የተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር ኢድሪስ የመልካምነት፣ የሰላምና የይቅርታ አሻራ ሊጠና፣ ለትውልድ ሊተላለፍ፣ ለበደለኞች ትምህርት እንዲሆን ዕለት ዕለት ሊዘከር ይገባል!! አባታችን ፈርጥ ነበሩ፤ አባታችን አንደበታቸው ከማር የሚጣፍጥ፣ ቃላቶቻቸው የሚያንጹ፣ መካር፣ ሩህሩህ ወዘተ ነበሩ። ሩጫቸውን ፈጽመው ሲሄዱ ያወረሱንን መልካምነት በመከተል ልናስታውሳቸውና በዚህም ያለንን ክብር ልንገልጽላቸው ይገባል!!
ሰው መሆንን አስተምረዋልና እናመስግንዎታለን። ኢትዮጵያ ሰው ባጣችበት ወቅት እርስዎን አግኝታለች። ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ወቅት ፈተናዋን የተጋሩ ጀዝመኛ፣ ትሁት፣ ነብስዎንና እንደ ዕምነትዎ አክባሪ፣ የዕለቱን ሳይሆን የወደፊቱን አሻግሮ ተመልካች ነበሩና እልፈትዎ ዘር፣ ሃይማኖትና ሰፈር ሳይለይ አሳዝኗል። ነብስዎ በገነት ትረፍ!! የትውልድ መማሪያ ቅርስ ነዎት!!
የተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር ኢድሪስ ህልፈት የኢትዮጵያ እስልምና ዕምነት ተከታዮችን ብቻ ሳይሆን መላውን ኢትዮጵያውያንን ያሳዘነ ሁነት ለመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ ዓለም ተረድቷል። የእርሳቸው ሞት “የሚያስቀና ህልፈት” እንደሆነ የምንረዳው የኖሩበትን የፅድቅ ህይወትና የተዉትን በጎ ውርስ ስንመለከት ነው። ሃጂ ሙፍቲ በ94 ዓመት የህይወት ዘመናቸው የመልካም ሙስሊምንና የመልካም ኢትዮጵያዊን ተክለ-ሰብዕና በተግባር አሳይተዋል። ትውልድ ይማርባቸዋል። ሕያው ያደርጋቸዋል።
” ሀገራችንን አላህ ሰላም ያድርግልን። ሀገራችንን አላህ አማን ያድርግልን። እኛም የምንዋደድ አላህ ያድርገን። የምንከባብር አላህ ያድርገን። የምንረዳዳ አላህ ያድርገን። የምንመካከር አላህ ያድርገን። ጥላቻን ከውስጣችን አላህ ያጥፋው። በሃይማኖትም ሆነ በፖለቲካ መገዳደልን፣ መጋጨትን፣ መለያየትን ከሀገራችን ከውስጣችን አላህ ያንሳልን። እንደ አባቶቻችን ከዛም በበለጠ የምንተባበር ፣ የምንከባበር፣ የምንዋደድ ፣ የምንረዳዳ አላህ ያድረገን። ” ታላቁ አባት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ
ከእርሳቸው ህይወት ልንማራቸው የሚገቡት እሴቶች በርካታ ናቸው። ሃጂ ሙፍቲ በሩህሩህ ልብ፣ በረጋ አንደበትና በፈጣሪ ፊት ራሳቸውን ዝቅ ባደረገ ትህትና ይታወቁ ነበር። ሁሉንም የሰው ልጅ እና እምነት ተከታይ በአክብሮትና በቅንነት የሚመለከቱበት መንገድ፣ የእስልምናን እውነተኛ ገፅታ- የሰላም፣ የፍቅር፣ የመቻቻል እና የመዋደድ ሀይማኖት መሆኑን አጉልቶ አሳይቷል።
እርሳቸው በመንግሥት ባለሥልጣኖች የተወደዱ ሆነውም እንኳ የባለሥልጣኖች ልሣንና አገልጋይ መሆንን ሳይሆን፣ የፈጣሪያቸውን አገልጋይነትና የሀገር መካሪነትን የመረጡ ህሊናቸውን ያከበሩ ሰው ነበሩ። ልዕልናቸው የጠበቁና የዚህችን ዓለም ብልጭልጭ ንቀው፣ በትዕግስትና በስክነት የተመላለሱ አባት መሆናቸው ሁላችንም ልናጠናው የሚገባ ትምህርት ነው።
እሳቸው ተገልጦ የማያልቅ መጠሐፍ ናችው። ድርሳን ናቸው። ሙፍቲ መጠናት ያለባቸው እሳቸውን የሚተካ ትውልድ ስለሚያሻንና አሁን ላሉት ልበ ደንዳኖች፣ ሌቦች፣ ዋሾዎች፣ ከሃጂዎች፣ በሰው ልጅ ሕይወት ለሚቆምሩ፣ ከተጠሩበ ሰማያዊ ጥሪ በማፈንገጥ ለሚቅበዘበዙቱ ቢሰሙ ወደ ቀልባቸው ይመለሱ ዘንዳ ዕድል ናቸውና ደግመን ደጋግመን ልናነሳቸው፣ ህይወታቸውን ልንዘክረው፣ ኑሯቸውን ለንቃኘው ግድ ይሆናል።
ሃጂ ሙፍቲ ኡመር ኢድሪስ የብዝሃነት ውበት በጎላባት ኢትዮጵያችን የሰላም፣ የአብሮነትና የመተሳሰብ መምህር ነበሩ። ህልፈታቸው ቢያሳዝንም፣ በህይወታቸው ያሳዩን የመልካምነት ብርሃን ለእኛ ለትውልዱ እንደ መልካም አርዓያነት ይቆይልን። የተቀደሰ መንገዳቸውን እንድንከተል፣ ሃይማኖትን ከሃቅና ከፍቅር ጋር አዋህደን እንድንኖር፣ የእርሳቸው ውርስ ዘላለማዊ መልዕክት ነው።

ፎቶ ምስሉ የአባታችን ሽኝት ነው። ዘር፣ ጎሳ፣ ሓይማኖት ሳይለይ በራስ ተነሳሽነት እንዴት ደምቀው እንደተሸኙ ያሳያል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር ለሚገባው እንዲህ አድርጎ ክብር መስጠት ይችልበታል።
ፈጣሪ በጀነት ያኑራቸው!
አዲስ ሪፖርተር እገሌ ከእገሌ ሳትለይ ለመላው ኢትዮጵያውያን በሙሉ መፅናናትን ይመኛል። አባታችን እናመሰግናለን!!




