አሜሪካ ህወሃትን እንጂ ሌሎችን ግምት ያስገባች አትመስልም። “የማታሸንፉት ጦርነት ውስጥ ነው የገባችሁት” በማለት የኃይል ሚዛኑን ጠንቅቃ የምታውቀው አሜሪካ ህወሃትን ነቅፋና ኮንና ባወጣችው መግለጫ ማስጠንቀቂያም አክላለች። አዲስ የተፈጠረውን የሰባት ነጻ አውጪና ግንባሮች ስብስብ በስም እንኳን ባልተነሱበት የአሜሪካ ማሳሰቢያ፣ ህወሃት ማዘኑን ገልጿል። አምባሳደር ማሲንጋ ንግግርን ወደኋላ በማለት ጦርነት የከፈተውን ህወሃትን በበቂ የጦር ትንተናና መረጃ ተደግፈው በሰጡት “አታሸንፉም” መግለጫ ለትግራይ ህዝብ ሌላ መከራ እንጂ ጠብ የሚል በጎ ነገርም ከትህነግ ዘንዳ እንደሌለ ይፋ አድርገዋል።
አዲስ ሪፖርተር ዜና — በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኤርቪን ጄ. ማሲንጋ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ትህነግ) በአፋር ክልል እና በአቅራቢያ ባሉ አካባቢዎች ላይ አዲስ መጠነ ሰፊ የጦርነት ስምሪት መክፈቱን በጽኑ የሚኮንን እና እስካሁን ከተሰሙት ሁሉ እጅግ ጠንካራ የተባለ መግለጫ አውጥተዋል። “የማታሸንፉት ጦርነት ውስጥ ነው የገባችሁት” በማለት ትህነግንና ተባባሪዎቹን ተስፋ የሚያስቆርጥ መልዕክትም አስተላልፈዋል።
ይህ የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ዲፕሎማት የመንግሥታቸውን አቋም ያንጸባረቁበት አስቸኳይ መግለጫ ይፋ የሆነው ሰባት የታጣቂ ቡድኖች በጋራ በመሆን አዲስ ወታደራዊ ኅብረት መመሥረታቸውን ባስታወቁ ማግስት ሲሆን፣ ዋሽንግተን በሁኔታው ላይ ያላትን ጥልቅ ስጋት እና ቁጣ በግልጽ ያሳየችበት ሆኗል።
አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ትህነግ በሰላማዊ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ከመደራደር ይልቅ እንደገና ወደ ደም አፋሳሽ ውጊያ ለመመለስ ባደረገው የተሳሳተ ውሳኔ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን እና ቅሬታ ገልጸዋል።
አምባሳደሩ በሰጡት ይፋዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፣ የትህነግ አመራር በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አደራዳሪነት የተዘረጋውን የሰላም እጅ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጓል።
ዲፕሎማቱ ትህነግ የፖለቲካ ውይይትን ትቶ ወደ ግጭት መመለሱን በከፍተኛ ሁኔታ የነቀፉ ሲሆን፣ ቡድኑ አሁን ላይ የጀመረውን ውጊያ ትህነግ በፍጹም ሊያሸንፈው የማይችለው ከንቱ ጦርነት ሲሉ በግልጽ አስታውቀዋል። ይህ ትህነግ በፍጹም ሊያሸንፈው የማይችለው ከንቱ ጦርነት ለትግራይም ሆነ ለአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያመጣው ምንም ዓይነት ፋይዳ እንደሌለ አምባሳደሩ በምሬት አስገንዝበዋል።
ትህነግ አዲስ ወታደራዊ ግስጋሴ ከመጀመሩ በፊት አምባሳደር ማሲንጋ እና ሌሎች ከፍተኛ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በአካል እስከ መቀሌ ከተማ ድረስ በተደጋጋሚ በመመላለስ፣ የታጣቂው ቡድን አመራሮች ከጦርነት አማራጭ እንዲቆጠቡ በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ማድረጋቸው ይታወሳል። ይሁን እንጂ ትህነግ እነዚህን የተዘረጉ የሰላም እጆች እና የአፍሪካ ሕብረትን የሰላም አማራጮች በሙሉ ወደ ጎን በመተው ወደ አዲስ የትርምስ ምዕራፍ መግባቱን መግለጫው ያሳያል።
አምባሳደሩ ይህ ትህነግ ሊያሸንፈው የማይችለው ጦርነት ሊያስከትል የሚችለውን ውድመት አስመልክተው ለሌሎች ኃይሎችም ግልጽ መልዕክት አስተላልፈዋል። በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ሌሎች የታጣቂ ቡድኖች እና የአካባቢ ሚሊሻዎች ከዚህ የትህነግ አስከፊ ስህተት ሊማሩ እንደሚገባ የጠቆሙት አምባሳደሩ፣ ይህንን ጦርነት በፍጹም ሊያሸንፉት እንደማይችሉ በመገንዘብ ሁኔታዎችን ይበልጥ ከማባባስ እንዲታቀቡ ጥብቅ ምክራቸውን ሰጥተዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በዋና ዋና የትህነግ አመራሮች ላይ ጠንካራ ማዕቀብ መጣሉን ያስታወሱት አምባሳደር ማሲንጋ፣ አሁንም ኢትዮጵያን ወደ ቀውስ እና ወደ የተሳሳተ መንገድ ለመግፋት በሚሞክሩ ተጨማሪ አመራሮች ላይ ዋሽንግተን ጠንካራ ማዕቀቦችን ለመጣል የሚያስችሏት የተለያዩ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ መሳሪያዎች በእጇ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
“Other armed groups would be wise to avoid this. While the U.S. has tools to sanction additional leaders who try to push Ethiopia down the wrong path.” ጥምረቱን በስም አልጠሩም
አምባሳደሩ አሁንም ቢሆን ምክንያታዊ እና ሁሉን አቀፍ የሆነ የፖለቲካ ውይይት ብቸኛው እና ትክክለኛው መንገድ መሆኑን በጽኑ እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
ይህ የአሜሪካ ዲፕሎማት እጅግ የከረረና ግልጽ መልእክት ይፋ የሆነው ከዚህ ቀደም በነበረው የትግራይ ጦርነት ወቅት ደርሶ የነበረውን እጅግ አሰቃቂ የሰው ሕይወት እልቂት ታሪክ መሠረት በማድረግ ነው። በትግራይ የሚገኙ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ይፋ እንዳደረጉት፣ ባለፈው የ2013 እስከ 2015 ዓ.ም ጦርነት ወቅት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የትግራይ ተዋጊዎችና ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ይህ ዓይነቱ እጅግ አሰቃቂ ታሪካዊ እልቂት ዳግም እንዳይደገም፣ በአፍሪካ ሕብረት የሚመራውን አካታች የፖለቲካ ውይይት መደገፍ እና የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በተግባር መተርጎም የሁሉም ወገኖች አስቸኳይ ኃላፊነት መሆን እንዳለበት ተመልክቷል።
በተለይ ግን አሜሪካ “የማታሸንፉትን ጦርነት” በማለት የጠቀሰችውናን በዚህ መጠን አክርራ ይፋ ያደረገችው መግለጫ፤ በትህነግ አጋፋሪነት ሰባት ታጣቂ ቡድኖች ጥምረት፤ ትብብር መሥርተናል ባሉበት ማግስት መሆኑ ሁሉንም እጅግ ተስፋ ያስቆረጠ ክስተት መሆኑ አዲስ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ይጠቁማል። አምባሳደሩ ከትህነግ በስተቀር ሌሎቹን በስም ለመጥራት የተጠየፉ በሚመስል መልኩ “ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች” በማለት የጠቀሷቸው ፋኖ፣ ሸኔ፣ ኦብነግ፣ ወዘተ እንደሆነ ያመለከቱ፣ “አሜሪካ በዚህ ደረጃ ህወሃትን አራክሳና ምናምንቴ አድርጋ መግለጫ መስጠቷ የህወሃትን መጨረሻ አመላክች እንደሆነ አመልካች ነው። ውለታ ቆጥረው ሊያተርፏቸው ብዙ ሞክረዋል። አሻፈረኝ ብለዋል። ንግግሩ ‘ስራቹህ ያውጣቹህ’ ዓይነት ነው” ብለዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm







