ኢትዮ ቴሌኮም 215.82 ቢሊዮን ብር ገቢ ሲያስመዘግብ፣ ቴሌብር 4.19 ትሪሊዮን ብር የገንዘብ ዝውውር አከናወነ

Date:

አዲስ ሪፖርተር ዜና | አዲስ አበባ — ኢትዮ ቴሌኮም በ2018 በጀት ዓመት 215.82 ቢሊዮን ብር ገቢ በማስመዝገብ የዓመቱን የገቢ ዕቅድ 99.7 በመቶ ማሳካቱን አስታውቋል። ኩባንያው የሶስት ዓመት “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታል እና ከዚያም ባሻገር” ስትራቴጂው የመጀመሪያ ዓመት በጠንካራ የፋይናንስና የዲጂታል አፈጻጸም መጠናቀቁን ይፋ አድርጓል።

እንደ ኩባንያው መረጃ፣ ከተገኘው 215.82 ቢሊዮን ብር ገቢ ውስጥ የዳታና የኢንተርኔት አገልግሎቶች 31.1 በመቶ ድርሻ ሲይዙ፣ የሞባይል ድምፅ አገልግሎት ደግሞ የገቢውን 23.5 በመቶ አበርክቷል። አጠቃላይ ገቢውም ከ2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ33.2 በመቶ ከፍ ማለቱም ተመልክቷል።

በፋይናንስ አፈጻጸሙ መሠረት ያልተጣራ ትርፍ 113.1 ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህም የ51.9 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን አሳይቷል፤ የሥራ ማስኬጃ ትርፍ ደግሞ 92.9 ቢሊዮን ብር በመድረስ ከባለፈው ዓመት 47.5 በመቶ የድገት ልዩነት አሳይቷል።

በደንበኞች ቁጥርም ኢትዮ ቴሌኮም 90.12 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን በማድረስ የእቅዱን 101.7 በመቶ ማሳካቱን ገልጿል። በተመሳሳይ 217 አዳዲስ የሽያጭና የአገልግሎት ማዕከላት በመክፈት አጠቃላይ ቁጥራቸውን 1,145 አድርሷል።

በቴክኒካል መሠረተ ልማት 603 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ 195 የሚሆኑት በገጠር አካባቢዎች ተገንብተዋል። በዚህም የኔትወርክ አቅም 115.1 ሚሊዮን ደርሷል። እንዲሁም 4ጂ LTE አገልግሎት 1,200 ከተሞችን ሲደርስ፣ 5ጂ ኔትወርክም ወደ 33 ከተሞች ተስፋፍቷል። ኩባንያው በአረንጓዴ ኃይል መስክም 215 አዳዲስ የሶላር ጣቢያዎችን በመገንባት 39.72 ሜጋዋት አጠቃላይ የሶላር ኃይል አቅም እንዲፈጠረ ማስቻሉን አመልክቷል።

ቴሌብር 4.19 ትሪሊዮን ብር የገንዘብ ዝውውር አከናወነ

በሌላ በኩል የኩባንያው ዲጂታል ፋይናንስ መድረክ የሆነው ቴሌብር በ2018 በጀት ዓመት 2.61 ቢሊዮን ግብይቶችን በማስተናገድ 4.19 ትሪሊዮን ብር የገንዘብ ዝውውር ማከናወኑ ተገልጿል። ይህም በአማካይ በየቀኑ 11 ቢሊዮን ብር በቴሌብር እንደሚዘዋወር ያመለክታል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እንደገለጹት፣ የቴሌብር ደንበኞች ቁጥር 60.6 ሚሊዮን ደርሷል። ከዳሸን ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከሲንቄ ባንክ እና ከአዋሽ ባንክ ጋር በመተባበር ለ5.65 ሚሊዮን ደንበኞች 19.51 ቢሊዮን ብር የማይክሮ ብድር መሰጠቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም 1.3 ሚሊዮን ደንበኞች 18.75 ቢሊዮን ብር መቆጠባቸውን ሲገልጹ፣ ቴሌብር ከ33 ባንኮች ጋር የፋይናንስ ትስስር እንደፈጠረ፣ 410.7 ሺህ ወኪሎችና 440.1 ሺህ ነጋዴዎችም በአገልግሎቱ መሳተፋቸውን አመልክተዋል።

በኢ-ኮሜርስ ዘርፍም የቴሌብር መድረክ ከ2.4 ሚሊዮን በላይ ጉብኝቶችን በማስተናገድ፣ 739 የተመዘገቡ ነጋዴዎች ከ58.3 ሺህ በላይ ደንበኞች ጋር 72.1 ሺህ ግብይቶችን በማከናወን 377.9 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ የሽያጭ መጠን አስመዝግበዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም የበጀት ዓመቱን ውጤት አስመልክቶ ለደንበኞቹ ከሐምሌ 17 እስከ 19 ድረስ 1.5 ጊጋባይት ዳታ፣ 15 ደቂቃ የድምፅ ጥሪ እና 30 አጭር የጽሑፍ መልዕክት (SMS) በስጦታ መስጠቱንም አስታውቋል።

የ2018 በጀት ዓመት ውጤት ኢትዮ ቴሌኮም ከባህላዊ የቴሌኮም አገልግሎት በላይ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ተቋም በፍጥነት እየተሸጋገረ መሆኑን ያሳያል። በተለይ የቴሌብር የገንዘብ ዝውውር መጠን፣ የደንበኞች እድገት እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች መስፋፋት በኢትዮጵያ የካሽ አልባ ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ኩባንያው እየተጫወተ ያለውን ሚና ያጠናክራል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related