አዲስ ሪፖርተር – የፕሪቶሪያው ስምምነት በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረገ የአፍሪካ ሕብረት ጫና እንዲፈጥር የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር / ትህነግ ተማጸነ። የአፍሪካ ህብረት ለትህነግ ቀጥታ ምላሽ እንደማይሰጥ አሰራሩን የሚያውቁ አመልክተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ከትህነግ በሚቀርብለት ጥያቄ መሰላቸቱ ሌላ ችግር እንደሆነም ተመልክቷል።
“ፖለቲካዊ፣ የጸጥታ እና የአስተዳደር” ልዩነቶችን ለመፍታት የሰላም አማራጭ የተባለው የፕሪቶሪ ስምምነት መፈረሙ አይዘነጋም። ፈራሚዎች ፖለቲካዊ ውይይት እንዲያደርጉ ለመጥራት እና ለማመቻቸት የአፍሪካ ኅብረት እርምጃ እንዲወስድ ትህነግ የጠየቀው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት 39ኛ መደበኛ ጉባኤን ለማዘጋጀት በዝግጅት ላይ ባለችበት ወቅት ነው።
በምርጫ ቦርድ ዕውቅናውን የተገፈፈው ትህነግ ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ደብዳቤውን የጻፉት ጦርነት ሊያስነሳ የሚችል ጦርነት ሊነሳ እንደሚችል ስጋት ባየለበት ወቅትና ራሱ ትህነግ ሳይቀር ክ2013 ይልቅ አሁን ላይ በተሻለ አቋም ላይ እንደሚገኝ እያስታወቀ ባለበት ወቅት ነው።
ትህነግ ደብዳቤውን ሐሙስ ለአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የአንጎላ ፕሬዝደንት ዮዋዎ ሎሬንሶ፣ ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን፣ ለሀገራት እና መንግሥታት መሪዎች ማሰራጨቱ ታውቋል።
በፕሪቶሪያ በተፈረመው ግጭት የማቆም ሥምምነት የተካተቱ ቁልፍ ቃል ኪዳኖች ተግባራዊ የተደረጉት “በከፊል ብቻ” እንደሆነ የገለጸው የትህነግ ደብዳቤ፣ “አዲስ ወታደራዊ እንቅስቃሴ፣ እየጨመረ የመጣ ውጥረት እና አስገዳጅ እርምጃዎች” ሰላም ለማውረድ በተደረጉ ጥረቶች የተገኙ ውጤቶችን “የሚቀለብሱ ሥጋቶች” እንደሆኑ ገልጿል። ትህነግ የፕሪቶሪያው ስምምነት ሊቀለበስ መቃረቡን ሲያስታውቅ የትኞቹ ስምምነቶች እስካሁን በስራ ላይ እንደዋሉ በደብዳቤው አላመለከተም።
ትህነግ “የእንቅስቃሴ ገደብ፣ ኢኮኖሚያዊ ጫና እና ፖለቲካዊ መገለልን ጨምሮ ሰላማዊ ሕይወትን የሚገድቡ እርምጃዎች” የሰላም ሒደቱን እምነት እንደሚያሳጡ እና “ወደ ግጭት የመመለስ አደጋን” እንደሚጨምሩ አስጠንቅቋል። እንዲህ ዐይነት ሁኔታዎች የአካባቢውን መረጋጋት ብቻ ሳይሆን የቀጠናውን ደሕንነት እና የአፍሪካን የግጭት አፈታት ጥረቶች ተዓማኒነት አደጋ ላይ እንደሚጥል ገልጿል።
ግጭት የማቆም ሥምምነቱ እንዲፈረም “ቁልፍ እና ታሪካዊ” ሚና የተጫወተው የአፍሪካ ኅብረት ለተግባራዊነቱ “ግልጽ ፖለቲካዊ እና የሞራል ኃላፊነት” እንዳለበት ትህነግ ዕምነቱን በደብዳቤው ጠቁሟል።
በዚህም መሠረት የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የአንጎላ ፕሬዝደንት ዮዋዎ ሎሬንሶ እና በ39ኛው መደበኛ ጉባኤ የሚሳተፉ ሁሉም የአፍሪካ መሪዎች ሊወስዷቸው ይገባል ያላቸውን አራት ጉዳዮች ትህነግ በደብዳቤው ዘርዝሯል።
የመጀመሪያው ኅብረቱ ግጭት የማቆም ሥምምነቱን በአስገዳጅነት በይፋ እንዲያረጋግጥ እና ፈራሚዎቹ “በሙሉ” እና “በአፋጣኝ” ተግባራዊ እንዲደረግ ጥሪ እንዲደረግ፤
ትህነግ እና የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት የተፈራረሙትን ሥምምነት አተገባበር የአፍሪካ ኅብረት የሚከታተልበትን እና የሚያረጋግጥበትን ሥርዓት እንዲያነቃቃ እና እንዲያጠናክር ዶክተር ደብረፅዮን በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል።
የአፍሪካ ኅብረት “ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ወደ ነበረበት ለመመለስ፣ ተፈናቃዮች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እና ለሲቪል ሰዎች ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን እንዲደግፍ ትህነግ ጠይቋል።
የሲቪል ሰዎችን መተዳደሪያ እና የሰብአዊ ርዳታ ተደራሽነት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ እርምጃዎች እንዲወገዱ የአፍሪካ ኅብረት ማበረታታት እንደሚኖርበት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ትህነግ አሳስቧል።
የግጭት መነሾ የሆኑ “ፖለቲካዊ፣ የጸጥታ እና የአስተዳደር” ልዩነቶችን ለመፍታት የሥምምነቱን ፈራሚዎች ፖለቲካዊ ውይይት እንዲያደርጉ ለመጥራት እና ለማመቻቸት ኅብረቱ እርምጃ እንዲወስድ ትህነግ ጠይቋል።
ትህነግ አስራ አንድ ጊዜ ደብዳቤ መጻፉን ሊቀመንበሩ የካቲት 11 አከባበርን አስመልክቶ አስታውቀዋል። የጀርመን ድምጽ ያነጋገራቸው የህግ ባለሙያ የአፍሪካ ህብረት ለትህነግ በቀጥታ መልስ የማይሰጠው ትህነግ ባለው ስታተስ ህብረቱን በቀጥታ የማግኘት ህጋዊ አግባብነት ስለሌለው ነው።
በሐራ መሬት የሰፈረው የትግራይ ሰላም ኃይሎች በበኩላቸው ትህነግ ምንም ዓይነት ደብዳቤ ለመጻፍ አግባብነት የለውም ብለዋል። አክለውም መጻፍም ካለበት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲሆን እሱም ለፌደራል መንግስት እንደሆነ አመላክቷል። የፕሪቶሪያው ስምምነት ተግባራዊ እንዳይሆን፣ ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያቸው እንዳይመለሱ እንቅፋት የሆነው ራሱ “ጽንፈኛ” የተባለው የደብረጽዮን ቡድን እንደሆነ አመልክተዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






