አዲስ ሪፖርተር – ሼኽ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ “ህዝቡና አገሬ ይናፍቁኛል” በማለት ከሳዑዲ ያስተላለፉት ልብ የሚነካ መልዕክት፣ “የሰራተኛ ቁጥር ጨምሩ፤ መካከለኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ተፈጥሮ ማየት እፈልጋለሁ፤ የዋጋ ግሽበቱ ደሀውን እየጎዳው ስለሆነ ሸክሙን የሚያቀል መስክ ላይ ኢንቨስት አድርጉ” የሚለው መመሪያቸው፣ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ዓመታዊ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በሚቀርብበት ወቅት ሁሉን የገዛ መልዕክት ነበር። ቢቢሲ ወደ ኋላ ሶስት ዓመታትን ተጉዞ ሚድሮክ ሆራይዘን ፕላንቴሽን ሕጻናትን ጉልበት እንደሚበዘበዝ ጠቅሶ የከሰሰው በዚህ መመሪያና ድርጅታዊ መርህ የሚመራውን ተቋም እንደሆነ ኃላፊዎቹ በሃዘኔታ ይገልጻሉ።
አሰፋ አለምነህ ዘገየ የተወለደው ምዕራብ ጎጃም፣ ሜጮ ወረዳ ነው። በአስራ ሰባት ዓመቱ ወደ አዲስ አበባ መጣ። ሕይወት ባሰበው መልኩ ባለመቀጠሏ ጎዳና ላይ ወደቀ። ማስቲሽና ቤንዚን እየሳበ ሱሰኛ ሆነ። በማስቲሽ እየሰከረ ውሎው ስታዲየም አዳሩም ስቴዲየም ዙሪያ አደረገ። አምስት ዓመት በዚህ መልኩ ሕይወቱን በጎዳና ላይ ገፋ።
ፖሊስ እንደሱ ጎዳና ላይ ከሚኖሩት ጋር ወስዶ ቃሊቲ መጠለያ አኖረው። ከዛም ልብሱ ተቀይሮለት ከሚያሰክረው ዕጽ እንዲያገግም ከተደርገ በኋላ የህይወት ክህሎት ስልጠና ተሰጥቶት በቀረበለት አማራጭ በፈቃደኛነት ወደ ሆራይዞን እርሻ ቡና ለመልቀም እንደሱ ከተስማሙት ባልደረቦቹ ጋር አመራ።
ዛሬ አሰፋ ባለ ትዳርና የልጅ አባት ነው። የድርጅቱ ቋሚ ሰራተኛ እንደሆነ ይናገራል። የልጁ እናትና እሱ በጓሯቸው አቮካዶና ቀላል የጓሮ አትክልት አላቸው። ስለጎዳና ሕይወት ሲያነሳ ይቆጫል። በጎዳና ላይ ስላሉት ሁሉ ልቡ ያዝናል። አሰፋ ለአዲስ ሪፖርተር በስልክ እንዳለው ከሆነ እሱ እስከሚያውቀው ድረስ በግድ የተደረገ ጉዳይ የለም። እንግዲህ እንዲህ ያሉትን አይቶና ምስክርነት ጠይቆ እንዲሰራ የቀረበለትን ጥያቄ ነው ቢቢሲ ያልተቀበለው፣ ግብዣውን አለመቀበሉ የድርጅቱ አመራሮች የሪፖርቱ ዓላማ ሌላ እንደሆነ ማሳያ አድርገው ይቆጥሩታል። ዛሬ ላይ ቢቢሲ ያነሳው ችግር ስለመኖሩ አዲስ ሪፖርተር ያነጋገራቸውን አሰባስቦ ሙሉ መረጃ በተከታታይ ያቀርባል።

ሚድሮክ ኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ሆን ተብሎ የተደረገና በኢትዮጵያ ቡና ኤክስፖርት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ለማሳደር የተያዘ ዕቅድ ጅማሮ ነው። በቢቢሲ ዘገባ ዋቢ የሆነው የኢትዮጲያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን “የዜናው ፍላጎት አልገባኝም” ሲል፣ ክስ የተሰነዘረበት ሆራይዞን ፕላንቴሽን በበኩሉ ቢቢሲ ሶስት ዓመት ወደኋላ ተመልሶ ያነሳው ጉዳይ አጀንዳው እንደ አገር ሊታይ የሚገባና በቡና ኤክስፖርት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን አመልክቷል።
ቢቢሲ “የሚድሮኩ ሆራይዘን ፕላንቴሽንስ እንዴት በሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ እና በታፈሱ ሰዎች ቅጥር ተጠያቂ ሳይሆን ቀረ?” በሚል ርዕስ አማኑኤል ይልቃል በተባለ ሪፖርተር ህዳር 3 ቀን 2018 ያተመው ዘገባ የዘመናዊው የግራጫ ጦርነት አካል መሆኑ የተሰማው ዜና ይፋ በሆነ ቅጽበት ነው። ስልቱ በአገር ደረጃ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን ኩባንያዎችና ተቋማት በሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ማሳጣት፣ ማፍረስ፣ ስራቸው ላይ አሉታዊ ጫና ማሳረፍ፣ የመሳሰሉት መሆኑን ለአዲስ ሪፖርተር አስተያየት የሰጡ የሕግ ባለሙያ አመልክተዋል። ከዚህ በፊትም ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው መንግስት ጥንቃቄ እንዲወስድ ማሳሰባቸውን ተናግራዋል።
“ጎዳና ላይ ቤንዚንና ማስቲሽ እየሳቡ የሚወድቁ፣ በሱስ የሚሰቃዩ ዜጎች አገግመው ወደ ሕይወት ተመልሰዋል። ሄዶ ማየትና ማመስገን ሲገባ ከሞቀ ቤታቸው፣ ከተስተካከል ኑሮ የተፈናቀሉ በማስመሰል መረን የወጣ ሪፖርት ማቅረብ ዓላማው ለመብት የመቆርቆር አይደለም። በኢትዮጵያ ቡና ኤክስፖርት ላይ የተነጣጠረና የተሳሳተ ገጽታ መፍጠር ነው” ሲሉ የሚድሮክ ኃላፊዎች ይናገራሉ።
ቢቢሲ ያወጣው ዘገባ መፍትሄ የተበጀለትን ጉዳይ ወደኋላ ሄዶ ያጣቀሰ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በተለይ ለአዲስ ሪፖርተር አስታውቋል።
ከቅርብ ጊዜው ወዲህ ኢትዮጵያ ከቡና ኤክስፖርት እያገኘች ያለው ገቢ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን በመግለጽ “ቢቢሲ የተጠና ጥቃት ሰንዝሯል” ያሉት የሕግ ባለሙያ ፣ ቢቢሲ ከህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ጋር በማያያዝ ማስተካከያ ተደርጎበት በተቋጨ ጉዳይ ሚድሮክን ጠቅሶ የዘገበው ዘገባ ፍላጎት ግልጽ ሊሆንለት እንዳልቻለ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ገልጿል።
“ሚድሮክ ተራ ነጋዴ ድርጅት አይደለም። በዚህ ደረጃ አይገለጽም ” የሚሉት ኃላፊዎች፣ እጅግ ኃላፊነት በተሞላው አግባብ በህግ ሳይሆን በሞራል የማህበረሰብን፣ የአገርን፣ የአካባቢ ጥበቃን ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ የሚሰራና በዚህም መርሁ ድርጅታቸው በበጎ ምግባሩ የሚነሳ ድርጅት እንደሆን ያስረዳሉ። ቢቢሲ ሪፖርቱን ከማተሙ በፊት በጽሁፉ እንደተመለከተው በስፍራው ድረስ ተገኝቶ እንዲታዘብ ቢጋበዝም የመጣ እንደሌለ በማመልከት የዘገባውን ልዩ ዓላማ ያጎላሉ። ቢቢሲ በጽሁፉ ለምን ስፍራው ድረስ ለመሄድ እንዳልፈለገ ያለው ነገር የለም።

ቢቢሲ በዘገባው ኮሚሽኑ ባለፈው ሐምሌ ወር ያወጣውን ሪፖርት ይጠቅሳል። አያይዞም የጠቀሳቸው ባለሙያዎች የትና መቼ ትንታኔ እንደሰጡ ወይም በምን ቀን ለቢቢሲ ለይተው መረጃ እንደሰጡ ይፋ አላደረገም። “ቢቢሲ የተመለከተው ይፋ ያልተደረገ የኢሰመኮ ሪፖርት እርሻ ጣቢያዎቹ የሚድሮኩ ሆራይዘን ፕላንቴሽንስ ንብረት እንደሆኑ አስፍሯል። ለዚህ ዘገባ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ከ10 በላይ የቀድሞ እና የአሁን ሠራተኞችም የኩባንያው እርሻዎች ተማሪዎችን ቡና ሲያስለቅሙ እንደነበር አረጋግጠዋል” ብሏል።
በወቅቱ አንድ መምህር ትምህርት ቤቱን በገቢ ለመደጎም በሚል ተማሪዎችን በስራ ላይ እንዲሰማሩ እርሻው ላይ ካለ ኃላፊ ጋር ስምምነት አድርጎ የተፈጠረ ስህተት ወዲያውኑ በኮሚሽኑ እርማት ከመስተካከሉ ውጭ ሌላ ታሪክ እንደሌለ ከእርሻው ሰራተኞች ያናገርናቸው ምስክርነት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሚዲያና ኮሙኒከሽን ዳይሬክትወር አቶ ሰለሞን እጅጉ እንደሚሉት ቢቢሲ የጠቀሰው የሆራይዘንና ፈይሰል የቡና እርሻ ልማት እርሻ ጣቢያዎች ውስጥ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ አስመልክቶ በዓመቱ መጨረሻ በወጣው የኮሚሽኑ ጥቅል ሪፖርት ላይ በምክክር መፍትሄ የተበጀለት ጉዳይ ሆኖ የተዘጋ ነው።
አቶ ሰለሞን ለጥናት ግብአት የሚሆኑ ጉዳዮች ሁሉ በዓመታዊ ጥቅል ሪፖርት እንደማይካተቱ አመልክተው፣ ቢቢሲ የጠቀሰውን የሆራይዘንና ፈይሰል የቡና እርሻ ልማት እርሻ ጣቢያዎች ውስጥ የታየው ችግር በወቅቱ ምክር ቀርቦበት፣ ማሻሻያ ተደርጎበት ችግሩ መወገዱ ታይቶና ተረጋግጦ በዓመቱ ማብቂያ ሪፖርት የቀረበበት ጉዳይ መሆኑን አስታውሰዋል።
ከሰኔ 2016 እስከ ሰኔ 2017 ድረስ ያለውንና የአገሪቱን አጠቃላይ የሰብአዊ መብት አያያዝ በሚያስረዳው ጥቅል ሪፖርት ላይ “በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ሊሙ ወረዳ በሆራይዘን ፕላንቴሽን ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ሥር ሚገኙ ሊሙ ኮሳ፣ ጉመር እና ሱንጡ የቡና እርሻ ጣቢያዎች እንዲሁም በሃይደር እና ፈይሰል የቡና እርሻ ልማት ሥር ባለው የሃይደር እርሻ ጣቢያዎች ኢሰመኮ ቀደም ሲል በሰጠው ምክረ ሐሳብ መሠረት ሕፃናትን በቡና ለቀማ ላይ የማሰማራት አሠራር እና የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ መቆሙ” ሲል በሪፖርቱ ገጽ 83 ቁጥር 271 ላይ ገልጿል። ይህ ሪፖርት በሀምሌ መጨረሻ ለፓርላማና ለሕዝብ ይፋ የሆነ በድርጅቱ ድረ ገጽ ላይ የተቀመጠ ነው።
ይህን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፣ ቢቢሲ እሳቸው በሚያውቁት ደረጃ ከኮሚሽኑ የተሰጠው አዲስ መረጃ የለም። አዲስ የተጠና ወይም እየታየ ያለ ተመሳሳይ ጉዳይ የለም። በመሆኑም ያረጀና በመፍትሄ የተዘጋን ጉዳይ አንስቶ ቢቢሲ ዛሬ ላይ ይህን መረጃ ለማስተላለፍ የፈለገበት ዓላማው ሊገባቸው እንዳልቻለ ገልጸዋል።

ሬይን ፎረስት እና ካፌ ፕራክቲስ የተባሉ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ድርጅቱ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ስራውን እየሰራ ለመሆኒኡ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት በየወቅቱ እንደሚያገኝ ከሚድሮክ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በተመሰከረላቸው ገለልተኛ የውጭ ተቋማትን በመላክ ኦዲት ካደረጉ በሁዋላ የምስክር ወረቀቱ እንደሚሰጥ ከአሰራሩ ለመረዳት ተችሏል። ቢቢሲን ጨምሮ ሚድሮክ ይህን ሽልማት ሲያገኝ ዘግበዋል። ሽልማቱ የሚሰጠው አሁን ድርጅታቸው የታማመበትንም ጉዳይ ጨምሮ በሚደረግ ኦዲት መሆኑን አስታውሰው አሁንም የዚህ ዜና ዓላማ ሊገባቸው እንዳልቻለ ይገልጻሉ።
ይህ ግዙፍ የዘመናዊ የቡና እርሻ ኩባንያ ከቡና ተከላ፣ ለቀማ፣ ማሸግ እና ለገበያ እስከማቅረብ ድረስ ባሉ የአቅርቦት ሰንሰለት ሂደት ውስጥ ተቀባይነት ያላቸውን የአየር ንብረት፣ ማህበራዊ እና አስተዳደራዊ ደረጃዎችን በማክበር ታሪኩ የሚታወቅ ከትትል የሚድርግብት(Traceable) እና የተረጋገጠ (Certified) ቡናን በከፍተኛ መጠን ከሚያመርቱ መልካም ስምና ዝና ካላቸው የኢትዮጵያ ቡና አቅራቢ ኩባንያዎች ዋነኛው ነው ፡፡
አዲስ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ “ ይህ ጅማሮ ነው” ይላሉ። “ ቢቢሲ በአማርኛ፣ በትግርኛ፣ በኦሮሚኛ ሳያሰለስ መረጃ የሚረጭበት ዓላማ ስለሚታወቅ፣ ሕዝብ፣ ተቋማት፣ ፖለቲከኞች ወዘተ መንግስትን ጨምሮ አካሄዱን በጥንቃቄ ሊከታተሉት ይገባል” ሲሉ ዜናውን ከብሄራዊ ደህንነት ጋር ያያይዙታል።
ሚድሮክ ሆራዘን ፕላንቴሽን ኢትዮጵያ ለዓለም ዓቀፍ ገበያ ለምታቀርበው የቡና ምርት የበኩሉን የሚወጣ ግዙፍ የቡና አምራችና ላኪ ኩባንያ ነው። እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ግዙፍ ዘመናዊ የቡና እርሻዎች (እንደ በበቃ እና ሊሙ ያሉ) ኦርጋኒክ የአረቢካ ቡናዎችን ያመርታል። ኩባንያው ቡናውን በዋናነት በሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ (በተለይ ጀርመን) እና እስያ (ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን) የቡና ገበያዎች ላይ በስፋት በማቅረብ ይታወቃል። ኢትዮጵያ ባለፈው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከላከችው ቡና 2.65 ቢሊዩን ዶላር ገቢ ምግኘቷን በቅርቡ የወጡ መረጃዎች ያመልክታሉ። ከዚህ ገቢ ውስጥ ሚድሮክ ኢትዮጵያ የራሱ ድርሻ አለው። የሕግ ባለሙያው እንደሚሉት እዚህ ላይ ነው ቢቢሲ ከተቋቋመለት ዓላማ አንጻር ቃታውን የሳበው።
ይህ የቢቢሲ “የምርመራ ሪፓርት” የተባለ ዘገባ ተቋማዊ የማስተካከያ መፍትሄ የተበጀለትን ጉዳይ ወደኋላ ሄዶ ያጣቀሰ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ለአዲስ ሪፖርተር አስታወቋል። የቢቢሲ ሪፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ታላላቅ ኩባንያዎች ላይ የተጀመረውና ቀጣይነት ያለው የስም ማጥፋት ዘመቻ አካል እንደሆነ ተመልክቷል።
ቢቢሲ በዘገባው ኮሚሽኑ ባለፈው ሐምሌ ወር ያወጣውን ሪፖርት ይጠቅሳል። አያይዞም የጠቀሳቸው ባለሙያዎች የትና መቼ ትንታኔ እንደሰጡ ወይም በምን ቀን ለቢቢሲ ለይተው መረጃ እንደሰጡ አልጠቀሰም። ይሁንና “ቢቢሲ የተመለከተው ይፋ ያልተደረገ የኢሰመኮ ሪፖርት እርሻ ጣቢያዎቹ የሚድሮኩ “ሆራይዘን ፕላንቴሽንስ” ንብረት እንደሆኑ አስፍሯል። ለዚህ ዘገባ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ከ10 በላይ የቀድሞ እና የአሁን ሠራተኞችም የኩባንያው እርሻዎች ተማሪዎችን ቡና ሲያስለቅሙ እንደነበር አረጋግጠዋል” ይላል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሚዲያና ኮሙኒከሽን ዳይሬክትር አቶ ሰለሞን እጅጉ እንደሚሉት ቢቢሲ የጠቀሰው የሆራይዘንና ፈይሰል የቡና እርሻ ልማት እርሻ ጣቢያዎች ውስጥ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ አስመልክቶ በዓመቱ መጨረሻ በወጣው የኮሚሽኑ ጥቅል ሪፖርት ላይ መፍትሄ የተበጀለት ጉዳይ ነው።
ከሰኔ 2016 እስከ ሰኔ 2017 ድረስ ያለውንና የአገሪቱን አጠቃላይ የሰብአዊ መብት አያያዝ የሚያስረዳው ጥቅል ሪፖርት ላይ “በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ሊሙ ወረዳ በሆራይዘን ፕላንቴሽን ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ሥር ሚገኙ ሊሙ ኮሳ፣ ጉመር እና ሱንጡ የቡና እርሻ ጣቢያዎች እንዲሁም በሃይደር እና ፈይሰል የቡና እርሻ ልማት ሥር ባለው የሃይደር እርሻ ጣቢያዎች ኢሰመኮ ቀደም ሲል በሰጠው ምክረ ሐሳብ መሠረት ሕፃናትን በቡና ለቀማ ላይ የማሰማራት አሠራር እና የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ መቆሙ” ሲል በሪፖርቱ ገጽ 83 ቁጥር 271 ላይ ገልጿል።
ከሚድሮክ እያንዳንዱ ኩባንያዎች ትርፍ ላይ አስር ከመቶ የሚሆነውን ለማህበረሰብ አገልግሎት በማዋል እንደሚታወቅ የገለጹ ሰራተኞች 2015 ዓ.ም ታይቶ የነበረን ለደብዳቤ ማስጠንቀቂያ እንኳን ያልበቃ ጉዳይ በማንጠልተል ሶስት ዓመት ወደኋላ የተመለሰው ቢቢሲ ዛሬም ነገም ስፍራው ላይ ደርሶ ከጎዳና ተነስተው ሕይወታቸውን የቀየሩትን ጭምር አነጋግሮ ስህተቱን እንዲያርም ጥሪ አቅርበዋል።
ምንም እንኳ የቢቢሲ ሪፓርት ከአንድ ዓመት በፊት ማስተካከያ በተደረገበት መረጃ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ዘገባው በኩባንያው እና በሃገሪቱ የውጪ ንግድ ገቢ ላይ ሊፈጥረው የሚችለውን ስልታዊ የፓለቲካ ስጋቶች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በተቀናጀ መልኩ አስፈላጊው ቅድመ መከላከል እርምጃዎች መወሰድ እንዳለበት የሕግ ባለሙያው ምክር ለግሰዋል። ይህ ዘመቻ በተከታታይ በሌሎች ታላላቅ የንግድ ተቋሞች ላይ ቀጣይነት ያልው ዘመቻ ስለሚካሄድ መንግስትም ሆነ ሕዝብ ጉዳዩን በቀላሉ እንዳይመለከቱት መክረዋል።
በተጠቀሰው እርሻ ልማት ውስጥ ከ30 እስከ 40 ሺህ ሰራተኞች አሉ። የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ተቁማት ተገንብተውላቸዋል። ሰራተኞች መኖሪያ አላቸው፣ በተለይም ከጎዳና ሕይወት ራሳቸውን ቀይረው ለሌሎች ምሳሌ የሚሆኑ በርካታ ዜጎች አብረው ይኖራሉ። እዛ ሌላ አለም ተፈጥሯል። የሚፈለገው ዓይንን ገልጦ ማየት ብቻ ነው” ከሰራተኞች ባገኘነው መረጃ በኪሎ አስራ አምስት ብር ሂሳብ ቡና የሚለቅሙ ሰራተኞች የቀን ገቢ ትንሽ የሚባል አይደለም። እንደ አሰፋ አይነቶች ዛሬ ላይ በጎዳና ላይ በሱስ ራሳቸውን ስተው ለሚወድቁ ወገኖች ምሳሌ ናቸው። “ኑና እዩን” ሲል ለጎዳና ወንድምና እህቶቹ ብቻ ሳይሆን፣ የተሳሳተ መረጃ ላቀረቡትም የነጋገርነው የቀድሞ ጎዳና ተዳዳሪ ጥሪ አቅርቧል።
አስተያየታቸውን በጽሁፍ የላኩት የሕግ ባለሙያ ሚድሮክ ኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ ቃታ ሲሳብበት ዝም ማለቱ አግባብ እንዳልሆነ አመልክተው፣ ራስን በመከላከልና ዘመቻን በማምከን ረገድ ለሌሎች አርአያ የሚሆን የህዝብ ግኙኙነት እንዲገነባ መክረዋል። የሕግ ክፍሉም ጥርስ ሊኖረው እንደሚገባ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ አውሮፓ ንግድ ምክር ቤት ምስክርነት

በሚድሮክ ሆራይዞን ፕላንቴሽን ውስጥ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ችግር አለማየቱን በኢትዮጵያ የአውሮፓ ንግድ ምክር ቤት ለአዲስ ሪፖርተር ምስክርነቱን ሰጥቷል።
ቢቢሲ ሶስት ዓመት ቆይቶ ስላነሳውና “ በምክረ ሃሳብ ተዘግቷል” ተብሎ ሪፖርት ስለቀረበበት የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ጉዳይ፣ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት የህብረቱ ንግድ ምክርቤት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ባህሩ “ በአዲስ አበባ የሚገኙ የአውሮፓ አገራት አምባሳደሮችና የህብረቱ ልዑካን በመያዝ በጀማ ጉብኝት አድረገናል። ጉብኝታችን ሕብረቱ ያወጣውን በቡና እርሻ ምክንያት የሚካሄደውን የደን ጭፍጨፋ ቁጥጥር ህግ አስመልክቶ ለመታዘብ ነበር። በዚሁ ጉብኝታችን በድርድጅቱ የጉልበት ብዝበዛ የሚባል ነገር አላየነም። አልታዘብንም” ብለዋል።
የአውሮፓ ሕብረት የደን ጭፍጨፋ ቁጥጥር ህግ ዓላማው የተፈጥሮ ጥበቃን ዘላቂነት ለማረጋገጥ ሲሆን በኢትዮጵያ የአውሮፓ የንግድ ምክር ቤት የአውሮፓ አገራትን የንግድ ፍላጎት ስለሚወክል ህጉ ምን ያህል ተፈጻሚ እንደሆነ ለማሳየት የመስክ ጉብኝት አድርጓል።

አንድ መቶ ሰማኒያ አባላት ያሉት የአውሮፓ ንግድ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ስራ አስፈጻሚ ይህንኑ ህግ አስመልክቶ አባል አገራት በተጨባጭ ያለውን ሃቅ እንዲረዱ ማድረጉን ዋና ሰራ አስፈጻሚው አቶ ባህሩ ለአዲስ ሪፖርተር ስረድተዋል። በኢትዮጵያ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የጫካ ቡና ምረት አሰራርን በማስቀጠል የሕብረቱን ዓላማ ያሟላ ስራ መሰራቱን ተመልክቷል።
የአውሮፓ ህብረት የአዲሱ የደን መጨፍጨፍ መቆጣጠሪያ ደንብ (EUDR) የተፈፃሚነት ጊዜ እንዲራዘም የቀረበው ጥያቄም በዚሁ አግባብ መነሻነት እንዲራዘም መደረጉን ያስታወሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ የሚድሮክ ሆራይዘን ፕላንቴሽን ቢቢሲ ባለው አግባብ እሳቸውም ሆኑ የልዑክ ቡድኑ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ እንዳላስተዋለ ለአዲስ ሪፖርተር ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
በንግድ ምክር ቤታቸው የሕጻናት መብት ጉዳይ ቁልፍ ጉዳይና ለአፍታም ቸል የማይባል እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ባሕሩ፣ “በተባለው ደረጃ የተፈጠረ ችግር ቢኖር ከማንም በላይ ምክር ቤታቸው ቅድሚያ የሚያነሳው ጉዳይ ነበር። ግን አልሆነም”ብለዋል።





