በዛች የተረገመች ቀን በቁጥር 65 ኢትዮጵያውንና 9 ቻይናውያን በጠቅላላው 74 ንፁሃን ሕይዎታቸውን አጡ። ሌሎች 9 ቻይናውያን ታግተው ተወሰዱ። ይህን የፈፀመው ኤርትራ ውስጥ መቀመጫውን ያደረገው፣ በኢሳያስ አፈወርቂ ትጥቅና ስንቅ የሚቀርብለት የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ነበር።
በአለባቸው ጉብሳ …………..
አብዲና ጓደኛቹ በኦጋዴን ተፋሰስ በአቦላና አቦሌ የነዳጅ ዘይትና ጋዝ ፕሮጀክት ሳይቶች ውስጥ ለቻይናው ዦንግያን ፔትሮሊየም ካምፓኒ ተቀጥረው ይሰሩ ነበር። ወርሃ ሚያዝያ 1999 ዓመተ ምህርት ከዕለታት በአንዱ ቀን እንደተለመደው የፀሃዩ ንዳድ፣ ሃሩር እና የበረሃ ንፋስና አቧራ ሳይበግራቸው የነዳጅ ፍለጋ ቁፋሮ ስራቸውን ፈፅመው በድካም የዛለውን ሰውነታቸውን ለማሳረፍ ድንኳናቸው ውስጥ ገቡ። ሃገር ሰላም ብለው እንቅልፍ ሸለብ እንዳደረጋቸው ከየት መጣ ሳይባል የሩምታ ተኩስ ተከፈተባቸው። ግማሹ በተኛበት እስከ ወዲያኛው አሸለበ። ሌሎች ከተኙበት በርግገው ተነስተው እግሬ አውጭኝ ብለው ለመሸሽ ቢሞክሩም ከእሩምታ ተኩሱ አላመለጠም ነበር። በዛች የተረገመች ቀን በቁጥር 65 ኢትዮጵያውንና 9 ቻይናውያን በጠቅላላው 74 ንፁሃን ሕይዎታቸውን አጡ። ሌሎች 9 ቻይናውያን ታግተው ተወሰዱ። ይህን የፈፀመው ኤርትራ ውስጥ መቀመጫውን ያደረገው፣ በኢሳያስ አፈወርቂ ትጥቅና ስንቅ የሚቀርብለት የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ነበር። በጥቃቱ የሰው ሕይወት ብቻ አልነበረም ያጠፋው የፕሮጀክቱን ሳይት ቁሳቁሶችና ንብረቶችን ጭምር ነበር ሙሉ በሙሉ ያወደመው። ይህን እውነት በኩራት ያወጀልን ኦብነግ ሲሆን፣ የኢሳያስ መንግስት በጋላቢዎቹ አቅርቦትና ድጋፍ ስልጠናና ትጥቅ ሲያቀርብ እንደነበር የ “እኛው” ተላላኪዎቹ ካልተሟገቱላት በቀር አይክደውም።
“… ኒወርክታይምስ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ “ፀረ ሽብር ጥረት” አጋር የሆነችው ኢትዮጵያ ጥቃት ደረሰባት ብሎ ዘገበ። የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባርም ሃላፊነቱን ውስዶ መግለጫ አወጣ። የታገቱትን የምለቀው በኦጋዴን ተፋሰስ ውስጥ ነዳጅ ፍላጋ ላይ የተሰማሩ የወጭ ሃገር ካምፓኒዎች ከአካባቢው ለቀው ሲወጡ እንደሆነ ገለፀ። ሻዕቢያ በሩን ዘግቶ ከበሮውን ደለቀ። አዲስ አበባ ያሉት የሻዕቢያ ወዳጅና “ሰራተኞቹም” እንደተለመደው በማህበር ስም ተጠራርተው አውካኩ”
ይህ መርዶ መላ ኢትዮጵያውያንን ከሊቅ እስከ ደቂቅ በሃዘን አንገት ያስደፋ ነበር። ዜናውን ዓለም አቀፍ ሚድያዎች የተለየያ ትርጉምና አንድምታ እየሰጡ አስተጋብተውታል። ኒወርክታይምስ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ “ፀረ ሽብር ጥረት” አጋር የሆነችው ኢትዮጵያ ጥቃት ደረሰባት ብሎ ዘገበ። የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባርም ሃላፊነቱን ውስዶ መግለጫ አወጣ። የታገቱትን የምለቀው በኦጋዴን ተፋሰስ ውስጥ ነዳጅ ፍላጋ ላይ የተሰማሩ የወጭ ሃገር ካምፓኒዎች ከአካባቢው ለቀው ሲወጡ እንደሆነ ገለፀ። ሻዕቢያ በሩን ዘግቶ ከበሮውን ደለቀ። አዲስ አበባ ያሉት የሻዕቢያ ወዳጅና “ሰራተኞቹም” እንደተለመደው በማህበር ስም ተጠራርተው አውካኩ። እነሱ ቢረሱ እኛ አንረሳውም። ቁጭት አለብንና!!
ይህ ጥቃት ኢትዮጵያውያንን ተስፋ አላስቆረጣቸውም እንዳውም ይበልጥ በቁጭት እንዲነሳሱ አደረጋቸው። “ቁጭት” ለኢትዮጵያዊያን መፈክራቸው ሊሆን የተመረጠበት አግባብ ብዙ ቢሆን ይህ አንዱና ዋና ከሚባሉት ውስጥ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ መግለጫ ሳይደናገጥ የተጠና፣ በታቀደና በተቀናጃ የፀረ-ሽምቅ ጥረት እና የአመራር ቅብብሎሽ አካባቢውን ከስጋት ነፃ አደረገው። እነሆ ከአስራ ዘጠኝ ዓመት ውጣውረድ፣ መስዋዕትነትና ጥረት በኋላ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የተፈጥሮ ጋዝ የማምረት ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚንስቴር አብይ አህመድ፣ የፌደራል መንግስት እና የሶማሌ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በወርሃ መስከረም 22 ቀን 2018 ዓም አስመርቀች።

የዝግጅት ክፍላችንም ይህ የአብዲና ጓደኞቹ የሕይወት መስዋዕትነት የፈጠረውን ኢትዮጵያዊ ቁጭት ወደ ስኬት የቀየረ ፕሮጀክት ታሩካዊ ዳራ፣ የአመራርና የፓሊስ ለውጥ ያስገኘውን ውጤት እና የተፈጥሮ ጋዝ የምግብ እና የኢነርጁ ሉዓላዊነት በማረጋጥ በኩል የሚኖረውን ሃገራዊ ፋይዳ ዝርዝር ዘገባ እንደሚከተለው አቅርቧል።
የነዳጅ ዘይት ፍለጋ ዳራ
የኢትዮጵያ ዘመናዊ የነዳጅ እና ጋዝ ፍለጋ ታሪክ ወደ አንድ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን የተጀመረውም በ1921 እኤአ እንደሆነ በመስኩ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። የአካባቢ የከርሰምድር ዳሰሳ በማድረግ ፍለጋውን የጀመረው የአንግሎ አሜሪካ ካምፓኒ ነበር። በተለይም ይህ ጥረት የተጠናከረው በመካከለኛው ምስራቅ ታላላቅ የዘይት ግኝቶች ከተደረጉ በኋላ ነው። የኦጋዴን ተፋሰስ የከርሰምድር ቅርፅ ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር ተመሳሳይነት ስለነበረው የዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲጨምር አድርጓል።
በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት መጨረሻ አካባቢ (1964 ዓም) ቴኒኮ የተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ በኦጋዴን ተፋሰስ ውስጥ የነዳጅ ፍለጋ በማድረግ በቃሉብ አካባቢ የንግድ መጠን ያለው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አገኘ ። ይህ ግኝት 76 ቢሊዮን ሜትር³ (BCM) እንደሚሆን የተገመተ ትልቅ የጋዝ ክምችት ነበር። በተጨማሪም፣ ይኸው ኩባንያ በሂላላ አካባቢ አንድ ሜትር ውፍረት ያለው የንግድ ያልሆነ የድፍድፍ ዘይት ክምችት ሊያገኝ ችሏል። ኩባንያው ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ጋር የ50 ዓመት ስምምነት ተፈራርሞ የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ በሃገሪቱ ውስጥ በተፈጠረ የመፈንቅለ መንግስት ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት የማልማት ስምምነቱ ሊሰረዝ ችሏል።
በ1966ዓ.ም ወታደራዊው የሶሻሊስት አስተዳደር (ደርግ) ስልጣን ከያዘ በኋላ የኢኮኖሚ አቅጣጫውን ለወጠ። የንጉሠ ነገሥቱ አገዛዝ ከተገለበጠ በኋላ በ1968 ዓ.ም. ደርግ ቴኒኮን እና ሌሎች በርካታ የምዕራባውያን ኩባንያዎችን ከአገሪቱ አስወጥቶ የነዳጅ ንብረቶቹን ወርሶ ሀገራዊ አደረገ ።
ከምዕራባውያን ኩባንያዎች መውጣት በኋላ፣ ደርግ ለቀጣይ የነዳጅ ፍለጋ ጥረቶች ወደ ሶቪየት ኅብረት እና ሌሎች የምስራቅ ብሎክ አገሮች ፊቱን አዞረ። የሶቪየት ፔትሮሊየም ፈላጊ ኩባንያ (SPEE) በ1970ዎቹ በካናወነው ጥናት በኦጋዴን ተፋሰስ በካሉብ እና ሂላላ አካባቢዎች 118 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የጋዝ ክምችት መኖሩን አረጋግጧል። ምንም እንኳ ይህ ጥረት በፓለቲካና ኢኮኖሚያዊ ስጋት ምክንያት ወደ ኢኮኖሚያው ጥቅም ባይቀየርም በደርግ ዘመን የወጣው የኢትዮጵያ የነዳጅ ኦፕሬሽኖች አዋጅ ቁጥር 295/1986 የሀገሪቱን የነዳጅ ዘርፍ ለወደፊት የሚመራ ወሳኝ የህግ ማዕቀፍ ፈጥሯል። ይህ አዋጅ ከደርግ ውድቀት በኋላም ቢሆን የነዳጅ ሥራዎች የሕግ መሠረት ሆኖ መቀጠሉ፣ ሶሻሊስት አስተዳደሩ በኃይል ዘርፍ የረዥም ጊዜ የአስተዳደር መዋቅር መፍጠሩን ያሳያል።
የደርግ አገዛዝ በ1983 ዓ.ም. ከወደቀ በኋላ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ፍላጎት ቢያሳዩም፣ በተለይ የዮርዳኖስና ማሌዥያ ኩባንያዎች በኦጋዴን ተፋሰስ ውስጥ “ድርብ ስጋት” ስላጋጠማቸው ስኬታማ ሊሆኑ አልቻሉም። አንደኛው ስጋት የጂኦሎጂካል አደጋ ሲሆን (ከጋዝ ሌላ በቂ የዘይት ክምችት አለመገኘቱ)፣ ሁለተኛው ደግሞ በዚህ ጽሁፍ መግቢያ ላይ የተገለፀው በኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር የተፈፀመው ጥቃት ሌሎች ኩባንያዎችን እንዲሰጉ በማድረግ ከባድ የፖለቲካ ስጋት ፈጥሮ ነበር። ስጋቶች ተደምረው ኩባንያዎች ዘላቂ ኢንቨስትመንት እንዳያደርጉ አግዷቸዋል።
ይህንን ችግር ያባባሰው ደግሞ የፌዴራል መንግሥቱ የሀብት አስተዳደር ስትራቴጂ ሲሆን፣ የልማት ፕሮጀክቶች ለአካባቢው ህዝብ ተጨባጭ ጥቅም ሳያስገኙ መተግበራቸውና የአካባቢው ማህበረሰብ ከጥቅሞቹ መገለሉ የፀጥታ ስጋቱን የበለጠ አጠናክሮታል። ስለዚህ የኢትዮጵያ የነዳጅ ዘርፍ አለመሳካት የጂኦሎጂ፣ የፖለቲካ ግጭት እና የማህበራዊ ፍትህ ጉዳዮች ውስብስብ መስተጋብር ውጤት እንደሆነ መረዳት አያዳግትም።
የአመራር እና የፓሊሲ ለውጥ ስኬት….
የጠቅላይ ሚንስቴር የአብይ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በነዳጅ ዘይትና በጋዝ ፍለጋ አስተዳደር ላይ ሲስተዋሉ የነበሩ መሰረታዊ የፓለቲካና የማህበራዊ ፍትህ ስጋቶችን ለመቅረፍ ችሏል። የመጀመሪያ እርምጃው በሶማሌ ክልል ውስጥ ተቀባይነት ያላቸውን እንደ ሙስጠፌ መሃመድ ያሉትን የፓለቲካ ሊሕቃን ወደ ስልጣን ማምጣት ነበር። በመቀጠል ኤርትራ ውስጥ መቀመጫውን አድርጎ በክልሉ ውስጥ የፓለቲካ ግጭት ሲፈጥር የነበረውን የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ጋር የሰላም ስምምነት በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ በማድረግ የነዳጅና የጋዝ ማዕድን የሚገኝባቸው አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም እንዲኖራቸው ለማድረግ ተችሏል። የአካባቢው ማህበረሰብ ከማዕድ ልማቱ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል ከተፈጥሮ ጋዝ ወይም ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ ከሚገኘው ገቢ የትርፍ ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሃገር አቀፍ ተፈፃሚነት ያለው አዋጅ በማውጣት ወደ ስራ ተገብቷል። ይህ ለፕሮጀክቱ አስተዳደርና ስኬታማነት ወሳኝና ተጨባጭ ገቢር ነበብ የሆነ የአመራር ውሳኔ ነበር።
ሌላኛው የስኬቱ ምንጭ እንዲሁ ከአመራር ውሳኔ ጋር የሚገናኘው በነዳጅ ዘይትና ጋዝ ዙሪያ መንግስት ለዘመናት የውጭ ገበያ ላይ የተመሰረተውን ፓሊሲ መሰረታዊ በሚባል መልኩ ለውጥ ማደረጉ ነው። የቻይናው ኩባንያ ፖሊ-ጂሲኤል ፔትሮሊየም ግሩፕ ከ2013 ዓመተ ምህረት ጀምሮ የቃሉብና ሂላላ ጋዝ መስኮችን በመቆጣጠር፣ በኦጋዴን የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ በ767 ኪሎ ሜትር የቧንቧ መስመር ወደ ጅቡቲ በመዘርጋት ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል 4.5 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያለው ሜጋ ፕሮጀክት አስጀምሮ ነበር። ይህ ዕቅድ ኢትዮጵያን ቁልፍ የኃይል ላኪ ለማድረግ ያለመ ነበር።

ሆኖም የቃሉብና ሂላላ ጋዝ ኮምፕሌክስ ከፍተኛ የተረጋገጠ ክምችት (56.94 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር) ቢኖረውም፣ ፖሊ-ጂሲኤል ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ማቅረብ እና የትግበራ መለኪያዎችን ማሟላት አልቻለም (Failed to meet implementation benchmarks)። በዚህ ምክንያት በ2016 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሮጀክት መዘግየቶች እና የገንዘብ እጥረት ችግሮችን በመጥቀስ የኦጋዴን ጋዝ ወደ ውጭ የመላክ ዕቅዱን በይፋ በመሰረዝ የቻይናውን ኩባንያ ከሥራው እንዲወጣ አደረገ።
ከ2016 ዓም ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት የኃይል ፖሊሲ መሰረታዊ ስልታዊ ለውጥ አደረገ። ቀደም ሲል ጋዝን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ከማለም ይልቅ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ቅድሚያ በመስጠት የኢነርጂ ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ ላይ የተመሰረተ አደረገው።
የተጀመረውን ሰላምና ፀጥታ የማከበር ስራ በዘላቂነት ማስከቀጠል ወሳኝ ሲሆን፣ ይህም በክልሉ እና በፌዴራል መንግሥት መካከል በገቢ መጋራት እና በአካባቢው ተጠቃሚነት ላይ ፍትሃዊ፣ ግልጽና አስገዳጅ ስምምነቶች መተግበርን ይጠይቃል።
ይህ አዲስ ስትራቴጂ ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች አሉት። አንደኛ፣ የፊስካል ተጋላጭነትን መቀነስ ነው። ጋዝን ለአገር ውስጥ ነዳጅና ኤሌክትሪክ በመጠቀም በአመት ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆነውን የነዳጅ ግዢ ወጪ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል። ሁለተኛ፣ በዋነኛነት ለምግብ ዋስትና ወሳኝ የሆነውን ጋዝን ለኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ ግብአትነት በማዋል ማደበሪያንና ሌሎች ውጤቶችን በማምረት ጥቅም ላይ ማዋል ነው። ይህን ስትራቴጂክ አላማ እውን ለማድረግ መንግስት በጎዴ ከተማ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር 2.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት በዓመት 3 ሚሊዮን ቶን የአሞኒያ/ዩሪያ ማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የመገንባት ዕቅድ ይፋ አድርጎ የግንባታ ስራ ተጀምሯል። ይህ ተቋም በተሳካ ሁኔታ ከተገነባ ውድ ከሆነው ማዳበሪያ ማስመጣት ጥገኝነትን በማስወገድ የማዳበሪያ ግዢ ወጪን ከ80% በላይ በመቀነስ ለአገር ውስጥ የምግብ ዋስትና ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። ከሃገር ውስጥ ገበያ ባለፈ ወደ ምስራቅ አፍሪካ የውጭ ንግድ ዕድሎችን ይፈጥራል። እንዲሁም ከማክሮ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር ከዓለም አቀፍ የገበያ ተጋላጭነት ይከላከላል።
በአጠቃላይ፣ የዝግጅት ከፍላችን አሁን የተጀመሩ ቁጭትን ወደ ሃገራዊ ብሄራዊ ድልና ስኬት የቀየሩ የነዳጅ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ ልማት ዘርፍ ውጤታማ ስራዎችን የበልጥ ለማረጋገጥ ወሳኝ የሆኑ የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል፤ ከነዚህም መካከል የማዕድን ሚኒስቴር (MoM) የአስተዳደር አቅሙን ማጠናከር ወሳኝ ነው። በተለይም የምርት መጋራት ስምምነቶችን (PPSAs) የማስተዳደር፣ የኮንትራት ቁጥጥርን የማካሄድ እና የኩባንያዎችን ወጪ መልሶ ማግኛ ግምገማዎች የማድረግ ብቃት ማሻሻል አለበት። በተጨማሪም፣ በሶማሌ ክልል በተለይም በኦጋዴን ዞን ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ሰላምና ፀጥታ የማከበር ስራ በዘላቂነት ማስከቀጠል ወሳኝ ሲሆን፣ ይህም በክልሉ እና በፌዴራል መንግሥት መካከል በገቢ መጋራት እና በአካባቢው ተጠቃሚነት ላይ ፍትሃዊ፣ ግልጽና አስገዳጅ ስምምነቶች መተግበርን ይጠይቃል። በመጨረሻም፣ የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማጠናከር እና ለወደፊት የንግድ መሠረት ለመጣል የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ትስስርን ማጠናከር፣ በተለይም አሁን ያሉትን የጋዝ-ለ-ማዳበሪያ እና ጋዝ-ለ-ኃይል ፕሮጀክቶችን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ ያስፈልጋል።
ዝግጅት ክፍሉ = ይህ ነጻ አስተያየት ነው። አሳቡ ሙሉ በሙሉ የጸሃፊው ብቻ ነው። ምላሽ ወይም ተጨማሪ አስተያየት ካለዎ info@addisreporter.com ይላኩልን እናስተናግዳለን።




