የጠቅላይ ሚኒስትሩ “የትግራይን ሕዝብ አትንኩ” መልዕክት እና የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው “የዕምነት ክህደት” ደብዳቤ ሰበዞች

Date:

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስት ግጭት የጀመረው ኢትዮጵያ ሉአላዊ የባህር በር በመጠየቋ ሳይሆን የኤርትራ ጦር በትግራይ ክልል በነበረው ቆይታ የፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና የንብረት ዘረፋ ለማስቆም መንግሥታቸው ባደረገው ጥረት ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል። ይህን የኤርትራ ሰራዊት ሕገ ወጥ ድርጊት ለማስቆም ከወሰዱዋቸው ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎች መካከል በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ወደ አስመራ በመላክ “ሕዝቤን አትንኩ” የሚል ጥብቅ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል። ዛሬ ማምሻውን አቶ ገዱ በስደት ከሚኖሩበት ሃገር በሰጡት ማስተባበያ መልዕክቱ ስለ “ሰብአዊ መብት ጫና እንጂ ስለ ሕዝብ ተቆርቋሪነት አልነበረም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህ የአቶ ገዱ ማስተባበያ ያስታወሰኝ የሀገራችንን ምሳሌያዊ አባባል ነው። “ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” የሚለው ብሂል፣ አንድ ሰው ቃል አባይ ሆኖ የራሱን ስም፣ ክብርና የተናገረውን ቃል ከመካድ አብዝቶ የሚወደውን ልጁን ቢያጣ እንደሚመርጥ አበክሮ የሚያስረዳ አባባል ነው፣ ቃል የእምነት እዳነው እንዲሉ።  አቶ ገዱ ዛሬ ላይ ቆመው ትናንት ራሳቸው አስመራ ድረስ ሄደው የፈጸሙትን ተልዕኮ “ለሕዝብ ታስቦ አይደለም” በማለት ለማጣጣል መሞከራቸው፣ የገዛ ቃላቸውን እያጠፉ እና ታሪካቸውን እየገደሉ መሆኑን ያሳያል። በዚህ የጡረታና የማረፊያ ዘመናቸው፣ እንዲህ ያለ ዓይን ያወጣ ውሸት ለፖለቲካ ትርፍ ሲሉ ሲዋሹ ማየት በእጅጉ ያሳዝናል።

ለማንኛውም ይህን ውሸታቸውን ራሳቸው ከሰጡት ማሰተባበያ አንጻር እስኪ እንመርምረው። ይህም እውነታውን ፍንትው አድርጎ ያሳየናል።

ጠቅላይ ሚንስቴሩ እና አቶ ገዱ በጋራ የሚያምኑት ሀቅ ቢኖር፣ የኤርትራ ጦር ከሕገ ወጥ ድርጊቱ እንዲታቀብና የሰብአዊ መብት ጥሰቱ እንዲቆም የሚያሳስብ መልዕክት ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ መላኩን ነው። ባልተካደ ጉዳይ ላይ ብዙም ማለት አያስፈልግም። ይህን ተልዕኮ ይዘው አስመራ መሄዳቸውን አምነዋልና!!

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በሰጡት ምላሽ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ማዕረጋቸውን መሳሳታቸውን እንደ ትልቅ መከራከሪያ ለማቅረብ ሞክረዋል። እውነት ነው፣ በወቅቱ አቶ ገዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳይሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚኒስትር ማዕረግ የብሔራዊ ደህንነት ዋና አማካሪ ነበሩ። ሆኖም ይህ የሥልጣን ስያሜ ስህተት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉትን ዋና መልዕክትም ሆነ የተልዕኮውን ምንነት በምንም መልኩ አያፈርሰውም። እንዲያውም የብሔራዊ ደህንነት ዋና አማካሪን መላክ ጉዳዩ ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባለፈ ከሁለቱ አገራት ደህንነትና በስፍራው ካለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደነበረው ያረጋግጣል።

አቶ ገዱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ለማስተባበል የሞከሩበት መንገድ ካለባቸው ወቅታዊ የፖለቲካ አቋም አንፃር ሲታይ እጅግ ደካማና ሚዛኑን ያልጠበቀ ነው። አቶ ገዱ ባመስተባበያቸው ላይ እንዳደርስ የተሰጠኝ መልዕክት “አንዳንድ የወያኔ ደጋፊዎች እና የኢትዮጵያን እና የኤርትራን መልካም ግንኙነት የማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ሚዲያዎች አማካኝነት ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍተውብናል። ይህ ነገር ውሎ አድሮ በሁለታችንም ላይ ጣጣ ሊያመጣብን ስለሚችል የጋራ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል” የሚል ነው ብለዋል።  አቶ ገዱ ያመኑት ይህ መልዕክት የሚያስረዳው ጠቅላይ ሚንስትሩ መልዕክታቸውን በስትራቴጂካዊ ቃላት አስረው መላካቸውን ነው።  “ጥንቃቄ ይደረግ” ማለት በስፍራው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና የንብረት ዘረፋ መኖራቸውን አምኖ መቀበልና ሕገ ወጥ ድርጊቶቹ  እንዲቆሙ በይፋ መጠየቅ መሆኑን አቶ ገዱ ሊዘነጉት አይገባም ነበር። ግን ዘንግተውታል። እዚህ ላይ የሚገርመው፣ የሚያሳዝነውና ወደኋላ መለስ ብዬ ካሰብኩ በኋላ አንገቴን ያስደፋኝ በአቶ ገዱ ይህን መሰል አቅም አማራ ክልል መመራቱ፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በእነ አቶ ከተማ ይፍሩ፣ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ወንበር ላይ መቀመጣቸው ነው።

አቶ ገዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለሕዝቡ ተቆርቁረው ሳይሆን ለሥልጣናቸውና ለዓለም አቀፍ ጫና ፈርተው ነው መልዕክቱን የላኩት” በማለት የዓላማ (Motivation) ልዩነት ላይ ትኩረት አድርገዋል። ሆኖም ግን፣ አንድ መሪ የሰብአዊ መብት ጥሰት “ጣጣ ያመጣብናል” ብሎ መልዕክት መላኩ በራሱ ጥሰቶቹ እንዲቆሙ ፍላጎት እንዳለው ያሳያል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ንግግራቸው የገለጹት “ድርጊቱ ይቁም” የሚለውን የመልዕክቱን ዋና ፍሬ ነገር ሲሆን፣ አቶ ገዱ ደግሞ መልዕክቱ የተላከበትን ምክንያት (Context) ላይ በማተኮር የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስብዕና ለመንቀፍ ሞክረዋል። ይህ ደግሞ በፖለቲካዊ ልዩነት ምክንያት የሚመጣ የአገላለጽ ልዩነት እንጂ መልዕክቱ መላኩን የሚክድ አይደለም። በመሰረቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለትግራይ ሕዝብ ባይቆረቆሩ ኖሮ፣ እንዲህ ዓይነት “ጥንቃቄ ይደረግ” የሚልና ለፕሬዝዳንቱ መመሪያ እንዲሰጡ የሚያሳስብ ልዑክ አይልኩም ነበር። መልዕክቱ ባይላክ ኖሮ፣ የኤርትራ ወታደሮች ያለምንም ገደብና ያለ ምንም ተጠያቂነት የፈለጉትን እንዲያደርጉ ፈቃድ እንደመስጠት ይቆጠር ነበር። በመሆኑም ልዑክ መላኩ በራሱ ድርጊቱን ለማስቆም የተደረገ ጥረት መሆኑን ያረጋግጣል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት በአቶ ገዱ ተልዕኮ ብቻ የተገደበ አለመሆኑ ደግሞ የንግግራቸውን እውነተኝነት ይበልጥ ያረጋግጣል። የኤርትራ ሰራዊት ሕገ-ወጥ ድርጊቱን ሊያቆም ባለመቻሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን በተከታታይ ወደ አስመራ በመላክ ድርጊቱ እንዲቆም ግፊቶችን አድርገዋል። ይህ የሚያሳየው “ሕዝቤን አትንኩ” የሚለው አቋም የአንድ ወቅት ስሜት ሳይሆን፣ መንግሥት ለትግራይህ ህዝብ ወይም ለዜጎቹ ደህንነት የነበረውን ጽኑና ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት ነው።

የአቶ ገዱ መግለጫ ትልቁ ድክመት የመልዕክቱን ይዘት ሳይሆን የመልዕክቱን ምክንያት ላይ ማተኮሩ ነው። አንድ መሪ የሰብአዊ መብት ጥሰት “ጣጣ ያመጣብናል” ብሎ ካሰበ፣ ያንን ጣጣ ለመከላከል መጀመሪያ ድርጊቱን ማስቆም እንዳለበት ግልጽ ነው። ስለዚህ “ሕዝቤን አትንኩ” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የመልዕክቱን የመጨረሻ ግብ የሚያሳይ እንጂ አቶ ገዱ እንደሚሉት የቃላት ጨዋታ አይደለም። አቶ ገዱ ዛሬ ላይ ቆመው የትላንቱን ተልዕኳቸውን ለማሳነስ መሞከራቸው ለሕዝብ ከመቆርቆር ይልቅ ለፖለቲካ ትርፍ የታለመ መሆኑን ያሳብቃል።

በሌላ በኩል፣ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የሰጡት ምላሽ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ትልቅ ምስክር ነው። አቶ ገዱ በማስተባበያቸው የጠቅላይ ሚንስቴሩን የጥንቃቄ መልዕክት ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ካስተላለፉ በኋላ ፕሬዝዳንቱ የሰጡት ምላሽ ለበታች መዋቅሮቻችን መመሪያ እናስተላልፋለንየሚል ነው። ፕሬዝዳንቱ ይህን ማለታቸው፣ ጥሰቶቹን ለማረም ቃል መግባታቸውን ያሳያል። ይህ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል የቀረበው “ድርጊቱ ይቁም” የሚል ጥያቄ ምን ያህል ኃይለኛና ፕሬዝዳንቱን ለምላሽ ያስገደደ እንደነበረ ያረጋግጣል። አቶ ገዱ ይህን ግልጽ ምላሽና ውጤት ወደ ጎን በመተው በመልዕክቱ አቀራረብ ላይ ለመከራከር መሞከራቸው በወቅቱ የነበራቸውን ሚና ራሳቸው ዝቅ እንዲያደርጉ አድርጓቸዋል።

አቶ ገዱ በአሁኑ ወቅት በተቃውሞ ጎራ ውስጥ መሆናቸውና በስደት መኖራቸው፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን ጥላቻ ወደ መረጃ ማዛባት እንደወሰዳቸው መረዳት ይቻላል። አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን የነበረ ሰው፣ በወቅቱ የነበረውን አገራዊ ኃላፊነት ዛሬ ካለበት የፖለቲካ ቂም ጋር አላክኮ ለመተርጎም መሞከሩ በታሪክ ፊት ተጠያቂ ያደርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታ ተቋቁመው በአቶ ገዱም ሆነ በአቶ ደመቀ መኮንን በኩል ለኤርትራው መሪ እንዲህ ዓይነት መልዕክት መላካቸው፣ ለትግራይ ሕዝብ ያላቸውን ኃላፊነት የተወጡበት ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ነው።

የአቶ ገዱ በማስተባበያው ላይ “የሰብአዊ መብት ጥሰት ስም ማጥፋት ዘመቻ” የሚለውን ሐረግ መጠቀሙ፣ እርሳቸውም ቢሆኑ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በውጭ ጫና ስም ለመከላከል ሲሞክሩ እንደነበር ያሳያል። ዛሬ ግን ያንን ተልዕኮ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ በመግፋት ራሳቸውን ንጹሕ ለማድረግ መሞከራቸው የግል ጥቅምን ያስቀደመ የፖለቲካ ቁማር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን በግልጽ በፓርላማ ፊት ቀርበው ኃላፊነቱን በመውሰድና የተደረገውን ተከታታይ ጥረት በመግለጽ እውነቱን ለሕዝብ አሳውቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ንግግር በተጨባጭ ማስረጃዎችና በተከታታይ በተከናወኑ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት የሚደገፍ እውነት ነው። አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለማስተባበል የሞከሩበት ጽሑፍም ቢሆን፣ በመሠረታዊነት መልዕክቱ መላኩንና ፕሬዝዳንት ኢሳይያስም ምላሽ መስጠታቸውን ስለማያስተባብል፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ይበልጥ ያጠናክረዋል። እውነት በአቶ ገዱ የፖለቲካ ቃል አባይነት ብትሸፈንም፣ በተለያዩ የልዑካን ቡድኖች በኩል የተከናወኑ ጥረቶች ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሕዝብ ተቆርቋሪነት በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው።

ሰላሙ ዮሐንስ / ነጻ አስተያየት

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related