ህወሓት በተለያዩ ግንባሮች በይፋ ጦርነት ጀመረ፤ የትግራይ ሰላም ኃይሎችን ለመቁረጥ ታስቦ ነበር፤ ተተኳሽ በአህያ እየተጓጓዘ ነው፣ ከትግራይ አየር ማረፊያዎች የፌደራል ፖሊሶች ታፈኑ   

Date:

አዲስ ሪፖርተር ዜና —  ህወሓት በአፋር ክልል ቶንሳ እና በአማራ ክልል ጀመዶ ግንባሮችን ጨምሮ በተለያዩ አቅጣጫዎች በእግረኛና በሜካናይዝድ ኃይል የተደገፈ ከባድ ውጊያ መጀመሩ ተገለጸ። ዛሬ ማለዳ በሁለት የተለያዩ ግንባሮች በይፋ የተጀመረው ጦርነት በየአቅጣጫው ምላሽ እየተሰጠው መሆኑ ተመልክቷል። ከትግራይ አየር ማረፊያዎች የፌደራል ፖሊሶች ታፈኑ።

በአካባቢው በደረሱን መረጃዎች መሠረት፣ በአፋር ቶንሳ እና በአማራ ክልል ጀመዶ ግንባሮች የተጀመረው ጦርነት፤ ሌሊት ላይ የተሞከረው ውጊያ ኪሳራ ካስከተለ በኋላ አዲስ ኃይል በማስገባት የተጀመረ ነው።

የህወሓት ኃይል በዛታ-ሰቆጣ ግንባርም በተመሳሳይ ከጠዋቱ 1:30 ጀምሮ ውጊያ ከፍቷል። አላማጣ ላይ ያከማቸው መሣሪያ በትናንትናው ዕለት የተመታበት ህወሓት፣ በሰቆጣ ግንባር በይፋ ጦርነት የጀመረው ተጨማሪ ተተኳሽ በጋማ ከብቶች ሌሊቱን ሲያጓጉዝ አድሮ እንደሆነ የራያ ዘብ አባላት ለአዲስ ሪፖርተር አመልክተዋል።

ቡድኑ ከፋኖ ኃይሎች ጋር በመሆን ዛታን ተሻግሮ በሦስት አቅጣጫዎች—አክመ ጽረዋ፣ ዳብል ማርያም እና ጣቅልላ ጊዮርጊስ በተባሉ አካባቢዎች—ቀደም ሲል ባሰለፋቸው ኃይሎች የእግረኛ ውጊያ መጀመሩን እነዚሁ ወገኖች ጠቁመዋል።

ህወሓት ወደ አፋር ለመዝለቅ በቶንሳ እና በሰቆጣ ግንባሮች የከፈተው ውጊያ በትግራይ ሰላም ኃይሎች አሸናፊነት ተጠናቆ ለጊዜው ቢቆምም፣ ኃይል አከማችቶ እንደገና ውጊያ መጀመሩ ታውቋል። በተካሄደው ጦርነት በህወሓት ላይ “የደረሰው ኪሳራ ከባድ እና የሚያሳዝን ነው” ሲሉ የትግራይ ሰላም ኃይሎች ከፍተኛ መኮንን አመልክተዋል።

የትግራይ ሰላም ኃይሎችን ለመቁረጥ፣ ወደ አፋር ክልል ለመዝለቅ እንዲሁም ሰቆጣን ለመቆጣጠር ሌሊቱን በሁለት አቅጣጫ በተካሄደ ውጊያ ህወሓት ከፍተኛ ኪሳራ ማስተናገዱን የተናገሩት ለየሃ ሚዲያ ዝርዝር መግለጫ የሰጡ ወታደራዊ መኮንን ናቸው።

ትናንት ሌሊት አርሚ 33 ከግንባር አንድ በመነሳት በቶንሳ አቅጣጫ ወደ አፋር ለመዝለቅ፣ ሀራ መሬት በሰፈሩት የትግራይ ሰላም ኃይሎች ላይ ጥቃት የከፈተው ምሽት 2:00 አካባቢ ነበር።

የሃ ሚዲያ ያናገራቸው መኮንን እንዳሉት ከሆነ፣ ከምሽቱ 2:30 አካባቢ “አብሪ” የሚባሉ ቃኚዎች ትንኮሳ ጀመሩ፤ ከምሽቱ 4:00 አካባቢ ደግሞ ሙሉ ጦርነት ተጀመረ። ለአራት ሰዓታት ያህል በተካሄደው ውጊያ ህወሓት ከፍተኛ ሰብአዊ ኪሳራ አስተናግዶ ወደመጣበት ሸሽቷል። ይሁን እንጂ ተመልሶ ኃይል በማሰባሰብ እንደሚመጣ በመጠበቁ እና በዚሁ ግምት መሠረት፣ አሁን ላይ ድጋሚ ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል።

ከትግራይ ሰላም ኃይሎች ጋር የአፋር ሚሊሻ በጥምረት ለወረራ የመጣውን ኃይል እንደመከቱና በመልሶ ማጥቃት ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱበት ያስታወቁት መኮንኑ፣ “እናዝናለን፤ ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳት አስተናግደዋል” በማለት በህወሓት እብሪት የተነሳ የደረሰውን ጉዳት እያዘኑ ዘርዝረዋል። አክለውም አሁንም በቀጠለው ጦርነት የተለየ ነገር እንደማይኖር አስታውቀዋል።

ለጊዜው የጉዳቱን ዝርዝር ያላስረዱት መኮንኑ፣ ህወሓት ከቀኑ 8:00 እስከ ሌሊቱ 6:00 ድረስ በሰቆጣ ግንባር ከሀራ መሬት ኃይሎች ጋር ውጊያ መግጠሙን አመልክተዋል።

የትግራይ ሰላም ኃይሎች በውጊያው የበላይ በመሆናቸው የህወሓት ኃይሎች ለማፈግፈግ መገደዳቸውን ጠቁመዋል። ውጊያው ለጊዜው ቢቆምም ተጨማሪ ኃይል ከምዕራብ ግንባር በማጓጓዝ ኃይሉን አጠናክሮ ዳግም ለመግጠም ዝግጅት እንዳለው ጠቁመዋል። እንዳሉትም ዳግም ጦርነቱ ተፋፍሟል።

የትግራይ ሰላም ኃይሎች ወደ ዋጅራት የማቅናት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ እንዳላቸው አንዳንድ ምንጮች ይናገራሉ። የስለውጊያ እውቀት ያላቸው ወገኖች እንደሚሉት፣ ከመቀሌ በ33 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ዋጅራት ከተቆረጠች ህወሓት ያለው ዕድል ወደ መቀሌ ማፈግፈግ ብቻ ነው። በዚህም ሳቢያ ህወሓት አስቀድሞ ሙሉ ሰቆጣን በመቆጣጠር ግዛቱን የማስፋት ዕቅድ እንዳለው አስረድተዋል። ለየሃ ሚዲያ አስተያየት የሰጡት መኮንን፣ የትግራይ ሰላም ኃይሎች ወደ መሆኒ የማቅናት ዕቅድ ስለመያዛቸው ያሉት ነገር የለም። ስማቸውን ያልጠቀሱ አንድ መኮንን እንደገለጹት፣ ህወሓት ከሁሉም አየር ማረፊያዎች በሥራ ላይ ያሉ የፌደራል ፖሊስ አባላትን አግቶ መውሰዱ የመጨረሻው መጀመሪያ አመልካች ነው።

ከወር በፊት አዲስ ሪፖርተር ይፋ እንዳደረገው፣ ህወሓት የድሮን ፍርሃቻ በመኖሩ የጦር መሣሪያዎችን በጋማ ከብቶች እያጓጓዘ እንደሚገኝ በፎቶ የተደገፉ መረጃዎች እየወጡ ነው። ተተኳሽ ጭነው ወደ አማራ ክልል ሊገቡ ሲሉ በመከላከያ ሰራዊት በተከፈተባቸው ድንገተኛ ጥቃት በቁጥጥር ስር የዋሉ መኖራቸው ተመልክቷል። በአህያ የሞርተር ጥይት ጭነውበት ወደ ሰቆጣ ጉዞ ላይ በነበሩበት ሰዓት በተወሰደ ባቸው ድንገተኛ ጥቃት አህያዎቹን ጥለው ከሸሹት መካከል ለጊዜው ቁጥራቸው ይፋ ያልተገለጸ ተይዘዋል።

ህወሃት ጦርነቱን በተጠቀሱት ግንባሮች በይፋ ከመጀመሩ በፊት በአክሱም፣ ሸሬና መቀለ አውሮፕላን ማረፊያ ጥበቃ ላይ የነበሩ የፌደራል ፖሊስ አባላትን የስራ ትጥቃቸውን አስፈትቶ ማገቱ ይፋ ተደርጓል፤ በመላው ትግራይም የአየር ትራንስፖርት እንዲቋረጥ ሆኗል።

የትግራይ የተቃዋሚ ድርጅቶችና የዓይን ምስክሮች እንዳሉት ህወሃት በተጠቀሱት የአውሮፕላን ማረፊያ የሚሰሩ የፌደራል ፖሊስ ኃይሎችን አግተው ሲያጓጉዙ ማየታቸውን አመልክተዋል። ድርጊቱ ቀደም ሲል በመከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመውን የክህደት እርምጃ እንዳስታወሳቸው የገለጹ እንዳሉት፣ ይህ የመጨረሻው ቀይ መስመር ነው። ምን አልባትም የመንግስት ትዕግስት ሊያበቃ ይችላል ብለው እንደሚያስቡ አመልክተዋል። ህወሃት ቀደም ሲል ወጣቶች ትግራይን ለቀው የሚወጡት በአየር ትራንስፖርት በኩል እንደሆነ በተለያዩ ወቅቶች ሲያስታውቅ እንደነበር እነዚህ ወገኖች አስታውሰዋል።

የአየር ማረፊያዎችን የማስተዳደርና የመጠበቅ ሙሉ ኃላፊነት የፌደራል መንግስት እንደሆነ በህግ በግልጽ የተቀመጠ ሆኖ ሳለ ህወሃት በስራ ላይ ያሉ የፌደራል ፖሊስ አባላትን ማገቱ በቀጣይ ምን እንደታቀደ የሚያመላክት እንደሆነ ተጠቁሟል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

በአላማጣ እና አካባቢው በተካሄደ ከባድ የድሮን ጥቃት ምን ተፈጠረ? የፋጫ ትምህርት ቤት ጥቃት

አዲስ ሪፖርተር አዲስ ዜና —  ከሰሞኑ ከተካሄዱት የድሮን ጥቃቶች...

ከሻዕቢያ ደጅ ለኢትዮጵያ ምን ይከጀላል? ለቁጭትም ግዜ የለም! ዋ!ዋ!…

አንተ አገርህን ብለህ ስትሟገት፣ በየስርቻው የሚዶልቱትን ስታጋልጥ "ባንዳ፣ ተከፋይ"...

ONLF Categorically Denies Joining Armed Opposition Coalition, Calls Reports “False”

In its strongest concluding message, ONLF told the Federal...