የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በውጭ አገራት የሚገኙ ሐዋላ አስተላላፊ ድርጅቶች እና ከንግድ ባንኮች ጋር በመመሳጠር በሕገ- ወጥ እንቅስቃሴ ላይ ያሉ አካላት ከተግባራቸው እንዲታቀቡ ያስጠነቀቀ ሲኾን በሕገ-ወጥ የሐዋላ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ላይ ከባድ እርምጃ እንደሚወሰድ እወቁልኝ ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በውጭ አገራት የሚገኙ ሐዋላ አስተላላፊ ድርጅቶች እና ከንግድ ባንኮችን ማስጠንቀቂያ ያስተላለፉ ሲኾን በሚወሰዱ ሕጋዊ እርምጃዎች ዙሪያ ገለፃ አድርገዋል ተብሏል።
የብሄራዊ ባንክ ዋና ገዢው እዮብ ተካልኝ በማብራርያቸው መንግሥት በርካታ የሐዋላ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ሕጋዊ በሆነ መንገድ እየሰሩ በዘላቂነት በቢዝነስ ዘርፉ እንዲቆዩ ፍላጎት እንዳለው ገልፀው በሕገ-ወጥ የሐዋላ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ላይ መንግስት ከባድ እርምጃ እንደሚወሰድ ማስጠንቀቃቸው ተገልጿል።
እዮብ ከአክለውም፣ መንግሰት በተደጋጋሚ ወደ ሕጋዊ መንገድ እንዲገቡ ጥሪ ያደረገላቸውና ጥሪውን ያልተቀበሉ አንዳንድ የሐዋላ ገንዘብ አስተላላፊዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ብሔራዊ ባንክ በእነዚህ ሕገ ወጥ የሐዋላ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ላይ በጥናት እና በመናበብ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ አሳስበዋል።
ገዥው፣ በዋነኝነት ገንዘብ በነዚህ ሕገ ወጥ ተቋማት በኩል የሚልኩ ዜጎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን መረጃ እንዳለው ገልፀው፣ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማሳሰብያ የሰጡ ሲኾን አንዳንድ አስመጪ እና ላኪ ድርጅቶችም አሁን ላይ የሚወሰደውን ርምጃ አውቀው ሊጠነቀቁ ይገባል ብለዋል።
በሀገር ደረጃ ሰፊ የውጭ ምንዛሬ ሀብት መኖሩን የጠቀሱሳ ዋና ገዢው ብሔራዊ ባንክ በአስተማማኝ ሁኔታ ይህን ሀብት እያቀረበ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ በዚህም መሰረትም የተመቻቸው እድል እንዲጠቀሙ እንዲሁም ለባንኮችም ይሁን ለሀዋላ አስተላላፊ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል
ሕጋዊ አካሄድን ይዞ ለመንቀሳቀስ እንዲያስችላቸው ከመንግሥት እንዲደረግላቸው የሚፈልጉትን ዝርዝር ነጥቦች አንስተዋል። ይሁንና አሁንም የሕገወጥ እንቅስቃሴዎች አዝማምያ እየተስተዋለ መኾኑን ጠቁመው ባንኩ እርምጃ የሚወሰድበት መንገድ አመቻችቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም አውጥቶት በነበረው አጭር መግለጫ በሕገ- ወጥ የገንዘብ ዝውውር የወነጀላቸው ድርጅቶች የገንዘብ አስተዳደሩን ስርዓት የሚያቃውስ መኾናቸውንና በውጪ ሀገራት የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ድርጅቶቹን እንዳይጠቀሙ መክሮ እንደነበር አይዘነጋም ።
ባንኩ፣ ሐዋላ አስተላላፊዎቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች ያሉ የሕግ አካላት እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ምርመራ ለማካሔድ እንዲተባበሩ ጥያቄ ያቀረበ ሲኾን ለግዜው በውጪ ሀገራት የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ድርጅቶቹን ገንዘብ ለማስተላለፍ እንዳይጠቀሙ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
በመግለጫው በስም የተጠቀሱት አራት ድርጅቶች መካከል ሸጊ፣ አዱሊስ፣ ራማዳ ፔይ (ካህ) እና ታጅ የተባሉ የሐዋላ አስተላላፊዎች ሲሆኑ የሐዋላ አስተላላፊዎቹ በሜሪላንድ፣ ቨርጂኒያ እና ሚኒሶታ በሚገኙ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ መኾናቸውን ማረጋገጡን ተናግሯል።
የውጪ ምንዛሪ ግብይት ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በገበያ ወደሚመራበት ስርዓት እንዲሸጋገር ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው አንድ ዓመት በሐዋላ አስተላላፊዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ ጥረት እያደረኩ ነው ሲል በተደጋጋሚ መግለፁን አይዘነጋም ።
ያለ ፈቃድ የሐዋላ እና የገንዘብ ዝውውር አገልግሎት መስጠት ወይም መጠቀም ሕገ-ወጥ እና በኢትዮጵያ ሕግ የሚያስቀጣ መሆኑን የተደነገገ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው 91 ሕጋዊ የገንዘብ አስተላላፊ ኤጀንሲዎች እንደሚገኙ የማእከላዊ ባንኩ መረጃ ያስረዳል።
የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ከተደረገ ወዲህ ባለፉት ወቅቶች የኢትዮጵያ መንግሥት ጠቀም ያለ የውጪ ምንዛሪ ካገኘባቸው ዘርፎች አንዱ ሐዋላ መሆኑን የሚታወቅ ሲሆን በበጀት አመቱ 7.1 ቢሊዮን ዶላር ገደማ በግል ሐዋላ የገንዘብ ማስላለፍያ ዘዴ ወደ ኢትዮጵያ መላኩን የሚታወስ ነው።
ፎቶ ክሬዲት ሪፖርተር




