“ክልሉ ስላሙን ያጣው ከዝርፊያ ጋር በተያያዘ ስጋትም ነው”
“የኮሙኒኬሽን ሊቅ” በሚል ካድሬዎች የሚያሞግሷቸው አቶ በረከት ስምዖን የአማራ ክልል መጨረሻ መድቀቅ እንደሆነ በትንቢት መልክ መናገራቸውን አብረዋቸው ያወጉ መኮንን ለአዲስ ሪፖርተር ገልጸዋል። ዛሬ ላይ በሚያዩት እንደሚያዝኑም አመልክተዋል።
” የዛሬ ሶስት ዓመት ግድም ከበረከት ጋር ቁጭ ብለን ስንጫወት የአማራ ክልል መጨረሻ መድቀቅ ነው ብሎኛል” ሲሉ የተናገሩት መኮንን እንዳሉት፣ አቶ በረከት ከዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ሶስት አበይት ምክንያቶች እንዳሉዋቸው አመልክተዋል።
በመጀመሪያ ያቀረቡት ምክንያት የአማራ ኃይሎችና ይህንኑ ኃይል የሚመሩ የክልሉ አካላትና የኤርትራ መንግስት ሙሉ በሙሉ ትህነግን የማጥፋት ዕቅድ ስለነበራቸው የፕሪቶሪያው የሰላም አማራጭ የተኩስ ማቆም ስምምነት ሲደረግ ማኩረፋቸውን ነው። በዚህም የተነሳ ልክ የኤርትራ ኃይሎች ወዲያውኑ አቋማቸውን ቀይረው ከመንግስት ጋር ቅርሾ እንደገቡት የአማራ ኃይሎችም ተመሳሳይ ስሜት ተፈጥሮባቸዋል።

ጦርነቱን ተከትሎ በአማራ ክልል ያሉ ባለስልጣናትና የሚታወቁ ባለሃብቶች ከወልቃይት ሃብት ማጋዛቸውንና በዚህም ከፍተኛ ጥቅም የሰበሰቡ ትህነግ መጥፋት እንዳለበት አቋም ይዘው እንደነበር በወቅቱ በሚነገር የዘመቻ ቅስቀሳ ወቅት በገሃድ ይሰማ እንደነበር የሚታወስ ነው። በሌላው ወገን “ተዘረፍን” የሚሉት የትግራይ ባለሃብቶች ደግሞ ” ዋጋችሁን ታገኛላችሁ” የሚል ምላሽ በአክቲቪስቶቻቸው አማካይነት ሲሰጡም ነበር። አቶ ጌታቸው “የሰሊጥ ፖለቲካ” በማለት ደጋግመው ይህንኑ ይናገሩ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። እነዚህን ነጥቦች በማገናኘት መኮንኑ አቶ በረከት ገና ከጅምሩ ለድምዳሜያቸው ያነሱትን የመጀመሪያ ምክንያት ለመቀበል እንዳልተቸገሩ ገልጸዋል።
በሁለተኛ ደረጃ አቶ በረከት ያነሱት ምክንያት የአማራ ኃይሎች በጦርነቱ ወቅት የሰበሰቡትን ትጥቅ እንዲፈቱ መታወጁና የልዩ ኃይሉ አደረጃጀት እንዲቀየር የተወሰደው እርምጃ ቀደም ሲል ከተፈጠረው ስሜት ጋር አንድ ላይ መደመሩን ነው።

መኮንኑ እንዳሉት የአማራ ኃይሎች የፋኖን ስም በማንሳት ውሳኔውን በመቃወም ልክ እንደ ኤርትራ ኃይሎች በኩርፊያ ሲነሱ ማስቆም የሚችሉና ቀደም ሲል በጦርነቱ ወቅት የአማራውን ኃይል ሲመሩ፣ ሲያስተባበሩና ሎጅስቲክ ሲያሟሉ የነበሩት የሚታወቁ አካላት ዝምታ መምረጣቸው “ተጠያቂነትን ፍርሃቻ ነው” በሚል የሚቀርበውን አመክንዮ ያጎላዋል።
በአማራ ክልል አርሶ አደሮች የማዳበሪያ ጥያቄ አንስተው በባህር ዳርና በተለያዩ ከተሞች አድርገውት የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ፣ በአማራ ክልል በኩርፊያና በስጋት የተጀመረውን አመጽ ሕዝባዊ እንዳደርገው አቶ በረከት በውይይታቸው ወቅት በሶሰተኛ ደረጃ ማንሳታቸውን መኮንኑ አመልክተዋል። የማዳበሪያውን አምጽ ሕዝባዊ በማድረጉ በኩል የመንግስት መዋቅር ላይ የነበሩት ሳይቀሩ ተሳታፊ ስለነበሩበት የፋኖ ኃይል በሰው እንዲጠናከር መደረጉንም የተለያዩ ወገኖች ቀደም ሲል ሲሰጡ ከነበረው አሳብ ጋር የሚገጥም መሆኑን መኮንኑ አመልክተዋል።
አቶ በረከት ባያነሱትም በሌ/ጄ አሳምነው ጽጌ ትዕዛዝ እንዲገደሉ ከተደረጉት የክልሉ ቁልፍ አመራሮች መካከል ፕሬዚዳንቱ ዶክተር አምባቸው፣ በክልሉ የተካሂደውን ዝርፊያ፣ ዝርፊያውን የመሩት ክፍሎች፣ በዝርፊያው የተሳተፉ አካላት፣ ዝርፊያው የተካሂደባቸው ቦታዎችና የተዘረፈው ንብረት ወዴትና እንዴት ለገባያ እንደዋለ አስጠንተው ለውሳኔ እንዲያመች አድርገው በዝግጅት ላይ ነበሩ።
ከአማራ ክልል የወቅቱ አመራሮች ጋር ቅርበት ያላቸው እንደሚሉት በወቅቱ ከወልቃይት ሁመራ የተዘረፈውን ንበረትና ሰሊጥ የኤርትራ ደላሎችና ባለሃብቶች በሆማጀር በኩል ወደ ኤርትራ አግዘዋል። በምጽዋ በኩል ወደ ውጭ እንደተጋጋዘ የተለያዩ መገናኛዎች ሲዘገቡ እንደነበር የሚታወስ ነው። እነዚሁ ወገኖች የአማራ ክልል ታጣቂዎችና የኤርትራ ኃይሎች ግንኙነት “የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በሚል ሽፋን” እንዲጠነክር የሆነበት ዋና ምክንያት ይህ እንደሆነ ይናገራሉ።
ስም ገልጾ መናገር አስፈሪ እንደሆነ የሚናገሩ እንደሚሉት ከሆነ የአማራ ክልል አመራሮች ግድያ ጥንስሱ እዚህ ላይ ነው። ዝርፊያው በአካባቢና በሰፈር በተደራጁ ቡድኖች የተደረገ በመሆኑ የወቅቱን የአማራ ክልል መሪዎች ይኸው የአካባቢያዊነት ስሜት ሰለባ ስለመሆናቸው ስም፣ አካባቢና የግድያውን ዝርዝር አካሄድ የሚያውቁ ዘልቀው ባይሄዱበትም በየአጋጣሚው ሲገልጹት የቆዩት ጉዳይ ነው።

በዚህ በየሰፈሩና አካባቢያዊ ስሜት የተጀመረው ቡድንተኛነት አድጎ የፋኖ አደረጃጀትን ስለበጣጠሰው ወጥ አደረጃጀት ሊይዝ እንዳልቻለ አቶ በረከት ተናግረዋል። ከሶስት ዓመት በፊት ያደረጉትን ውይይት በማንሳት አስተያየታቸውን የሰጡት መኮንኑ ” ፋኖ እስከወዲያኛው አንድ ሊሆን የማያስችለው አፈጣጠር ስላለው ችግሩ ረዥም ጊዜ ይቆያል። አማራ ክልልም እንደ ክልል ይደቃል። ውጤቱ ይህ ነው” ሲሉ አቶ በረከት የተነበዩት ትንቢት ደርሶ ማየታቸውን አመልክተዋል።
የሰሜን ወሎ ነዋሪ መሆኑን የሚናገር ነጋዴ እንደሚለው ከሆነ፣ አሁን ላይ ሕዝብ ተማሯል። ምክንያቱ ደግሞ አገልግሎት ማግኘት አልቻለም። ልጆቹ ትምህርት አቁመዋል። እንዳሻቸው መነቃነቅ አልቻሉም። ብዙ ጉዳት ደርሶባቸዋል። አካባቢው በድን ሆኗል። በሰሜን ወሎ ብቻ ሳይሆን በጎጃም በአብዛኛው ቀበሌዎች እንቅስቃሴ የለም። መንግስታዊ አገልግሎት መስጫዎች ወድመዋል። በሸዋና ጎንደር ባይጋነነም ተመሳሳይ ችግር አለ።
ከጦርነት ሳያገገም፣ ጦርነቱ ያወደመውን መሰረተ ልማት በወጉ ሳይጠግን ዳግም ጦርነት የተነሳበት የአማራ ክልል መጨረሻ አሳሳቢ እየሆነ ነው። መፍትሄ ይገኛል? በሚል ለመኮንኑ ጥያቄ ቀርቦላቸው፣ ” አማራ ክልል የተለያዩ ፍላጎት ባላቸው ታጣቂዎች ሳቢያ ወጥነት ያለው ሌሎች ሊገዙት የሚችል አጀንዳ ሊተክል አልቻለም። እንደውም ሌሎችን የሚያገልና የሚያስፈራራ፣ ሙስሊሞችን የሚያስጨንቅ አካሄድ የመረጠ በመሆኑ ችግሩን ያወሳስበዋል” የሚል መልስ ሰጥተዋል።
“አንድ ካልሆኑና የተለያየ ዓላማ ከያዙ ኃይሎች ወጥ አጀንዳ ሊዘጋጅ ስለማይችል እንዲሁ በተፈረካከሰ አካሄድ ክልሉን ከማፈራረስና የሕዝቡን አበሳ ከማባባስ የዘለለ ምንም ፋይዳ ይኖረዋል የሚል ግምት የለኝም። በረከት እንዳለው ክልሉ ይደቃል” ያሉት እኚሁ ከፍተኛ መኮንን አሁን ላይ ያለው ሁኔታና ሕዝብ እያሰማ ያለው ሮሮ አቶ በረከት ካሉት ጋር የሚገጥም፣ የጭንቅቱ መጀመሪያ ነው። የአማራ ክልል መሪዎች ግድያና የግድያውን ሴራ በተመለከተ አዲስ ሪፖርተር የምርመራውን ዳራ በስፋት በሳምንቱ መጨረሻ በሚጀመረው የዩቲዩብ ገጹ ይዞ ይቀርባል።
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/profile.php?id=61577410241403
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393





