አዲስ ሪፖርተር – በቀናት ልዩነት የኤርትራ ወታደሮች በተቀነባበረ፣ ዝግጅት በተደረገበትና ማሳካት የሚፈልገውን ዓላማ ባማስቀመጥ በትግራይ የፈጸሙትን የጅምላ ጾታ ጥቃት፣ ዝርፊያና ግፍያ ‘ዘ ሴንትሪ’ የተባለ ተቋማና ዘጋርዲያን ይፋ ካደረጉ በሁዋላ ራሱን “የትግራይ ጀኖሳይድ አጣሪ ኮምሽን” ሲል የሚጠራ አጣሪ አዲስ ሪፖርት ይፋ ማድረጉ የተአማኒነትና የህጋዊነት ጥያቄ ተነሳበት፤ በተለይም ቀደም ባለው ሪፖርት በከፍተኛ ወንጀል ከተከሰሰው የኤርትራ መንግስት ጋር አብሮ እየሰራ ይህንን ሪፖርት ማዘጋጀቱ አነጋጋሪ ሆኗል።
ይህ ራሱን “የትግራይ ጀኖሳይድ አጣሪ ኮምሽን” የሚለው አካል በሁለት ዓመቱ ጦርነት ወቅት በ152 ሺህ 108 የትግራይ ሴቶች በኤርትራና በኢትዮጵያ ሃይሎች መደፈራቸው የሚገልፅ የጥናት ሪፓርት አውጥቶ በተለያዩ ሚዲያዎች ያሰራጨ ሲሆን የጀርመን ድምጽ በስፋት ከዘገቡት መካከል ይጠቀሳል፡፡
“ለመስማት የሚዘገንን” የተባለው የዘጋርዲያን ሪፖርት ላይ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ሴቶች ማሕጸን ውስጥ “የዛጉ ብሎኖች፣ ስፒሎች እና የፕላስቲክ ቆሻሻዎች ይጨምራሉ” ብሏል፡፡ ዘጋርዲያን የኤርትራ ወታደሮች ዕድሜ ሳይመርጡ በትግራይ ሴቶች ላይ የፈጸሙትን ዘግናኝ የጅምላ ወሲባዊ ጥቃት ያቀረበው በማስረጃ ሲሆን ኤርትራ አስተባብላ ነበር።
ከትግራይ አዲስ የተሰራጨው የኮሚሽኑ “ጥናት” እንደሚያሳየው በሁለት ዓመቱ ጦርነት ወቅት በ152 ሺህ 108የትግራይ ሴቶች መደፈራቸው የሚያመለክት ሲሆን ሌሎች በርካቶች ደግሞ በተለያየ መልኩ የሚገለፁ ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንደደረሰባቸው አስታውቋል።
የጀርመን ድምጽ ጥናቱን እንደጠቀሰ አመልክቶ እንዳለው 55 በመቶ የጠቀሱትን ጥቃት ፈጻሚዎቹ የኤርትራ ሰራዊት አባላት ናቸው ብሏል። 35 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች መፈፀማቸው ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ 5 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆነው በአማራ ሐይሎች የተቀሩት ደግሞ የተለያዩ ሐይሎች በጋራ የተፈፀሙ ስለመሆናቸው ጥናቱ አመልክቷል። ኤርትራ የዘጋርዲያንን ሪፖርት ባጣጣለችበት ፍጥነት ለዚህ ሪፖርት ይህ እስከታተመ ድረስ ምላሽ አልሰጠችም።
እንደ ሪፖርቱ ጥናቱ ከጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ ጦርነቱ እስከቆመበት ጥቅምት 2015 ዓ.ም ድረስ ተፈፀሙ የተባሉትን ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች የዳሰሰ ነው። ይህ 166 ገጾች አሉት የተባለለት ጥናት በአጠቃላይ 481 ሺህ 201 ሴቶችን የተካተቱበት መሆኑን ያትታል።
ጥናቱ ከጠቀሰው አሃዝ ውስጥ ከ286 ሺህ በላይ የሚሆኑት ሴቶች በተለያየ መልኩ በሚገለጽ የፆታ ጥቃት የተፈጸመባቸው እንደሆነ ያመለክታል። ለእነዚህ ወንጀሎች ዓለምአቀፍ የፍትህ ስርዓት እንዲኖርም ይጠይቃል።

Nail clippers and screws removed from the wombs of survivors of sexual violence in Tigray. Photograph: Ximena Borrazas
ሪፖርቱን ከጀርመን ድምጽ እንዳዩ ያመለከቱ “ገርሞናል” ይላሉ። ቀደም ሲል ትህነግና የኤርትራ መንግስት በጠላትነት በሚፈላለጉበት ወቅት በተሰማው ሪፖርት የኤርትራ በተጠቀሰው ወንጀል የኤርትራ ኃይሎች ተሳትፎ ከ78 በመቶ በላይ መሆኑ ሲገለጽ እንደነበር አስታውሰው፣ በአንዴ ወደ 55 በመቶ መውረዱና የተፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል በዝርዝር አለመቀረቡ ሰፊ ጥርጣሬ እንደፈጠረባቸው አመልክተዋል።
አቶ ሃምሳሉ ኃይሉ የተባሉ የስራ ኃላፊነታቸውን ያልገለጹ የህግ ባለሙያ ኢትዮጵያ ሁልጊዜ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ስትነሳ ዘወትር የተቀነባበረ የሚዲያ ዘመቻ እንደሚነሳባት አመልክተዋል። ተበዳዮች ፍትህ እንደሚሹ ጠቅሰው የፍትህ ሂደቱም ሆነ ምርመራው በገለልተኛ አካላት የዓለም ዓቀፉን መርህና ደረጃ በጠበቀ መልኩ ሊከናወን እንደሚገባ ይጠቁማሉ። ከዚህ አንጻር በትግራይ አስተዳደር ስር የተቋቋመው አጣሪ ለዚህ ስራ አግባብነት አለው ብለው እነደማያምኑ አስታውቀዋል። ጉዳዩ የፖለቲካ አጀንዳ ማራመጃ እንዳይሆንም ስጋታቸውን ገልጸዋል። እንዲህ ያለው አካሄድ ተበዳዮች ፍትህ እንዲያገኙ እንደማያስችልም ገልጸዋል።
«የትግራይ ጀኖሳይድ አጣሪ ኮምሽን» የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለም አብርሃ ጥናቱ ዓለምአቀፍ ደረጃ በጠበቀ መልኩ የተሰራ እና የቤትለቤት ዳሰሳ ጭምር የተደረገበት መሆኑ ዶቼቬሌ አስታውቋል። አቶ ሃምሳሉ እንደሚሉት የተገለጹት ባለሙያን ባያውቋቸውም እዛው ትግራይ ያሉና ኮሞሽኑም በወንጀሉ ውስጥ ስሙ የሚነሳው የትግራይ አስተዳደር ስር መሆኑ ብቻ የዓለም ዓቀፉን መርህ የሚያሟ አድርገው ማቅረባቸው እንዳስደነገጣቸው ይናገራሉ።
ከ15 ዓመት በላይ የሆኑ የፆታ ጥቃት ሰለባዎች ቀጥታ በማነጋገር ከ15 ዓመት በታች የሆኑት ደግሞ በወላጆች ወይም ቤተሰባቸው በኩል መረጃ ማሰባሰቡ የሚገልፀው የትግራይ ጀኖሳይድ አጣሪ ኮምሽን ሪፖርት በበርካታ ሴቶች በተደጋጋሚ፣ በቡድን እንዲሁም ለወራት ከተፈፀሙ መድፈርና እና ሌሎች ዓይነት የፆታ ጥቃቶች በተጨማሪ 529 ሴቶች ጥቃቱ ከተፈፅሞባቸው በኃላ መገደላቸው በጥናቱ ተረጋግጧል ብለዋል። ይህን የፈጸመው የትኛው አካል እንደሆነ ግን “ጥልቅ” ጥናት ተደርጎበታል በተባለው የዶቼቬሌ ሪፖርት ላይ አልሰፈረም።
“እኛ የኤርትራ ልጆች ጀኞች ነን፤ ለዚህም እራሳችንን ሰጥተናል፤ በዚህ ተግባራችን ወደፊት እንቀጥላለን፤ የትግራይ ሴቶችን መካን እናደርጋለን ወይም ማሕጸናቸውን እናደርቃለ” የሚለው ማስታወሻ የተገኘው በትግራይ ሴቶች ማህጸን ውስጥ ነው። ደብዳቤውን በእጃቸው ጽፈው በላስቲክ በመጠቅለል በትግራይ እናቶችና ህጻናት ማህጸን ውስጥ ያስቀመጡት የሻዕቢያ ወታደሮች ናቸው። ይህ የሚሆነው ደግሞ በደቦ የአስገድዶ መድፈር ከተፈጸመ በሁዋላ ነው። ይህ ያለው ዘጋርዲያን ነው፤ ዛሬ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ነኝ የሚለው ትህነግ ይህን ተግባር ሆን ብሎ፣ በትዕዛዝ ከፈጸመው ሻዕቢያ ጋር እኩል መግጠሙን የባይቶና ሊቀመንበር “በአንድ ፖፖ ተቀምጠዋል” ሲሉ በአንድ አፍታ በኩል ገልጸውታል።

“Sons of Eritrea, we are brave,” the note reads. “We have committed ourselves to this, and we will continue doing it. We will make Tigrayan females infertile.”
ባዕድ ነገሮች ወደ ሴቶች መራብያ አካል ማስገባት፣ ለወሲብ ባርነት መገልገል፣ በኬሚካል ማቃጠል እና የመሳሰሉ ሌሎች ተግባራትም በትግራይ ሴቶች ላይ መፈፀማቸው በጥናቱ መመለክቱን የዘጋርዲያን ዘገባ ያስረዳል።
የዝግጅት ክፍላችን ራሱን የትግራይ ጄኖሳይድ አጣሪ ኮሚሽን በማለት የሚጠራውና ተቀማጭነቱ ትግራይ የሆነው የምርመራ ቡድን ይፋ ያደረገውን ሪፖርት አስመልክቶ መረጃ ለማሰባሰብ ሞክሯል።
በዚሁ መሰረት የቀረበው “ጥናት” ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርምራ መመዘኛዎች አንፃር ምን ያህል ተአማኒነት እንዳለው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ጉባኤ አቋቁሞት በነበረው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ልዩ ባለሙያን አስተያየት ጠይቀናል።
ባለሙያውን ስለ ትግራይ ጀኖሳይድ አጣሪ ኮሚሽን የፓሪስ መርሆዎች ተብሎ ከሚገለፁት መርሆዎች አንፃር ገለልተኝነት እና ከአድሎ የፀዳ ስለመሆኑ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡን ማብራሪያ፣ ” ማንኛውም የጦር ወንጀልና ሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን የሚያጣራ ኮሚሽን ከማንኛውም የጦርነቱ ተሳታፊ ሃይሎች ገለልተኛ እና አሰራሩም ከአድሎ በፀዳ መልኩ እንዲሰራ ሆኖ መቋቋም እንዳለበት ይደነግጋል” ብለዋል።
አስተያየት ሰጪው አክለውም በዚህ መመዘኛ በትግራይ ክልላዊ መንግስት ጊዜያዊ አስተዳደር የተቋቋመው ኮሚሽን ይህንን መርሆዎች መሰረት አድርጎ ስለመቋቋሙ መረጃ እንደሌለ አመልክተዋል። ባለሙያው ለድምዳሜያቸው ማስረጃ ሲሰጡ፣ “ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሙ፣ ከጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች አንዱ ከሆነ አካል ጋር በቀጥታ የተቆራኘ እንዲሆን ያደርገዋል” በማለት የአሰራሩን ህጋዊነትና ዓለም ዓቀፍ መርህ ላይ ስለመመስረቱ ያላቸውን እያታ ያስቀምጣሉ። ይህ ግምገማ ለትግራዩ ኮሚሽን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሚሰራ በመሆኑ በዚሁ አገባብ ሊታይ እንደሚገባው ያስረዳሉ።
“ኮሚሽኑ በፓሪስ መርሆዎች የተደነገገውን ከመንግስት ወይም ከፖለቲካ ተፅዕኖ የፀዳ የመሆን መርህ ሙሉ በሙሉ እንዳይከተል ያደርገዋል” ሲሉ ሌላ የህግ ባለሙያ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።
የጀርመን ድምጽ በሰራጨው የሪፖርቱ ጭማቂ ጥናቱ ደረጃውን የጠበቀ፣ ዓለም ዓቀፍ መርሆችን የተንተራሰና ግልጽ አሰራር የተከተለ መሆኑን አመልክቷል። ሬዲዮ ጣቢያው የዓለም ዓቀፉን አሰራር የሚረዳ ሆኖ ሳለ ዘገባውን ከገለልተኛ ወገን መረጃ ባለማካተቱ የጭብጥ መዛነፍ እንዳለበት የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲ ከሆኑት መካከል ለአዲስ ሪፖርተር አስታውቀዋል።
የትግራይ ተቃዋሚ ድርጅት አመራሩ እንዳሉት በትግራይ የተጠቀሰው ችግር ስለመኖሩ አያስተባብሉም። ሆኖም ግን የትግራይን ሕዝብ የረሸነና የትግራይን ሴቶች በደቦና፣ በተናጠል እንዲሁም በስልት የደፈረው የሻዕቢያ ኃይል መሆኑ እየታወቀ ሪፖርቱ ይህንንን በደምሳሳው ማቀረቡ በድርጅት ደረጃ ምላሽ የሚሰጥበት በመሆኑ ለጊዜው ዝርዝር ከመስጠት ትቆጥበዋል። ” ትህነግ የትግራይን ሕዝብና ሴቶች ከፈጀው ሻዕቢያ ጋር አብሮ ይህን ሪፖርት ማውጣቱ ለትግራይ ሕዝብ ንቀት ነው” ብለዋል።
” በዓለም ዓቀፍ መመዘኛዎች መሰረት ገለልተኛ ያልሆነ ተቋም ያወጣው ሪፖርት፣ የጥቃት ሰለባ የሆኑትን ሁሉ ፍትህ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆነውን ዓለም አቀፍ ተቀባይነትና እምነት እንዳያገኝ ያደርገዋል” ሲሉ ለጊዜው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ መመህር ተናግረዋል። ሙሉ ሪፖርቱን ከመረመሩ በሁዋላም ዝርዝር ማብራሪያዎችን ሊሰጡ እንደሚፈቅዱም ለአዲስ ሪፖርተር አስታውቀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ኮሚሽኑ ካለው ውስን ሃብት እና የባለሙያ ጥራትና ብዛት አንፃር ግማሽ ሚሊዩን የሚደርሱ የክልሉን ሴቶች በጥናት ናሙናነት በመውሰድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርመራ ለማድረግ እንደማይቻል ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ይህም ወደፊት ሊደረጉ የሚችሉ ምርመራዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችልም የግልጻሉ።

ኮሚሽኑ “የትግራይ ጀኖሳይድ” በሚል ስም መቋቋሙ፣ ትኩረቱ በሌሎች የጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች የተፈፀሙትን የሰብአዊ መብት ፆታዊ ጥቃቶችላይ ብቻ ያተኮረ እንዲሆን ሊያደርገው ችሏል።
ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ምርመራዎች ደግሞ የጥቃት ሰለባ የሆነው ወገን ማን እንደሆነ ሳይለይ፣ በሁሉም ተዋጊ ኃይሎች የተፈፀሙ ጥሰቶችን በፍትሃዊነትና ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ መዳሰስን ስለሚጠይቅ የኮሚሽኑ ጥናት ሪፓርት የተሟላ እንዳይሆን እንደሚያደርገው እነዚሁ ወገኖች ይገልጻሉ።
በመጨረሻም ወደፊት ምንም መደረግ እንዳለበት ለጠይቀናቸው ባለሙያው ሲያስረዱ፣ ከዚህ በፊት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ጉባኤ ስር የተቋቋመው ገለልተኛ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ስራውን እንደገና የሚጀምርበትን ሁኔታ ላይ ግፊት የማድረግ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለበት ገልፀውልናል።
የጀርመን መንግስት የሚያስተዳድረው ሬዲዮ የጠቀሳቸውን አቶ ዓለምን ለማነጋገር በተደጋጋሚ በእጅ ስላካቸው ላይ ያደረኘው ሙከራ አልተሳካልንም። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ህግ ክፍል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን “እኛ የማንንም ሪፖርት ዕውቅና አንሰጥም። ልክ አይደለም አንልም። አስተያየት እንድንሰጥበትም መላኩንና አለመካኡን አላውቅም” ብለዋል።
ፎቶ ዘጋርዲያን




