳያ እንደሆነ የአዲስ ሪፖርተር የመረጃ ሰዎች አመልክተዋል።
አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የሃዊዬ ጎሳ ብቻ ድምጽ ሊያገኙ ቢችሉም ዳግም ሊመረጡ ባለመቻላቸው ሐሰን ሼኽ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላቸውን የሶስቱን ክልል መሪዎችና የጎሳ አለቆች ለማግባባት ኢትዮጵያን እየተማጸኑ እንደሆነ መረጃዎች አሉ።
ይህን አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግስት አቋም ምን እንደሆነ ለመረዳት አግባብ ያላቸው አካላት መረጃ እንዲያጋሩ በስልክ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል የግል ስላካቸው ላይ በስካይፒ ደውለን ” መልሼ እደውላለሁ” በማለት ጉዳዩን ከሰሙ በሁዋላ ቃልቸውን ባለመጠበቃቸው ሃሳባቸውን ማከተት አልቻልንም።
ግብጽ ኤርትራንና ትግራይን በመያዝ በማራ ክልልና በኦሮሚያ እንዲሁም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ጦርነት የማስፋትና ኢትዮጵያን ሰላም የመንሳት ዕቅድ ይዛ በከፍተኛ በጀት “ኢትዮጵያዊ” የሚባሉ ሚዲያዎችን ይዛ እየሰራች መሆኑ በተደጋጋሚ በማስረጃ የሚቀርብ ጉዳይ ነው። ከግብጽ ጋር እየሰሩ ያሉ ቡድኖችና ሚዲያዎችም በገሃድ ይህንኑ አምነው ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው።





