የ “ጋዜጠኝነት” ስም የሚሰጠው ለሚታወቅ ስራና “ሙያተኛ ” ብቻ ነው። የአገራችንን እውነታ ለይተን ስንመለከት አክቲቪስቶች፣ የፖለቲካ ድርጅት አፈ ቀላጤዎች፣ የታጣቂዎች ልሳኖች፣ የመንግስት ካድሬዎች፣ የማህበራዊ ሚዲያና ዩቲዩብ ተንታኞች ወዘተ በጅምላ የሙያውን ስም ወስደውታል። ጎራው ተደበላልቆ በሙያ ስም ለመጥራት እንኳን የማያስደፍርበት ደረጃ ደርሷል።
የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም አሳልፈው የሰጡና እየሰጡ ያሉ፣ የሌሎች አገራትን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር አገራቱ ላዘጋጁት የብሄራዊ ጥቅማቸው ማስከበሪያ ሚዲያዎች መርህ ምላውና ተገዝተው አገራቸውን እንደ ዘነዘና የሚወቅጡ ቅጥረኞች፣ ከመንግስት ካድሬ በላይ ካድሬ ሆነው በውዳሴ መንግስት የሚያዝሉ አሸርጋጆች፣ ከጦር ሜዳ አዋጊ ሆነው እየዘገቡ ሲያዙ “ ጋዜጠኛ እገሌ ታሰረ ” ተብሎ በዘመቻ የሚዘፈንላቸው፣ በቡድንና በቲፎዞ ስም እየተጫነባቸው የሚሸለሙና የሚደነቁቱ ወዘተ ከሞራልና ከሙያው መርህ አንጻር ራሳችንን ልንመርመር እንደሚገባን እናምናለን። ምክንያቱም ብዙ ጥፋት ጠፍቷል። በኢትዮጵያ በሚዲያና በሚዲያ “ ባለሙያዎች” አማካይነት የደረሰው ጥፋት ሊሸሸግ የሚችል አይደለምና!! ይህን ስንል ክብራቸውንና ሙያቸውን አክብረው የሰሩ፣ ለመስራት የሚሞክሩ እንዳሉ በመካድ አይደለም።
አዲስ ሪፖርተር በሶስት የመረጃ አውዶች ብቅ ያለቸው በዚህ ቀውስ ውስጥ ነው። ሶስቱ አውዶች voice of Ethiopia VOE, Ethiopian News Factory ENF, በየደረጃው በተከታታይ አየር ላይ የሚበቁ ተመጋጋቢ ሚዲያዎቻችን ናቸው። በሁሉም አውዶች በማህበራዊ የመገናኛ መድረኮች ላይ በቅርቡ አንኖራለን።
ለመሆኑ በሙያው ስም መጠራት የምንችል ስንቶች እንሆን? “ ጋዜጠኛ ” ብለው ራሳቸውን በሚጠሩ የሚዲያ ባለቤቶችና በስራቸው ባደራጇቸው ባለሙዋሎች አማካይነት በተለቀቁ፣ በተረጩ፣ በተላኩና ጭፎሮቻቸው ሳያላምጡ በመቀባበል ባዛመቱዋቸው መረጃዎች፣ እንዲሁም በገፊና ጎታች ስልት በተፈበረኩ ወሬዎች ስንቶች አለቁ? የስንት ዜጎች ንብረት ወደመ? ስንት ዜጎች ተፈናቀሉ? ስንቶች ተንከራተቱ? ስንት እናቶች ጫካ ውስጥ ተገላለግሉ? ስንቶች ባጫካ ውስጥ ታረሱ? ስንቶች በሕዝብ ስቃይና እምባ ነገዱ? ስንቶች ዛሬ ድረስ የመከራ ሕይወት እየገፉ ነው ……….. ቤት ይቁጠረው!! ስንቶቻችን ከዚህ ሁሉ በደል እጃችን የጸዳ ነው?
ልምዳችንን፣ በሙያው ስም፣ ሙያው ከማይፈቅደው አግባብ ከሰራነው ጥፋት በመማር በይፋ ከላይ በተዘረዘሩት አውዶች ስራ ስንጀምር “እውን እኛ ጋዜተኞች ነን?” የሚለውን አሳብ አጉልተን በመጠየቅ ይሆናል። የዚህም መነሻው ምክንያት አገራችን ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟ፣ ፖለቲካውና የግል ጥላቻ በተሳከረባቸው አካላት እየከፈለች ያለችውና ወደፊትም ልትከፍል የምትችለው ዋጋ እጅግ ስለሚያሰጋን ነው። ከምንም በላይ እንደ ሚዲያ የሕዝብን የፈራጅነት መብት ተነጥቋል ብለን ስለምናምን ይህ እንዲቆም የበኩላችንን ለማበረከት ነው!!
መረጃን በወቅቱና በሰዓቱ በመስጠትና ማብራሪያ ሲጠየቁ በፍጥነት በመተባበር በኩል የመንግስትና የመንግስት ኃላፊዎች ድካም፣ ፈቃደኛ አለመሆን፣ በተለይም ኢትዮጵያ እንደ አገር የተዋጣለት የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች ልታገኝ ባለመቻሏ የተፈጠሩት ክፍተቶች ያስከተሉት ጉዳት፣ እንደ አገር ያስከፈለን ዋጋ ተዘርዝሮ አያልቅምና በዚህ አጋጣሚ መንግስት ሆይ ስማ!! ለማለት እንወዳለን።
ለዛሬው መንግስትን ማማታችንን ቆም አድርገን፣ ወደ ራሳችን ጉዳይ ስንመለስ በእውነት እኛ “ጋዜጠኞች” ነን? የሚለውን ጥያቄ ራሳችንን አካተን እንተይቃለን። ለመሆኑ በሙያው ስም መጠራት የምንችል ስንቶች እንሆን? “ ጋዜጠኛ ” ብለው ራሳቸውን በሚጠሩ የሚዲያ ባለቤቶችና በስራቸው ባደራጇቸው ባለሙዋሎች አማካይነት በተለቀቁ፣ በተረጩ፣ በተላኩና ጭፎሮቻቸው ሳያላምጡ በመቀባበል ባዛመቱዋቸው መረጃዎች፣ እንዲሁም በገፊና ጎታች ስልት በተፈበረኩ ወሬዎች ስንቶች አለቁ? የስንት ዜጎች ንብረት ወደመ? ስንት ዜጎች ተፈናቀሉ? ስንቶች ተንከራተቱ? ስንት እናቶች ጫካ ውስጥ ተገላለግሉ? ስንቶች ባጫካ ውስጥ ታረሱ? ስንቶች በሕዝብ ስቃይና እምባ ነገዱ? ስንቶች ዛሬ ድረስ የመከራ ሕይወት እየገፉ ነው ……….. ቤት ይቁጠረው!! ስንቶቻችን ከዚህ ሁሉ በደል እጃችን የጸዳ ነው?
ባጭሩ ጋዜጠኛ ማለት የዕውነትና የሕዝብ ወገንተኛ ማለት ነው። የጋዜጠኞች ሥነ-ምግባር ስንል ደግሞ ባጭሩ እውነተኛ መረጃን ማቅረብ ፣ የህዝብን መብት እና እሴት መጠበቅና ማክበር፣ ስራን በገለልተኛነት፣ በሰብአዊነት፣ በርህራሄ፣ አደጋን በማስላት፣ በተጠያቂነት፣ በኃላፊነት ስሜት፣ በፍትህና በሞራል ልዕልና ወዘተ መርህ መስራት ማለት ነው። በፈረንጅኛው Truth and Accuracy, Independence, Fairness and Impartiality, Humanity, Accountability በማለት የሚዘረዝሩት ነው። ስለዚህ
1. Independence ከገለልተኛነት አንጻርስ? ለመሆኑ ምን ያህሎቻችን ከፖለቲካ፣ ከዘር ቋት፣ ከንግድና ከግል ፍላጎታችን እንዲሁም ከጥቅም ግጭት በመራቅ ነጻ ሆነን ስንሰራ ኖረናል? እየኖርን ነው? ወደፊትስ አቋማችን እንዴት ነው?
2. Truth and Accuracy ከዚህ አግባብ ራሳችንን ብናየው ስንሰራ የኖርነው፣ እየሰራን ያለነውና ወደፊት የምንሰራበት መርህ ከእውነትና ከትክከለኛነት አንጻር እንዴት ይታይ ይሆን?
3. Fairness and Impartiality ከሚዛናዊነትና ከአድሏዊነት አንጻር ብንፈተን በግል ስንቶቻችን፣ እንደ ሚዲያና እንደተቋም በመቶኛ ደረጃችን ቢሰላ እምን ላይ እንገን ይሆን? ተዓማኒነት ያለው መረጃ ከማሰራጨት አንጻር ብንገመገም ምን ያህል ለሞራላችንና ለህሊናችን ክብር ሰጥተናል? ስንቶቻችን የቅጥፈት ዜናና መረጃ አጋርተን፣ እውነቱ ሲገለጥ ይቅርታ ጠይቀናል? “አየባይ ግድብ ተሸጠ” ብለን ዛሬ ድረስ ማስተካከያ ያላተምን በዚህ የሞራል ሚዛን እንዴት እንመዘናለን?
4. Humanity ከሰብአዊነት አንጻር ስንፈተን ውጤታችን ምን ይመስላል? የሰውን ልጅ ክብር ከመጠበቅ፣ አደገኛ መረጃዎችን ከማሰራጨት አንጻር በአገራችን የጋዜጠኛነት ሙያ “የተከበረ” በሚባል ደረጃ ይቀመጣል? ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በነጻ ጋዜጣና ጋዜጠኝነት ስም የተፈጸመውን ትተን፣ ባሳለፍናቸውን ጥቂት ዓመታት በመላ አገሪቱ የተረጨውና ዛሬም እየተረጨ ያለው መረጃ ከሰብአዊነት አንጻር ቢመዘን ሕዝብ ፊት በድፍረት የሚያስቆም ነው?
5. Accountability ስለ ተጥያቂነት ስናወራ ወይም ስናስብ በስራችን ምን ያህል ግልጽ ነን? ምን ያህልስ ለትችትና ወቀሳ ክፍት ነን? በዚህ ረገድ በታማንነት ራሳችንን ብንገመግም ከየትኛው ሰፈር እንመደባለን? ሊተቹን የሞከሩትን በደቦ ፍርድ ቤሰቦቻቸው ሳይቀር በስም እየተጠሩ ሲቀጠቀጡ፣ እጅግ ክብር በሚነካ አኳኋን ማሸማቀቂያ ሲሰራባቸው አላየነም? ከዚህ አንጻር ኃላፊነት ወስደን ለምን ያህል ዜጎች ተቆርቋሪ ሆነናል?
ለምሰራው ስራ ወይም ለምናቀርበው ሪፖርት ኃላፊነት መውሰድና በምናቀርበው ሪፖርት ወይም ዜና ወይም ትንታኔ ሳቢያ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መመዘን ላይስ እንዴት ነን? እንዴትስ ራሳችንን እንገመግመዋለን? ኢትዮጵያና ህዝቧ ላይ ከሆነው አንጻር ሚዲያዎች ብዙ ቢጠየቁ፣ በብዙ መልኩ ቢመረመሩ አግባብ እንጂ ነቀፌታ ሊቀርብ የገባል ብለን አናምንም ምክንያቱም የሙያው መመዘናዎች ሲበርበሩን ውጤታችን ሌላ አይሆንምና!!
እኛም ሆን ሌሎች ጊዜው አልረፈደምና በስሙ ለምንምልበት ሙያ ክብርና ለራሳችን የሞራል ልዕልና ስንል ራሳችንን መርመረን እናርቅ። መንግስትም በርህን ከርችመህ፣ መረጃ ላይ ተኝተህ፣ ሁሉን ሚስጢር አድርገህ አትዘልቀውምና መረጃ የሚሰጡትን አካላት አስጠንቅቅ። ሕዝብ መረጃ የማግኘት መብት ስላለው ባለስልጣናት መረጃ መስጠትን “ ችሮታ” አድርገው የሚያዩበትን አግባብ አስቁም። መረጃ በማይሰጡ ባለስልጣኖች ላይ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ የጠራ መረጃ ሕዝብ ጆሮና ዓይን ዘንድ እንዲደርስ ካልሰራህ የመጀመሪያው ተጎጂ አንተ ነህና አስብበት። የመንግስት የኮሙኒኬሽን አካላት ዝምታ ሃሰትና የፈጠራ ወሬ እንዲነግስ በር ይከፍታልና ይህን የሚመኙ ካድሬዎች ካሉም ራስን መመርመር ይበጃል።
ሚዲያ በወጉ ሲጠቀሙበት አገር ይገነባል፣ ሕዝብን ተጠቃሚ ያደርጋል፣ ለመንግስትም መነጽሩ ነው፤ ሚዲያ በወጉ ካልተጠቀሙበት አገር ያፈርሳል፤ ያጋድላል፤ አገር አልባ ያደርጋል፤ እናም የቱ ይበጃል? የኢትዮጵያ ጉዳይ የአገር ባለቤትነት ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ ጉዳይ “ ውሃ ሲወስድ እያሳሰቀ ነው” በሚል ተረት የሚታለፍ ሳይሆን አገር አልባ እንዳንሆን የምንሰጋበትና የምንጠነቀበት ውላችን ነው። ሌላ አገር የለንምና በአንድ ዓይን አንጫወትም። ብሄራዊ ጥቅማችንንም አሳልፈን አንሰጥም።
መንግስት ያልፋል፤ ፖለቲከኞች ይከስማሉ፤ ጊዜ ይቀያየራል፤ አገር ግን ትውልድን ይዛ ትቀጥላለች። እንደዋዛ አገር አልባ የሆኑ ብዙ ምሳሌዎች ስላሉ በአገራችን መዛበት አግባብ ባለመሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ ሊዋጋው ይገባል። በተለይም ሚዲያው!! እናም “ጋዜጠኞች” ከሆን እንደ ስሙ ከነክብሩ እንጠቀምበት። ካልሆነ ግን በትክክለኛው ስማችን እንጠራ። በትክክለኛው ማንነታችን እንገለጥ። ሙያውን አርክሰን አናራክሰው። ጋዜጠኞች እንሁን፣ ዘርኝነትን በድፍረት እናውግዝ፤ በዘርና በኃይማኖት ካባ ውጥ ሆነው ኢትዮጵያን ሊያጎድሉ ለተነሱ ሁሉ እኛ መርሃችን “Truth in Every Word, Ethiopia in Every Story” ነው እንበላቸው!! ኢትዮጵያዊንት ይለምልም!! ሙያው ከሚፈቅደው ውጭ የቀማነውን የሕዝብ ፈራጅነት መልሰን እናስረክብ!!