አዲስ ሪፓርተር አዲስ አበባ – ጥቅምት 7 ቀን 2018 ዓ.ም – የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ (EIB) በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ማሻሻያ ፕሮግራም (RUFIP III) ለመደገፍ የ110 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል።
ይህ ቃል የተገባው የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በአሁኑ ወቅት ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እና ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ነው።
በውይይቱ ላይ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የዓለም አቀፍ አጋርነት ዳይሬክቶሬት ጄነራል ወ/ሮ ማሪያታ ጃገር እና ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የዓለም አቀፍ አጋርነት ዳይሬክተር ወ/ሮ ቱራያ ትሪኪ ተሳትፈዋል። በውይይቱ ወቅት በዋናነት ቀጣናዊ የመሰረተ ልማት ትብብርን ማጠናከር እና በተለያዩ ማሻሻያዎች ላይ የሚደረገውን የፋይናንስ ድጋፍ ማጠናከር ላይ ትኩረት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ጥያቄዎች እና የባንኩ ምላሽ
አቶ አህመድ ሺዴ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እና የሴቶች የስራ ዕድል ፈጠራን ጨምሮ በበርካታ ዘርፎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አመስግነዋል። በቀጣይም ባንኩ በገጠር አካታች እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት (RISED) ኢኒሼቲቮች እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
በምላሹ ወ/ሮ ቱራያ ትሪኪ የባንኩ ተቋም ለገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ማሻሻያ ፕሮግራም (RUFIP III) ሶስተኛ ምዕራፍ ማስፈጸሚያ የሚሆን የ110 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ በይፋ አረጋግጠዋል።
ይህ ውይይት የኢትዮጵያ መንግስት እና የአውሮፓ ህብረት ተቋማት በዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ልማት ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር እንዲሁም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።
ፎቶ Nicolas Bouvy/EPA




