ምርጫ እንዳይካሄድ ጥምረት ተፈጥሮ ነበር። ከምርጫ በኋላ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክክሩን እንዳያደርግ ሌላ ጥምረት ተመስርቶ ነበር። ሁለቱም ስላልተሳኩ በሸረሪና በኃይል ለመግባት ተሞከረ። በውጤቱም አስደንጋጭ ዜና ተሰማ። በመረዋ ተመሳሳይ ሙከራ ተሞከረ አልተሳካም። በመጨረሻም በመስከረም የአዲስ መንግስት ምስረታ እንዳይደረግ ቀደም ሲል ከነበሩት ጥምረቶች የላቀ ጥምረት ተፈጠረ። ይህ ሰባት አባላት አሉት የተባለ ጥምረት በሳምንት ውስጥ መንግስት እንደሚያፈርስ፣ የጅቡቲን መንገድ ቆርጦ መንግስትን እንደሚያንበርከክ ተገለጸ። ሁሉም ሳይሆን ቀርቶ ሰኞ በአዲስ አበባ አዲስ መንግስት እንደሚመሰረት ታውቋል። መርሃ ግብሩ ቀደም ሲል የተያዘ የክልሎች የመንግስት መስረታ ማGጠቃለያ ነው። ትግራይም ኮማንድ ፖስት አቋቁማ የሽግግር ጊዜ መንግስት ተመሰርታለች ….
አዲስ ሪፖርተር ዜና — ከጀርባ ያሉትን ግብፅንና ኤርትራን ሳያካትት ሕወሐት በበላይነት የሚመራው «የትብብር ለሕልውና» የተሰኘው የሰባት ታጣቂ ኃይሎች ጥምረት ሲመሠረት “በሁሉም አቅጣጫ ጦርነት በመክፈት የብልፅግናን መንግሥት እናፈራርሳለን” በማለት መግለጫ ተሰጥቶ ነበር።
ሰባቱ ተጣማሪዎች ብልፅግናን በሳምንታት ቀብረው የአገር መከላከያን እንደሚያፈርሱ፣ አየር ኃይል እንደሚበተን እና ኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ እንደማይኖራት በይፋ በማስታወቅ ደጋፊዎች የሚባሉ፣ የግብፅ ሚዲያዎች፣ የኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች፣ “ኢትዮጵያዊ ነን” የሚሉ ነገር ግን በሻዕቢያ በኩል ክፍያና መመሪያ የሚሰጣቸው ሚዲያዎች በመቀባበል ይህንኑ ሲያሰራጩ ነበር።
ጥምረቱ ከትግራይ፣ በሕወሐት ቲቪና የመረጃ አውታሮች በዘመነ ካሴ አማካይነት ከላይ በተገለጸው አግባብ ይፋ ሲሆን “ከአገዛዙ ጋር የቆማችሁ ከወዲሁ ተስፋ ቆርጣችሁ እጅ ስጡ” በማለት በተለያዩ አውዶች ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያም ተሰጥቶ ነበር። በተለይ ለትግራይ የሰላም ኃይሎች “ቀብራችሁ ደርሷል” በማለት በገሃድ ስም እየተጠቀሰ ሳይቀር ማስጠንቀቂያ እየተነገረ ጎን ለጎን በአላማጣ፣ በራያ፣ በሰቆጣ እና በአፋር ግንባር ጦርነት ተከፈተ።
ጦርነቱ እንደተጀመረ በፈጣን ማጥቃት ሕወሐት የሚመራው ጥምረት ብልጫ የያዘ ቢመስልም፣ በመከላከል ማጥቃት ማድረሱን በመረጃና ማስረጃ የሚገልጸው የአገር መከላከያ በአራተኛው ቀን ወደ ሙሉ ማጥቃት ተዛወረ። በስምንተኛው ቀን ከትግራይ የሰላም ኃይሎች ጋር በመሆን መቀለን መቆጣጠር ተቻለ።
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ሰላም ኃይሎች ጋር በመሆን ባካሄዱት በዚሁ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ዛሬ የመቀለ ከተማን በቁጥጥር ስር ቢያውሉም፣ ለጥንቃቄ ሲባል እስከ ማምሻው ድረስ ከተማዋን የማፅዳት ሥራ እንደሚሠራ ታውቋል።
ከተማዋን በስልትና በጥናት የመቆጣጠሩ ሥራ ምሽቱን የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ወዲያውኑ የመከላከያ ሠራዊት፣ የትግራይ ሰላም ኃይሎች፣ የፌደራል ፖሊስና የአገር ሽማግሌዎች የሚሳተፉበት አስቸኳይ ኮማንድ ፖስት ይቋቋማል። ይህ ኮማንድ ፖስት በትግራይ ለውጥ ፈላጊዎች ምክር ቤትና አግባብ ባላቸው አካላት (ብልፅግናን ጨምሮ) አዘጋጅነት አስቸኳይ የሽግግር ጊዜ መንግሥት የማቋቋም ሥራውን ያከናውናል ተብሏል።
በሕወሐት አስተባባሪነት የተቋቋመውና «ትብብር ለሕልውና» የተሰኘው የሰባት ድርጅቶች ስብስብ የፊታችን ሰኞ አዲስ አበባ ላይ አዲስ መንግሥት ሳይመሠረት በርካታ ቦታዎችን በመቆጣጠር መንግሥትን እንደሚያፈርሱ፣ መከላከያንና የአየር ኃይልን እንደሚበትኑ እንዲሁም ኢትዮጵያ እንደ ሁኔታው ሦስት ቦታ ልትከፋፈል እንደምትችል የውጭ አገር አስተባባሪዎቻቸው ማስታወቃቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።
ነገር ግን የተባለው ሳይሆን የፊታችን ሰኞ «በአዲስ አበባ አዲሱ መንግሥት በይፋ ሲቋቋም በትግራይ የኮማንድ ፖስት ሥራውን በይፋ ይጀምራል» የሚል መርሃ ግብር መዘጋጀቱ ተሰምቷል። መንግሥትን እንደሚያፈርሱ ያስታወቀው ሻዕቢያ መራሹ ስብስብ ተበታትኖ የፌደራል መንግሥት ለመጪው አምስት ዓመታት ከሕዝብ ጋር ኮንትራት የሚገባበትን አዲስ መንግሥት እንደሚመሠርት ታውቋል።
እንደ ሮይተርስ ያሉ የውጭ ሚዲያዎችና በተለያዩ አገባቦች በተገኙ የተለያዩ ማረጋገጫዎች፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የአሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያን ከዘረፋና ከውድመት ለመታደግ አስቀድሞ የተቆጣጠረ ሲሆን፣ የጋራ ኃይሎቹ በከተማዋ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር እንዳይፈጠር በጥንቃቄ መቀለን የመቆጣጠር ሥራቸውን እየሠሩ ነው።
በሌላ በኩል፣ በግብፅና በኤርትራ መንግሥታት የሚደገፈው ይህ ስብስብ በመሸነፉና ዕቅዱ በመክሸፉ ምክንያት በሁኔታው ሥጋት የገባቸው የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ግብፅ ማምራታቸው ይፋ ሆኗል።
በተውሶ አውሮፕላን ወደ ግብፅ ያቀኑት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ የኢትዮጵያን ድንበር ላለፉት አምስት ዓመታት የወረረው ሠራዊታቸው በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ ከኢትዮጵያ መንግሥት አስቸኳይ ትዕዛዝ እንደሚሰጠው ምንጮች ለአዲስ ሪፖርተር አስታውቀዋል።
በስለላ፣ በኮንትሮባንድና በገንዘብ ማጠብ ሥራ ላይ የተሰማሩት የኤርትራ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች ከአዲስ አበባ ለቀው እንዲወጡ መታዘዙን ተከትሎ “ድሮም ስንወተውት ነበር፤ ዘግይቶም ቢሆን አቋም መያዙ ድንቅ ነው” በማለት የኢዜማ አመራር ለአዲስ ሪፖርተር አመልክተዋል።
የኤርትራን አሥር፣ የግብፅን አንድ ዲፕሎማት ከአዲስ አበባ ያባረረው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በተመሳሳይ በኤርትራ እና በካይሮ ያሉት ዲፕሎማቶቹ እንዲወጡ ተደርጓል።
የሕወሐት መሸነፍ ያስከተለውን ጫና ለመቋቋም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ካይሮ ካመሩ በኋላ መቀለን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው የመንግሥት ኃይል ቀጣይ ኦፕሬሽን ለጊዜው አልታወቀም። የትግራይ ሰላም ኃይሎች መሪ በተደጋጋሚ “ሻዕቢያ የትግራይን ሕዝብ ሊረሳ በማይችል ግፍ ጨፍጭፏል፣ ዘርፏል፣ ደፍሯል፤ ለዚህ ሁሉ በደሉ ቅጣት ይጠብቀዋል” በማለት በእነ ዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው ሕወሐት ይህን ሁሉ ረስቶ ከእነሱ ጋር ሕብረት መፍጠሩን “ባንዳነት” በማለት ሲያወግዙ እንደነበር አይዘነጋም። እናም በርካቶች እንደሚሉት፣ የአገር መከላከያና የትግራይ ሰላም ኃይሎች ከቀይ ባሕር አፋሮች ጋር ሆነው የሻዕቢያን ዕድሜ ያሳጥሩታል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






