እንደ “የዘር ፍጅት”፣ “መፈናቀል” እና “የአድዋ ሙዚየም” ያሉ ቃላትን በመደጋገም አንባቢው በአመክንዮ ፋንታ በስሜት እንዲመራ ለማድረግ ሞክሯል። ጀበሉ የመንግሥትን ውሳኔ ከአድዋ መንፈስ ጋር በማጋጨት የሞራል ጫና ለመፍጠር ቢሞክርም፣ የአድዋ ድል ትርጉም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማስከበር ጋር የተያያዘ እንጂ በሌሎች ሀገራት የድንበርና የሰፈራ ጉዳይ ላይ የመንግሥትን የዲፕሎማሲያዊ ምርጫ የሚገድብ የሕግ ሰነድ ወይም ቃልኪዳን አይደለም።
[ይድረስ ለጀበሉ ነጻ አስተያየት]
አህመዲን ጀበል ኢትዮጵያ በእስራኤል ሰፈራ ጉዳይ በጀኔቭ የወሰደችው አቋም ከታሪክ፣ ከፍትህና ከሞራል አንፃር ትክክል እንዳልሆነ በግለፅ ለጠቅላይ ሚንስቴር አብይ አህመድ የፃፈውን ግልፅ ደብዳቤ አነበብኩት። ግሩም ነው። እኔም ለውይይት መነሻ ይሆን ዘንድ በቅን ልቦና የጀበሉን ደብዳቤ ግድፈቶች ከአሁናዊ የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ እና ገቢር ነበብ የውጭ ጉዳይ ፓለቲካ(Realpolitik) አንፃር ለማሳየት እሞክራለሁ።
እነሆ ጀበሉ ይናገራል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መባቻ በኋላ አይሁዳውያንን በሃረርጌ ለማስፈር እቅድ ቢያዝም በንጉሱ ውሳኔ ሳይሳክ ቀርቷል። የሰፈራው እቅድ ቢሳካ ዛሬ ሃረርጌ እንደ ጋዛ ትሆን ነበር በማለት ይደመድማል። እሚገርም ነው። ወዴት ወዴት የሚያስብል አስደማሚ ጉዳይ!
ጀበሉ ያልተገነዘበው ጉዳይ ሁለቱ ኩነቶች በታሪካዊ አውዳቸው ፈጽሞ የተለያዩ መሆናቸውን ነው። የሐረርጌው ጉዳይ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት በተከሰተው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀውስ ሰብዓዊ መፍትሔ ለመፈለግ የቀረበና ያልተሳካ ሙከራ እንጂ፣ እንደ ፍልስጤሙ አሁናዊ የእስራኤል ሰፈራ ለሺህ ዓመታት የሚዘልቅ የታሪክ፣ የሃይማኖትና የርዕዮተ-ዓለም ጥያቄ ያለበት አይደለም። ጀበሉ ሊያነሳው የፈለገውን ጉዳይ ሊሞሽርና ሊያዳምቅበት ካልሆነ በቀር ነገሩ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ መሆኑን ለአንባቢያን ለማመላከት እንጂ እሱ ይህ ይጠፋዋል ብዬ አይደለም።
“ያ ዕቅድ ቢሳካ ኖሮ ዛሬ ሐረርጌ ጋዛ ትሆን ነበር” የሚለው የጀበሉ መደምደሚያ በማስረጃ ያልተደገፈና በግምት ላይ የተመሰረተ ተራ የስሜት መቀስቃሽ ስልት ነው። እንደውም በወቅቱ በናዚ የዘር ፍጅት የደረሰባቸውን እና መጠጊያ ጥላ ከለላ ያልነበራቸውን አይሁዳውያንን ኢትዮጵያ ተቀብላ ብታሰፍራቸው የነጃሽን ታሪክ በመድገም የፍትህና ርትዕ ሃገር መሆኑዋን ዳግም የምታሳይበት ገድል ይሆን እንደነበር ለሚያስቡ ቀና ዜጎች ኢትዮጵያ ጥያቄውን አለመቀበሏ የሚያስቆጫቸው ጉዳይ ነው።
የጀበሉ ሁለተኛው ግድፈት ደግሞ የኢትዮጵያን የጄኔቫ ድምፅ አሰጣጥ ከአድዋ ድልና ከሊግ ኦፍ ኔሽንስ ታሪክ ጋር በማገናኘት ከአውድ ውጭ ለመሞገት መሞከሩ ነው። ጀበሉ፣ አሁናዊና ዘመናዊ ዲፕሎማሲ ከታሪክ ትዝታ ባሻገር ወቅታዊ የሃገር ደህንነትን፣ ስትራቴጂካዊ ጥቅምንና የጂኦ-ፖለቲካዊ አሰላለፍን (Realpolitik) በዋነኝነት ግምት ውስጥ ያስገባል። አንድ ሀገር በዓለም አቀፍ መድረክ የምትሰጠው ድምፅ በታሪካዊ ስሜትና በሞራል የበላይነት (Moralistic Fallacy) ብቻ መመራት አለበት ብሎ ማሰብ የዲፕሎማሲን ጥበብና የሃገራዊ ጥቅምን ሚዛን ካለመረዳት የሚመነጭ ስህተት ነው።
በተጨማሪም አህመዲን በከፍተኛ ሁኔታ ስሜት ላይ የተመሰረተ ተማፅኖ (Appeal to Emotion) ስልትን ተጠቅሟል። እንደ “የዘር ፍጅት”፣ “መፈናቀል” እና “የአድዋ ሙዚየም” ያሉ ቃላትን በመደጋገም አንባቢው በአመክንዮ ፋንታ በስሜት እንዲመራ ለማድረግ ሞክሯል። ጀበሉ የመንግሥትን ውሳኔ ከአድዋ መንፈስ ጋር በማጋጨት የሞራል ጫና ለመፍጠር ቢሞክርም፣ የአድዋ ድል ትርጉም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማስከበር ጋር የተያያዘ እንጂ በሌሎች ሀገራት የድንበርና የሰፈራ ጉዳይ ላይ የመንግሥትን የዲፕሎማሲያዊ ምርጫ የሚገድብ የሕግ ሰነድ ወይም ቃልኪዳን አይደለም።
ሌላኛው ያስገረመኝ ጉዳይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ሥልጣን ካመጣቸው የሃገር ውስጥ ፖለቲካዊ መነሻ (Background) እና ከመሬት ባለቤትነት (አባ ለፉማ) እሴት ጋር የጄኔቫውን ድምፅ በማያያዝ የሞራል ተቃርኖ ለመፍጠር መሞከሩ ነው። እውነት ለመናገር ጀበሉ ያነሳት የመሬት ጉዳይና መሬትን አስመልክቶ የተነሳ አመጽ የሚለውን ሃረግ ሲጠቀም ጃዋር ጥሎለት የሂደውን ማስታወሻ እለት እለት እየደገመ እንደሚያድር ያረጋገጠልኝ ሆኗል። “ይናበባሉ፣ አይነጣጠሉም” ሲባል በገደምዳሜ የሰማሁትን ፍንትው አድርጎ አሳይቶኛል። ወደፊት የምለው ይኖረኛል። ወደ ጉዳዬ ለመልሰ።
ጀበሉ ያነሳው “አባ ለፋ” ጨዋታ በሀገር ውስጥ የሚደረግ የመሬት ጥያቄ ትግልና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረግ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አሰላለፍ ፍጹም የተለያዩ የሕግና የፖለቲካ መድረኮች ናቸው። ማቀንቀን የተፈለገውን ጉዳይ ለማዳመቅ በሚል የመላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ምሬት የወለደው የተቀናጀ ሁሉ አቀፍ ምሬት የወለደውን ለውጥ “ዶሮ ብታልም” ጥሬዋን እንዲሉ ገደል ከቶ የመሬት ጉዳይ አድርጎ ማቅረብ ሲጀመር የጃዋር ደቀ መዝሙርነትህን ዳግም የሚያሳይ ጉዳይ ነው።
ጠለቅ ወዳለው እሳቤ ስንሄድ የአንድን መሪ የግል ማንነት ወይም የበትረ ስልጣን ምንጭ ከሃገር አቀፍ ዲፕሎማሲ ጋር በቀጥታ ማነጻጸር አግባብነት የሌለው ነው። ይህንንም ደፍሮ መፃፉ የሚገርም፣ ሌሎችም በትረ-ስልጣን ለማግኘት ተመሳሳይ ምክንያት ሊኖራቸው ይገባል እንደማለት የሚቆጠር የጃዋር ርዕዮት ነው።
ጀበሉ አሁንም አላቆመም፣ ይጠይቃል። “ኢትዮጵያ ወይ ፍትህን መደገፍ አለባት ካልሆነ ግን ታሪኳን ክዳለች” በሚል ምርጫውን በሁለት ጎራ ብቻ ከፍሎታል። ነገር ግን በዲፕሎማሲ ውስጥ “No” የሚል ድምፅ መስጠት የግድ ድርጊቱን መደገፍ ማለት ላይሆን ይችላል። ይልቁንም ከእስራኤል ጋር ካለው የቴክኖሎጂ፣ የደህንነትና የኢኮኖሚ ትብብር አንጻር የሚወሰን ስትራቴጂካዊ “የጥቅም ሚዛን” ሊሆን ይችላል። ጀበሉ ይህንን ሦስተኛ አማራጭ—ማለትም ብሔራዊ ጥቅምን—ሙሉ በሙሉ ወደ ጎን በመተው ለስሜታዊ ትርክቱ ቅድሚያ ሰጥቷል።
ከዚህም በላይ፣ ደብዳቤው የኢትዮጵያን የፓን-አፍሪካዊነት ታሪክና የኔልሰን ማንዴላን ድጋፍ በመጥቀስ ዛሬ ካለው ሁኔታ ጋር ለማዛመድ ቢሞክርም፣ ወቅታዊው የዓለም ፖለቲካዊ አሰላለፍና የሀገራት ግንኙነት የተቀየረ መሆኑን ግምት ውስጥ አላስገባም። ዲፕሎማሲ በትላንትናው ውለታ ላይ ብቻ የሚቆም ሳይሆን፣ የነገውን የሀገር ህልውናና ጥቅም ታሳቢ የሚያደርግ ሂደት ነው። ደብዳቤው ታሪካዊ ክብርን እንደ ዋነኛ የፖሊሲ መለኪያ ማድረጉ፣ መንግሥት ለሀገር ህልውና ሲል የሚወስዳቸውን ገቢር ነበብ (Pragmatic) ውሳኔዎች ዝቅ አድርጎ እንዲመለከት አድርጎታል።
እንደ መውጫ
የአሕመዲን ጀበል ደብዳቤ የሙግት መነሻ በታሪክ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ብሔራዊ ጥቅም ከታሪካዊ ስሜትና ከሞራላዊ ግዴታዎች ጋር በማጋጨት ረገድ የአመክንዮ ህጸጽ የታየበት ነው። በፖለቲካዊ ሳይንስ እይታ፣ የሀገርን የዲፕሎማሲ ነጻነትና ስትራቴጂክ ምርጫዎች በስሜታዊ ትረካዎች ላይ እንዲመሰረት መሞከር ተገቢነት የለውም። በአሁኑ ወቅት ሃገርን ከዓለም አቀፋዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች እና በሃገራዊ ጥቅሞችን ግምት ውስጥ ባስገባ ዲፕሎማሲ የሚመራ ነው።
ሌላኛው ጀበሉ ያልተረዳው ጉዳይ ኢትዮጵያ ለበርካታ አስርተ ዓመታት በኢስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ለሚታየው ግጭት ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው ሁለቱ አገራት በሰላምና በሉዓላዊነት ጎን ለጎን እንዲኖሩ የሚያስችለው የ”ሁለት መንግስታት” (Two-state solution) አማራጭ መሆኑን በጽናት የያዘችው አቋሟን ነው። ይህ አቋሟ ከዓለም አቀፍ የሕግ መርሆዎች፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድንጋጌዎች እና ከአፍሪካ ሕብረት የጋራ አቋም ጋር የተጣጣመ ነው። አገሪቱ ይህንን ሚዛናዊ አቀራረብ የምትከተለው የፍልስጤምን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በማክበር እና የእስራኤልን ደህንነት የተጠበቀ የመሆን መብት እውቅና በመስጠት ላይ ተመስርታ ነው።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ በቅርቡ (መጋቢት 2026) በጄኔቫ በተካሄደው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ የወሰደችው አቋም የጀበሉን ስጋት ውድቅ ያደርገዋል። ኢትዮጵያ “ለፍልስጤም ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት” በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ (A/HRC/61/L.37) ላይ “YES” (አዎን) በማለት ድምፅ ሰጥታለች። ይህ ውጤት ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ለነበራት ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ አቋም ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጠችበት ነው።
የኢትዮጵያ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት በስሜት ወይም በጊዜያዊ ጫና ሳይሆን፣ በቆየው የሁለት መንግስታት መፍትሔ ፖሊሲዋ ላይ የተቃኘ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ይህም አገሪቱ የፍልስጤምን ሕዝብ መብት እየደገፈች፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከእስራኤል ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የምታስቀጥልበትን ጥበብ የተሞላበት መንገድ ያሳያል። በመሆኑም የጀበሉ ደብዳቤ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እና የጥቅም አሰላለፍ ካለመረዳት የመነጨ መሆኑን ጽሁፉ በግልጽ ያሳያል። እናም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምትረጋግጣቸው ቦታዎችና ልታነሳቸው የምትሞክራቸው አጀንዳዎችን ሳትደክም ገልጽ አድርገህ አቅርባቸው። የማይገናኙ ጉዳዮች እያነሳህ ጨዋዎችን አታስት። ዙሪያውን እየዞርክ ከምትደክም ፍላጎትህን ግለጽ አድርግ!!
ዝግጅት ክፍሉ፣ ይህ ጽሁፍ የጸሃፊው አስተያየት ብቻ ነው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






