” የትግራይ ሕዝብ እንኳን በጥይት በቲማቲም ለመፈናከት አይፈቅድም ” የትግራይ ጄኔራል ፤ እነ ደብረጽዮን ሕዝብና ሰራዊት ማስተባበር አልቻሉም

Date:

አዲስ ሪፖርተር – “ህወሓት እና አንዳንድ የጦር ጀነራሎች የፕሪቶሪያ የተኩስ አቁም ስምምነትን መሰረት በማድረግ ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ትግራይን ወደ ሌላ ዙር ጦርነት ለማስገባት እየፎከሩና የጦርነት ዝግጅት እያደረጉ ነው ” ይላል የትግራይ ልሂቃንና ባለሙያዎች ማሕበር ባሳለፈው ጥሪ። አዲስ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የጦር ጄኔራል ደግሞ ” የትግራይ ሕዝብ እንኳን በጥይት በቲማቲም ለመፈናከት አይፈቅድም” ብለዋል።

የትግራይ ልሂቃን እና ባለሙያዎች ማሕበር (GSTS) በትግራይ ያንዣበበው የጦርነት ዳመና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥሪ ባቀረበበት መግለጫው ” የትግራይ ሕዝብ ዋና ፍላጎቱ ሰላምና ሰላም ብቻ ነው” በትግራይ ውስጥ ሕዝብ የያዘውን አቋም ደግሟል።

የትግራይ ክልል መሪ የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት “ በርካታ ቁጥር ያላቸው የትግራይ ኤሊቶች ጦርነቱ እንዲቆም የማድረግ አቅም አላቸው። ግኙነትም አላቸው። ስራቸው ጦርነት ማስቆም መሆን አለበት” በማለት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጡት ሰፊ ቃለ ምልልስ መናገራቸውን ተከትሎ ነው ማህበሩ “ የትግራይ ሕዝብ ጦርነቱን እምቢ በል” ሲሉ ጥሪ ያቀረቡት።

“መላው የትግራይ ህዝብ ጦርነትና የጦርነት ወሬ መስማት አይፈልግም” ያለው የትግራይ ልሂቃንና ባለሙያዎች ማህበር፣  ” ትህነግ እና አንዳንድ የጦር ጀነራሎች የፕሪቶሪያ የተኩስ አቁም ስምምነትን መሰረት በማድረግ ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ትግራይን ወደ ሌላ ዙር ጦርነት ለማስገባት እየፎከሩና የጦርነት ዝግጅት እያደረጉ ነው ” ሲል ስጋቱንና ግምገማውን አኑሯል።

የማህበሩ መግለጫ ” ሕዝብን የሚመራ አካል ጦርነት ለማስቀረት ይጥራል እንጂ ወደ ጦርነት የሚያመሩ ንግግሮችና ተግባራትን መፈጸም የለበትም ” በማለትም የክልሉን ጊዚያዊ አስተዳደር በጽኑ ወቅሷል። ጦርነት እንዳይነሳ ማድረግ የሚገባውን ሁሉ እንዲያደርግ አሳስቧል።

” የእናቶች ለቅሶ እስካሁን ሊቆም አልቻለም። እናቶች እያለቀሱ ናቸው። ጦርነቱ ያሳረፈው ቁስል ገና አልተሻረም ” ያሉት አቶ ገብሩ ከዚህ ለቅሶና ባላገገመ ቁስል ውስጥ የሚነገዱ እንዳሉ ስም ጠርተው ተናግረዋል።

“ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ የለም” አሉ ገብሩ አስራት። “ ጦርነት እልቂት ፣ ጉዳት፣ ውድመት እንጂ ምንም አይነት ትርፍ አይገኝበትም። ማወቅ ያለብን ግን በጦርነት የሚያተርፉ አሉ። ስልጣናቸውን ማስጠበቅ የሚፈልጉ፣ ስልጣናቸውን ከፍ ማድረግ የሚፈልጉ” በማለት አትራፊዎቹን አመላከቱ።

“በጦርነት የሚነግዱ አሉ። ይሄ  በግልጽ ታይቷል። በትግራይ ጦርነት በልፅገው የወጡ ፣ በጣም ሃብታሞች ሆነው የወጡ ሰዎች አሉ። ሌላው ግን የነበረውን ሃብት ነው የጨረሰው፤ የነበረው ሃብት ተንኮታኮተ ፤ በመቶ ሚሊዮኖች የነበራቸው ኢንቬስተሮች፣ ነጋዴዎች ከስረዋል። በዚህ ጦርነት ፤ ፋብሪካቸው ተቃጥለዋል ፤ የነበራቸው ሃብት ተሽጦም ዕዳቸውን አይከፍልም። ይሄን ያየ ባለሃብት እና ነጋዴ እንደገና ጦርነትና የጦርነት ወሬ መስማት አይፈልግም” በማለት አቶ ገብሩ ዝርዝር ጉዳይ አንስተው ተቃውሞ አሰምተዋል።

በተመሳሳይ የባለሙያዎቹና ልሂቃኖቹ ስብስብ “ አሁን በአካባቢው እያንዣበበ ያለውን የጦርነት ድባብን ለማስቀረት ሕዝቡ፣ በትግራይ ኃይሎችና በዓፋር ያሉ የታጠቁ ሐይሎች እንዲሁም የዳያስፖራው ማሕበረሰብ ለሰላም መቆም እንዳለባቸው” ብሏል።

የትግራይ ሕዝብ ጦርነት እንደማይፈልግ በተደጋጋሚ ማስታወቁን ተከትሎ አዲስ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የጦር ጄኔራል፣ “ ዛሬ ላይ የትግራይ ሕዝብ እንኳን በጥይት በቲማቲም መፈናከት አይፈልግም” ብለዋል። ለጊዜው በሌላ ስራ ላይ እንደሆኑ ያመለከቱት ጄኔራሉ “ ጦርነት በዚህ ዘመን ችግር ያባብሳል እንጂ መፍትሄ አያመጣም። ይህንን ከጦርነቱ በሁዋላ ተምሬያለሁ” ብለዋል።

“ይህ አሁን ያለንበት ዘመን” አሉ ጄኔራሉ “ ያለንበት ዘመን የጠብ መንጃ ትግል የሚደረገበት አይደለም። ከሆነም ትርፉ የባሰ ችግርን መታቀፍና ወደ ሌላ ውስብስብ ጣጣ መግባት በመሆኑ ጦርነትን አማራጭ አድረገው የሚወስዱ ሁሉ ሊያስቡበት የገባል። ቀድሞ በጀመሩት ጦርነት ሳቢያ ውስብስብ ቸግር ውስጥ ተገባ እንጂ የተቃለለ አንድም ችግር የለም። የአሁኑ ደግሞ የባሰ ይህናል”

እንደ እሳቸው ገለጻ ከሆነ በተከፈለው ትህነግ ውስጥ ሌላ ክፋይ አለ። የእነ ዶክተር ደብረጽዮን ቡድን ውስጥ ጦርነት የማይፍለጉ አሉ። እነዚህ ወገኖች ከሻዕቢያ ጋር እየተደረገ ያለውን ግንኙነትም አይፈለጉትም። ይህ ክፍልፍል ቀደም ሲል ጀመሮ የነበረ በመሆኑ በሂደት አሸናፊ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ጄኔራሉ “ትህነግን የማፍረሱ ኃላፊነት ለትግራይ ሕዝብ ብቻ ቢሰጥ የተሻለ እንደሚሆንም እግረ መንገዳቸውን ተናግረዋል። ሲያስረዱም ትህነግን ሌሎች አካላት ሊያፈርሱት በሞከሩ ቁጥር ትህነግ ጉልበት ያገኛል። ይህን እውነታ በጦርነቱ ወቅት በረሃ ሆነው ሲዋጉ ማየታቸውን የሚናገሩት እኚሁ የትግራይ ክልል ተወላጅና የትህነግ አባል ጄኔራል “ አሁን የጦርነት ደመና ይታየኛል፤ በርበርብ ልናስቆመውና የፖለቲካ መፍትሄ ልንፈልግለት ይገባል” ብለዋል።

ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/profile.php?id=61577410241403
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related