ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እስረኞች እንደሚፈቱ ፍንጭ ሰጡ፤ የትግራይ ወጣቶች ለሱዳን እንዲዋጉ በግዳጅ እየታፈሱ የሚላኩ መሆኑንም ይፋ አደረጉ

Date:

አዲስ ሪፖርተር – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሥራ ዘመኑን ላጠናቀቀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ በቀጣይ ሰላምን ለማስፈንና ኢትዮጵያን ተረዳድቶ ለማሳደግ መንግሥታቸው ካለው የጸና እምነት አኳያ፣ እስረኞችን መፍታትን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ አመለከቱ። በተጨማሪም የትግራይ ወጣቶች ለሱዳን ጦርነት በህዳጅ እየታፈሱ የሚሄዱ መሆኑን በይፋ አስታወቁ።

ከምክር ቤቱ አባላት ሰላምን አስመልክቶ ለቀረበው የስጋትና “ይህንን ስጋት እንዴት መቀልበስ ይቻላል?” የሚል ሰፊ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በርካታ መሣሪያ ያነገቱ አካላት ወደ ሰላም አማራጭ መምጣታቸውን አመልክተዋል። አሁንም ቢሆን ይህንን የሰላም አማራጭ መከተል እንደሚገባና መንግሥታቸው ለዚህ ስኬት የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

እስረኞችን ከመፍታት ጀምሮ ኢትዮጵያን ወደ ሰላም የሚወስዱ ማናቸውም እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ያመለከቱት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር፤ መንግሥት እስረኞችን ለመፍታት በሒደት ላይ መሆኑን የሚያመላክት ተደርጎ ተወስዷል። ይፋ ባይወጣም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር “ሰላም ለኢትዮጵያ” የሚሉ ወገኖች አገራቸው ሰላም እንድትሆንና አለመግባባቶች በስምምነት እንዲፈቱ ሌት ተቀን የሚያደርጉት ጥረት ተስፋ እያፈራ መሆኑን አመላካች ሆኗል። አዲስ ሪፖርተር እስረኞች እንዲፈቱ ጥረት የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን ቀደም ሲል መዘገቡ ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕወሓትን ጨምሮ መሣሪያ ያነሱ ወገኖች ወደ ሰላም እንዲመጡ፣ በሀገራቸው ጉዳይ እንዲመክሩና ልዩነቶቻቸውንም በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።

“ባንዶች” በማለት የገለጿቸው አካላት ኢትዮጵያን ለማተራመስ ተልዕኮ ወስደው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህ ወገኖችም ሆኑ ላኪዎቻቸው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም እንዳይደፍሩ የሚያደርግ ጠንካራ ኃይል መገንባቱን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እግረ መንገዳቸውን አመልክተዋል። በዚህ ረገድ “ቅንጣት ጥርጥር አይግባችሁ” ሲሉም ተደምጠዋል።

የሕወሓት አሮጌ አመራሮች ለሃምሳ ዓመታት በፖለቲካ ድርጅት መሪነት ኖረው ወጣቱን እንደማያምኑ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “አንድን ድርጅት ለሃምሳ ዓመታት የመሩ አካላት ወጣቱን ካላመኑ፣ ይህንን ማድረግ የተሳነው ፓርቲ እንደ ሞተ ይቆጠራል” ብለዋል።

“ሕወሓትና ድል ተለያይተዋል” በማለት ድርጅቱ አሁን ያለበትን ቁመና ያሳዩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የትግራይ ወጣቶች ለሱዳን ጦርነት እየተሸጡ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ተናግረዋል። ይህ ንግግራቸው ሰሞኑን ከአሜሪካ ከተሰማውና ሕወሓትን አሸባሪ አድርጎ ሊያስፈርጅ ከሚችለው የሕግ ረቂቅ ጋር የሚገናኝ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም ቢሆን ለንግግር ዝግጁ መ መሆናቸውን ደጋግመው ሲገልጹ “ሕወሓት ዳግም ወደ ሥልጣን የሚመጣው ኢትዮጵያ ከሞተች ብቻ ነው” ሲሉ ድርጅቱ ያበቃለት መሆኑን አመላክተዋል። ይሁንና ለውይይት ክፍት የሆነው መንግሥታቸው፣ ሕወሓትን ጨምሮ ከየትኛውም ወገን ጋር ችግሮችን በውይይት መፍታት ቀዳሚ መርሆው እንደሆነ አስገንዝበዋል።

“የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በርካታ ጥቅሞችን ያስገኘ ቢሆንም፣ ‘ለምን ተስማማችሁ?’ በሚል ያኮረፉ በርካታ ኃይሎች ተፈጥረዋል። ከሕወሓት ባሻገር በትግራይ ላይ ጥፋት ሊቀጥል ይገባ ነበር ብለው የሚያስቡ አካላት በማኩረፍ ከእኛ የራቁ ሲሆን፣ በተቃራኒው ደግሞ እርስ በእርስ ለመተባበር የሞከሩበት ሁኔታ አለ” ሲሉ የጎረቤት ሀገር ኃይሎችና ሕወሓት አሁን ላይ የመሠረቱትን ሌሎችን ያካተተ ግንኙነት ጠቆም አድርገዋል።

“አሁን ላይ በትግራይ ባሉ ኃይሎች በየቀኑ አዳዲስ ግጭቶችንና ጦርነትን ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ትንኮሳዎች እየተፈጸሙ ይገኛሉ። ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነውና የከፋው ጉዳይ ግን በአሁኑ ወቅት በርካታ የትግራይ ወጣቶች በጉልበት ታፍሰው በሱዳን እየተካሄደ ላለው ጦርነት እንዲሰለፉ መደረጉ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “እነዚህ ወጣቶች በማያውቁትና በማይመለከታቸው ጉዳይ በሱዳን ጦርነት ውስጥ ሕይወታቸውን እያጡ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ሳይበቃ፣ ጉዳዩ ወደ ሱዳንም ተሻግሯል” በማለት ድርጅቱ እያደረሰ ያለው ቀውስ ስፋት ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል።

“በዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ የትግራይ ሕዝብ የችግሩ ፈጣሪ ሳይሆን፣ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ነው። የትግራይን ሕዝብ ይበልጥ የጎዳውና ጉዳቱን ያባባሰው የማይታይ የውስጥ ቁስል መኖሩ ሲሆን፣ እንዲህ ዓይነቱ የውስጥ ቁስል ደግሞ በቀላሉ የማይሽር ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ዛሬ በትግራይ ውስጥ ከሚኖረው ይልቅ በደሴ፣ በጎንደር፣ በአዲስ አበባ እና በአዳማ በሰላም እየኖረና ያለምንም ሥጋት ወጥቶ የሚገባው የትግራይ ተወላጅ ቁጥር ይበልጣል” በማለት በትግራይ ውስጥ ለውጥ መምጣቱ እጅግ ወሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር የሰሙ ታዛቢዎች “ይህ ንግግር ሕወሓት ወደ ሰላም መጥቶ ሥልጣኑን በማስረከብ፣ ምሕረት ጠይቆ ለመኖር ካልወሰነ ዕድሉ እስከወዲያኛው እንደሚሰናበት የሚያሳይ ነው” የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

“ለኢትዮጵያ ስንል እንተው” ዐቢይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ፤ የ2019 በጀት 2.339 ትሪሊየን ብር ሆኖ ፀደቀ፤ “አንራብም”

አዲስ ሪፖርተር –“ስኬት የሰጠን በዕቅዳችን ልክ ውጤታማ እንድንሆን፣ ያደረገን ፈጣሪያችን...

ከአሜሪካ ወደ ሎንዶን የዞረው የትጥቅ ትግል አዲስ ግንባር አዝማች፦ ሕዝቅዔል ገቢሳ፣ አብዱራህማን ማህዲ እና መሐመድ ሃሰን

አዲስ ሪፖርተር (ዋሽንግቶን) — “ኢትዮጵያ ወደብ ልትወስድባችሁ ነው። ድሬደዋና...