በሃያላን ሀገራት የፉክክር ዘመን፡ የግራጫ ጦርነትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት
አዲስ ሪፖርተር – ዘመንን መዋጀት ከአንድ አገር መንግስት፣ ተቀናቃኝም ሆነ ገዢን ሳይለይ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ ራሳቸውን አክቲቪስት ብለው ከመደቡ፣ ከሚዲያዎችና በጥቅሉ ከምሁራንና “አዋቂ” ነን ባዮች ይTeበቃል። ግድም ነው። ይህ ሲሆን አንድ አደጋ ሲያጋጥም የእሳት አደጋ ስራ ከመስራት፣ እንደ እሳት አደጋና አምቡላንስ ተሽከርካሪ ከመጯጯህ እንድናለን። ምክንያቱም የሚያsተውሉ አይገለበጡምና!!
አሁን ባለንበት የሃያላን ሃገራት የፉክክር ዘመን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዳዲስ የጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች በየጊዜው እየተፈጠሩ ይገኛሉ። በዚህ ወቅት፣ “ግራጫ ጦርነት” (Gray Zone Warfare) የተሰኘውን ስልት ሃገራት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግብ ማስፈፀሚያ በማድረግ በስፋት መጠቀም ጀምረዋል። ይህ አሁናዊ የጦርነት ስልት፣ እንደ አደገኛ ብሔራዊ ስጋት በመቁጠር የደህንነት ተቋማት በትኩረት ሊሰሩበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ጂኦስትራቴጂካሊ ወሳኝ ቦታ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ የሃያላን ሃገራት የፉክክር መድረክ እየሆነች ባለችበት በአሁኑ ወቅት፣ ይህ ስልት ትልቅ የደህንነት ስጋት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ባይ ነን።
ግራጫ ጦርነት ማለት ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት ሳያስፈልግ የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ወይም የሌላ ሀገርን አቅም ለማዳከም የሚውል፣ ከመደበኛው የጦርነት ወለል በታች የሚፈፀም ስልት ነው። የዚህ ጦርነት ዋና መለያ ባህሪ ደግሞ ጥቃት ፈፃሚውን በውል አለመታወቁ (Non-attributable) እና ኃላፊነት የሚወስድ አካል መለየት አለመቻሉ ሲሆን፣ ይህም ለጥቃቱ ምላሽ መስጠት ወይም ተገቢውን የዲፕሎማሲ እርምጃ ለመውሰድ እጅግ ፈታኝ ያደርገዋል።
ይህ ስውር የጦርነት ዘዴ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት በቀጥታ ስጋት የሆኑ በርካታ የጥቃት አይነቶችን ያጠቃልላል። ከእነዚህም መካከል፣ በግለሰብ፣ ተቋም እና ማኅበረሰብ ላይ ዒላማ አድርጎ ሚካሄድ የስነ-ልቦና ጦርነት፣ የሀሰት መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን በማሰራጨት በመንግስትና በሕዝብ መካከል ያለውን መተማመን መሸርሸር ዋነኛው መገለጫው ነው።
በተመሳሳይ፣ ወሳኝ መሰረተ ልማት የሆኑትን እንደ መብራት፣ ቴሌኮም፣ አየር መንገድ፣ ውሃና ባቡር የመሳሰሉትን ዒላማ የሚያደርጉ የሳይበር ወይም ሌላ አይነት ጥቃቶች የሀገርን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ሽባ የማድረግ አቅም አላቸው። በተጨማሪም፣ በኢኮኖሚ ላይ ቀጥተኛ ጉዳት በማድረስ፣ የሀገርን ልማት በማደናቀፍና የቢሮክራሲውን ቅልጥፍና በማበላሸት የሕዝብን ቅሬታ ማባባስ ዓላማው ነው። የሽብርተኝነት ተግባራት (ሚስጢራዊ ጅምላ ግድያ፣ የታዋቂ ሰው ግድያ) ሃገራዊ መረጋጋትን ለማጥፋት የሚደረጉ ጥረቶች ናቸው።
የውጭ ኃይሎች ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ወይም የሀገራችንን አቅም ለማዳከም እነዚህን የግራጫ ጦርነት ስልቶች በውስጥ ባንዳዎች በኩል ሊፈፅሙ እንደሚችሉ መገንዘብ ወሳኝ ነው። ለዚህ ነው ከላይ የዘረዘርናቸውም ሆኑ ሌሎች የሚመለከታቸው ሁሉ “ዘመኑን መዋጀት አለባቸው” የምንለው፤ አለያ እንደ መንግስት ብቻ ሳይሆን እንደ አገርም “ መገልበጥ” አለና!!
ስለሆነም፣ ቁልፍ መፍትሄው በቅንጅትና በትብብር መስራት ነው። ይህንን ስጋት ለመመከት የግሉ ዘርፍ በተለይም በመረጃና በፋይናንስ ቴክኖሎጂ ውስጥ ያሉ ተቋማት ከመንግስት የደህንነት አካላት ጋር የቅርብ የመረጃ ልውውጥ ማድረግና የሳይበር ደህንነት አቅምን በጋራ መገንባት አለባቸው። በተጨማሪም፣ የጥቃት ፈፃሚዎችን ለይቶ ለማወቅ እና ለሕግ ለማቅረብ የሚያስችል ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ መዘርጋት፣ ከአጋር ሀገራት ጋር የመረጃ ዲፕሎማሲ መፍጠር እና የሀገር ውስጥ ዝግጅት ማድረግ ወሳኝ ነው። በተለይ የሕዝብን የዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀም እውቀትን (Digital Media Literacy) ማሳደግ፣ የስነ-ልቦና ጦርነትን ለመከላከል ወሳኝ የመከላከያ መሳሪያ ነው።
በመጨረሻም፣ ግራጫ ጦርነት ለሀያላን ሀገራት ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ላላቸው ሀገራትም ከፍተኛ አደጋ መሆኑን በመገንዘብ፣ ይህንን ዘመናዊና ስውር የጦርነት ስልት ተረድቶ በንቃት መዘጋጀት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ እነዚህን ከቀዝቃዛው ጦርነት የተወረሱ እና አዲስ የተፈጠሩ ስጋቶችን በትብብር እና በብልህነት በመመከት፣ ብሔራዊ ጥቅሟንና የሕዝቧን ሰላም ማስከበር የሁላችንም የቤት ሥራ መሆን አለበት። እዛም እዚህም የንሰማቸው መርዶዎች የዚህ በሽታ ጅማሮ ሊሆኑ ይቻላሉና ዘመኑን በጥንቃቄ እንመርመር!!






