This Content Is Only For Subscribers
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበጀት ዓመቱ አዲስ የምንጀምረው የኮሪዶር ልማት ፕሮጀክት እንደማይኖር አስታወቁ፤ ወደፊት አዲስ ጥናት እንደሚደረግና ከሕብረተሰቡ ጋር ውይይት ለማድረግ ዕቅድ መያዙን አመልክተዋል። የበጀት ዓመቱ ትልቁ ትኩረት የቤት ግንባታ፣ መንገድና የውሃ አቅርቦት እንደሆነም ተናግረዋል።
ከንቲባ አዳነች ይህን የተናገሩትጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው የአዲስ አበባ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ከምክርቤቱ የኮሪደር ልማት ዕቅድ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅት ነው።
ከንቲባዋ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 ዓ.ም ትልቁ ትኩረት የቤት ግንባታ እና የውሃ አቅርቦት መሆኑንና ለዚህም የሚሆን በጀት የከተማይቱ ምክር ቤት ባለፈው በተካሄደው መደበኛ ጉባኤ መፅደቁን አስታውቀዋል።
የዘንድሮ በጀት ከዘርፎቹ ሁሉ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን የተመደበለት የመንገድ ልማት ዘርፍ መኾኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ ለመንገድ ልማት የተያዘው በጀት 31 ቢሊዮን ብር መኾኑን አስታውቀዋል።
በበጀት አመቱ የከተማ መስተዳድሩ እቅድ አስመልክተው በሰጡት ማብራርያ “ቤቶች እንገነባለን በጥናታችን መሰረት ከህዝብ ጋር ቅድሚያ የምንሰጣቸው ቦታዎች ያልናቸው ላይ ውይይቶች እናደርጋለን” ሲሉ ገልፀዋል ።
ከንተባ አዳነች አቤቤ አክለውም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ባደረገው መደበኛ ጉባኤው ካጸደቀው በጀት ውስጥ ለቤቶች ልማት ዘርፍ የሚውል 24.66 ቢሊዮን ብር መመደቡን አስታውሰዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የዘንድሮ በጀት ከዘርፎቹ ሁሉ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን የተመደበለት የመንገድ ልማት ዘርፍ ሲኾን በጀቱም 31.49 ቢልየን ብር እንደተያዘለት ምክር ቤቱ ያፀደቀው የከተማዋ በጀት ሰነድ ያስረዳል።
ይሁንና በአዲስ አበባ ከተማ በዚህ ዓመት የሚጀመር አዲስ ኮሪደር ልማት እንደማይኖር ቢገለፅም ቀጥተኛ የኮሪደር ልማት ሳይኾን ከወንዞች ልማት ጋር ተያይዞ የሚሰሩ የመንገድ ስራዎች አንደሚቀጥል ግን ከንቲባዋ አልሸሸጉም።
የከተማይቱ አስተዳደር የወንዞች ዳርቻ ልማት ከኮሪደር ልማት ጎን ለጎን ለመስራት ባለፈው ዓመት ከመረከቡ በፊት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በውጭ እርዳታ እና ዜጎች የተከናወነው ስራ ሁለት ኪሎ ሜትር ብቻ እንደነበር ከንቲባዋ ይፋ አድርገዋል።
የአዲስ አበባ ከተማን “የማደስ፣ የማዘመን፣ የማጽዳት” እንዲሁም “መሰረተ ልማቶችን ለህዝብ ተደራሽ የማድረግ ስራ” ለሁሉም አካባቢዎች እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
የተጀመሩት ስራዎች እና የተገኙት ውጤቶች ከከተማችን ስፋት አንጻር ገና መኾኑን ጠቅሰው ገና ከዚህ በላይ መስራት ይገባናል ያሉት አዳነች ነገር ግን ተመሳሳይ ስራዎች ሲሰሩ እቅድ እና ዝግጅት እንደሚያፈልግ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ባደረገው መደበኛ ጉባኤው ያጸደቀው በጀት 350.13 ቢሊዮን ብር ሲኾን ከዘንድሮው የአዲስ አበባ በጀት ውስጥ ለቤቶች ልማት ዘርፍ የተመደበው 24.66 ቢሊዮን ብር ነው።
የፀደቀውን በጀት ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ግንባታ መጀመሩን ከንቲባ አዳነች በከተማዋ ምክርቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ይፋ አንስተዋል ።