“ … የትግራይ ህዝብ ላይ የደረሰው መከራ በፍፁም አጀንዳዎም አልነበረም” የሚሉት አቶ ገዱ አስመራ ያቀኑት ስለ ትግራይ ሕዝብ ካልሆነ ስለጋሞ ህዝብ ለማውራት ነበር? ወይስ ስለ ስልጢ፣ ከንባታ፣ ሶማሊ፣ ቤኒሻንጉል፣ ኦሮሞ፣ አፋር፣ አማራ፣ ጋምቤላ ህዝብ ወይስ ስለየትናው ማህበረሰብ? ሲሉ ይጠይቃሉ። አክለውም አቶ ገዱ ደብዳቤያቸውን ሲያዘጋጁ ዝግጅት ይጎድላቸዋል ወይም የስደት ብስጭትና አሁን ላይ የሚከተሉት የትግላቸው ሕዝብረት ጫና ፈጥሮባቸዋል ባይ ናቸው።
አዲስ ሪፖርተር – የቀድሞ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የደህንነት አማካሪ የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ እንዲደረግ የሚያሳስብ መልዕክት ይዘው ወደ አስመራ አቅንተው እንደነበር አመኑ። በትግራይ የሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ጉዳይ ዋና አጀንዳ እነደነበር አስታወቁ። በተከያዩ ጉዳዮች የሚታሙት አቶ ደመቀ መኮንን ዝምታ መምረጣቸው አነጋጋሪነቱ እየጨመረ ነው።
ባለፈው ማክሰኞ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በፓርላማ ውሏቸው የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ህዝብና ንብረት ላይ እየፈጸሙት ያለው ወንጀል እየበዛ በመሄዱ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አቶ ደመቀ መኮንን እና ሶስት ስማቸውን ያልጠቀሷቸውን ባለስልጣናት አስመራ መላካቸውን ተናግረው ነበር።
ይህንኑ ተከትሎ በውጭ አገር ያሉ የመንግስት ተቃዋሚ ሚዲያዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የሻዕቢያ ልሳኖች፣የትህነግ ደጋፊ አክቲቪስቶች፣ የሻዕቢያ ባለስልጣን፣ እንዲሁም “ኢትዮጵያዊ ነን” የሚሉ ነገር ግን በቀጥታ ለሻዕቢያ የሚሰሩ የሚታወቁ ግለሰቦችና የዩቲዩብ ባለቤቶች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “ለምን ኤርትራን ነኩ” በሚል አወገዙ። በተለያዩ የሚዲያ አውዶች ጠቅላይ ሚኒስትሩን “ውሸታም” በማለት አጣጣሉ። የወቅቱን የፖለቲካ አሰላለፍ በሚፈቅደው መሰረት ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አድልተው በትግራይ ሕዝብ ላይ ምንም ዓይነት ወንጀል እንዳልተፈጸመ አድርገው ያቀርቡም አሉ።
ይህ ከሆነ በሁዋላ አቶ ገዱ በስደት ከሚኖሩበት አሜሪካ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ አስመራ ልከዋቸው እንደነበር አምነው ሰፊ ደብዳቤ ጻፉ። በደብዳቤያቸው ተራ ቁጥር ስድስት ላይ “በፓርላማ ንግግርዎ ትንሽ እውነታነት ያለው የእኔ ወደ ኤርትራ መሄድ ነው፡፡ ቀኑን በትክክል ለማስታወስ ባልችልም፣ ጥር መጀመሪያ አካባቢ 2013 ዓመተ ምህረት ላይ፣ አንድ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባለስልጣን ይዞ የእርስዎ መልእክት ለፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቅ እንዲደርስ ልከውኝ በማግስቱ ደርሼ ተመልሻለሁ፡፡ የመልእክቱ ጭብጥም በሚከተሉት ሶስት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር” በማለት አስመራ ተልከው መሄዳቸውን አስታውቀዋል።
አቶ ገዱ አስመራ ሲልኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዳልነበሩ ቢገልጹም ወደ አስመራ በተላኩበት ወቅት በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ እንደነበሩ ይፋ ማድረግ ያልፈለጉበትን ምክንያት ሳይጠቅሱ አልፈዋል።
ገዱ አንዳርጋቸው ወደ አስመራ ተልከው ሲሄዱ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ እንዲያደርሱ የታዘዙት መልዕክት በሶስት የትኩረት ጉዳዮች ጨምቀው ያቅርቡ እንጂ፣ የደብዳቤውን ይዘት ቃል በቃል አላኖሩም። ይህንን አስመልክቶ አዲስ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ከፍተኛ ባለስልጣን “ንትርክ ውስጥ መግባት አያስፈልግም። ተልክተው አስመራ መሄዳቸውና የተላኩት በሰብአዊ መብት ጥሰት ጉዳይ መንግስት ያለውን ስጋት ለመግለጽ መሆኑን ማመናቸው ብቻ በቂ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ያሉት ይህንኑ ነው” ብለዋል።
አቶ ገዱ በአስመራ ጉዟቸው ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ ካቀረቡት መልዕክት መካከል “የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አካል የሆነው የሰሜን ዕዝ ጥቃት በደረሰበት ወቅት፣ ሰራዊቱን ተቀብለው ላደረጉለት እንክብካቤ እና ኋላም ለመልሶ ማጥቃት እንዲዘጋጅ ላደረጉልን ወንድማዊ ድጋፍ ለኤርትራ መንግስት እና ህዝብ ምስጋና ማቅረብ” እንደሚገኝበት በደብዳቤያቸው ቁጥር ስድስት ንዑስ ቁጥር አንድ ላይ አስፍረዋል።
አቶ ገዱ ያነሱት በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን የ”ክህደት” ጥቃት አቶ ሴኮ ቱሬ በይፋ በትግራይ ቲቪ በድል ዜናነት ያረጋገጡት፣ በደቂቃዎች ውስጥ የተከናወነ መብረቃዊ ጥቃትና ልዩ ጀብድ ተደርጎ የቀረበ፣ ጦርነቱን አሸንፈው አራት ኪሎ እንደሚገቡ ያመኑ የትህነግ ደጋፊዎች የትህነግን ሰራዊት ያደነቁበት ነበር።
በተቃራኒው ደግሞ “በክህደት” ከተፈጸመው የጅምላ ዕልቂት የተረፉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት እያለቀሱ ሕዝብ ፊት የተፈጸመባቸውን ሲተርኩት በመላው አገሪቱ ቁጣ ተነሳ። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የማይረሳው ይህ አስጀፊ ታሪክ እናት ልጇን መርቃ ለውትድርና እንድትልክ አደረገ። በለውጡ ማግስት ዓለምን ባስደነቀ መልኩ ኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል የነበረው የጸብ መጋረጃ ተቀዶ ስለነበር የአገር መከላከያ በግፈኞች በተኛበት ሲታረድ ከኤርትራ ወገን ለተደረገው ድጋፍ ሕዝብ አመስግኗል። ሕዝብ ያመሰገነው የክህደቱ ሰለባ የሆኑት የአገር መከላከያ አባላት ምን እንደተደረገላቸው በይፋ በመመስከራቸውም ነበር።
በወቅቱ ከጥቃት ያመለጠው የአገር መከላከያ ኃይል ራሱን ዳግም ለማደራጀት ወደ ኤርትራ ሲያፈገፍግ ከኤርትራ በኩል የተደረገውን አቀባበል ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ እንዲሁም መንግስት በይፋ እንዲያመሰግኑ አስገደደ። ውለታውም የማይረሳ መሆኑን መንግስት በሰነድ ማስታወቁን ተከትሎ አሁን በተቃውሞ የተሰለፉትን ሚዲያዎች ጨምሮ በስፋት መዘገባቸው የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው።
በዚህ መነሻ መንግስትም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል በይፋ የተባለውን ጉዳይ በደብዳቤ አስፍረው አቶ ደጉ እንዲያደርሱት በዋናነት ማስተላለፍ ለተፈለገው ቁም ነገር ማስደገፊያ ቢያደርጉት ከአሰራ አንጻር የተለመደ መሆኑን የአቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ደብዳቤ ያዩ ተናግረዋል። “በምስጋና ወይም በበጎ ጎን በመጀመር ዋና አሳብን ማስጨበጥ ስልጡን አሰራር ነው” ያሉ አቶ ገዱ ይህን ሲያነሱ ምን ለማለት ፈለገው እንደሆነ እንዳልገባቸው ያስታውሳሉ። እነዚህ ወገኖች አቶ ገዱ “የክር ወይም የማተብ ጉዳይ ከሆነባቸው ወልቃይትን እንዴት አጨብጭበው እነደሰጡ በደብዳቤያቸው ውስጥ አንድ አረፍተ ነገር ቢያክሉ ኖሮ የልቡናቸውን ጻዳት አይተን እናምናቸው ነበር” ሲሉ የስብዕናቸው ጥራት የሚፈትሽ ጥያቄ ጭረዋል።
ገዱ ሌላው ያነሱት ጉዳይ “በወያኔ ላይ በጋራ በወሰድነው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ለድል በመብቃታችን እንኳን ደስ አለህ” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደስታ መግለጫ ለፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ማስተላለፋቸውን ነው። በዋናነት ያነጋገረውና በተለያዩ የፖለቲካ ፍልጎት ታጅሎ ዥንጉርጉር ትርጉም የተሰጠውና አየሩን የያዘው ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ጸቡ ከትህነግ እንጂ ከትግራይ ሕዝብ ጋር አይደለምና ሕዝቡን አትንኩ” በማለት መልዕክት ልከው እንደ ነበር መናገራቸው ነው።
ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ገዱ በደብዳቤያቸው ላይ “አንዳንድ የወያኔ ደጋፊዎች እና የኢትዮጵያን እና የኤርትራን መልካም ግንኙነት የማይፈልጉ የውጭ ሀይሎች፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ሚዲያዎች አማካኝነት ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍተውብናል፡፡ ይህ ነገር ውሎ አድሮ በሁለታችንም ላይ ጣጣ ሊያመጣብን ስለሚችል የጋራ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል” የሚል መልዕክት ይዘው ወደ አስመራ እንደሄዱ ገልጸዋል። ታዲያ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋሹ ማለትን ምን አመጣው?” የሚሉ ወገኖች ሙግታቸው የሚከረው እዚህ ላይ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር የደህንነት አማካሪ ስልጣን አስመራ የሄዱት አቶ ገዱ ቃለ በቃልም ባይሆን ጨምቀው ባቅረቡት መሰረት “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰብአዊ መብት አንጻር ጥንቃቄ እንዲደረግ ማሳሰባቸውን ሲገልጹ ምን ማለታቸው ነው?” በሚል የህግ ባለሙያዎች እየሞገቱ ነው?
አቶ ገዱ ተልዕኮውን ተቀብለው ከመንቀሳቀሳቸው በፊት “ጦርነቱ መጠናቀቁን በይፋ ለህዝብ ተናግረናል፡፡ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እየጠየቀን ያለው የኤርትራ ሰራዊት ከኢትዮጵያ/ከትግራይ እንዲወጣ ነው፡፡ ስለዚህ ለምን የኤርትራ መንግስት ሰራዊቱን እንዲያወጣ በግልፅ አንነግራቸውም?” የሚል አሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ማቅረባቸውን በደብዳቤያቸው ጠቁመዋል። አክለውም ነ”ሰራዊታችሁን አስወጡ ብለህ በፍፁም እንዳትጠይቅ” ሲሉ አብይ አህመድ እንደመለሱላቸው ገልጸዋል። አቶ ገዱ በደህንነት አማካሪነታቸውም ይሁን ከዚያ ቀደም በነበራቸው ከፍተኛ ኃላፊነት በዛን ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከወያኔ ጋር ከሚያደርገው ጦርነት በተጨማሪ ኤርትራን በጉልበት አስገድዶ ሊያደርገው የሚችለው ጉዳይ ስለመኖሩ ዝርዝር መረጃ ቢያቀርቡ ያነሱት ነጥብ ከተራ ሃሜት ይዘልላቸው እንደነበር የሚገልጹ ብዙ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ትግራይ ስለላኳቸው ጉዳይ በደብዳቢያቸው ማብቂያ ላይ ምላሽ የሰጡት አቶ ገዱ አሁን ላይ ከሻዕቢያ ጋር ከተቀናጀው የትህነኛ የፋኖ ኃይል ጋር ስለሚሰሩ ሙሉ ደብዳቤያቸውን መረጃና ማስረጃ ሊቀርበበት በማይችል ሃሜት ማጨቃቸውን ምራቃቸውን የዋጡ አልወደዱላቸውም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ለምሳጣት በዝርፊያ፣ በወንጀል፣ በጭፍጨፋና በአስገድዶ መድፈር ከበቂ በላይ ማስረጃ የሚቀርበበትን ሻዕቢያን ጻድቅ ማድረጋቸው ዳግም ስህተት ተደርጎ በታሪክም እንደሚመዘገብባቸው ጠቁመዋል። አንድ ብወልቃይት ሽያጭ፣ ሁለት በአሁኑ ክህደት!!
ጨረቆስ ኃይሌ የህግ ባለሙያ ናቸው አቶ ገዱ “…የሰብአዊ መብት ጥሰት ክስ ሊያስተከትልብን የሚችለው ጣጣ ነው እንጂ፣ የትግራይ ህዝብ ላይ የደረሰው መከራ በፍፁም አጀንዳዎም አልነበረም” ሲሉ ለጻፉት “ገዱ አሁንም አልበሰሉም። እርጥብ ናቸው” ሲሉ ወርፈዋቸዋል።
“የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂነት ያመጣልና ጥንቃቄ ይወሰድ በሚል አቶ ገዱ አስመራ ሄደው ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ ሲናገሩ አብይ አሕመድ ስለየትኛው ሕዝብ እየተናገሩ እንደሆን ሳይገባቸው ቀርቶ ከሆነ በድን ነበሩ ማለት ነው” የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ “ … የትግራይ ህዝብ ላይ የደረሰው መከራ በፍፁም አጀንዳዎም አልነበረም” የሚሉት አቶ ገዱ አስመራ ያቀኑት ስለ ትግራይ ሕዝብ ካልሆነ ስለጋሞ ህዝብ ለማውራት ነበር? ወይስ ስለ ስልጢ፣ ከንባታ፣ ሶማሊ፣ ቤኒሻንጉል፣ ኦሮሞ፣ አፋር፣ አማራ፣ ጋምቤላ ህዝብ ወይስ ስለየትናው ማህበረሰብ? ሲሉ ይጠይቃሉ። አክለውም አቶ ገዱ ደብዳቤያቸውን ሲያዘጋጁ ዝግጅት ይጎድላቸዋል ወይም የስደት ብስጭትና አሁን ላይ የሚከተሉት የትግላቸው ሕዝብረት ጫና ፈጥሮባቸዋል ባይ ናቸው።

አቶ ገዱ ስማቸውን ካልጠቀሷቸው ጋር አስመራ መድረሳቸውን በደብዳቤ ካስታወቁ በኋላ “ የኤርትራ ባለስልጣናት በአስመራ ኤርፖርት ከተቀበሉን በኋላ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ወደሚገኙበት ቦታ ወስደውን ለፕሬዚዳንቱ የያዝነውን መልእክት አቀረብን፡፡ በያዝነው መልዕክት ላይ ምንም ያወዛግበ ነገር አልነበረም፡፡ የግንኙነቱ ሰው ስለተፈጠረው የሰብአዊ መብት ጥሰት ዘመቻ ለፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ሲነግሩአቸው፣ በበኩላቸው የሰጡኝ መልስ ‘የሚቻለው ጥንቃቄ ሁሉ እንዲደረግ እኛም እናንተም ለበታች መዋቅሮቻችን መመሪያ እናስተላልፍ፡፡ በተረፈ እኔና አብይ በተስማማነው መሰረት ገና ብዙ የሚሰሩ ስራዎች አሉ’ የሚል ነበር፡፡ በሁለቱ መሪዎች ስለሚባለው ስምምነት የማውቀው ነገር የሌለ ቢሆንም ውይይታችንን በሙሉ መግባባት ፈፅመን ወደ አገራችን ተመለስን” ይላሉ።
አቶ ገዱ አሁንም ከአብይ አሕመድ ተልዕኮ ተቀብለው መሄዳቸውን አምነው፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስም ችግሩ መኖሩን መቀበላቸውን ገልጸው፣ “ሁለታችን የተነጋገርነው ነገር” አለ በሚል ህልም መሳይ መረጃ የማይቀርበበት ሃረግ ከመሰንቀራቸው ውጪ መረጃቸው የፓርላማውን ንግግር የሚያጎላ እንጂ ውሸት እንደሆነ የሚያሳይ እንደማይሆን በርካቶች ገልጸዋል።
የህግ ባለሙያው “የሚቻለው ጥንቃቄ ሁሉ እንዲደረግ እኛም እናንተም ለበታች መዋቅሮቻችን መመሪያ እናስተላልፍ” የሚለው ቁልፍ ነገር አቶ ገዱ ስለምን ጉዳይ ወደ አስመራ እንዳቀኑ አስረግጦ የሚያስረዳ ጉዳይ ነውና “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋሹ” ለሚሉት አካላት ሁሉ ሽንፈት ነው። መርዶ ነው።
በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ የተሰማሩ በአብዛኛው “ትናንት እንዲህ ብለህ ነበር” ተብለው ስለማይጠየቁ፣ ሚዲያዎቹም ይህን ስለሚያውቁ ዕለት ዕለት ያሻቸውን እንደ ገበያው ፍላጎት ሲናገሩ መስማትና ማየት የተለመደ መሆኑን የሚገልጹ፣ ሻዕቢያን አውሬ አድርገው በቪዲዮ ሳይቀር ሲናገሩ የነበሩ ዛሬ ተገልብጠው ጻድቅ አድረገው ሲስሉት ማየት አሳፋሪ መሆኑን ይናጋራሉ።
“አሁን ያሉበት የፖለቲካ ሰፈር፣ ቁጭትና ንዴት እየገፋቸው ደብዳቤያቸው ውስጥ እርስ በእርሱ የሚጣላ ጉዳይ ቢሰገስጉም፣ አቶ ገዱ ተልዕኮ ተቀብለው አስመራ መሄዳቸውን ማመናቸው እንደሚያስመሰግናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ‘ዋሽተዋል’ በማለት ለሚከሱ ጥሩ ምላሽ እንደሆነ የገለጹ ጥቂት አይደሉም።
እነዚህን ወገኖች ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሚያነሱት ጥያቄ ግን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የሻዕቢያን ወንጀል ጊዜው ሲደርስ ይፋ ማድረጋቸው ሃጢያት የሆነበት አግባብ ነው። “ሻዕቢያ በትግራይ ምድር ቂሙን ለመወጣት ቀን ይቆጥር ነበር። አጋጣሚ ሲጠብቅ ትህነግ ሻዕቢያ ትግራይ ገብቶ ጥቃት እንዳያደርስ ሲከላከል በኖረው የሰሜን ዕዝ ላይ ቢላ አነሳ፤ ይህኔ ሻዕቢያ ዕልል በቅምጤ ዘፈነ። “ስለቴ ሞላልኝ” ብሎ የመከላከያን እግር እግር እየተከተለ ሲከሰስበት የኖረውን ወንጀል ፈጸም። በመመሪያ በትግራይ እህቶችና እናቶች ማህጸን ውስጥ ብረታ ብረት አኖረ። እንደሚያጠፋቸው የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፎ በማህጸናቸው ውስጥ አስቀመጠ” እንግዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለምን የሻዕቢያን ስም ጠሩ” ተብሎ እስክስታ የሚወረደው እንዲህ ያለውን አረመኔያዊ ቡድን ለመከላከል መሆኑ በርካቶችን አበሳጭቷል። አሳዝኗል።
በኤህአዴግ ታሪክ ለረዥም ጊዜ በቁልፍ የስልታን ወንበር ላይ የኖሩትና የአማራውን ድርጅት በሊቀመንበርነት የመሩት አቶ ደመቀ መኮንን የዛሬውን ጨምሮ በበርካታ ጉፍዳዮች ቢታሙም ወጥተው አለመናገራቸው አነጋጋሪ ከሆነ ሰንብቷል።
ከአማራ ክፍተኛ ባለሃብቶች፣ በተለይም አሁን ላይ በውጭ አገር ሆነው በተለያዩ ደረጃዎች የትጥቅ ትግል የሚደግፉትን የመቅረባቸውን ያህል አግባብተው ወደ ሰላም ለማምጣት ያላቸው ፍላጎት አነስተኛ መሆን ብዙዎችን ደስ አያሰኝም፡፡ የቅርብ ባልደረባቸው የሆኑትና እሳቸው ወደ ፖለቲካው ያመጧቸው አምባሳደር ብናልፍን በመያዝ በአማራ ክልል ሰላም እንዲሰፍን ባለሃብቶቹን አግባብቶ ወደ ሰላም ለማምጣት ከሳቸው የተሻለ እንደሌለ የሚናገሩ በዚህ ጉዳይ ያሉ መምታታቶች ሊጸዱ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ይጠይቃሉ። አዲስ ሪፖርተር በዚህ ዙሪያ ዶክመንታሪ እያዘጋጀች ሲሆን የምትጠብቀው አቶ ደመቀ መኮንን የሚሰጡትን ምላሽ ብቻ ይሆናል።
ባለፈው ማክሰኞ በፓርላማ የተነሳውን የአስመራ ጉዞ አስመልክቶ እንደ አቶ ገዱ ሰፊና ባይሆንም ምስክርነታቸውን ሊሰጡ እንደሚገባ በርካቶች እየጠበቁ ነው። የመንግስት ሚዲያዎችም በዚህ ረገድ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚገባቸው እየተገለጸ ነው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






