“በይቅርታ ወደ ሰላም፣ በምህረት ወደ ልማት መሄድ እንደምንችል እናሳያለን። አሸነፍን ብለን የቂም በቀል ካርድ አንመዝም። እነሱ በአሸናፊነት ስሜት ሲያደርጉት እነበደነበረው እኛም እንድናደርግ ይጠብቃሉ። ይህ አይሆንም። አገራችን ኢትዮጵያን በምህረትና በይቅርታ ወደ ሰላምና ልማት ማሻገር ብቻ አጀንዳችን እንደሆነ በማስተማር ያለፈውን የማይጠቅም ልምምድ ቀይረን ትውልድ አዲስ አሳብ እንዲከተለ በር እንከፍታለን” ብርጋዴር ጄኔራል ገብረ እግዚአብሔር በየነ
አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ | “የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነገር መረዳት አለበት” ይላሉ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረ እግዚአብሔር በየነ ኃይሉ፣ አክለውም “ህወሃት ከሚጠፉት ድርጅቶች አንዱ ነው። ስለዚህ ተባበረን ኢትዮጵያን የተረጋጋችና ሰላም የሰፈነባት አገር እናድርጋት” ሲሉ ጥሪ አቅርብርዋል። “እመኑኝ ቂም በቀል የለም” ብለዋል።
የትግራይ ክልል ፊደራል መንግስት ባለአደራ አስተዳደር የጸጥታና ሰላም ዋና አስፈጻሚ ሆነው ከተሾሙ በኋላ በተለየ ለአዲስ ሪፖርተር ቃላቸውን የሰጡት የትግራይ ሰላም ኃይል ዋና አዛዥ/መሪ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዚአብሔር በየነ / ወዲ አንጥሩ “ከአሁን በኋላ እዛና እዚህ መርገጥ አይቻልም። እኛ ኢትዮጵያዊ ነን። አገራችን ኢትዮጵያ ናት። በፍጹም ኢትዮጵያዊ ሆነን በጋር ለአገራችን እንሰራለን” ብለዋል።
አሁን የተሸነፍው “ጉጀሌው” ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ሲያስር እና ሲበቀል መኖሩን በማስታወስ “አሸንፈዋል ይበቀላሉ ብለው ይጠብቃሉ። በቂም በቀል ወነጀል ሲፈጽሙ ስለኖሩ እነሱም ላይ በተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድ ይጠብቃሉ። እኛ ግን አናደርገውም። በቀል የለም። አሁን ቅድሚያው ቂምና በቀልን ወደ ኋላ በማስቀረት ተባብሮ ወደ ልማት መመለስ ነው” በማለት ወዲ እንጥሩ ተናግረዋል።
“እርግጥ ነው? እንዴት እንመን?” በማለት ከአዲስ ሪፖርተር ለተጠየቁት “ዘመኑ የምህረትና የዕርቅ ሊሆን ይገባል። ኃላፊነቴና ምኞቴ ቀጣዩን የሰላም ጉዞ በመህረትና በዕርቅ ማስጀመር ነው” በማለት መልሰዋል።
“ብዙ መጥፎ ተግባራት መፈጸማቸውን ያወሱት ብርጋዴር ጄኔራል ገብረ እግዚአብሔር እስካሁን በሰላም የመጡ የተደረጉት ነገር የለም። ወደፊትም የሚሆነው ይህ ነው” በማለት መጠየቅም ካለ በቂምና በበቀል ሳይሆን በህግ እና በህግ የሚታይበት አግባብ ብቻ ተገባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ሰላም በህግ አስካባሪ ብቻ እውን ሊሆን ስለማይችል፣ ህዝብን ከጎን በማሰለፍ የተረጋጋች፣ ተስፋ ያላት፣ የተፈናቀሉትን በሰላማዊ አገባብ ወደ ነበሩበት የመመለስ እና ፊትን ወደ ልማት የመመለሱ ተግባር ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ያሳሰቡት ጄኔራሉ፣ “ከአሁን በኋላ በትግራይ ያለው ስነ ልቦና ሊቀየር ይገባል” ብለዋል።
“ስደት፣ መፈናቀ፣ ረፍት ማጣትና በጥርነት አዙሪት ውስጥ መኖር ያበቃል” በማለት ለአዲስ ሪፖርተር ያስረዱት ብርጋዴር ጄኔራል ገብረ እግዚአብሔር፣ “ውጊያው አቋል። የቀረው የመለቃቀም ስራ ነው። እሱም አሁን ያበቃል” በማለት አስፈሪው ጊዜ ማለፉን፣ ሕዝቡም በዚህ ደስተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
የኤርትራ ሰራዊት መቶ በመቶ በውጊያ መሳተፉን በማመልከት “የደረስበትን ጉዳት ያውቃል። ከማንም በላይ ያስተናገደው ምት ትምህርት እንደሚሆነው ይታመናል። የሚበጀው እጁን ከትርምስ ሰብስቦ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በሰላም መነጋገር ነው። የሚያዋጣውም ይህ ነው” ሲሉ ምክር እና ማስጠንቀቂያ ያስተላለፉት ብርጋዴር ጄኔራል ገብረ እግዚአብሔር፣ ኢትዮጵያ ሁሉንም እንደሚገባቸው የማስተናገድ አቅሟን በደንብ ስለተረዱ እጃቸውን ወደ መሰብሰቡ እንደሚሄዱ እምነታቸው መሆኑን አመልክተዋል።
በግል ከተሰጣቸው ኃላፊነት አንጻር፣ ትግራይን እንደ ክልል፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር ሰላም እንዲሰፍን እና ሕዝብ ረፍት እንዲሰማው ማድረግ ላይ ሙሉ ትኩረት አድረገው እንደሚሰሩ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረ እግዚአብሔር አስታውቀዋል። ከዚህ በኋላ እዛና እዚህ የሚረግጡ ቦታ እንደሌላቸው አመልክተዋል፤ አክለውም “ለኢትዮጵያ ዋጋ ከፍለናል። ኢትዮጵያዊያን ሁሉ አብረን እንቁም። የትግራይ ህዝብን እና ህወሃትን በመለየት አገራችንን በአንድነት አናቁም። ያለችን አንድ አገር ኢትዮጵያ ብቻ በመሆኗ ይህችኑ አገራችንን ሰላሟን አስጠብቀን በልማት እናሻግር” የሚል ጥሪ አቅርበዋል።

በተመሳሳይ ዜና በትግራይ ክልል የስድስት ወር ጊዜ ያለው ባለአደራ አስተዳደር መቋቋሙን የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ይፋ አድርጓል።
የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል የስድስት ወር ዕድሜ ያለው ባለአደራ ምክር ቤት መቋቋሙን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። ከአዲሱ አስተዳደር ጋር በተያያዘም የተለያዩ የሥራ ዘርፎችን የሚመሩ ዋና አስፈጻሚዎች ሹመት ተሰጥቷቸዋል።
በዚህም አቶ አሰፋ አብርሃ ሐጎስ የአስተዳደርና የሕዝብ አገልግሎት ዋና አስፈጻሚ፣ ዶክተር ቴዎድሮስ አረጋይ ወልደሥላሴ ደግሞ የኢኮኖሚና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ ሆነው ተሹመዋል። ብርጋዴር ጄኔራል ገብረ እግዚአብሔር በየነ ኃይሉ የጸጥታና ሰላም ዋና አስፈጻሚ ሆነዋል።
እንዲሁም አቶ ረዳኢ ኃለፎም ወልደሥላሴ የፖለቲካና የሕዝብ አደረጃጀት ዋና አስፈጻሚ ሆነው ሲሾሙ፣ ዶክተር ሽሻይ አማረ የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሆነው ተሹመዋል።
አዲስ የተሰየመው የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር ተግባራት በዝርዝር ተቀምተዋል። በዚህም መሠረት፦
- በትግራይ ክልል ውስጥ ተፈጥሮ ያለውን የሰላምና የመረጋጋት ችግር በፍጥነት በመፍታት የተረጋጋ ሁኔታን መፍጠር፣
- የፈረሱ የመንግሥት መዋቅሮችን መልሶ በመዘርጋት ሕዝቡ የመደበኛ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር፤
- በጦርነት ምክንያት የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን በመጠገንና ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ በሀገር ደረጃ የሚታዩ የልማት ትሩፋቶች ትግራይ ውስጥም መስፋፋት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤
- የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደየቀያቸው መመለስ፤
- በክልሉ ውስጥ ተቋርጠው የነበሩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ ማድረግ፤
- እንዲሁም የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ተፈጥሮ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ነጻና ግልጽ ምርጫ ተከናውኖ ትግራይ የፌዴሬሽኑ መደበኛ አካል የምትሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤
- ከፌዴራል የመከላከያ፣ የፖሊስና የደኅንነት ተቋማት እንዲሁም ከትግራይ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ከክልል እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር ውስጥ የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠር፣ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በማስረከብ ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱና ተሐድሶ እንዲያደርጉ ሁኔታውን ማመቻቸት፣ የክልሉን የጸጥታ መዋቅር እንደ አዲስ የማዋቀር ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡
- ሰላም እንዲጸና ፣ የሕዝቡ ሥነ ልቡና እንዲስተካከልና ወደ ልማትና የመልሶ ግንባታ ሥራ ለመግባት የሚያስችለው ዝግጁነት እንዲኖረው ማድረግ፤
- የሚዲያ ሥራዎችን የማስተባበር፤ በየደረጃው የሚደረጉ የሕዝብ መድረኮችን የማዘጋጀት፤ ለቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊና አካታች እንዲሆን የሚያስችሉ ተግባራትን የማከናወን ኃላፊነት አለበት፡፡
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






