አዲስ ሪፖርተር – በትግራይ ተፈጥሯል የሚባለው የአመራሮች ልዩነት ተከትሎ የትህነግ ስራ አስፈጻሚ፣ የኮርና አርሚ አዛዦች በጊዜያዊ አስተዳደሩ መሪ ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ የግል መኖሪያ ቤት የጀመሩት ስብሰባ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል። ዶክተር ደብረጽዮን “የት ናቸው” የሚል ጥያቄም በርክቷል።
የክልሉ የጸጥታ ኃላፊ ፍስሃ ማንጁስ እንደጠሩት የተነገረለት ይህ ስብሰባ በታደሰ ወረደ መኖሪያ ቤት እየተካሄደ ከመገለጹ ውጭ ስለ ስብሰባው አጀንዳና የተደረሰበት ውሳኔ የተባለ ነገር የለም።
ትህነግ ከተከፈለ በሁዋላ “የጽንፈኛ ኃይል” የሚባለው ቡድን ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደን “አትሰማንም፣የምትወስነው ሳታማክረን ነው፣ለፌደራል መንግስት ትታዘዛለህ፣ ከኤርትራ ጋር የተጀመረውን ጽምዶ አትደግፍም” የሚሉና ተመሳሳይ አቤቱታ እንደሚቀርብባቸው በተለያዩ አግባቦች እንደሚደመጥ የሚታወቅ ነው።
በዚህ መነሻ ይሁን በሌላ ቁልፍ ጉዳይ ባይታወቅም ካለፈ ረቡዕ ጀምሮ የክልሉ የጸጥታ ኃላፊ ጠሩት የተባለው ስብሰባ ይህ ዜና እስከታተመ ድረስ በጄኔራሉ መኖሪያ ቤት እየተደረገ ነው። የትግራይ የአዲስ ሪፖርተር ተባባሪ በምስል አስደግፎ እንዳለው፣ ባለስልጣናቱ ወደ ጄኔራሉ የግል መኖሪያ ሲገቡ በርካታ የአይን ምስክሮች አይተዋል። ተሽከርካሪዎቻቸውን ፎቶ በማንሳት አጋርተዋል።
በሌላ ዜና የዚሁ የታገደውና ሕገወጥ የተባለው ትህነግ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን መሰወራቸው እየተወራ ነው። ከሶስት ሳምንት በፊት በኤርትራ በኩል ዱባይ ከርመው የተመለሱት ዶክተር ደብረጽዮን፣ መታመማቸውን የሚናገሩም አሉ።
ለእሳቸው ቅርብ የሆኑ ሰዎች የሚጋነን ባይሆንም መጠነኛ የጤና መታወክ ገጥሟቸው እንደነበርና እንደተሻላሸው ለአዲስ ሪፖርተር ተባባሪ ነግረዋል። ይሁን እንጂ ህመማቸው ከባድ እንዳልሆነ ቢገለጽም አፅቡ ከተማ በተደረገው የልደት በዓል ላይ አልተገኙም። በግል ለወትሮው እንደሚያደርጉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም አላስተላለፉም።
ተባባሪያችን እንዳለው ታደሰ ወረደ የ”እንኳን አደረሳችሁ” መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን እሳቸው ከወትሮው በተለየ ዝምታን መምረጣቸው የጤናቸው ሁኔታ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ እንደሆነ በርካቶች እየተነጋገሩ ነው። በሌላ በኩል ግን ተመልሰው ወደ ውጭ መውጣታቸውን የሚናገሩ አሉ።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






