በአለባቸው ጉብሳ
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በኢትዮጵያ የቴሌኮም ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ “ኤም-ፔሳ ለሁሉም” (M-Pesa for All) መተግበሪያ ጉዳይ ነበር። ሳፋሪኮም የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች የራሳቸውን ሲም ካርድ ሳይቀይሩ ኤም-ፔሳን እንዲጠቀሙ የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ ይፋ ቢያደርግም አገልግሎቱ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል ሊታገድ ችሏል።
ኢትዮ ቴሌኮም ለዚህ ትብብር እምቢተኝነት ማሳየቱ ከንግድ ስትራቴጂ አንጻር የሚጠበቅ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ኩባንያው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ40 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ያፈራውን “ቴሌ ብር” (telebirr) የተሰኘ ግዙፍ የፋይናንስ መድረክ የገነባ በመሆኑ፣ ኤም-ፔሳ በኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ላይ ተጭኖ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ የገበያ ድርሻውን ሊቀንስበት ይችላል የሚል ስጋት ይፈጥራል። በተጨማሪም፣ የሀገሪቱ ትልቁ የቴሌኮም ኩባንያ ደንበኞች መረጃ በሌላ ሀገር ኩባንያ ሲስተም ውስጥ ማለፉ፣ ከብሔራዊ ደህንነት እና ከንግድ ሚስጥር ጥበቃ አንጻር ስጋት ሆኖ ሊቀርብ ይችላል።
የዲጅታል ክፍያ መተግበሪያዎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመሪያ መተግበሪያዎች እርስ በርስ ትስስር መፍጠር ወይም መናበብ (Interoperability) ቢደነግጉም፣ አተገባበሩ ግን በኩባንያዎች መካከል በሚደረግ የሁለትዮሽ ስምምነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ኢትዮ ቴልኮም የገበያ ድርሻውን እና የደንበኞቹን የውሂብ መረጃ ለመጠበቅ ሲል ፈቃደኛ እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል።
የሳፋሪኮም ቅሬታና የፕሬዝዳንት ሩቶ ጉብኝት
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎቴ በኢትዮ ቴሌኮም ቁጥሮች ላይ እንዳይሠራ ታግዶብኛል ብሎ ቅሬታ በማቅረቡ ምክንያት ችግሩን በንግግር ለመፍታት የኬንያ ፕሬዝዳንት ሩቶ ወደ ኢትዮጵያ እንዳቀኑ ትላንት በማህበራዊ ድረገፃቸው ካሰፈሩት መልዕክት መረዳት ይቻላል። ፕሬዝዳንቱ ሳፋሪኮም እና ኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያዎች በቀጠናው በጋራ ስትራቴጂካዊ አጋርነት እና የኢንቨስትመንት ትብብሮችን እንዲፈጥሩ እገዛ ለማድረግ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር ትናንት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል የተደረገው ስምምነት ከግል ኩባንያዎች ፉክክር ባለፈ “ድንበር ተሻጋሪ የዲጂታል ትብብር” ላይ ያተኮረ ነው። ይህም የሚያሳየው የኤም-ፔሳ እና የቴሌ ብር ጉዳይ የቴክኒክ ሽኩቻ ብቻ ሳይሆን፣ የምስራቅ አፍሪካን የኢኮኖሚ ትስስር (Regional Integration) የሚወስን ትልቅ የጂኦፖለቲካ አጀንዳ እንደሆነ መረዳት አይከብድም።
በመሆኑም አዲስ ሪፓርተር ይህ የሳፋሪኮም እና የኢትዮ ቴልኮም ድንበር ተሻጋሪ የዲጅታል ትብብር ለኢትዮጵያ ቴልኮም ኢንዱስትሪ ምን አይነት እድሎችንና ስጋቶችን ሊፈጥር እንደሚችል እንዲሁም ብሄራዊ የደህንነት ስጋቶችን ቀድሞ ለመከላከል መወሰድ ስላለባቸው ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች አግባብነት ካላቸው የሃገራችን ሕጎች እና የአውሮፓ ተሞክሮ አንፃር እንደሚከተለው ለመዳሰስ እንሞክራለን።
የስትራቴጂካዊ ትብብሩ ዕድሎች
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የደረሱበት “ስትራቴጂካዊ አጋርነት” ተግባራዊ መሆን መጀመሩ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ይዞ ይመጣል። ከእነዚህም መካከል ቀዳሚውና ዋነኛው የፋይናንስ አካታችነትን (Financial Inclusion) ማረጋገጥ ነው። በአሁኑ ወቅት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ መደበኛ የባንክ አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነበት ሁኔታ፣ የቴሌኮም ኩባንያዎች ተቀራርበው መስራታቸው ይህንን ክፍተት በከፍተኛ ደረጃ ይሞላዋል። “ኤም-ፔሳ ለሁሉም” የሚለው መርህ ሲተገበር፣ አንድ የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኛ በገጠርም ይሁን በከተማ የሳፋሪኮም ሲም ካርድ ሳይገዛ የኤም-ፔሳን አገልግሎት መጠቀም መቻሉ፣ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱን ያለምንም የኔትወርክ ገደብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ያደርገዋል። ይህም በተለይ ለጥቃቅንና አነስተኛ ነጋዴዎች እንዲሁም የባንክ ቅርንጫፍ በማይደርስባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች ትልቅ የምስራች ነው።
በሁለቱ የቴሌኮም ኩባንያዎች መካከል የሚፈጠረው አጋርነት በገበያው ውስጥ ጤናማ ፉክክር እንዲሰፍንም በር ይከፍታል። እስከዛሬ በነበረው አሰራር ኩባንያዎቹ ደንበኞቻቸውን በራሳቸው መተግበሪያ ብቻ “አጥሮ” የመያዝ (Exclusivity) ዝንባሌ ነበራቸው። ይሁን እንጂ ስምምነቱ ተግባራዊ ሲሆን፣ ፉክክሩ ደንበኛን በሲም ካርድ ከማሰር ይልቅ የአገልግሎት ጥራትን በማሻሻልና የክፍያ ተመኖችን በመቀነስ ላይ ያተኮረ ይሆናል። ይህም ደንበኞች የተሻለ የቴክኖሎጂ አማራጭ፣ ፈጣን የገንዘብ ዝውውር እና አስተማማኝ የዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎት በዝቅተኛ ኮሚሽን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ኩባንያዎቹም ይበልጥ ፈጠራ የታከለባቸውን (Innovative) የብድር፣ የቁጠባ እና የኢንሹራንስ አገልግሎቶችን ለተጠቃሚው ለማቅረብ እንዲሽቀዳደሙና እንዲፎካከሩ ያደርጋቸዋል።
ከሀገር ውስጥ ፋይዳው ባሻገር፣ ይህ ትብብር ለምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር እንደ ትልቅ ሞተር ያገለግላል። በኢትዮጵያ እና በኬንያ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ በኤም-ፔሳ እና በቴሌ ብር መናበብ (Interoperability) ቢታገዝ፣ ድንበር ተሻጋሪ ግብይት እጅግ ቀላልና ቀልጣፋ ይሆናል። ይህም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) ስምምነትን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚደረገውን ጥረት ያፋጥነዋል። በሁለቱ ሃገራት ድንበሮች ላይ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች የገንዘብ ምንዛሬ እና የጥሬ ገንዘብ ስጋት ሳይኖርባቸው በዲጂታል መንገድ ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ በማድረግ፣ ቀጠናዊ የንግድ ትስስሩን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል። ይህ ዓይነቱ ዲጂታል ድልድይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ ባለፈ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ማዕከል ለመሆን ለያዘችው ራዕይ ትልቅ ግብዓት ይሆናል።
ትራብብሩ የሚፈጠረው ብሄራዊ ስጋቶች
የዜጎች የግል ውሂብ ጥበቃ መብት (Data Privacy) በሕገ መንግስት እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሲቪል እና የፓለቲካ ዓለም አቀፍ የቃል ኪዳን ሰነዶች እውቅና ከተሰጣቸው ሰብአዊ መብቶች መካከል አንዱ ነው። ሳፋሪኮም የኢትዮ ቴሌኮምን ደንበኞች መረጃ በመጠቀም አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ይህ መብት እንዴት ይከበራል የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው።
የአንድ ግለሰብ የገንዘብ እንቅስቃሴ፣ የመገናኛ አውታር እና የፍጆታ ሸመታ ባህሪ የሚያሳዩ ውሂቦች በሌላ ኩባንያ እጅ መውደቁ ደንበኛው ሳያውቀው ለተለያዩ የማስታወቂያ ስራዎች (Profiling) ወይም ላልተፈለገ ክትትል እንዲጋለጥ ሊያደርገው ይችላል። ኢትዮጵያ በቅርቡ ያጸደቀችው “የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅ” ቁጥር 1321/2016 መሰረታዊ አላማው ኩባንያዎች የዜጎችን መረጃ ለታለመለት አላማ ብቻ እንዲጠቀሙ ማስገደድ ቢሆንም፣ መረጃው በድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎች ሲያዝ ግን የመቆጣጠር አቅሙን ሊፈታተነው ይችላል።
ከብሔራዊ ደህንነት አንጻር ሲታይ
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የገንዘብ እንቅስቃሴ እና የዲጂታል እንቅስቃሴ መረጃ (Metadata) በአንድ የውጭ ሀገር ኩባንያ ቁጥጥር ስር መሆኑ ከፍተኛ ስጋት ይፈጥራል። ይህ መረጃ በትክክል ካልተያዘ ወይም ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ ቢሰጥ፣ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አዝማሚያ፣ የዜጎችን ስነ-ልቦናዊ ሁኔታ እና ስትራቴጂካዊ እንቅስቃሴዎችን ለመሰለል መንገድ ሊከፍት ይችላል። በተለይም በዚህ በጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረት ወቅት፣ የውሂብ ሉዓላዊነት (Data Sovereignty) የሚባለው ጽንሰ-ሀሳብ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል። መረጃው የሚከማችበት ሰርቨር (Server) ከሀገር ውጭ ከሆነ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በራሱ ዜጎች መረጃ ላይ ያለው የበላይነት ሊዳከም ይችላል።
የንግድ ሚስጥር ጥበቃን በተመለከተ
ኢትዮ ቴሌኮም ለበርካታ አስርት ዓመታት ያፈራውን የደንበኛ መረጃ እና የገበያ ጥናት ለተቀናቃኙ ሳፋሪኮም አሳልፎ መስጠት እንደማለት ሊቆጠር ይችላል። ሳፋሪኮም የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ምን ያህል ገንዘብ እንደሚንቀሳቀሱ፣ በየትኛው ሰዓት ግብይት እንደሚያደርጉ እና የትኞቹን አገልግሎቶች እንደሚመርጡ በዝርዝር ማወቅ ከቻለ፣ እነዚህን ደንበኞች ወደ ራሱ ለመሳብ (Targeted Marketing) ከፍተኛ የንግድ ብልጫ ያገኛል። ይህ ደግሞ በነፃ ገበያ ስም የኢትዮ ቴሌኮምን የንግድ ህልውና አደጋ ላይ የሚጥልና ኢ-ፍትሃዊ የንግድ ፉክክር የሚፈጥር በመሆኑ፣ ኩባንያው ትብብሩን በጥርጣሬ እንዲመለከተው ሊያደርግ ይችላል።
ይህንን ስጋት በአለም አቀፍ ደረጃ ለመቅረፍ የአውሮፓ ህብረት ያወጣው የውሂብ ጥበቃ ደንብ (General Data Protection Regulation) እንደ ትልቅ ማጣቀሻ ይወሰዳል። ይህ ደንብ ማንኛውም ኩባንያ የዜጎችን መረጃ ሲሰበስብ ጥብቅ የሆነ ግልጽ ፈቃድ (Explicit Consent) ከደንበኛው ማግኘት እንዳለበት፣ መረጃው በምን መልኩ እንደሚቀመጥ እና ደንበኛው በማንኛውም ጊዜ መረጃው እንዲሰረዝ የመጠየቅ መብት እንዳለው ይደነግጋል። ከሁሉም በላይ መረጃን ከድንበር ማሻገር (Cross-border data transfer) ላይ እጅግ ጠንካራ ገደቦችን ያስቀምጣል።
ኢትዮጵያም በሳፋሪኮም እና በኢትዮ ቴሌኮም መካከል ያለውን ትብብር ስታስተናግድ፣ እንደ የአውሮፓ ውሂብ ጥበቃ ደንቦች ያሉ ጥብቅ የህግ ማዕቀፎችን በመጠቀም መረጃው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንዲከማች (Data Localization) እና ለታለመለት የክፍያ አገልግሎት ብቻ እንዲውል በማድረግ ስጋቱን መቀነስ ትችላለች።
በጠቅላላ በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል የሚደረገው ትብብር የቴክኖሎጂ አጋርነት ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነት እና የዜጎች መብት ጥበቃ ጉዳይ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን እና የብሔራዊ ባንክ፣ የሳፋሪኮም “ኤም-ፔሳ ለሁሉም” መተግበሪያ የኢትዮ ቴሌኮምን የንግድ ሚስጥር በማይነካ እና የዜጎችን የግል ውሂብ በማይጋፋ መልኩ ስለመስራቱ ጥብቅ ቁጥጥርና የቴክኒክ ኦዲት ሊያደርጉ ይገባል።
የአውሮፓ ሕብረት ተሞክሮ ፣ የውሂብ ጥበቃ ደንብ
የአውሮፓ ህብረት የውሂብ ጥበቃ ደንብ (GDPR) መረጃን ከድንበር ማሻገር ላይ የጣላቸው ጥብቅ ገደቦች፣ ለኢትዮጵያ የውሂብ ሉዓላዊነት እና በሳፋሪኮም-ኢትዮ ቴሌኮም ትብብር መካከል ለሚኖረው የውሂብ ፍሰት እንደ ዋነኛ ማጣቀሻ ሊያገለግሉ ይችላሉ። ደንቡ መረጃን ከድንበር ማሻገር የሚፈቅደው ተቀባዩ ሀገር ወይም ተቋም እንደ አውሮፓ ህብረት ዓይነት እኩል የሆነ የጥበቃ ደረጃ (Adequacy Decision) ማረጋገጥ ሲችል ብቻ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ኩባንያዎች መረጃውን ከድንበር ለማሻገር እጅግ ጥብቅ የሆኑ የውል ግዴታዎችን (Standard Contractual Clauses) እንዲፈርሙ ይገደዳሉ። ይህ መርህ ለኢትዮጵያ ሲተረጎም፣ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ኩባንያ እንደመሆኑ መጠን የኢትዮጵያ ዜጎች መረጃ በኬንያ ወይም በሌላ ሀገር ሰርቨሮች ላይ ከመቀመጡ በፊት፣ የሀገሪቱን የውሂብ ሉዓላዊነት የማይጋፋ መሆኑ በህግና በቴክኒክ መረጋገጥ አለበት።
የኢትዮጵያን የውሂብ ሉዓላዊነት ለማስከበር በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል ሊኖር የሚገባው ዋነኛው ገደብ “የውሂብ አካባቢያዊነት” (Data Localization) ግዴታ ነው። ሳፋሪኮም የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞችን መረጃ የሚያስተናግድበት ሲስተም እና ዳታቤዝ በኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ውስጥ ብቻ እንዲቀመጥ መደረግ አለበት። ይህ አሰራር መረጃው ወደ ውጭ እንዳይወጣ በማገድ፣ የኢትዮጵያ መንግስት እና ተቆጣጣሪ አካላት በማንኛውም ጊዜ መረጃውን የመቆጣጠር፣ የመመርመር እና የዜጎችን መብት የማስከበር የበላይነት እንዲኖራቸው ያስችላል። መረጃው ከድንበር ሳይሻገር በሀገር ውስጥ መቆየቱ፣ በሌሎች ሀገራት ህጎች ጣልቃ ገብነት የኢትዮጵያውያን መረጃ ለሶስተኛ ወገን ወይም ለውጭ ደህንነት ተቋማት ተደራሽ የመሆን ስጋቱን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሰዋል።
በመቀጠልም በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል የሚደረገው የውሂብ ልውውጥ “የአላማ ገደብ” (Purpose Limitation) ሊኖረው ይገባል። ይህም ማለት ሳፋሪኮም ከኢትዮ ቴሌኮም የሚያገኘውን የደንበኛ መረጃ ለታለመለት የፋይናንስ አገልግሎት (ለኤም-ፔሳ ግብይት) ብቻ እንዲጠቀም የሚገድብ ነው። መረጃው ለንግድ ማስታወቂያዎች፣ ለገበያ ጥናቶች ወይም ለተጠቃሚዎች ስነ-ልቦናዊ ትንተና (Profiling) እንዳይውል ጥብቅ የቴክኒክ እና የህግ አጥር ሊበጅለት ይገባል። በተጨማሪም በሁለቱ ሲስተሞች መካከል የሚደረገው የውሂብ ፍሰት በኢንክሪፕሽን የታጠረ መሆን ያለበት ሲሆን፣ መረጃው ከድንበር ተሻግሮ ወደ ሳፋሪኮም ግሎባል ሰርቨሮች እንዳይሄድ የሚከላከሉ የሳይበር ደህንነት ግድግዳዎች (Firewalls) መኖራቸው በገለልተኛ ኦዲተር በየጊዜው መረጋገጥ ይኖርበታል።
በመጨረሻም፣ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል የሚደረገውን የድንበር ተሻጋሪ ውሂብ ፍሰት የሚቆጣጠር “የውሂብ ዝውውር ስምምነት” (Data Transfer Agreement) እንዲፈርሙ ማስገደድ ይኖርባቸዋል። ይህ ስምምነት ሳፋሪኮም በማንኛውም ምክንያት የኢትዮጵያውያንን መረጃ ከሃገር ለማውጣት ቢገደድ አስቀድሞ ከመንግስት ፈቃድ እንዲጠይቅ እና ለተፈጠረው ማንኛውም የውሂብ መተላለፍ (Data Breach) ሙሉ ኃላፊነት እንዲወስድ የሚያደርግ ነው። እንዲህ ዓይነት የአውሮፓ የግል ዳታ ጥበቃ ደንብ መንፈስ የተቀረጹ ጥብቅ ገደቦች መኖራቸው፣ በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል የሚደረገው የቴክኖሎጂ ትብብር የሃገሪቱን ዲጂታል ሉዓላዊነት ሳይሸረሽር ለዜጎች ምቾትን እና ኢኮኖሚያዊ ዕድልን እንዲያመጣ ያደርገዋል።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






