[ሳይቃጠል በቅጠል]የግራጫ ጦርነት ከመደበኛው የሳንጃ ባፈሙዝ ጦርነት በመለስ የሚፈፀም የጥቃት አይነት ሲሆን በተግባር ፍፁም ሰላም ሊባል በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ የሚካሄድ የዘመናዊ ስትራቴጂክ ትግል ስልት ነው። ይህ ስልት የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ ዓላማዎችን ለማሳካት የሚረዱ የተቀናጁ እና ግልጽ ያልሆኑ ዘዴዎችን በመጠቀም የሚፈፀም ነው። በዋናነት ጥቅም ላይ የሚውሉ ስልቶች እንደ የመረጃ ጦርነት (ሐሰተኛ መረጃና ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት)፣ የሳይበር ጥቃቶች (በወሳኝ የመሰረተ ልማት እና ኔትወርኮች ላይ)፣ በሕቡዕ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን መግደል፣ እና የፖለቲካ ተቋማትን ከውስጥ የማናጋት ድርጊቶችን ያጠቃልላል። ይህን አስቀድሞ አለመረዳትና እንደ አገር ስትራቴጂካል ጥቅሞችን በወጉ ማስላትና መንከባከብ አለመቻል አደጋውን ዞሮ ዞሮ የጋራ ያደርገዋል። እናም ስያቃጠል በቀጥል ነው ነገሩ

———————————- በአለባቸው ጉብሳ – የአዲስ ሪፖርተር ቋሚ አምደኛ ————————————-
እንደ መግቢያ
አሁን ባለንበት የሃያላን ሃገራት የፉክክር ዘመን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዳዲስ የጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች በየጊዜው እየተፈጠሩ ይገኛሉ። በዚህ ወቅት፣ ሃገራት በሌላ ሃገር ላይ ያላቸው ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ውዴታ ላይ የተመሰረተ የንግድ፣ የፋይናንስ የኢንቨስትመንት እና የቴክኖሎጂ ማባበያ በመስጠት (Accommodation) ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ በሃይል የማስገደድ (coercion) ተግባራትን ይፈፅማሉ። በማስገደድ ላይ የተመሰረተ የጥቅም ማስከበሪያ ስልቶች መካከል “ግራጫ ጦርነት” (Gray Zone Warfare) እየተባለ የሚጠራው ስልት ዋነኛው ሲሆን ለሃገር ብሄራዊ ደህንነት እና ልማት ቁልፍ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ላይ አካላዊ እና የሳይበር ጥቃት በመፈፀም ፣ ሀሰተኛ መረጃ አምርቶ በማሰራጨት፣ ታዋቂ ሰዎችን ኢላማ ያደረገ ግድያ በመፈጸም እና ሌሎች መሰል ጥቃቶችን በመፈፀም በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለውን መተማመን በመሸርሸር፣ የዲሞክራሲ ተቋማት በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ተማኝነት በማሳጣት፣ የሀገርን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ሽባ በማድረግ፣ ሕዝብ ለህዝብ እንዲጠራጠር ወዘተረፈ በማድረግ በሂደት ሃገርና መንግስትን በማዳከም ስትራቴጂክ ግባቸውን ያሳካሉ። በአንፃሩ ደግሞ የሃገራቸው ቁልፍ መሰረተ ልማቶች፣ መሪዎች እና ሕዝባቸው የዚህ ጥቃት ሰለባ እንዳይሆኑ ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር በታቀደና በተቀናጀ መልኩ የመከላከል ተግባራትን ይፈፅማሉ።
ጂኦስትራቴጂካሊ ወሳኝ ቦታ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ የሃያላን ሃገራት የፉክክር መድረክ ስትሆን ታሪካዊ ጠላቶቻችን ደግሞ ከመቸውም ጊዜ በላይ ሃገራችንን በማናቸውም መንገድ ለማዳካም ቆርጠው በተነሱበት በአሁኑ ወቅት፣ ይህ የግራጫ ጦርነት ስልት ትልቅ የደህንነት ስጋት ሆኗል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ ለሃገራችን የኢኮኖሚ እድገት እና የማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦት ቁልፍ ሚና እየተጫዎቱ የሚገኙ በመንግስት እና በግል አጋርነት ስምምነት መሰረት ለግል የተሰጡ ወይም በጋራ የሚተዳደሩ ስትራቴጂክ የመሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች የዚህ ግራጫ ጦርነት ጥቃት ሲፈፀምባቸው ተስተውሏል። ከነዚህም መካከል በኦቪድ ሆልዲንግስ ስር በሚተዳደረው የኦቪድ ሪልእስቴት ላይ በታቀደና በተቀናጀ መልኩ በውስጥና በውጭ አካላት የተፈፀመ የሚዲያ ስም ማጥፋት ዘመቻ አንዱ ነው። የዚህ ጥቃት ዓላማ የኦቪድን መልካም ስም፣ ከደንበኞች ጋር ያለውን ግንኙነት እና ከመንግሥት ጋር ያለውን ስትራቴጂያዊና ሕጋዊ አጋርነት ማዳከም ሲሆን፣ ይህ ደግሞ በውጭ ሃገር ከተለመደው የንግድ ባላንጣ የተግባቦት ጥቃት (black PR) በላይ የሆነ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት መሆኑን ያመለክታል።
በመሆኑም በዚህ ፅሁፍ በኦቪድ ሪልእስቴ ሃገራዊ ወሳኝ ስትራቴጂክ ሃብት ለምን እንደሆነ፣ የተፈፀመው ጥቃት እና በብሄራዊ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ በመመርመር መንግስት ይህን መሰል ጥቃቶችን በመከላከል ሌሎች ተመሳሳይ ስትራቴጂክ ሃብቶች ቀጣይነት ያለው የግንባታና የአገልግሎት ተግባራቸውን (Operations) ለማረጋገጥ፣ ሃብቶቹን የሚያስተዳድሩ እና የባለቤትነት መብት ያላቸውን ቁልፍ ግለሰቦች ደህንነት ጥበቃ ስለሚያረጋግጥበት ሁኔታ ከሌሎች ሃገሮች ተሞክሮ አንፃር የመፍትሄ ሃሳብ እናመላክታለን።
ኦቪድ ሆልዲንግስ እንደ ወሳኝ ብሄራዊ ስትራቴጂክ ሃብት

የአሜሪካ ብሔራዊ መሰረተ ልማት ጥበቃ እቅድ (NIPP) ወሳኝ መሠረተ ልማት (Critical Infrastructure – CI) የሚባሉት ለሃገር ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ አገልግሎት፣ የህዝብ ጤና እና ደህንነት ወሳኝ የሆኑ እና መስተጓጎል ሲገጥማቸው ከፍተኛ ብሄራዊ ጉዳት ሊስከትሉ የሚችሉ ንብረቶች፣ ሲስተሞችና ኔትወርኮች እንደሆኑ ይገልፃል። ንብረቶችን እንደ ስትራቴጂካዊ ወሳኝ ሃብት ለመመደብ የተለያዩ ዘዴዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ፤ ከእነዚህም ውስጥ ወሳኝነትን መሠረት ያደረገ ምደባ እና ተግባርን መሠረት ያደረገ ምደባ ይገኙበታል። በወሳኝነት ላይ የተመሰረተ ምደባ ትኩረት የሚያደርገው ንብረቶቹ ለአንድ ድርጅት ኦፕሬሽን፣ ደህንነት እና ተልዕኮ ባላቸው አስፈላጊነት ላይ ተመስርቶ ነው። ለሃገራዊ ፕሮጀክት ትግበራ ወሳኝ የሆኑ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች ወይም ስርዓቶች (systems and networks) ሲስተጓጎሉ ወይም ሲጎዱ ከፍተኛ መዘዝ ያስከትላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ እነዚህን ወሳኝ ሃብቶች በግል ባለቤትነት የሚያስተዳድሩ ግለሰቦች ወሳኝ የሰው ሃብት ተብለው ይፈረጃሉ። እነዚህ ከፍተኛ ስራ አስፈፃሚዎች፣ ትልልቅ ባለአክሲዮኖች፣ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ወይም የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች መሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ። የእነዚህ ግለሰቦች ደህንነት ጥበቃ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ የሚሆነው፣ የሰውየው መጎዳት (ለምሳሌ በአፈና፣ ግድያ ወይም ማስፈራራት) በንብረቱ ላይ የአመራር መናጋት፣ የፋይናንስ መውጣት(Capital flight) ወይም ወሳኝ የፕሮጀክት ስረዛን ስለሚያስከትል ነው ። ኦቪድ ሆልዲንግስ ብሄራዊ ስትራቴጂክ ሃብት ስለመሆኑ ከነዚህ አለም አቀፋዊ መመዘኛዎች አንፃር እንደሚከተለው እናያለን።
ከፍተኛ ሃብት የሚያንቀሳቅስና ግንባታ ላይ የተሰማራ መሆኑ
የኦቪድ ሆልድንግስ ድረገፅን ከፍቶ የሚመለከት ሰው አስገራሚ እና ተአምር የሚያሰኝ የስኬት የቁጥር መግለጫ ጋር ፊት ለፊት ይገናኛል። ከ15 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚገመት የወደፊት የግንባታ ውሎችን እንደተፈራረመ እና ይህም የገበያ ወቅታዊ አቋሙንና ለለውጥ ፕሮጅክቶች ያለውን ቁርጠኝት እንደሚያሳይ ይገለፃል። ይህ ሰኬት የመጣው በ12 ዓመት ልምድ፣ ከአስር ባላይ በሆኑ የኮንስትራሽን ዘርፍ ላይ በግብአት አቅርቦት በተሰማሩ እህት ኩባንያዎቹ፣ ከ10 ሺህ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞቹ እና ዘመኑ ባፈራቸው አዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ፈጣንና ጥራት ባለው መልኩ 32 ትልልቅ የመኖሪያ፣ የንግድ እና የመሰረተ ልማት የግንባታ ፕሮጀክቶችን በልህቀት ውጤታማ በሆነ መልኩ በመፈፀሙ እንደሆነ ተመላክቷል።
ኦቪድ ሆልዲንግስ በአሁኑ ሰአት እህት ኩባንያው በሆነው ኦቪድ ሪል ስቴት አማካኝነት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር የመንግስትና የግል አጋርነት የቤቶች ግንባታ ውል ስምምነት በመፈፀም ከ60 ሺሕ በላይ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ ኩባንያው መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ ያስጀመራቸው አራት የዘመናዊ መኖሪያ ቤት ልማት ፕሮጀክቶች አሉት። ከእነዚህም ውስጥ 1,900 ቤቶችን የያዘው ጫካ መኖሪያ ቤት ፕሮጀክት፣ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት የሚገኘው ሐረር ሆራይዘን ፕሮጀክት፣ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጠውና 1,740 ሰፋፊ መኖሪያዎችን የያዘው ኪንግስ ታወር እና ያሸበረቀው አፍሪካን ሃይትስ የተሰኘው ፕሮጀክት ይገኙበታል።
ከሪል ስቴት ግንባታዎቹ በተጨማሪ ኩባንያው በአራት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕንፃ ግንባታዎችን በመስራት ላይ ይገኛል። እነዚህ ፕሮጀክቶች የሃገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠን እና ማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦትን በስፋትና በአይነት ለማሳደግ ወሳኝ ከመሆናቸውም በላይ የአዲስ አበባን ውበትና ባህል ለመጠበቅና ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል። ከዚህም ባሻገር ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት በኩል 500 ቤቶችን በነፃ ገንብቶ በማስተላለፉ እና ሌሎች በጎ አድራጎት ተግባራትን እየፈፀመ ይገኛል።
በአጠቃላይ የኦቪድ ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ ታደሰ ከፋና ብሮድካስት ኮርፓሬሽን ጋር በነበራቸው ቃለ መጠየቅ የኦቪድ በአሁኑ ሰአት ከ64 ሺሕ ቤቶች በላይ እያለማ መሆኑን እና ከነዚህም መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት በመንግሥትና በግል አጋርነት የሚለሙ መሆኑንም የገለፁ ሲሆን ይህም የኦቪድን ወሳኝ ብሄራዊ ስትራቴጂክ ሃብት መሆኑን በግልጽ ያመላክታል።
ዘመኑ የደረሰበት የግንባታ ፈጠራ ቴክኖሎጂ መጠቀሙ
በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ በዘርፉ ከተሰማሩ ሌሎች ሪል እስቴ ኩባንያዎች በተለየ ሁኔታ ኦቪድ እያሳየ ያለው ያልተለመደ ፈጣን ዕድገትና ስኬት ምንጩ በዋነኛነት የተመሰረተው የግል ካፒታልን ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠቀም፣ የፈጠራ የግንባታ ቴክኖሎጂዎች ላይ በማተኮር፣ ጠንካራ የአመራር ብቃት እና በግንባታው ዘርፉ ልምድ ካላቸው የውጭ ሃገር ኩባንያዎች ጋር ስትራቴጂክ ሽርክና በመፍጠሩ ነው።
ኦቪድ ሆልዲንግስ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዘርፍ ያሳየው ስኬት መሰረት የሆነው፣ በምህንድስና እና የፕሮጀክት አስተዳደር ዘርፍ ከ65 ዓመታት በላይ ልምድ ካለው የጀርመኑ ክሊንግ ኮንሰልት (Kling Consult) ጋር በመተባበር ኦቪድ-ክሊንግ ኮንሰልት (Ovid-Kling Consult PLC) የሚባል እህት ኩባንያ መመስረቱ ነው። ይህ ስትራቴጂያዊ ሽርክና ኦቪድ የላቀ የምህንድስና የቴክኒክ ብቃት እና ደረጃውን የጠበቀ የዓለም አቀፍ የፕሮጀክት አስተዳደር ዕውቀትና ልምድ እንዲያገኝ አስችሎታል። ይህም ኦቪድ ፕሮጀክቶቹን በዘላቂነት፣ በወጪ ቆጣቢነት እና በታቀደበት ጊዜ ፈጠራንና ቅልጥፍናን ባጣመረ መልኩ በመፈፀም ረገድ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያሳድግ አስችሎታል፤ ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን ኮንስትራክሽን ዘርፍ የሥራ አፈጻጸም ደረጃ ከፍ እንዲል አድርጓል።

በአጠቃላይ፣ ኦቪድ ከክሊንግ ኮንሰልት ጋር ያለው አጋርነት ፈጠራንና ቅልጥፍናን እንዲያጣምር አስችሎታል። በተጨማሪም፣ ኦቪድ-ክሊንግ ኮንሰልት የኦቪድ ግሩፕ የተቀናጀ የአቅርቦት ሰንሰለት (A-to-Z integrated approach) አቅምን በብቃት እንዲያስተዳድር በመርዳት የፕሮጀክት መቆራረጥን በመቀነስ ቅልጥፍናን ጨምሯል። ይህ ስትራቴጂያዊ እንቅስቃሴ ኦቪድ በኢትዮጵያ ውስጥ የቤት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ጥራት ያለው፣ የሕዝቡን ገቢ ያገናዘበ ተመጣጣኘ ዋጋ ያላቸውን ቤቶች በፍጥነት በማቅረብ የመሪነት ቦታውን እንዲያጠናክር አስችሎታል።
ከዚህ በተጨማሪም፣ ሌላኛው የኦቪድ የስኬት ምንጭ በግንባታ ፈጠራ ቴክኖሎጂ ታዋቂ ከሆነው የደቡብ ኮሪያው ኩምጋንግ ኪድ (Kumkang Kind) ጋር ስትራቴጂክ አጋርነት በመፍጠር የአልሙኒየም ፎርም ዎርክ ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለግንባታ በማዋል እየተጠቀመ መገኘቱ ነው። ይህ አብዮታዊ ቴክኖሎጂ ከተለመደው የግንባታ ዘዴ በተለየ ሁኔታ በአንድ ወር ውስጥ እስከ አምስት ወለሎችን የመገንባት አስደናቂ አቅም ያለው ሲሆን፣ በአንድ ፕሮጀክት ውስጥ እስከ 250 ጊዜ ያህል በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ሊውል ስለሚችል ወጪ ቆጣቢ ነው። የቴክኖሎጂው ሌላው ጠቀሜታ ደግሞ ለመገጣጠም እና ለመለያየት በጣም ቀላል በመሆኑ ከፍተኛ ችሎታ ያለው የሰው ኃይል አለመፈለጉ ነው። ኦቪድ ፈጠራ ያላቸው ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባትና በተግባር በመጠቀም፣ የኢትዮጵያን የቤት አቅርቦት ችግር ፈጣን፣ ወጪ ቆጣቢና ጥራት ባለው መልኩ ለመፍታት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ በመሆኑ በመንግሥት ጭምር ተመራጭ ድርጅት ሆኗል።
የኦቪድና የመንግስት አጋርነት
የመንግስትና የግል አጋርነት (public private partnership) የዘመናዊ የኢኮኖሚ ልማት ዋና ምሰሶ ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን አግኝቷል። ይህ የአሠራር ዘዴ መንግስታት መሠረተ ልማቶችንና የሕዝብ አገልግሎቶችን ለማቅረብ የግል ካፒታልን፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራንና የአመራር ብቃትን እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት፣ ይህ አጋርነት ከፍተኛ የካፒታል ወጪ የሚጠይቁ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለማስፈፀም አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ ከመፍጠር ባሻገር፣ የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ ናቸው ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየከተማ መስፋፋት እና የህዝብ ቁጥር መጨመር ምክንያት የተፈጠረውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ባለፉት ዓመታት ከተተገበረው የመንግስት የተቀናጀ የቤቶች ልማት መርሃግብር (IHDP) አልፎ በተጨማሪ የመንግስትና የግል አጋርነት ላይ ተመሰረተ የቤት ልማት ፖሊሲ መተግበር ጀምሯል። ይህ የፓሊሲ አማራጭ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንደገለጹት፣ የቤት አቀርቦት ችግርን ለመፍታት መንግስት አዲስ አቀራረብ በመከተል የሕዝብ፣ የግልና የሕዝብና የግል አጋርነት ሞዴሎችን (Public, Private, and PPP) በአንድ ላይ የያዘ ነው። ይህ የስትራቴጂ ለውጥ የመንግስት አቅም ላይ ብቻ ተመርኩዞ የሚፈጠርን የግንባታ መዘግየትና የአፈፃፀም ብቃት ማነስ ችግርን ለመቅረፍ ያለመ ነው። በመሆኑም መንግስት ይህ አጋርነት ግልፅነት፣ ተጠያቂነት እና ፍትሃነት ባለው መልኩ ለመፈፀም የአሰራር ስርዓት ድንጋጌዎችን የያዘ የመንግስትና የግል አጋርነት አዋጅ ቁጥር 1076/2010 (በአዋጅ ቁጥር 1283/2015 እንደተሻሻለ) በማውጣት ተፈፃሚ አድርጓል።
ከተማ አስተዳደሩ በመንግስት እና ግል ዘርፍ አጋርነት ሊገነባቸው በእቅድ ከያዛቸው 100,000 ቤቶች ውስጥ 60,000 የሚሆኑትን በ558 ሄክታር መሬት ለመገንባት ከኦቪድ ሪል እስቴት ጋር የአጋርነት ስምምነት አድርጓል። የዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት አጠቃላይ የኢንቨስትመንት መጠን 450 ቢሊዮን ብር እንደሚገመት ይፋ ሆኗል። ይህ የአጋርነት ስምምነት 70/30 የተሰኘው የአጋርነት ሞዴል ሲሆን ኦቪድ 70 በመቶ ቤቶችን ገንብቶ ለሽያጭ ሲያቀርብ 30 በመቶ የሚሆኑ ቤቶችን ለመንግስት ያስረክባል።
ከተማ አስተዳደሩ ለዚህ ፕሮጀክት ኦቪድን የመረጠበት ምክንያት ኦቪድ የግንባታ ካፒታል የመሰባሰብ አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ፣ የፕሮጀክቱን ውስብስብነት ለመቋቋም በመስኩ በዲዛይንና ፕሮጀክት አመራር ልምድ እና የግንባታ ፈጠራ ቴክኖሎጂ ካላቸው ከጀርመኑ ክሊንግ ኮንሰልቲንግ እና ከደቡብ ኮሪያው ኩምጋንግ ኪድ ጋር ስትራቴጂክ ትብብር በመፍጠሩ የፕሮጀክቱን ቴክኒካዊ ብቃት፣ የጥራት ደረጃ እና በታቀደበት ጊዜው ውስጥ ገንብቶ ለመጨረስ አቅም እንደሚኖረው በመታመኑ ነው።
በመሰረቱ ይህ የአጋርነት ሞዴል ከተለመደው የመንግስት የግንባታ የግዥ ዘዴ የሚለየው ዋነኛ ነጥብ ስጋቶችን ወይም አደጋዎችን (Risks) በመንግስትና በኦቪድ መካከል ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲካፈሉ ማድረጉ ነው። በከተማ አስተዳደሩና በኦቪድ 70/30 አጋርነት ውስጥ የፋይናንስና የግንባታ አደጋ (Financial and Construction Risk) እና የግብዓት አቅርቦት አደጋ (Input Risk) በኦቪድ ትከሻ ላይ የሚያርፍ ይሆናል። ይህም ማለት ኦቪድ 60 ሽኅ ቤቶችን ለማገንባት የሚያስፈልገው ካፒታል ብር 450 ቢሊዮን የማሰባሰብ ሃላፊነት የሚኖርበት ሲሆን መንግስት ለግንባታ ሊያውለው ይገደድ የነበረውን ገንዘን ለሌሎች ወሳኝ የህዝብ አገልግሎቶች (ትምህርት፣ ጤና) እንዲያውል ያስችለዋል። በተጨማሪም የፕሮጀክት የዋጋ ጭማሪ (Cost Overrun) እና በግንባታ መዘግየት ምክንያት የሚመጣን ማንኛውንም ኪሳራ ከመንግስት ላይ ያነሳል። ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ እንዲሁ በኢትዮጵያ ውስጥ የግንባታ ግብዓት እጥረት ወይም የመሠረተ ልማት እጦት (ውሃ፣ ኤሌክትሪክ) የተለመደ ቢሆንም፣ ኦቪድ የራሱን ፍላጎት የማሟላት ግዴታ አለበት ። ይህ ፕሮጀክቱ በመንግስት ቢሮክራሲ ምክንያት እንዳይዘገይ ዋስትና ይሰጣል።
በከተማ አስተዳደሩ በኩል የሚጠበቁ አደጋዎች ደግሞ የመሬት አቅርቦትና ተደራሽነት (Land Availability Risk) እና የፖለቲካ/የቁጥጥር አደጋ (Political/Regulatory Risk) ናቸው። ከተማ አስተዳድሩ ለግንባታ አስፈላጊ የሆነውን 350-558 ሄክታር መሬት ለኦቪድ ማቅረብ እና ከቦታው ጋር የተያያዙ ማህበራዊ አደጋዎችን (እንደ የቦታ ማስለቀቅ፣ ካሳና ምትክ ቦታ መስጠጥት) የመቆጣጠር ሃላፊነት አለበት። በተጨማሪም የአጋርነት ስምምነት ውል ከተፈረመ በኋላ መንግስት ህጎችን ወይም ደንቦችን ከቀየረ፣ በግሉ ባለሃብት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የማካካሻ ዋስትና የመስጠት ግዴታ አለበት።
በአጠቃላይ ኦቪድ ሆልዲንግስ ከ15 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚገመት የወደፊት የግንባታ ውሎችን የተፈራረመ መሆኑ፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የፈጠራ ቴክኖሎጂ እና ልምድ ካላቸው የውጭ ሃገር ኩባንያዎች ጋር በሽርክና እየሰራ መሆኑ እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር የቤት ግንባታ አጋርነት በመፈራረም የሃገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት እና ማህበራዊ አገልግሎቶች አቅርቦትን ለማፋጠን እየሰራ የሚገኝ ወሳኝ ብሄራዊ የመሰረተ ልማት ተቋም ነው። ኦቪድ ሆልዲንግስ በአሁናዊ የግራጫ ጦርነት ስልቶች በሆኑት የሳይበር ጥቃት፣ የመረጃ ጦርነት ወይም አካላዊ ጥቃቶች በፕሮጀክቶቹ እና በወሳኝ ሰው ሃብቱ ላይ ቢደርስበት በአጠቃላይ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል።
በኦቪድ ላይ የተሰነዘሩ የግራጫ ጦርነት ጥቃት

የግራጫ ጦርነት ከመደበኛው የሳንጃ ባፈሙዝ ጦርነት በመለስ የሚፈፀም የጥቃት አይነት ሲሆን በተግባር ፍፁም ሰላም ሊባል በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ የሚካሄድ የዘመናዊ ስትራቴጂክ ትግል ስልት ነው። ይህ ስልት የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ ዓላማዎችን ለማሳካት የሚረዱ የተቀናጁ እና ግልጽ ያልሆኑ ዘዴዎችን በመጠቀም የሚፈፀም ነው። በዋናነት ጥቅም ላይ የሚውሉ ስልቶች እንደ የመረጃ ጦርነት (ሐሰተኛ መረጃና ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት)፣ የሳይበር ጥቃቶች (በወሳኝ የመሰረተ ልማት እና ኔትወርኮች ላይ)፣ በሕቡዕ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን መግደል፣ እና የፖለቲካ ተቋማትን ከውስጥ የማናጋት ድርጊቶችን ያጠቃልላል።
የዚህ ስልት ዋና መለያው ግልጽነት ማጣት (Ambiguity) ሲሆን፣ ጥቃቱን ማን እንደፈፀመው ለመለየት አስቸጋሪ በማድረግ፣ ተጠቂው ሃገር ውጤታማ እና ተመጣጣኝ የሆነ የአጸፋ እርምጃ እንዳይወስድ የሚከለክል መሆኑ ነው። ዓላማው የተጠቂውን ሃገር ብሔራዊ ጥቅም፣ ደህንነት፣ ኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ ተቋማት እና የህዝብ መተማመን በስውርና በዘላቂነት ማዳከም ነው።
በዚህ ፅሁፍ መግቢያ ላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ ጂኦስትራቴጂካሊ ወሳኝ ቦታ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ የሃያላን ሃገራት የፉክክር መድረክ ስትሆን ለማጥቃትና ለመከላከል ታሪካዊ ጥላቶቻችን ደግሞ ከመቸውም ጊዜ በላይ ሃገራችንን በማናቸውም መንገድ ለማዳካም የግራጫ ጦርነት ስልትን እየተጠቀሙ ይገኛል። ይህ ጥቃት በመደበኛው ጦርነትና በሰላም መካከል ባለው ክፍት ቦታ የሚፈጸም ሲሆን ተጠቂው ሃገር እንደ መደበኛ ጦርነት ቆጥሮ ምላሽ ለመስጠት
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ ለሃገራችን የኢኮኖሚ እድገት እና የማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦት ቁልፍ ሚና እየተጫዎቱ የሚገኙ በመንግስት እና በግል አጋርነት ስምምነት መሰረት ለግል የተሰጡ ወይም በጋራ የሚተዳደሩ ስትራቴጂክ የመሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች የዚህ ግራጫ ጦርነት ጥቃት ሲፈፀምባቸው ተስተውሏል። ከነዚህም መካከል በኦቪድ ሆልዲንግስ ስር በሚተዳደረው የኦቪድ ሪልእስቴ ላይ በታቀደና በተቀናጀ መልኩ በውስጥና በውጭ አካላት የተፈፀመ የሚዲያ ስም ማጥፋት ዘመቻ አንዱ ነው።
ይህ ኦቪድን ኢላማ ያደረገው የስም ማጥፋት ዘመቻ ሆን ተብሎ በታቀደ መልኩ የሐሰት ትርክቶችን በማምረት እና በተለያዩ የዲጂታል ሚድያዎች በማሰራጨት የተፈፀመ ነው። የዚህ ዘመቻ ተዋንያን በግልፅ የሚታወቁ ተፅዕኖ ፈጣሪ ዲጅታል ሚድያዎች እና የማህበራዊ ሚድያ ሀሰተኛ መለያ ያላቸው (false personas) ነበሩ። በግልፅ የሚታወቁት ሚድያዎች እና አክቲቪስቶች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ (wittingly or unwittingly) የዚህ ዘመቻ ተሳታፊ ነበሩ። አንዳንዶቹ ትኩረት ሳቢ ዜና ያገኙ መስሏቸው የተመልካቾቻቸውን ትኩረት ለመሳብና ገቢ ለማግኘት ባለማወቅ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ከመንግስት ጋር ባለቸው ተቃርኖ ምክንያት ሆን ብለው የፓለቲካ ትርፍ ለማግኘት የዘመቻው ተሳታፊ ሆነዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሀሰተኛ መለያዎች ደግሞ በግልፅ የሚታወቁትን የተፅዕኖ ፈጣሪ የማህበራዊ ሚድያ መለያዎችን like, share and comment በማድረግ መልዕክቱን በማናኘት (viral and Trending) ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድረገዋል።
የዚህ ጥቃት ዓላማ የኦቪድን መልካም ስምና ዝና ማጥፋት፣ ከደንበኞች ጋር በተመተማመን ላይ የተመሰረተውን ግንኙት በጥርጣሬ እንዲሞላ ማድረግ እና ከመንግሥት ጋር ያለውን ስትራቴጂያዊና ሕጋዊ አጋርነት ማዳከም ናቸው። ጠቅላላ ግቡ እንደ ጥቃት ፈጻሚው የተለያየ ቢሆንም የታሪካዊ ጥላቶቻችን ግብ ግን በግልጽ የታወቀ ነው። ይኸውም የሃገራችን የኢኮኖሚ እድገት እና ማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦትን በማዳከም የፓለቲካ መረጋጋት የሌለባትና በድህነት አረንቋ ውሰጥ ተዘፍቃ እንድትቀጥል ማድረግ ነው።
የመፍትሄ ሃሳብ፡ ሳይቃጠል በቅጠል
ይህ የታቀደና የተቀናጀ የሀሰተኛ መረጃ ዘመቻ ከሳይበር እና ሌላ አካላዊ ጥቃት ጋር ሲቀናጅ ኦቪድ ከሚያንቀሳቅሰው ካፒታል፣ ስትራቴጂካሊ በሽርክና በጋራ ከሚሰሩት የውጭ ኩባንያዎች ወሳኝነት እና ከመንግስት ጋር በአጋርነት ለመስራት ከገባው የቤቶች ግንባታ ውል አንጻር በሃገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል መገመት አይከብድም።
ኦቪድ ከፍተኛ የሆነ ኪሳራ ውስጥ ከመግባቱም ባለፈ መንግስት የቤት አቅርቦትን ተደራሽ በማድረግ ዘላቂ የልማት እቅዱን ለማሳካት የሚያደርገውን ጥረት የሚደናቀፍ ሲሆን የኦቪድ ደንብኞች በሚያነሱት ጥያቄ ሌላ ማህበራዊና ፓለቲካዊ ቀውስ እንዲፈጠር ያደርጋል። እንዲሁም ኦቪድ የሃገሪቱን የሪል እስቴት ኮንስትራክሽን ለማዘመንና ለማሳደግ የግንባታ ፈጠራ ቴክኖሎጂ እና በፕሮጀክት አመራር ልምድ ያላቸው በጋራ ሽርክና ለመስራት የመጡ የውጭ ኩባንያዎች ወደ ሌላ ሃገር ይሄዳሉ። ይህም በአጠቃላይ ሃገሪቱ በቤቶች ግንባታ ዘርፍ ልታስመዘግብ የምትችለውን የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦት እድገት ወደ ኋላ ከመጎተቱም ባለፈ የፓለቲካ ስትራቴጂክ ስጋት በመፍጠር ሃገሪቱ ለኢንቨስትመንት የማትመች ያደርጋል።
በመሆኑም ይህ ጅምር የስም ማጥፋት ዘመቻ ከሌሎች የግራጫ ጦርነት ስልቶች ጋር ተቀናጅቶ ከመፈፀሙና የማይተካ ጉዳት ከማድረሱ በፊት መንግስት ኦቪድ ሆልዲንግስ ሃብቱ፣ አመራሮቹና ሸሪኮቹ ወሳኝ ስትራቴጂክ ብሄራዊ ሃብቶች መሆናቸውን በመረዳት የሀሰተኛ መረጃ ዘመቻ፣ የሳይበር እና አካላዊ ጥቃትን ለመከላከል በታቀደ፣ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ልዩ የደህንነት ጥበቃ ሊያደርግለት ይገባል። ይህ የመከላከል ስትራቴጂ ለኦቪድ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ወሳኝ ስትራቴጂክ ሃብቶችና ባለቤቶች ኢላማ ቢሆኑ ከሚያስከትለው ሃገራዊ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና የደህንት ጉዳት አንጻር በጥናት በመለየት ተግባራዊ ሊሆን ይገባል።
ፎቶ ከኦቪድ ድረ ገጽ የተወሰደ
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/profile.php?id=61577410241403
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






