አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ | “ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ምርጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው” ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ አስታወቁ። የኤርትራና የኢትዮጵያ ግንኙነት በመደበኛ የመንግሥታት ግንኙነት ሳይሆን በአንድ ግለሰብ ውሳኔና ባህሪ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አቶ ጌታቸው ረዳ አመልክተዋል። ኢሳያስ አፈወርቂ የኤርትራን የውጭ ፖሊሲ በግል ውሳኔያቸው የሚመሩ በመሆናቸው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በተለዋዋጭና በማይታመን ሁኔታ እንዲመራ ማድረጉንም ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው ይህን የተናገሩት ሆርን ሪቪው ባዘጋጀው ኤርትራን የተመለከተ መድረክ ላይ ነው። በመድረኩ ተናጋሪ ሆነው የቀረቡት አምባሳደር ዶክተር ተቀዳ አለሙ ሲሆኑ፣ ያቀረቡት ንግግር በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል የተካሄዱትን ስምምነቶች፣ ስምምነቶቹ የፈረሱበትን አግባብ፣ የውጭ አገራትና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ያደረሱትን ጫና በዲፕሎማትነት በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ሲያገለግሉ የታዘቡትን እውነታ ላይ የተነተራሰ ነበር።
አምባሳደር ተቀዳ አለሙ የተለያዩ አገራትና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ ላይ ያደረጉትን ጫና በስፋት ባብራሩበትና አቶ መለስ ዜናዊ ከኤርትራ ጋር የተደረሰው ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው ጥረት ማድረጋቸውን አድንቀው ባቀረቡት ንግግር ላይ ትችትና ወቀሳ አጋጥሟቸው ታይቷል። በግልጽ አቶ መለስን ከኢትዮጵያ ይልቅ ለኤርትራ የሚያደሉ፣ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው የሰጡ መሪ እንደነበሩ በሳቸው ደረጃ የነበሩ ዲፕሎማቶች ተችተዋል። በዚሁ መድረክ ንግግር ካደረጉት መካከል አቶ ጌታቸው ረዳ፣ “ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ምርጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው” በማለት ተሰብሳቢዎችን አስፈግገዋል።
ቀደም ሲል አቶ ጌታቸው ፕሬዚዳንት ኢሳያስን «የተሳሳተ ስሌት አባት» በማለት ይተቿቸዋል። አቶ ጌታቸው ኢሳያስ በዓለም አቀፍ መድረኮች (ለምሳሌ በሞስኮ በተካሄደው የሩሲያ–አፍሪካ ጉባኤ) የሚያደርጓቸው ንግግሮችና የሚከተሏቸው ፖሊሲዎች ኤርትራን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሲያገሏት፣ በተቃራኒው የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ አቋም ትክክለኛነት ለዓለም የሚያሳዩ ሆነዋል የሚል መልእክት ነበረው።
አቶ ጌታቸው ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሰጡትን አዲስ የምጸት ሹመት (Political Sarcasm / Irony) ያደመጡ እንዳሉት፣ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋና ሥራ ሀገሩን በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚና ተቀባይ እንድትሆን ማድረግ ሆኖ ነው። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በሚያሳዩት ጠንካራና ግትር አቋም ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ብዙ ሳይደክሙ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም እያደረጉ ነው የሚል የምፀት አገላለጽ እንደሆነ አመልክተዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ ኤርትራ እስከ አሁን ድረስ ከአንድ ሰው አምባገነናዊ አገዛዝ ያልተላቀቀች ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፣ የኢሳያስ የግል ባህሪ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ከመንግሥታዊ ደረጃ ወደ ግለሰባዊ ደረጃ አውርዶታል ብለዋል። በ2018 የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያደረጉት የእርቅ ጥረት ይህንኑ ሁኔታ የሚያሳይ ምሳሌ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በ1998 የተጀመረው የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት ወቅት የኤርትራ ጦር የአልጀርስ ስምምነት ድርድር እየተካሄደ ዛላንበሳን ለመቆጣጠር ወታደራዊ እርምጃ መውሰዱን አቶ ጌታቸው አስታውሰዋል። ኤርትራ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እያፈገፈች መሆኗን በደብዳቤ በምትገልጽበት ወቅት በመሬት ላይ የኤርትራ ወታደሮች ዛላንበሳን ለመቆጣጠር ይዋጉ እንደነበር ገልጸዋል። ይህም ኢትዮጵያ በወቅቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ጫና እንዲደርስባት አድርጓል ብለዋል።
በ2018 የእርቅ ሂደት ወቅት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚታመን ሰው አይደሉም የሚል ቅሬታ አቶ ጌታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አቅርበው እንደነበር ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ድክመት ላይ የሚመሰረት ወዳጅነት ዘላቂ እንደማይሆንም በወቅቱ ይታወቅ ነበር አስገንዝበዋል።
የኤርትራ ተቃዋሚዎች ኢሳያስን ከስልጣን ለማውረድ እንጂ ስህተቶችን ለማረምና አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት ፍላጎት እንደሌላቸው አቶ ጌታቸው ተችተዋል። ተቃዋሚዎቹ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ለምን ጦርነት ውስጥ ገባች ከሚለው ይልቅ ለምን ተሸነፈች የሚለው እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል። በቅርቡም ለሉዓላዊነት ሲባል ኢሳያስን እንደግፋለን የሚል አቋም ይዘው ብቅ ማለታቸውን የኤርትራን ገዢና ተቃዋሚ ኃይሎች አስተሳስብ ተመሳሳይነት የሚሳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የፋኖና የኦነግ ኃይሎችን የማስታጠቅ ስልት ተጠቅማ እንደነበርና ይህ ስልት ሙሉ በሙሉ እንደከሸፈ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል። ኢሳያስ በቀጣይ ምን እንደሚያደርጉ ለመገመት አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ከባህሪያቸው በመነሳት መግለጫው ኤርትራ ለዲፕሎማሲ በሯ ክፍት ነው የሚል መግለጫ ማውጣቷ ዓለም አቀፍ ማህበረሱን ለመሸወድ የሄደችበትን ርቀት የሚያሳይ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
አሜሪካ የኤርትራና የኢትዮጵያ ግንኙነትን ለማስተካከል የምታደርገው ጥረት ኢሳያስ ቢያደናቅፉትም የአሜሪካ ተወካይ ማሳድ ብሎስ ወደ አፍሪካ በመጡበት ወቅት የመጀመሪያ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የኤርትራን ግንኙነት ማስተካከል እንደነበርም ጠቅሰዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ ኢሳያስ አፈወርቂን “የኢትዮጵያ ምርጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር” በሚል የገለጹ ሲሆን፣ ኢሳያስ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እና የሚደረጉ የሰላም ጥረቶችን እንደሚያደናቅፉ አስረድተዋል። ኢትዮጵያ የምታቀርበው የሰላም ጥሪ ቦታ ሳይሰጠው ለኤርትራ ትንኮሳ የምትሰጠው ምላሽ ወቀሳ እንደሚቀርብበት፣ በተቃራኒው ኤርትራ ፀብ ጫሪነቷን ለመሸፈን የምትጠቀመው የሰላም ጥሪ እውቅና እንደሚያገኝ ተችተዋል። በተጨማሪም ኮፊ አናን በአንድ ወቅት ስለ ሰላም ጥረት ኢሳያስን ያመሰገኑበት ክስተት እንደሚታወስ ጠቅሰዋል። አቶ ጌታቸው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ዲፕሎማሲንና ሰላምን ዋነኛ አማራጭ ማድረግ እንዳለባት በመግለጽ፣ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚፈለገው ልክ ማስከበር እንዳልቻለ የግል አስተያየታቸውን አቅርበዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






