አዲስ ሪፓርተር – በአባይ ግድብ የውሃ ሙሌትና አጠቃቀም ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ለዓመታት የከረረ ውዝግብ ውስጥ የቆየችው ግብፅ፣ ኢትዮጵያ በዓባይ ውሃ ድርድር ላይ “መለሳለስ” ካሳየች የቀይ ባሕር የባሕር በር መዳረሻ እንድታገኝ ለማገዝ ፍላጎት እንዳላት የሚጠቁም አዲስና አነጋጋሪ ጥያቄ ማቅረቧ ተሰማ። ዜናው በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ሆኗል። ቀደም ሲል ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “አባይና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የህልውና ጉዳዮች ናቸው” ማለታቸውና አባይ ግድብ ሲጣናቀቅ የተለያዩ የዓለም ታላላቅ ሚዲያዎች “ኢትዮጵያ የኒክሉዬር ቦንብ ታስጠቀች” በማለት መዘገባቸው አይዘነጋም።
The National የተሰኘው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የዜና ምንጭ የካይሮ የውስጥ አዋቂዎቹን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው፣ ግብፅ ይህን የጥቅም ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት አቅርባለች። ይህ ዕቅድ ለዋሽንግተንም ተልኳል። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጉዳዩ ላይ እንዲሸመግሉ ግብፅ ፍላጎት ማሳየቷ ደግሞ ጉዳዩ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ያደርጋል ተብሏል።
ዶናልድ ትራምፕ ለግብጽ ያጋደለ የተባለና የአባይ ግድብን አስመልክቶ የተፋለሰ መረጃ በማቅረብ ለማሸማገል ያላቸውን ፍላጎት በድብዳቤ ማስታወቃቸው አይዘነጋም። ግብጽም ቀደም ሲል ለፕሬዚዳንቱ ደብዳቤ መላኳ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ መንግስትም ለመጪው ትውልድ ላይ እዳና ታሪካዊ ጫና ለማስቀመጥ ፈቃደኛ አለመሆኑን በመጥቀስ እስካሁን ድረስ ግድቡን አስመልክቶ ስምምነት ሳይደረግ ቆይቷል። ግብጽም ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ ታጣቂዎችን ከማደራጀትና ማስታጠቅ ጀምሮ ኢትዮጵያን ለመክበብ እየተንቀሳቀሰች ይገኛል።
የአባይ ግድብ ውዝግብ በዚህ መልኩ በቀጠለት በዚህ ወቅት የተሰማው ዜና ግብፅ ሁለት ገጽታዎችን የያዘ ሃሳብ ማቅረቧ ነው። የመጀመሪያው የግብጽ አዲስ አሳብ “የጥቅም ማባበያ” ማቅረብ ነው። ይህም ኢትዮጵያ በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ ለካይሮ ስጋት ምላሽ የሚሰጥ “ሕጋዊ አስገዳጅ ስምምነት” ላይ እንድትደርስ የሚጋብዝ ነው። ኢትዮጵያ ይህን ከተቀበለች ግብፅ በምላሹ ከአፍሪካ ወዳጆቿ ጋር በመሆን ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ወደቦችን እንድትጠቀም የዲፕሎማሲ ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ገብታለች። ይህ አካሄድ ግብፅ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ እንደ ድርድር ካርድ ለመጠቀም የወሰነችበት ስልት መሆኑን ያሳያል።
ዜናውን የሰሙ የህግ ባለሙያ “አባይ ዝም ብሎ ያገኘውን እያግበሰበሰ ወደ ግብጽ ሲጓዝ ኖሮ በዚህ ትውልድ መገደቡ፣ የኢትዮጵያን የመደራደሪያ አቅም እንዳጎላው ማረጋጋጫ ነው። ጥያቄው በጥንቃቄ የሚያዝ ቢሆንም፣ አባይ አቅም ሆኖን ማየት ግን ትልቅ ፖለቲካዊ ድል ነው” በማለት አስተያየት ሰጥተዋል። “ኢትዮጵያ የኒኩሊየር ቦንብ ታጠቀች” በማለት የግድቡን ጫና የተረዱ ሲዘግቡ፣ በፖለቲካ ልዩነትና ፍላጎት፣ እንዲሁል ከጀርባቸው ባዘሉት አጀንዳ መነሻ የግድቡን መጠናቀቅ የነቀፉ “ኢትዮጵያዊያን” እንደነበሩ የሚታወስ ነው። “ግድቡ ተሸጠ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድቡ ለግብጽ ጥቅም እንዲውል ተስማሙ” ያሉና አሁን ድረስ ይቅርታ ወይም ማስተካከያ ያላደረጉ ሚዲያዎችም መኖራቸው አይዘነጋም።
ግብጽ ከመጀመሪያው የትብብር አሳቧ አስከትላ በሁለተኛው ገጽታው ላይ ድብቅ ማስጠንቀቂያን ያዘለ ነው አሳቧን አካታለች። ኢትዮጵያ ይህን ጥያቄ ውድቅ ካደረገች ግብፅ በሱዳን፣ በሶማሊያ እና በጅቡቲ ያላትን ወታደራዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ በመጠቀም፣ እንዲሁም በቀይ ባሕር ደቡባዊ ክፍል ያለውን የባሕር ኃይል አቅሟን በማሰለፍ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት “ለመዝጋት” እንደምትሞክር በውስጠ-ታዋቂነት ገልጻለች። ይህ “የካሮት እና ዱላ” (Carrot and Stick) ስልት አዲስ አበባን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት የታለመ የጠበቀ የጫና እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል።
ይህ የካይሮ እንቅስቃሴ ከቱርክ ሚና እና ከቀጠናው የኃይል አሰላለፍ መለወጥ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን ጋር በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የ130 ሚሊዮን ሕዝብ ሀገር “የጂኦግራፊ እስረኛ” ሆና መቀጠል እንደማትችል መናገራቸው ይታወሳል። ሆኖም በአሁኑ ወቅት ካይሮ እና አንካራ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ መምጣታቸው፣ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ይበልጥ ውስብስብ እና አስቸጋሪ ሊያደርገው እንደሚችል የሚገምቱ አሉ።
ግብፅ ከሶማሊያ፣ ኤርትራ እና ጅቡቲ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር ማጠናከሯ የታቀደ “የዲፕሎማሲያዊ ከበባ” (Diplomatic Encirclement) አካል እንደሆነ ተንታኞች ይገልጻሉ። ካይሮ የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት እንደ ስልታዊ ተጋላጭነት (Vulnerability) በመመልከት፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የጀመረችውን ስምምነት ለማክሸፍ “እውነተኛውን ቁልፍ የያዝኩት እኔ ነኝ” የሚል መልእክት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳየት እየሞከረች ትገኛለች።
እስካሁን ከአዲስ አበባ በኩል የተሰጠ ይፋዊ ምላሽ አለመኖሩም የራሱ የሆነ ትርጉም አለው። ተንታኞች እንደሚገምቱት ኢትዮጵያ የካይሮን ጥያቄ እንደ “ባዶ ማስፈራሪያ” በመቁጠር በራሷ መንገድ የቀጠናው አጋሮቿን በማስተባበር የባህር በር ጥያቄዋ ምላሽ ስለምታገኝበት ሁኔታ እየሰራች ትገኛለች። በሌላ በኩል ደግሞ የቀረበው ጥያቄ ዝርዝር ጉዳዮች፣ በተለይም የወደብ ባለቤትነት እና የውሃ መጠን ጉዳዮች በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተመዘኑ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። በዝምታ ፖሊሲው የሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን በጥንቃቄ ስለመያዙ ይደመጣል።
ግብፅ የሕዳሴውን ግድብ “የህልውና ስጋት” አድርጋ በመመልከት፣ በድርቅ ወቅት የሚለቀቀውን የውሃ መጠን የሚወስን ሕጋዊ አስገዳጅ ስምምነት እንዲፈረም አሁንም ትወተውታለች። ኢትዮጵያ በበኩሏ የባሕር በር ማግኘት ለኢኮኖሚ እድገቷና ለሀገራዊ ደህንነቷ ወሳኝ መሆኑን ትገልጻለች። ይህ አዲስ የካይሮ ሃሳብ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለዓመታት የቆየውን የውሃ ውዝግብ በባሕር በር ጥቅማ ጥቅም ለመለወጥ የታለመ ቢመስልም፣ በውስጡ የያዘው ማስፈራሪያ ግን ግንኙነቱን ይበልጥ ሊያሻክረው ይችላል የሚል ስጋት የፈጠረባቸው አሉ። በሌላ በኩል ግን በአሸማጋዮች ፊት የመላዘብና ይዘው የቀረቡትን የማመቻቸመች አጋጣሚዎች የተለመዱ በመሆናቸው የተሻለ ስምምነት ሊደረስ እንደሚችልም ግምት አለ።
በአጠቃላይ ይህ የግብፅ እንቅስቃሴ ከሱዳን ጦርነትና ከቀይ ባሕር የደህንነት ስጋት ጋር ተዳምሮ፣ ቀጠናውን ወደ አዲስ የዲፕሎማሲያዊ ፍጭት ሊከተው እንደሚችል ይታመናል። ግብፅ በወደቦች ልማትና በወታደራዊ ስምምነቶች በኩል በኢትዮጵያ ጎረቤቶች ዘንድ ያላትን ተሰሚነት በማሳደግ ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋን ለማስከበር የምታደርገውን ጉዞ ለመግታት መሞከሯ ለቀጠናው ውጥረት ሌላ ገፊ ምክንያት እንደሚሆን ተንታኞች ይገልፃሉ።
ኢትዮጵያ የ130 ሚሊዮን ሕዝቧን የውሃና የባሕር በር ፍላጎት ሳታስከብር ለካይሮ “መለሳለስ” ታሳያለች ተብሎ አይጠበቅም። የካይሮ አዲሱ “ካሮት እና ልምጭ” ዲፕሎማሲ ወደ ሰላማዊ መፍትሔ ያመራል ወይንስ የቀጠናውን ውጥረት ያባብሳል የሚለው ጉዳይ፣ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሳምንታት ለጥያቄው በምትሰጠው ምላሽ እና በትራምፕ አስተዳደር ጣልቃ ገብነት የሚወሰን ይሆናል። ኢትዮጵያ ህልውናዋ በአባይና በቀይ ባህር ላይ መሆኑን በሰፊት ማስረጃና መረጃ አቅርበው የባህር በር ጥያቄን ብሔራዊ አጀንዳ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “በባሌም በቦሌም የባህር በር እናገኛለን” ማለታቸው አይዘነጋም።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






