አዲስ ሪፖርተር – በማርበርግ ቫይረስ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች አስከሬን ለቤተሰብ አይሰጥም ተባለ በሽታው በንክኪ የሚተላለፍ በመሆኑ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች አስከሬን ለቤተሰባቸው እንደማይሰጥ ነው የተነገረው። ህይወታቸው ካለፈ በኋላ አስከሬኑ የማይታጠብ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፥ ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ የቀብር ስርዓታቸው ይፈፀማል ተብሏል።
ቀብር የተፈፀመባቸው ቦታዎችም በደንብ መጠበቅ እንዳለባቸው ተገልጿል። ማህበረሰቡ የበሽታውን ከባድነት ተረድቶ ይህንን ውሳኔ መቀበል እና መተባበር አለበት ተብሏል። በሌላ በኩል ቫይረሱ በወንድ የዘር ፈሳሽ ውስጥ ለአንድ አመት ጊዜ የሚቆይ በመሆኑ ፥ ከህመሙ ያገገሙ ሰዎች ልቅ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነት ከማድረግ መቆጠብ አለባቸው ነው የተባለው። ተገቢው ክትትል እና ህክምና ተደርጎለት የዳነ ሰው በሽታውን ማስተላለፍ አይችልም።
እንደ ኮሮና ቫይረስ በአየር ይተላለፋል የሚል የተዛባ አመለካከት መኖሩ የተገለፀ ሲሆን፥ ህመሙ በአየር የማይተላለፍ ነው ተብሏል። ህመሙ በንክኪ የሚተላለፍ በመሆኑ ህመሙ ካለባቸው ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ከንክኪ የራቀ መሆን እንዳለበትም ተገልጿል። ማርበርግ እንደ ኮቪድ በአየር የሚተላለፍ ባይሆንም፥ከኮቪድ በበለጠ ህይወት የሚነጥቅ ነው ተብሏል። እንደ ወረርሽኙ ክብደት የሞት ምጣኔው ከ24 እስከ 88 በመቶ ይደርሳል።
33 ሰዎች ተመርምረው 6 ሰዎች ህመሙ የተገኘባቸው ሲሆን፥ ሶስቱ ህይወታቸው ሲያልፍ ሶስት ሰዎች ደግሞ በህይወት አሉ ተብሏል። ይህን መረጃ ያገኘነው ጤና ሚኒስቴር ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በማርበርግ በሽታ ምንነት ዙሪያ ለሚዲያ ባለሙያዎች ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ ነው።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






