አዲስ ሪፖርተር – ብልጽግና ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ አበባን እንዲወክሉ ካቀረባቸው 20 ዕጩዎች ውስጥ 16 ያህሉ የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ናቸው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፣ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንዲሁም የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናት አለም መለሰ ተጠቃሽ ናቸው።
በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የከተማ ምክር ቤት አባል ሆነው የተመረጡት የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም በላይ እንዲሁም የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ አሁን ለተወካዮች ምክር ቤት ታጭተዋል።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና፣ የጤና ሚኒስትር ዲኤታዋ ሰሃረላ አብዱላሂ፣ የጉምሩክ ኮሚሽነሩ ደበሌ ቃበታ እንዲሁም የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሯ ሰላማዊት ዳዊት ለተወካዮች ምክር ቤት ከቀረቡ ዕጩዎች መካከል ይገኙበታል።
ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የፌደራል አመራሮችን ዕጩ ያደረገው ከፓርላማ ብቻ አይደለም። የፍትሕ ሚኒስትሯ ሃና አርአያሥላሴ እና የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ ተገኝ ለከተማዋ ምክር ቤት አባልነት ታጭተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሯ ዓለምፀሐይ ጳውሎስም ለዚሁ ምክር ቤት ዕጩ ሆነዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ የሆኑት እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ ተሳትፏቸው የሚታወቁት ፈዲላ ቢያ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ይወዳደራሉ።
ብልጽግና ፓርቲ የከተማዋ ምክር ቤትን እንዲቀላቀሉ ካቀረባቸው ዕጩዎች መካከል በመዝናኛ ኢንዱስትሪ ተሳትፏቸው የሚታወቁ ግለሰቦችም ይገኙበታል።
ስመጥሩ የሙዚቃ አቀናባሪው ካሙዙ ካሳ በየካ ክፍለ ከተማ በዕጩነት ቀርቧል። የቀድሞው የኢቲቪ መዝናኛ ፕሮግራም አቅራቢ እና ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ የተካሄደው ኦዳ አዋርድ አዘጋጅ በሻቱ ቶለማሪያምም በዚሁ ክፍለ ከተማ ትወዳደራለች።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






