“ጉድ አንድ ሰሞን ነው” ሶማሌላንድ እና “ጥቅምን” መሰረት ያደረገው ጩኸት፣ ጎራ የለየው የፕሮፓጋንዳ ትርክትና ዘመቻ

Date:

አዲስ ሪፖርተር – “ጉድ አንድ ሰሞን ነው” የዘመናችን የዓለም መዝሙር ነው። ጉልቤዎቹ ያሻሸውን ለማድረግ ይወስኑ እንጂ የሚለወጥ ነገር የለም። ዛሬም ሶማሌላንድ አገር ሆና እንድትሞሸር በጓሮ ያለቀ ጉዳይ ላይ የሚሰማው ጩኸትና ዘመቻ በተለይ ከኤርትራ፣ ከጅቡቲና አንድ ጎሳ ብቻ ከሚደግፋቸው፣ ውና ከተማቸው ውስጥ እንኳን መዘዋወር ከማይችሉት ፕሬዚዳንት ሃሰን ሼኽ መሰማቱ ጩኸቱን “ጉድ አንድ ሰሞን ነው” ከመሆን እንደማያልፍ የዓለምን ተሞክሮ የሚያጤኑ ይናገራሉ።

በዲሴምበር 26 ቀን 2025 እስራኤል ለሶማሌላንድ ግዛት እውቅና ከሰጠች በኋላ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራትን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚሰነዘረው ተቃውሞ ተጠናክሯል። የአፍሪካ ህብረት(AU) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (IGAD) ጋር በመሆን “በአህጉሪቱ መገንጠልን ያበረታታል” በሚል ስጋት ውሳኔውን አውግዘዋል። ቆየት ብሎም የአውሮፓ ሕብረት የድምጹ ይዘትና አጯጯሁ ቢለያይም አንጎራጉሯል። የተባበሩት መንግስታት ተጠጥታው ምክር ቤትም ስብሰባ እንደሚቀመጥ ተመልክቷል። ዓለም እንዴት እንደምትመራ የገባቸው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ንግግርም እየተቀሱ ነው። በአንድ ወቅት “ነገር ሲያልቅ፣ ጉዳይ ሲያከትም የማይገባቸው” ሲሉ ለአገር ውስጥ ፖለቲከኞች የተናገሩትን!!

እነዚህ በተለያየ የአህጉሪቱ ክፍል ያሉ ሀገራት፥ “ለሶማሊያ ተቆርቋሪ ነን” ከሚለው የማስተባበያ የአቋም መግለጫ በስተጀርባ የሶማሌላንድ ሀገር መሆን በቀጠናው የሚያመጣውን ኢኮኖሚያዊ ለውጥና እና እነርሱ የሚቀርባቸውን ጥቅም ሰፋ አድርጎ መመለከት የጩኸቱን ምክንያት የፍትህና ርትዕ ጉዳይ እንዳልሆነ ያሳያልና እንዳሰው።

ግብፅ

የሶማሌላንድ ግዛት ሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና እንደተሰማ በሰዓታት ልዩነት የአቋም መግለጫ ለማውጣት እና ሀገራትን ለማስተባበር ግብፅን የቀደማት አልነበረም።

በኢትዮጵያ ቀጠናዊ እና ድንበር ተሻጋሪ ግጭቶች ላይ በእጅ አዙር ገብታ ስትፈተፍት ለኖረችው ግብፅ ግን የጭንቀቷ መንስኤ ሶማሊያ፣ ሶማሌላንድ ወይም ፍትህ አልነበረም።

እውቅናው ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ መደበኛ ደረጃ በማሳደግ የቀይ ባህር መዳረሻ የሆነውን የመግባቢያ ስምምነት እንድታጠናክር ያስችላታል። ወይም “ቀይ ባህር ላይ ድርሽ እንዳትይ” ተብላ አድማ የተመታባት ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር ለዚያውም ጉሮሮው ላይ ጉብ የማለቷ ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያን በመከረኛው አባይ ሳቢያ ከባ አሳር እያሳየች ያለቸው ግብጽ ሰሞኑን በአሰብ ወደብ ላይ ለመነገድ በሚል ከኤርትራ፣ በጅቡቲም በተመሳሳይ ወደብ መገናባት በሚል የማይተገበር ውል ፈጽማ እያጯጯኸች ባለችበት ሁኔታ የሶማሌላንድ የአገርነት ዜና ፖለቲካዊ ውልቃት ሆኖባታል።

የግብጽን አካሄድ የሚረዱ ምንም እንኳን ውሉ የጨበጣና ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ አስገዳጅ ስምምነት እንድትፈርም ጫና ለማሳደር ያደረገችውን ሩጫ ቢሆንም እስራኤል ያፈነዳችው ዜና ሁሉንም በዜሮ የሚያባዛ እንደሆነ የሚናገሩ፣ አትላንቲክ ካውንስል ያነሳውን አሳብ በመጋራት ነው።

አዳዲስ የገቢ ምንጮችን በማመንጨት እና በነባር ኮሪደሮች ላይ ጥገኝነትን በመቀነስ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እንደሚደግፍ የተነገረለት የበርበራ ወደብና የሃያ ኪሎሜትር የባህር በር ጉዳይ፣ ፍትሃዊ ባልሆነ አግባብ ኢትዮጵያዊያን አጥተውት የነበረውን የቀጠናው የበላይነት ይመልሳል። ይህን ግብጽ ከማንም በላይ ስለምትረዳ ጥቅሟን አስልታ መቃወሟ ከአፈጣጠሯ አንጻር የሚገርም እንደማይሆን በዘርፉ ልምድ ይላቸው የሚስማሙበት ሃቅ ነው። አብይ አሕመድ “የምናደርገውና ልናደርግ ያሰብነው የሚገባቸው ጥGእላቶቻችን ናቸው” ያሉትን እዚህ ላይ ማንሳት አግባብ ይሆናል።

የኢትዮጵያ የባህር ሃይልን መልሶ ማጠናከር እና የባህር በር ባለቤት መሆን ለኢኮኖሚ ዕድገቷ፣ በተለይም ግብፅ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ድንበር በሚጋሯት አገራት በኩል ስታሳድር የነበረውን ጫና በእጅጉ እንደሚቀንስ አትላንቲክ ካውንስል ይህንኑ አስመልክቶ ያሰፈረው ጽሁፍ ያስረዳል። አትላንቲክ ካውንስል የአሜሪካ የፖሊሲ ጥንስስ መነሻ ጉዳዮች ተፈጥተው፣ ተቦክተው የሚጋገሩበት ተቋም መሆኑን ለሚረዱ ፅሁፉ ዝም ብሎ ለማለት የሚባል እንዳልሆነና ጉዳዩ ውስጥ የውስጥ ምክክር እንዳለ የሚያሳብቅ ነው።

ጅቡቲ

ጅቡቲ ከሶማሊያ እና ግብፅ ጋር በመሆን እውቅናውን የተቃወመች ሌላኛዋ ሀገር መሆኗ ይታወቃል። አምስት መቶ ሺህ ቋሚ ነዋሪ ያላትና የዕለት ጉርሷን ከኢትዮጵያ የምትሸምተው ጅቡቲም እሪታዋ ኢትዮጵያን እያለብኩ ልኑር እንጂ ሌላ ምንም ምክንያት ኖሯት አይደለም።

የ2024 የIMF ሪፖርት እንደሚያሳየው በባብ ኤል-ማንደብ ስትራቴጅያዊ ቦታ ላይ የምትገኘው ትንሿ ሀገር ጅቡቲ ከ95% በላይ የአዲስ አበባን ገቢ እና ወጪ ንግድ በማስተናገድ የኢትዮጵያ ዋና የባህር በር በመሆን በማገልገል ኢኮኖሚዋን በከፍተኛ ሁኔታ ትደግፋለች።  

እንደ ኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ ኢትዮጵያ ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ለወደብ ክፍያ ብቻ ለጅቡቲ ኢኮኖሚ ተገፈግፋለች። ይህ ክፍያ የቀን ተቀን ኪራይ፣ የሆቴሎች ገቢዎችንና ቀረጥን አያካትትም።

የሶማሊላንድ እውቅና መስጠቱ የኢትዮጵያ-ሶማሊላንድን የመግባቢያ ስምምነት በማፅደቅ በርበራን እንደ አማራጭ ወደብ እንድትጠቀም ያስችላታል።

ኢትዮጵያ 30 በመቶውን ጭነት እንኳን ወደ በርበራ ብታዞር ጅቡቲ ከፍተኛ የሆነ የገቢ እጥረት ሊገጥማት ይችላል፥ ይህም እንደ አዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር አይነት በቻይና ፋይናንስ የሚደረጉ ፕሮጀክቶች ላይ የዕዳ ጫናዋን ያባብሳል። እናም ጅቡቲ ጩኸቷ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዲሉ ነው።

ኤርትራ

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ዲሴምበር 28, 2025 እስራኤል ለሶማሌላንድ እውቅና መስጠቷን ክልላዊ ቀውሶችን ለማነሳሳት የታሰበ ተንኮል ስትል ማውገዟን አሳውቃለች።

እስራኤል ለሶማሌላንድ የሰጠችው እውቅና የ2024 የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ ስምምነትን በማፅደቅ የኤርትራን ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታ የሚሸረሽር ሲሆን ይህም ለኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን እንደ አማራጭ የባህር መስመር ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ይህም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ፉክክር ስትጠቀምበት የነበረውን የአሰብ ወደብን ስልታዊ ጠቀሜታ ይቀንሳል።

ኢትዮጵያ የኤርትራን ግዛት አቋርጣ አስተማማኝ በሶማሌላንድ በኩል የቀይ ባህር መስመር ላይ ከሰፈረች ኤርትራ በአፍሪካ ቀንድ የንግድ እንቅስቃሴ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የመደራደር ኃይሏን እና አጠቃላይ ቀጣናዊ ተሰሚነቷን ይከስማል። ይህ ደግሞ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው፣ “ሰዓት የቆመባት” የምትባለውን ኤርትራን የኋልዮሽ ጉዞ ከነበረው ያፈጥነዋል። ምን አልባትም አሁን ላይ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ሲሉ የሚጠቀሙባት አገራትም ጥቅማቸውን በኤርትራ በኩል ማግኘት ስለማይችሉ አብረዋት ማዝገማቸውን ያቆማሉ። ይህ ነው የኤርትራ ጩኸት ሚስጥርና ዕውነታ!!

የአል-ሸባብ አቋም

የፍራንስ 24 ዘገባ እንደገለፀው የሶማሊያው ታጣቂ ቡድን አልሸባብ ለተገነጠለው ግዛት እውቅና መስጠቱን ተከትሎ እስራኤል “የሶማሌላንድን የተወሰነ ክፍል ለመጠየቅ ወይም ለመጠቀም” የምታደርገውን ማንኛውንም ሙከራ እንደሚቃወሙ ገልፀዋል። አልሸባብ በመግለጫው ውሳኔውን “አንቀበለውም እና እንዋጋለዋለን” ሲል አስጠንቅቋል።

የሶማሊላንድ ዕውቅና ማግኘቷ የአሸባሪውን ቡድን ወደ ሰሜን አቅጣጫ መስፋፋት ከመግታቱም ባሻገር በኢትዮጵያ ፣ በእስራኤል እና በምዕራባውያን ኃያላን ሀገሮች መካከል ጠንካራ የፀረ ሽብርተኝነት ጥምረት እንዲኖር ያደረጋል። ይህ ደግሞ ሲወለድ ጀምሮ በጂሃድ እሳቤ ዓለምን ለተዋወቀው አሸባሪ ድርጅት መርዶ በመሆኑ ተቃውሞው ከዜና ያለፈ ቀልብ ሊስብ አልቻለም።

ከነዚህ ሀገራት በተጨማሪም ጆርዳን ፣ ሳዑዲ አራቢያ ፣ ኳታር ፣ ኩዌት ፣ ኢራን እና ኢራቅ እንዲሁም ናይጄሪያ እና ፓኪስታንን ጨምሮ በርካታ ሀገራት የሶማሌላንድን ሉዓላዊነት አጥብቀው ቢቃወሙም የእስራኤል ድፍረት የተሞላበት እውቅና በአሜሪካ መንግስት ከበስተጀርባ የተደገፈ እንደመሆኑ የሀገራቱን የፕሮፓጋንዳ ትርክት ስር የሰደደ ለውጥ እንዳያመጣ ያደርገዋል። ይህ ጥቅምን ያሰለ ጩኸት ሶማሌላንድን ሉዓላዊ መሠረት ያላት አገር ከመሆን እንደማያግዳት የበርካቶች እምነት ነው።

እንደ መውጫ

የሶማሌላንድ አገር መሆን መበጣጠስ የሚደገፍ ባይሆንም፣ በጀማ ለታነቀችው ኢትዮጵያ ብስራት ነው። ኢትዮጵያዊያን በየትኛውም ዓይነት የፖለቲካ እሳቤ ውስጥ ያሉ ሌሎች ብሄራዊ ጥቅማቸውን አስልተው እንደሚያደርጉት አቋም ሊይዙ እንደሚገባ ይታመናል። አገር፣ ብሄራዊ ጥቅምና የወደፊቱን ትውልድ አስቦ መራመድ አግባብ እንደሚሆን አሁን አሁን ለኢትዮጵያዊያን ነጋሪ አያስፈልጋቸውም።

ኢትዮጵያን ዛሬ ድረስ ዋጋ ያስከፈላት፣ እያስከፈላት ያለውና ቡና ሸጣ የሰበሰበችውን ለጅቡቲ እየገበረች እንድትኖር በፈረዱባት “መሪዎቿ” ያጣችውን የቀጣናውን የፖለቲካና የኃይል የበላይነት የምታስመልስበት ዘመን ላይ እንደሆነች መረዳትና ላልገባቸው ማስረዳት የሁሉም ኃላፊነት ነው።

እናም ይህ “ጉድ አንድ ሰሞን ነው” የተተረተለትን የሶማሌላንድ አገርነት ዜና ተከትሎ ጎራ ለይቶ የሚጮኸው ጩኸት ከራስ ጥቅም የመነጨ፣ ፍትህና ርትዕን የማያዋልድ፣ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው የሚዘፍኑት ዘፈን በመሆኑ ጉልበተኞቹን ከውሳኔያቸው ፈቀቅ እንደማያደርግ ይታመናል።

ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

የኤርትራ አፋር ተቃዋሚ ድርጅቶች ግንባር ፈጠሩ፤ “ስምምነቱ ለሻዕቢያ አስደንጋጭ መርዶ ነው” አቶ አብዲ ሼኽ መሐመድ

አዲስ ሪፓርተር - በኤርትራ የሚንቀሳቀሱት ሁለት የአፋር ተቃዋሚ ድርጅቶች...

ለኢትዮጲያ ሲሉ ቀይ ባሕር ላይ የወደቁት ጀግኖች አደራ ተቀባይ

ኢትዮጵያ ቀይ ባሕር የትናንትና ታሪኬ ኾኖ አይቀርም የሚል አጀንዳዋን...

ሀሰን ሼኽ በመጨረሻ “እኔም የቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት ዕጣ ይደርሰኛል” በሚል ጭነቀት ውስጥ መሆናቸው ተሰማ

አዲስ ሪፖርተር - እስራኤልን ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን ከሶማሊላንድ ጠራርገው...