በሲንጋፑር ቆይታው ወቅትም የባዕድነትና የብቸኝነት ስሜት እንዳይሰማው በሚል ሰበብ የስድሳዎቹን ትውልድ የፖለቲካ አመለካከትና ስልት ተሞክሮ እንዲቀስም ታቅዶ ከተዘጋጀ ግለሰብ ጋር እንዲገናኝ ተደርጓል። የቀድሞ የመኢሶን አባል ከነበረ ሰው ጋር የቅርብ ቤተሰባዊ ዝምድና እንዲፈጥር በማድረግ፣ ስለ “ያ ትውልድ” የአብዮት ትግልና የርዕዮተ-ዓለም ፍጭት እንዲጠመቅ ተደርጓል። ይህ ስልታዊ ግንኙነት ጀዋር ገና በወጣትነቱ የ60ዎቹን የፖለቲካ መንፈስ፣ ጥላቻና ግትርነት ላይ የተመሰረተ ስብዕና እንዲላበስ በማድረግ፣ ለወደፊት የፖለቲካ ጉዞው መሰረታዊ የሆነውንና ለመለወጥ አስቸጋሪ የሆነውን የልቦና ውቅር የገነባበት አጋጣሚ ሆኗል።
አለባቸው ጉብሳ- ነጻ አስተያየት
የውጭ የደህንነት ተቋማት በአንድ ሀገር ውስጥ ወደፊት ስልጣን ወይም ተፅዕኖ ሊኖራቸው የሚችሉ ወጣቶችን ገና በለጋ እድሜያቸው የመመልመልና የራሳቸውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግብ በሚያሳካ መልኩ ኮትኩቶ የማሳደግ ስልትን በስፋት ይተገብራሉ። ይህ ተግባር በዘርፉ “የልሂቃን ቀረጻ” (Elite Capture or Cultivation) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም የተመረጡ ወጣቶችን የዓለም እይታ (Worldview) ከሀገራዊ ጥቅም ይልቅ የውጭ ሃገር ፍላጎትና ጥቅምን በሚያሳካ መልኩ አድርጎ መቅረጽ ነው። እነዚህ ተቋማት የአንድን ወጣት የወደፊት የመሪነት ዝንባሌ ቀድመው በመረዳት፣ በትምህርት እና በተለያዩ ስልጠናዎች ስም ከሀገሩ በማውጣት የአስተሳሰብ አድማሱን በእነሱ የፍላጎት ልክ ይቀርፁታል።
ይህ “Formative age” ወይም የማንነት ቀረጻ ምቹ እድሜ የአንድ ሰው ስብዕና እና መሰረታዊ እምነት የሚገነባበት ወሳኝ ወቅት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፤ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም” እንደሚለው ሁሉ፣ በዚህ የእድሜ ክልል የሚሰጡ ስልጠናዎችና የሚፈጠሩ ግንኙነቶች ግለሰቡ ለቀሪው ዘመኑ የሚከተለውን የፖለቲካ መስመር ይወስኑታል። በመሆኑም፣ ምንም እንኳ ግለሰቡ “እኔ በራሴ ነፃ ፈቃድና እውቀት ነው የምንቀሳቀሰው” ብሎ ቢያስብም፣ የልቦና ውቅሩና የውሳኔ አሰጣጡ አስቀድሞ በሰለጠነበት “የአስተሳሰብ ማዕቀፍ” (Frame of Reference) የታጠረ እንዲሆን ይደረጋል። በዚህም ምክንያት፣ የውጭ ኃይሎች አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኙት ግለሰቡን እንደ ስትራቴጂያዊ መሳሪያ ይጠቀሙበታል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተደርጎ እንደተሾመ የሚነገርለት የጀዋር መሃመድ የፖለቲካ ጉዞ የዚህ ውስብስብ ኦፕሬሽን ውጤት መሆኑን ለመረዳት የግድ የመረጃና ደህንነት ባለሙያ መሆን አይጠበቅብንም። እርሱ ራሱ “አልፀፀትም” በሚል ርዕስ ለንባብ ያበቃውን የትግል ህይወት ታሪክ መጽሐፍ በጥሞና ማንበብና “ለምን?” ብሎ መጠየቅ ብቻ በቂ ነው። ጀዋር በዚህ መጽሐፉ፣ በጉልምስናው ወራት ወደ ሲንጋፑር ተወስዶ በወጣት አመራር ስልጠና ስም የህዝባዊ እምቢተኝነት የፖለቲካ ስልቶችን ከሀ እስከ ፐ እንዳስተማሩት በግልጽ ይተርካል። ይህም ለጀዋር ለወደፊቱ የፖለቲካ ስራው የሚያስፈልገውን ቴክኒካዊ እውቀትና ክህሎት እንዲገበይ ያደረጉበት ነበር። ጋዜጣ ላይ የሚወጡ የፓለቲካ ቅስቀሳ ጽሁፎችን እንዴት እንደሚፃፉ፣ ሚድያ እንዴት እንደሚመራ፣ የሕዝባዊ እምቢተኝነት አመራር፣ ስትራቴጂና እቅድ ዝግጅት ስልጠና እንደታሰጠው ጀዋር ያለምንም ሃፍረት ሳይደብቅ በመፅሀፉ ላይ ይገልፃል።
በሲንጋፑር ቆይታው ወቅትም የባዕድነትና የብቸኝነት ስሜት እንዳይሰማው በሚል ሰበብ የስድሳዎቹን ትውልድ የፖለቲካ አመለካከትና ስልት ተሞክሮ እንዲቀስም ታቅዶ ከተዘጋጀ ግለሰብ ጋር እንዲገናኝ ተደርጓል። የቀድሞ የመኢሶን አባል ከነበረ ሰው ጋር የቅርብ ቤተሰባዊ ዝምድና እንዲፈጥር በማድረግ፣ ስለ “ያ ትውልድ” የአብዮት ትግልና የርዕዮተ-ዓለም ፍጭት እንዲጠመቅ ተደርጓል። ይህ ስልታዊ ግንኙነት ጀዋር ገና በወጣትነቱ የ60ዎቹን የፖለቲካ መንፈስ፣ ጥላቻና ግትርነት ላይ የተመሰረተ ስብዕና እንዲላበስ በማድረግ፣ ለወደፊት የፖለቲካ ጉዞው መሰረታዊ የሆነውንና ለመለወጥ አስቸጋሪ የሆነውን የልቦና ውቅር የገነባበት አጋጣሚ ሆኗል።
ይህ የልቦና ውቅር የመቅረጽ ስራ በአሜሪካ ቆይታውም በከፍተኛ ደረጃ ቀጥሏል። ጀዋር እዚያም በነበረው ቆይታ ከቀድሞ የኢሕአፓ አባላትና እንደ ያሬድ ጥበቡና ነአመን ዘለቀ ካሉ የግራ ዘመም ፖለቲካ አራማጆች ጋር እንዲቀራረብ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረውለታል። ምንም እንኳን ጀዋር በዕድሜ የአዲሱ ትውልድ አባል ቢሆንም፣ በውስጡ የሰረጸው የፖለቲካ አስተሳሰብ ግን የዚያኛው ትውልድ ቅጂ ነው። ይህም የልቦና ውቅሩ ከአሁኑ ዘመን ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ይልቅ፣ ተሸንፎ በወደቀው የባለፈው ክፍለ ዘመን የርዕዮተ-ዓለም ትግልና የሴራ ፖለቲካ ላይ ብቻ ተቸንክሮ እንዲቀር አድርጎታል።
በዚህም ምክንያት፣ የጀዋር የፖለቲካ ትግል ከህዝባዊ እምቢተኝነትና ከአመፅ ውጪ ሌላ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ የሆነ አማራጭ መንገድን ለማሰብ ተቸግሮ ይታያል። አሁን ዓለም ያለችበትን ውስብስብ የጂኦ-ፖለቲካ ፉክክር፣ የኃያላን ሀገራትን ፍላጎትና ቀጣናዊ ስጋቶችን ተረድቶ የሀገሩን ህልውና ለማስቀጠል የሚያስችል የትግል ስልት መቀየር ሲገባው፣ እርሱ ግን በአሮጌው መንገድ ላይ ብቻ ተቸንክሮ ቀርቷል። ልዩነቶችን አጥብቦ፣ በአንድ ሀገር ልጅነት መንፈስ ተባብሮ ሀገራዊ ህልውናን ከማስጠበቅ ይልቅ፣ ሁልጊዜም የታሪካዊ ጠላቶቻችንን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግብ የሚያሳካውን የግጭት አዙሪት ይመርጣል።
ይህ ዓይነቱ የግጭትና የህዝባዊ አመጽ ትግል ስልት፣ ኢትዮጵያ ከውስጥ በራሷ ዜጎች እንድትዳከም በማድረግ የብልፅግና እና የዲሞክራሲ ሀገረ መንግስት ግንባታዋን ለዘመናት ወደ ኋላ ሲጎትት የኖረ አጥፊ መንገድ ነው።
ጀዋር ልክ እንደ ጋሪ ፈረስ ግራና ቀኝ መመልከት እንደተሳነውና በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲጓዝ እንደተገደደ መረዳት አይከብድም። የውጭ ኃይሎች ሆን ብለው የቀረጹትን የፖለቲካ የልቦና ውቅር ሀገራዊ ችግሮችን በሰከነ፣ በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት እንዳይችል ትልቅ እንቅፋት ሆኖበታል።
ጀዋር ይህ ማንነቱ፣ ሃገራችን ዛሬ ከምትፈልገው የትብብርና የሰጥቶ መቀበል ውይይትና ድርደር ፖለቲካ ይልቅ፣ በጠባብና በአንድ አቅጣጫ በሚነዳ የትግል ስልት ውስጥ ታስሮ እንዲቀር አድርጎታል። ጀዋር ለሀገር የሚያስብ ቢመስልም፣ በተግባር ግን እየተከተለ ያለው መንገድ የውጭ ኃይሎችን ስትራቴጂያዊ ፍላጎት የሚያገለግልና የሃገርን አንድነት የሚሸረሽር ነው። ይህን የሕሊና ትብታብ ተረድቶ ከባዕዳን የአስተሳሰብ እስር ቤት መውጣት ካልተቻለ፣ የፖለቲካ ትግሉ ምንጊዜም ለሃገር ግንባታ ሳይሆን ለሀገር መፍረስ መሳሪያ መሆኑ አይቀሬ ነው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






