“አቶ መለስ ቅድስት ስላሴ ከቆመው ከመቃብራቸው በላይ ጎልቶ የሚነበበው ታሪካቸው ኢትዮጵያን ሆነ ብለው የባህር በር አልባ እንድትሆን ሃፍረትን ጌጥ አድርገው የወሰኑት እርምጃ ነው” በማለት በዘመነ “ውህዳን” የትህነግ የመበላላት ዘመን በተከታታይ “ጓዶቻቸው” ሲገልጹት የነበረው ሰነዳቸው ያስረዳል። በወቅቱ በትህነግ አመራሮች መካከል ተነስቶ በነበረው አለምግባባት ብዙ መሰማቱ በርካቶች ያስታውሳሉ። ልዩነቱ በአቶ መልሰ አሸናፊነት ቢጠናቀቅም ሕዝብ ጆሮ የደረሱ፣ ለሰነድነት የበቁ በርካታ አስገራሚ መረጃዎች ዛሬ ድረስ አየር ላይ አሉ። የመለስ ሴናዊ በዚያ ደረጃ የሚመሯትን አገር መጥላትና ታሪክ አልባ ማድረግ ከምን የመነጨ እንደሆነ በርካቶች በገባቸው መተን ሲያስታውቁም ነበር።
“መለስ ግን በዚህ ደረጃ ለምን ተገረደዱ” በሚል ለእሳቸው ቅርብ የሆኑ ሰው ጥያቄ ቀርቦላቸው ” ትግራይ አገር ስትሆን አሰብን ከኢትዮጵያ ከመውሰድ ከኤርትራ መውሰድ ይቀላል” በሚል ከውሳኔያቸው በፊት እንደነገሯቸው መስማታቸውን የገለጹት ከሳቸው ጓዶች መካከል አንዱ የነበሩ ሲሆኑ ዘመኑ በህንፍሽፍሽ ወቅት ነበር።
ጠቅላይ ሚንስቴር ዐብይ አሕመድ በማክሰኞው የፓርላማ ንግግራቸው የሕዝብን ቀብ የሳቡ በርካታ ጉዳዮችን ቢያነሱም፣ ኢትዮጵያ እንዴት እንደተቆመረባት በግልጽ ያስረዱበት አግባብ የአቶ መለስን ታሪካዊና ትውልድ ይቅር የማይለውን ታሪክ ያስታወሰ ሆኗል።

ኤርትራ ከእናት ሃገሯ ኢትዮጵያ “በሕዝበ ውሳኔ” ስትገነጠል በኢትዮጵያ መንግስት እውቅና እንዴት እንደተሰጠ የሚያሳይ የካቢኔም ሆነ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃለ ጉባኤ ወይም ሌላ የቪድዮም ሆነ የፅሁፍ ማስረጃ ሊገኝ እንዳልቻለ እና ሂደቱ በራሱ ችግር የነበረበት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይፋ ሲያደርጉ፣ ” ታዲያ ውሳኔውን ማን ወሰነ? እንዴጽ ተከናወነ?” የሚለው ጥያቄ ይነሳል። ይህንኑ ተከትሎ በርካታ ዜጎች ጉዳዩን ዳግም መወያያ አድርገዋል። መዛግብትም ያገላበጡና የመረመሩ ጥቂት አይደሉም።
በዚህ ታላቅ “ሃፍረት የነገሰበት” ጉዳይ ዙሪያ የተፃፉ መረጃዎችን አገላብጠው መረጃ የላኩልን እንዳሉት ። የአምባሳደር ጥሩነህ ዜና ግለታሪክ የሆናውን “የዲፕሎማሲ ፋና” የተሰኘውን ድንቅ መፅሃፍን ድንቅ መረጃ ይዟል።
አምባሳደሩ ለንባብ ባበቁት ግለታሪካቸው፣ ኢትዮጵያ ለኤርትራ ነፃ ሃገርነት እውቅና ስለሰጠችበት ሁኔታ ሲገልፁ “እጅግ አሳፋሪና አወዛጋቢ ነበር” ይላሉ ፡፡ “ውዝግብ ፈጣሪው የአቶ መለስ ዜናዊ ደብዳቤ” በተሰኘው ንዕስ ርዕስ ስር ባሰፈሩት ፅሁፋቸው ( ገፅ 133 ይመለከቷል)።
አምባሳደሩ በወቅቱ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ የኢትዮጵያ ልዑክ ሆነው ከሌሎች የሚስዮኑ አባላት ጋር ተሳትፈዋል።
በጉባኤው ወቅት የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን “አሳፋሪና መሪ ያጣ” ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ ዋነኛ ምክንያት የነበረው፣ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ለተመድ “ኤርትራ ነፃነት እውቅና እንድታገኝ የድጋፍ ደብዳቤ መጻፋቸው” ነው ይሉናል። ይህ ደብዳቤ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ክብር የነካና በወቅቱ የነበሩትን ዲፕሎማቶች ክፉኛ ያበሳጨ ነበር።
ይህን መፅሃፋቸው ላይ የገለፁትን የዲፕሎማሲ ውርደት እና አንድምታ እንደሚከተለው በፈርጅ በፈርጅ ቀርቧል።
የውዝግቡ መንስኤ እና ይዘት
አሳፋሪው ደብዳቤ የተጻፈው ኤርትራ ነጻነቷን አውጃ በተመድ እውቅና እንድታገኝ ግፊት ይደረግ በነበረበት ወሳኝ ወቅት ሲሆን የሚከተሉት አንድምታዎች ነበሩት።
የአገርን ብሄራዊ ጥቅም መካድ:- ማንኛውም ሉዓላዊ አገር የራሱ አካል የነበረ የግዛት ክፍለ ሃገር ተገንጥሎ ዓለም አቀፍ እውቅና ሲያገኝ “በግንባር ቀደምትነት መቃወም” ሲጠበቅበት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት (በአቶ መለስ ደብዳቤ አማካኝነት) ” ደጋፊ ሆኖ መቅረቡ” የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ የመስጠት ተግባር ተደርጎ እንደሚቆጠር እንደሆነ አምባሳደሩ ገልፀዋል።
ከአፍሪካው አቋም መውጣት:- ጽሑፉ እንደሚጠቁመው፣ በወቅቱ “አብዛኛው የአፍሪካ አገሮች” የኤርትራ ነፃነት በተመድ እውቅና እንዲያገኝ “አልፈለጉም” ነበር። የአቶ መለስ ደብዳቤ ኢትዮጵያን ከጎረቤት እና ከወንድም አገሮች አቋም አውጥቶ በምዕራባውያን አገሮች (በአሜሪካ አስተባባሪነት) ከሚመራው የድጋፍ ዘመቻ ጎን እንድትሰለፍ አድርጓታል።
የልዑካን ቡድኑ ውርደት:- በጉባኤው ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ልዑክ ሁኔታ “አሳፋሪና መሪ ያጣ” መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ደብዳቤው ያስከተለው የሞራል ዝቅጠት በልዑኩ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። በተለይም የቀድመ ልምድ የነበራቸው አቶ ኃይለማርያም የፖለቲካ ሥራዎቹን ለጁኒየር ዲፕሎማቶች ትተው “ገሸሽ ማለታቸው” በኢህአዴግ ፓርቲው ወኪል (አቶ ፍስሀ አስገዶም) እና በመንግሥት ዘንድ ቅሬታ አስከትሏል ይሉናል አምባሳደሩ።
የዲፕሎማቶቹ ዕጣ ፈንታ
ውዝግቡ በልዑካን ቡድኑ ላይ አቶ መለስ የዲፕሎማሲያዊ እርምጃ እንዲወሰድ አድርጓቸው እንደነበር አምባሳደር ጥሩነህ ይገልፃሉ። ይህ የመለስ ዜናዊ አሳፋሪ ደብዳቤ፣ ደብዳቤው በደረሰ ማግስት አቶ ኃይለማርያም ሥራውን ለአቶ ፍስሀ አስረክበው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የተጻፈ ደብዳቤ ከደረሳቸው በኋላ፣ በማስከተለም ወዲያውኑ “ከሥራው ተነስተዋል” የሚል ሁለተኛ ደብዳቤ ደርሷቸዋል። ይህ የሚያሳየው፣ የልዑኩ ገሸሽ ማለት የመንግሥትን ቁጣና ፈጣን ምላሽ ማግኘቱን ነው።
ይህ የመለስ ዜናዊ እርምጃ ከደረሰባቸው ዲፕሎማቶች መካከል አምባሳደር ጥሩነህ ሌላኛው ሲሆኑ የጉባኤውን ስብሰባ ሳይጨርሱ ወደ አዲስ አበባ ተጠርተው ወደ ጋና የልዑክ ጉዳይ ፈጻሚ ሆነው እንዲሄዱ ታዘዋል። ምንም እንኳን ከሥልጣን መነሳት ባይሆንም፣ ጉባኤውን ሳይጨርሱ መጠራታቸው “መልካም ያልሆነ ነገር እንዳለበት” እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል።
ይህ ውሳኔ አምባሳደ” በብሄራቸው”/ምክንያት መድሎ እንደደረሰባቸው እንዲሰማቸው አድርጓል። ወደ ጋና መመደባቸውን “ከደቡብ ክልል” ለሚመጡ አምባሳደሮች ወደ አፍሪካ የመላክ ልማድ ጋር በማያያዝ እሳቸውም የዚህ ልምድ ሰላባ እንደሆኑ በማሰብ ቅሬታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል። ይህ የሥራ መመደብ በወቅቱ ከነበረው የአቶ መለስ ደብዳቤ ውዝግብ ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ ብስጭትና የሥራ መልቀቅ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸው ነበር።
ይህ አጠቃላይ ሁኔታ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ “የዲፕሎማሲ ውርደት” ተብሎ ሊሰየምና በታሪክ ሊመዘገብ የሚገባው የዘመነ ኢህአዴግ በተለይም የአቶ መለስ ቡድን ገድል ነው። አንድ ሀገር የራሷን የሉዓላዊነት ጥያቄ በማናፈስ “በግንባር ቀደምትነት ለገንጣይ ኃይል እውቅና እንዲሰጥ” ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ደብዳቤ መጻፉ፣ በዲፕሎማቶች ዘንድም ሆነ በብሔራዊ ጥቅም ላይ ያስከተለው አሳፋሪ ስሜት የረጅም ጊዜ መዘዝ ያለው መሆኑ ግልጽ ነው። ዳፋውንም አሁን ነፍስ ዘርቶ የሃገር የደህንነት ስጋት እና የትውልድ እዳ ሆኖ መቀጠሉን ዜጎች እየገለጹ ነው።





