አዲስ ሪፖርተር – የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዶ/ር አኔት ዌበር Dr. Annette Weber ለኤርትራ መሪዎች ጣልቃ ገብነታቸውን እንዲያቆሙ አሳስበው መመለሳቸውን ተልትሎ በግል የኤክስ ገጻቸው በዲፕሎማት ቋንቋ ያሰፈሩት መልዕክት ተቃውሞና አቤቱታ እያስተናገደ ነው። የጉብኝቱ ዋና ዓላማና ፖለቲካዊ ፋይዳ ግልጽ ባይደረግም የአውሮፓ ሕብረት ወደ ኤርትራ ያቀናው የአልቡርሃን መንግስት አሸባሪ ከተባለና ሕብረቱ የኢትዮጵያ መንግስት ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር ለማግባባት የጀመረው ጉዞ ብዙ ርቀት መሄዱ ከተሰማ በኋላ መሆኑ ዜናውን አክብዶታል።
“ባለፉት ጥቂት ቀናት በአስመራ አሳታፊ እና ገንቢ የሆኑ ውይይቶችን አድርገናል። የአውሮፓ ህብረትን እና ኤርትራን በሚያሳስቡ እና በሚያስተሳስሩ ቁልፍ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይቱን በመቀጠላችን ደስተኛ ነኝ። ላስተናገዱን ለአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ጆአና ዳርማኒን ምስጋናዬ ይድረስ።” በማለት የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዶ/ር አኔት ዌበር በግል የኤክስ ገጻቸው ያሰፈሩት መልዕክት በተቃውሞ አስተያየቶች ነው የታጀበው።
“ይህንን ውይይት (engagement) ብላችሁ ልትጠሩት ትችላላችሁ፤ ነገር ግን ይህ ገለልተኛ አካሄድ አይደለም። አንሸነጋገል። ለ30 ዓመታት ያህል ኤርትራ ውስጥ ምንም ዓይነት ምርጫ፣ የሕግ የበላይነት እና መሠረታዊ ነፃነት የሚባል ነገር አልታየም። በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ያለ ፍርድ ቤት ሂደት ታስረዋል። ሙሉ አንድ ትውልድ ማብቂያ በሌለው በብሔራዊ አገልግሎት ታስሯል። ሰዎች አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱት በውጫዊ ምክንያቶች ሳይሆን የወደፊት ተስፋቸውን በሚነፍጋቸው ሥርዓት ሳቢያ ነው። ታዲያ (Normalized) እየተደረገ ያለው ምንድን ነው?” በሚል ጠይቀው በመልዕክቱ ስር አስቀመጠዋል።
“የሕዝቡን ክብር ከሚነፍግ አገዛዝ ጋር እጅ መጨባበጥና ፎቶ መነሳት መረጋጋትን አይፈጥርም፤ ይልቁንም ለጭቆናው ሕጋዊ ዕውቅና የመስጠት ያህል ነው። የአውሮፓ ህብረት ስለ ሰብዓዊ መብቶች መከበር ከልብ የሚጭነቅ ከሆነ ፣ ይህንን እንደ ተራ ወይም መደበኛ የሥራ ግንኙነት መመልከቱን ማቆም አለበት። እውነተኛ ውይይት የሚጀምረው በተጠያቂነት እንጂ ወንጀልን በማድበስበስ አይደለም። ከዚህ ውጭ ያለው ሁሉ ሃፍረት ነው የሚሆናባችሁ። ምክንያቱም በፍርሃት ላይ የተገነባ መረጋጋት መቼም ቢሆን ዘላቂ ሊሆን አይችልም” የሚለው ተቃውሞ ቀዳሚው ነው።
በኤርትራ ያለውን የፕሬዚዳንት ኢሳያስ መንግስት በመቃወም ትችታቸውን ያሰፈሩት ወገኖች መንግስታቸውን ይገልጻል የሚሉ በርካታ ልብ የሚነኩ ምስሎችን አሳይተዋል።
ዶ/ር አኔት ዌበር እና ቡድናቸው ወደ ኤርትራ ያደረጉት ጉዞ በቀይባህር፣ በየመን ሁቲ እና በሱዳን ቀውስ ዙሪያ ኤርትራ የምታደርገውን ተሳትፎ እንድታቆም ለማሳሰብ እንደሆነ ጉዳዩን የሚከታተሉ ዲፕሎማቶች ይናገራሉ። በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ የተጀመረው ጦርነት ካስከተላቸው በርካታ ቀውሶች በመነሳት የኤርትራ መንግስት ለየመን ሃውቲዎች የሎጅስቲክና መሳሪያ ማስተላለፊያ በመሆኑ፣ በሱዳን የዕርስ በዕርስ ጦርነት ሰፊ ተሳትፎ ስላለው ይህን እንዲያቆምና በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጥብቅ መመሪያ እንደተሰጠው እነዚህ ወገኖች ይናገራሉ።
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከትህነግ ጋር የፈጠሩት ጥምረት ጦርነት ከተነሳ አካባቢውን ወደ ከፋ ቀውስ ስለሚከተው፣ ጣጣው አውሮፓንም ስለሚያናጋ፣ የኤርትራ መንግስት ጣልቃ ገብነቱን አቁሞ በጠረጴዛ ዙሪያ ልዩነቶችን ለማስወገድ እንዲሰራ ድጋፍ እንደሚደረግለት የአውሮፓ ህብረት ልዑካን ማስገንዘባቸውም ታውቋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኤርትራ ውስጥ በሲቪል ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ የጥቃቶች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ፣ ያለ አንዳች የፍርድ ቤት ውሳኔ የታሰሩ ባስቸኳይ እንዲፈቱ ጥሪ በንግግሩ ወቅት መነሳቱም ተሰምቷል። በትግራይ ጦርነት ወቅት በከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተከሰሰው የኤርትራ መንግስት፣ ከዚህ ተግባሩ እንዲታቀብ፣ በጎረቤት አገራት ጣልቃ በመግባት ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት፣ በማስታጠቀና፣ ጦረነትን ማስፋት ላይ ያለውን ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲያቆም የአውሮፓ ህብረት የአፍሪቃ ቀንድ ተወካይ ማሳሰባቸው ተሰምቷል።
ከሰማኤን ሱዳን ቀጥሎ የኤርትራ መንግስት ለየመን ህውቲዎች ከኢራን መሳሪያ ሲላክ የሚያቀባብል እንደሆነ በተደጋጋሚ መረጃ እንድተገኝበት ሲዘገብ መቆየቱ ይታወቃል። አውሮፓ ህብረት የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባርንና የኢትዮጵያን መንግስት በተለያዩ ጉዳዮች የማስማማት ስራ እየሰራ ባለበትና በበርካታ ጉዳዮች እየተስማሙ መሆኑ በሚገለጽበት ወቅት ኤርትራ መሄዱን የፖለቲካ ተንታኞች አቅልለው አያዩትም።
ዌበር በግርድፉ በቀላል የዲፖሎማሲ ቋንቋ ውይይቱን አድንቀው መኤክስ ገጻቸው መጻፋቸውን ተከትሎ በርካታ የኤርትራ ተወላጆች፣ የተቃወሙት ከዲፖሎማቷ የሚገሳ መልዕክት ጅርባ ያለውን መልዕክት ካለመረዳት እንጂ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝና ቀጠሮ የታሰሩ፣ በሃይማኖት ሳቢያ እስር ቤት የገቡ እንዲፈቱ፣ የሃሳብ ነጻነት እንዲፈቀድ፣ የዴሞክራሲ ፍሬዎች ለኤርትራ እንዲለቀቅ የመሳሰሉ ጥብቅ ትዕዛዞች ሕብረቱ ማስተላለፉ ታውቋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአስቸኳይ እንዲተገበሩ ከታዘዙት ውስጥ በጎረቤት አገር ያለውን ጣልቃ ገብነትና የሰብኢ መብቶችን የማያከብር ከሆነ ቀጣይ እርምጃዎች ይፋ እንደሚሆኑም ዲፕሎማቶች አመልክተዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm
“አምባገነናዊ ሥርዓት አገዛዝ ላይ የሚቆዩት በዚህ መንገድ ነው፤ አገር ቤት ሕዝብ ይጨቁናሉ፤ በውጭው ዓለም ልክ እንደ ሌሎች መንግስታት መስለው ይታያሉ። ይሁን እንጂ ባለሥልጣናቱ እጅ ለእጅ በሚጨባበጡበት ወቅት፣ የኤርትራ ሕዝብ ድምፅ አልባ ነው፤ መብት የለውም። ተስፋ ቢስ ሆኖ ቀርቷል። ይህ ዲፕሎማሲ አይባልም። ይህ በኤርትራ ውስጥ ያለውን እውነታውን መካድ ነው” ስትል ሃናን በአኔተ ዌበር አስተያት ስር ተቃውሞን በምስልና በማስረጃ በማስደገፍ ካቅረቡት መካከል አንዷ ናት። ሃና ለተቃውሞዋ ማስደገፊያ ያቀረበችው ምስል ይህ ነው።







