አዲስ ሪፓርተር – የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር ኢትዮጵያን “የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ አጋር” መሆኗን አስታወቁ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑም ተገልጿል። በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ ቀንድ፣ በተለይም በቀይ ባሕር አካባቢ ያለውን ስጋት በጋራ ለማስወገድ ውስነዋል።
ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በኢየሩሳሌም ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ ጋር ባደረጉት ውይይት ሲሆን፣ ውይይቱ በሁለቱ አገራት መካከል በቅርቡ ለሚካሄደው አራተኛው የፖለቲካ ምክክር መድረክ ስኬት መሠረት የጣለ መሆኑ ተገልጿል።
ጌዲዮን ሳር በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ውይይቱ በሁለቱ ቀጠናዎች ባሉ የጋራ ተግዳሮቶች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል። ሚኒስትሩ የኢራንን አመራር በተመለከተ ስጋታቸውን በማንሳት፣ እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ጥንታዊና ታሪካዊ ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ ውይይቱ በሁለትዮሽ፣ በቀጠናዊና በባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበርና በተለይም የኢኮኖሚ ትብብርን ማሳደግ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ምክክር መደረጉን አስታውቋል።
ይህ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ እስራኤል በአፍሪካ ቀንድ እያደረገች ያለችው ሰፊ ስትራቴጅክ ጥረት አካል ተደርጎ ተወስዷል። ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር ከዚህ ቀደም ጥር ታህሳስ 28 2018 ዓም በሃርጌሳ ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ይህም እስራኤል የሶማሊላንድን ሉዓላዊነት እውቅና ከሰጠች በኋላ የተከናወነ የመጀመሪያው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጉብኝት ነበር። ይህ በኢየሩሳሌም የተደረገው አዲስ ውይይትም እስራኤል በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ስትራቴጂካዊ ተጽዕኖ ለማሳደግና ከአካባቢው አገራት ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር የምታደርገው ጥረት ማሳያ ተደርጎ ተተርጉሟል።
ስለ ውይይቱ ዝርዝር መረጃ ባይወጣም ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪቃ የቀደመ ቦታዋን ለመያዝና በቀይ ባህር ላይ መሪ ተዋኛን ለመሆን የጀመረችው እንቅስቃሴ ምላሽ የሚያገኝበት ሰዓት መቃረቡን የሚያሳይ እንደሆነ አስተያየት እየተሰጠ ነው።
አሜሪካ በአስመራ ያላትን ኤምባሲ እንደምዘጋ ባስታወቅችበት በዚህ ወቅት እስራኤልና ኢትዮጵያ ግንኙነታቸው ወደ ከፍተኛ ደረጅ ማደጉ መገለጹ ለኤርትራ የዲፕሎማሲ ጀንበር መጥለቁን የሚያሳይ እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰር ገነነ ገደቦ ለአዲስ ሪፖርተር አስታውቅዋል።
በአስመራ የአማኤሪካን ኤምባሲ እንዲዘጋ በተወሰነ ማግስት በኤርትራ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ወጥተው 2 ሰዓት ከሃያ ሁለት ደቂቃ ያወሩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን በንዴትና እልህ በወለደው ስሜት የተሳደቡበት ምክንያት ይኸው የዲፕሎማሲ ውድቀት እንደሆነ በስፋት እየተገለጸ ነው።
የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ገነነ፣ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በአስመራ የሚገኘውን ኤምባሲውን በጥር ወር መጨረሻ ላይ ሙሉ በሙሉ ለመዝጋት መወሰኑ የአፍሪካ ቀንድን ፖለቲካዊ አሰላለፍ በአንድ ጀምበር እንደቀየረው ተናግረዋል። ይህ ውሳኔ ተራ የአስተዳደር ለውጥ ሳይሆን፣ የትራምፕ አስተዳደር ለኤርትራ የሰጠውን ዝቅተኛ ዋጋና የዲፕሎማሲ ንቀት፣ እንዲሁም ፋይዳ ቢስነት የሚያሳይ ፖለቲካዊ ንቀት እንደሆነ አመልክተዋል።
“ማንኛውም የአካባቢው ጉዳይ ሲነሳ ዋሽንግተን መጀመሪያ የምታማክረው አዲስ አበባን ይሆናል። ይህም ኢትዮጵያን በጎረቤት ሀገራት ላይ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ያደርገዋል” ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ “ተወደደም ተጠላም የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች በአፍሪቃ ቀንድ ኢትዮጵያ ያላትን ኃያልነት አምኖ ከመቀበል ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም። ይህም በቅርቡ እውን የሚሆን ነው” በማለት አስታውቀዋል። ከረዳት ፕሮፌሰር ጋር የተደርገውን ቅቃለ ምልልስ ሙሉውን እናቀርባለን።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






