“የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ኢሮ ከሁለት ሳምንት የኢምሬትስ ቆይታቸው በሁዋላ እጅ ሰጥተዋል”

Date:

የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዱራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ (ኢሮ) እንዴት አዲስ አበባ መጡ? አዲስ ስታንዳርድ የተሰኘው የድረገጽ ሚዲያ እንዳለው የኢትዮጵያ መንግስት ባደረገላቸው ጥሪና ጉትጎታ፣ ወይስ ራሳቸው ኢሮ ጥያቄ አቅርበው?

ከኢትዮጵያ ጋር የባህር በር ውል አስመልክቶ የመግባቢያ ሰነድ እንደፈረሙ ከስልጣን የተነሱት ፕሬዚዳንት ሙሳ ባሂ ስምምነቱን ከመፈጸማቸው አንድ ቀን በፊት ጅቡቲ ነበሩ። በጅቡቲ ከሃሰን ሼኽ እና እስማዔል ጉሌት ጋር በመከሩ ማግስት አዲስ አበባ ሲገኙ የተቀበሏቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ነበሩ። ይህን የሚያስታውሱ ኢሮ ሲመጡ እንዴት አብይ አልተቀበሏቸውም? የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

ሙሳ ባሂ ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት የሚያደርገውን የመግባቢያ ሰነድ መፈረማቸው እንደተሰማ ግብጽ፣ ኳታር፣ ቱርክ፣ ሶማሌና እንደ አቅሚቲ ኤርትራ በአንድነት ተነሱባቸው። እነዚሁ አገራት አድመው በሶማሊላንድ ምርጫ እጃቸውን ከተቱ።

ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ሙሴባሂ አብዲ በሶማሊላንድ ምርጫ እንዴት እንደተሸነፉ የሚያጋልጡ እንደሚሉት ኳታር፣ ግብጽና ጅቡቲ ብቻ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለአዲሱ ፕሬዚዳንት አብዲራህማን ሞሀመድ አብዱላሂ ኢሮ የምርጫ ዘመቻ ይውል ዘንድ ለግሰዋል።

በሶማሊላንድ የጎሳ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ ሽማግሌዎች ተጽዕኖ አላቸው። ይህንኑ አጋባብ በመጠቀም ኢሮ በምርጫ እንዲያሸንፉ እስከ 5 ሚሊዮን ዶላር በተዋረድ የሚከፋፈሉት ገንዘብ ታደላቸው። የተጠቀሱት የማህበረሰብ ክፍሎች በውጤቱ “አብዲራህማን ሞሀመድ አብዱላሂ ኢሮ 65 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል” ተብለው ስልጣኑን እንዲረከቡ ሰሩላቸው። ይህ ሁሉ የሆነው ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ሙሴቢሂ አብዲ ከኢትዮጵያ ጋር የበህር በር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ተከትሎ ነው።

ከላይ የተቀመጠውን የምርጫ ድራማ ያጋሩን ዶክተር ኢስማኤል ጎርሴ የሶማሌ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ካውንስል ሊቀመንበር ናቸው። የሚመሩት ካውንስል በኢትዮጵያ አንድነትና ብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ አይደራደርም። የፖለቲካል ሳይንስና ጂኦፖለቲክስ ባለሙያ ሲሆኑ በአሜሪካ University of St. Thomas in St. Paul, Minnesota ያስተምራሉ።

ጉዳዩን በቅርብ እንደሚከታተል ተወላጅና፣ በሶማሊላንድ መንግስት ውስጥ ካሉ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ጋር ካላቸው ግንኙነት ተነስተው ለአዲስ ሪፖርተር “የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ኢሮ ከሁለት ሳምንት የኢምሬትስ ቆይታቸው በሁዋላ እጅ ሰጥተዋል” ብለዋል። አብዱራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ በኃላፊነታቸውና በስም የተዘረዘሩ የካቢኔ አባሎቻቸውን ይዘው አዲስ አበባ የገቡት በራሳቸው ጥያቄና በርበራ ላይ እየተደረገ ባለው ኤንቨስትመንት ግፊት የተነሳ አማራጭ አልባ በመሆናቸው የተነሳ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

ኢሮ እንደተመረጡ ግብጽ፣ ሳዑዲ፣ ካታር ተመላለሰዋል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ አልመጡም። በዚህ ሳቢያ ከሶማሊላንድ ምሁራን፣ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች እንዲሁም ነዋሪዎች “ለምን ኢትዮጵያ አይሄዱም?” የሚል ጥያቄ ይነሳባቸው እንደነበር ዶክተር እስማዔል ጎርሴ ያስታውሳሉ። እሳቸው በተገኙበት የውይይትና ክርከር መድረክም ይህ አሳብ በገሃድ መነሳቱን ይናገራሉ።

ኢሮ በመጨረሻ ለምንና እንዴት አዲስ አበባ መጡ?

አንዳንድ ሚዲያዎች “በኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ ወደ አዲስ አበባ አቀኑ” ያላቸው የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት አመጣጥ ከስር መሰረቱ ያስረዱት ዶክተር እስማዔል ጎርሴ ” ፕሬዚዳንቱ አዲስ አበባ ከመግባታቸው አንድ ቀን በፊት ለአስራ ሰባት ቀናት አረብ ኤምሬትስ ነበሩ” ይላሉ መረጃና ማስረጃ በማጣቀስ።

አንዳንድ ሚዲያዎች የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዱራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ (ኢሮ) በኢትዮጵያ ጥያቄ ወደ አዲስ አበባ እንደመጡ ለማስመሰል እንደፈለጉ ፈጽሞ እንደማይገባቸው ያስታወቁት ዶክተር እስማዔል ጎርሴ፣ ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ ገንዘብ አፍስሰው ባስመረጡዋቸው አገራት ፍላጎት መሰረት የመግባቢያ ሰነዱን አንቀው፣ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ወደኋላ ብለው ከከረመኡ በሁዋላ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ከኢምሬትስ የሁለት ሳምንት በላይ ቆይታቸው በሁዋላ መሆኑ ብዙ ጉዳዩን ወለል አድርጎ ያሳያል ባይ ናቸው።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኢንቨስትመንት

የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ/ አቡዳቢ ንብረት የሆነው DP WORLD በበርበራ ወደብ ከ442 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ማድረጉ፣ Abu Dhabi is involved in several large railway investments, including the $3 billion Ethiopia-Somaliland railway የበርበራ ወደብን በቀጥታ ከኢትዮጵያ ጋር ለሚያገናኘው የባቡር መስመር ግንባታ 3 ቢሊዮን ዶላር ማውጣቷ ከኢቶጵያ ጋር ለመነገድ እንጂ ለሌላ ተግባር ባለመሆኑ የሶማሊላንድ አዲሱ ፕሬዚዳንት በአቡዳቢ ቆይታቸው “ቀልዱን አቁም” እንደተባሉ ዶክተር እስማኤል ጎርሴ በቂ ማስረጃ እንዳላቸው ጠቅሰው ይናገራሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የእስራኤልና አሜሪካ ሶማሊላንድ ላይ የጦር መሰረት ለማቆም መወሰናቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር የተለያዩ ስምምነቶች ስላሉዋትና የኢትዮጵያ በርበራ ላይ ጦሯን ማስፈሯ ስለሚፈለግ ፕሬዚዳንቱ ከኢትዮጵያ ጋር አብረው መስራቱ ግዴታቸው እንደሆነ አክለው የሚያስረዱት ኢሳማዔል ጎርሴ፣ ” ከበርበራ 40 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ጋዝ እየወጣ፣ ቱቦ መዘርጋት እየተጀመረ፣ ማደበሪያ ፋብሪካ እየተሰራ ሶማሊላንድ ወዴት ነው የምትንሸራተተው? ይሕ ሁሉ ግንባታ በርበራን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ወደ ኢትዮጵያ ሄዶ የተቋረጠውን ውል እንዲያስቀጥል ታዞ አዲስ አበባ ሄዷል” ብለዋል።
በቀን አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የጫት ንግድ ወደ ሶማሊላንድ እንደሚጋጋዝ ያወሱት ዶክተር እስማኤል ጎርሴ፣ በዚያድባሬ ዘመን በአየር ቦንብ እየተጣለ የሶማሊላንድ ሕዝብ ሲያልቅ ከለላ የሰጠችው ኢትዮጵያ በመሆኗ ሕዝቡ ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅርና ውለታ አለብን ብሎ ስለሚያስብ፣ አቡዳቢ ኢትዮጵያን አስባ እያከናወነች ካለው ኢንቨስትመንትና ኢትዮጵያ በሶማሌ ክልል እየገነባች ካለው 10.2 ቢሊዮን በላይ ፕሮጀክቶች አንጻር ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን መግፋት እንደማይቻላቸው አምነዋል” ሲሉ አመጣጣቸውና የአመጣታቸውን ሚስጢር ከፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አውዱ አንጻር ለይተው አስታውቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ አቀባበል ያደረጉላቸው የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት አዲስ አበባ የገቡት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። አብረዋቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የገንዘብ ሚኒስትር፣ የአገሪቱ ጦር አዛዥ እንዲሁም የብሔራዊ ደኅንነት ኃላፊዎች አብረው ወደ አዲስ አበባ ከመጡት የካቢኔ አባሎቻቸው መካከል ይጠቃእሳሉ።

ማክሰኞ ጥቅምት 4 2018 ዓ.ም. ከካቢኔዎቻቸው ጋር አዲስ አበባ የገቡት ፐሬዚዳንቱ አብዛኛውን ቆይታቸውን ያደረጉት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስና አግባብ ካላቸው ባለስልጣናት ጋር እንደነበር አዲስ ሪፖርተር ሰምታለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የስራ መደራረብ ስለነበረባቸው በመጨረሻ ሰዓት ለ40 ደቂቃ ብቻ እንዳገኟቸው አዲስ ሪፖርተር የሰማችውን ዶክተር ኢሳማዔልም ለልዑካን ቡድኑ ቅርብ የሆኑ እንዳረጋገጡላቸው ነግረውናል።

ጉዞውን አስመልክቶ የሶማሊላንድ መንግሥት ቃል አቀባይ ባወጣት መግለጫ ላይ የፕሬዝዳንቱ ጉዞ የሁለቱ አገራትን ግንኙነት በተለይ በደኅንነት፣ በምጣኔ ኃብት፣ በንግድ እና በትራንስፖርት መስኮች ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ ማስታወቁ አይዘነጋም።

ከመንግስት ወገን ዝርዝር ባይነገርም ፕሬዚዳንቱ በመርጫ ለረዷቸው አገራት ፍላጎት ሲሉ ያዘገዩትን ወይም እንዲሰረዝ ዳር ዳር ሲሉት የነበረውን የሁለቱን አገሮች ጅምር ስምምነት ለማስቀጠል መስማማታቸውን ዶከተር ኢሳማዔል ከቅርብ አማካሪዎች መስማታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ታህሳስ 22 ቀን 2016 ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት ያደራጋታል የተብቫለ ስምምነት መፈራረማቸው አይዘነጋም። ይሁን እንጂ ጉዳዩ ከሶማሊያ፣ ግብጽ የአረብ ሊግ ኤርትራና እና ሌሎች አካላት ፍላጎት ተካቶበት ተግባራዊ ሳይሆን ሁለት ዓመት ሊሞላው ሁለት ወራት ቀርተውታል። የኢትዮጵያ መሪዎች ኢትዮጵያ ሁሉንም ጫና አልፋ ወደ ቀይ ባህር ለመመለስ ከጫፍ መድረሷን በልበ ሙሉነት እያስታወቁ ነው።

በኢትዮጵያ ታሪክ በሶማሌ ክልል 10 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ሲከናወን ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ የሶማሌ ሕዝብ ደስተኛ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር እስማኤል ጎርሴ ጋር በቀጠናው አጠቃላይ ጉዳይ ያደረገነውን ቃለ ምልልስ እናቀርባለን።

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

ሃገራዊ የወርቅ ገበያ ዋጋ መናሩ የተለያየ ትንተና እየቀርበበት ነው

አዲስ ሪፓርተር ጥቅምት 12 ቀን 2018 አዲስ አበባ -...

ኦርቶዶክስ በኢትዮጵያ የተለያየ የፓለቲካ ፍላጎት ያላቸው ወገኖች ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበች

አዲስ ሪፖርተር ጥቅምት 2 ቀን 2018 በኢትዮጵያ እየተወሳሰበ የመጣውን...

“ኤርትራ እንደ አገር ትክሰማለች”

የአየር ንብረት ለውጥ አደጋና ስጋትን መቋቋም ከማይችሉት አገራት መካከል...